የሑደይቢያ ክስተት
ኒያው ዑምራ፣ ፍጻሜው ሑደይቢያ
ጊዜው በሂጅራ ስድስተኛው ዓመት የዙልቀዕዳ ወር ነበር። አንድ ሌሊት የተከበሩት ነብይ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች ጋር ወደ መካ አል-ሙከረማ ሄደው ካዕባ አል-ሙዐዘማን ጠዋፍ እንዳደረጉ፣ ከፊሎቹ ጸጉራቸውን እንዳሳጠሩ፣ ከፊሎቹ ደግሞ እንዳስላጩ በሕልማቸው አዩ። ክቡር ረሱሉላህ ይህን ሕልማቸውን ለሶሓቦቻቸው በነገሩ ጊዜ እነርሱ እጅግ ተደሰቱ፤ ተነቃቁም። ከሂጅራ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወለዱበትና ያደጉበት፣ በመራርና በጣፋጭ ትዝታዎች የተሞላው ውቡ አገራቸው ወደሆነችው ወደ መካ ሊሄዱ ነበር። በአምስቱ ወቅት ሶላቶች ፊታቸውን ወደሚያዞሩባትና ወደሚናፍቋት የተቀደሰችው ካዕባ ሄደው ሊጎበኟትና ጠዋፍ ሊያደርጉ ነበር። ይህ ምንኛ ያማረ የምሥራች ነበር!… ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች የውዱ ነብያችንን፦ «በእርግጥ ወደ መስጂደል ሐራም ትገባላችሁ!» የሚለውን የምሥራች እንደተቀበሉ ወዲያውኑ ዝግጅት ጀመሩ። ሐቢቡል አክረም ዝግጅታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ዐብዱላህ ኢብኑ ኡሙ መክቱምን በመዲና ምክትላቸው አድርገው ተዉ። በዙልቀዕዳ ወር የመጀመሪያው ሰኞ ቀን ቀስዋ የተባለችውን ግመላቸውን ተቀመጡ። ከተዘጋጁት አንድ ሺህ አራት መቶ ሶሓቦቻቸው ጋር ሆነው በመዲና የቀሩትን ተሰናበቱ። ዑምራን ኒያ አድርገው ወደ ተቀደሰችው ከተማ ወደ መካ ገሠገሡ። ከእነርሱ ጋር የመንገደኛ መሣሪያ የሆኑትን ሰይፎቻቸውንና ለእርድ ሰባ ግመሎችን ይዘው ነበር። ከቅፍለቱ ሁለት መቶዎቹ ፈረሰኞች፣ አራቱ ደግሞ ሴት ሶሓቦች ነበሩ። ከሴቶቹ አንዷ የውዱ ነብያችን የተባረኩና ንጹሕ ባለቤት እናታችን ሰይደቲና ኡሙ ሰለማ ነበሩ። ሚቃት ወደሆነው ዙል ሑለይፋ በደረሱ ጊዜ ኢሕራም አደረጉ፤ የዙህርንም ሶላት ሰገዱ። ከዚያም የሚታረዱትን ግመሎች ጆሮዎች ምልክት አድርገው በአንገታቸው ገመድ አሰሩ። ናጂያ ኢብኑ ጁንዱብ አል-አስለሚ ረዳቶች ተሰጥቷቸው በግመሎቹ ላይ ኃላፊ ሆኑ። ዐባድ ኢብኑ ቢሽር ሃያ ሰዎች ባሉት የፈረሰኛ ጓድ ላይ አዛዥ ሆነው ተሹመው ለቅኝት ወደፊት ተላኩ። ቢሽር ኢብኑ ሱፍያን ወደ መካ መልዕክተኛ ሆነው ተላኩ።1 የኢሕራም ልብስ የለበሱት ውዱ ነብያችንና ጀግኖቹ ሶሓቦች በነጭ ተጠቅልለው አላሁ ተዓላን ማመስገን፣ የክብሩን ልዕልና ማረጋገጥና መማጸን ጀመሩ፦
«ለበይክ፣ አላሁመ ለበይክ! ለበይክ፣ ላ ሸሪከ ለከ ለበይክ! ኢነል ሐምደ ወኒዕመተ ለከ ወልሙልክ፣ ላ ሸሪከ ለክ!»
(እነሆ መጣሁ፣ አላህ ሆይ፣ እነሆ መጣሁ! ጥሪህን በቃሌም በማንነቴም ደጋግሜ ተቀበልኩ፤ ለትእዛዝህም ተገዛሁ። አጋር የለህም፤ በሙሉ ሕልውናዬ ወደ አንተ ዞርኩ። ምስጋናና ጸጋ ለአንተ ብቻ የተገቡ ናቸው። ንግሥናም የአንተ ነው። ተጋሪ የለህም።) በዚህ የተባረከ ተልቢያ ምድርና ሰማይ አስተጋቡ፤ ዙል ሑለይፋም በኑር የተሞላ ድባብ ለበሰች። ሁሉም በስሜት ተሞልቶ በተቻለ ፍጥነት መካ ለመድረስ ከዙል ሑለይፋ ተነሡ።
በመንገድ ላይ ሰይዲና ዑመርና ሰይዲና ሰዕድ ኢብኑ ዑባዳ ወደ ሐቢቡል አክረም ቀርበው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከእርስዎ ጋር በጦርነት ላይ ባሉ ሰዎች ላይ ያለ መሣሪያ ነው የምንሄደው? ቁረይሾች እርስዎን አጥቅተው በተባረከ አካልዎ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ እንፈራለን!…» ብለው ስጋታቸውን ገለጹ። የሁለቱ ዓለማት መሪም፦ «እኔ ዑምራን ኒያ አድርጌያለሁ። በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኜ መሣሪያ መያዝ አልፈልግም» አሏቸው።
ጉዞው በሰላም ቀጠለ። በመንገድ ላይ ባሉ የተለያዩ ጎሳዎች ዘንድ ጎራ ይሉ ነበር፤ ክቡር ነብያችንም ወደ እስልምና ይጠሯቸው ነበር። ከፊሎቹ ለመቀበል ያመነቱ ነበር፤ ከፊሎቹ ደግሞ ስጦታዎችን ይልኩ ነበር። በዚህ ሁኔታ የመንገዱን ግማሽ አልፈው ከዑስፋን ባሻገር ገዲሩል አሽጣጥ ወደሚባለው ቦታ ደረሱ። እዚህ ቀደም ብለው ለመካ ሰዎች መልእክት እንዲያደርሱ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰይዲና ቢሽር ኢብኑ ሱፍያን ከቁረይሾች ጋር ተነጋግረው ተመልሰው ነበር። ያዩትን ለክቡር ነብያችን እንዲህ ብለው ተረኩ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ቁረይሾች እርስዎ መምጣትዎን ሰምተዋል። ከፍርሃታቸው የተነሣ በአካባቢው ላሉ ጎሳዎች ጥሪ አቅርበው እርዳታቸውን ጠይቀዋል። ለቅኝት ወደ እርስዎ ሁለት መቶ ሰዎች ያሉት የፈረሰኛ ጓድ አስወጥተዋል። በአካባቢው ያሉ ጎሳዎች ይህን ጥያቄ ተቀብለው በልደሕ በሚባል ቦታ ተሰባስበዋል። እጅግ ብዙ ወታደር አከማችተዋል፤ እርስዎንም ወደ መካ ላያስገቡ ምለዋል።»
በዚህ ወሬ የዓለማት ሰይድ እጅግ አዘኑና፦ «ቁረይሽ ጠፋ። ጦርነት ቀድሞውኑ በልቶ ጨርሶታል… የቁረይሽ አጋሪዎች በራሳቸው ውስጥ ኃይል ያለ ይመስላቸዋልን? ወላሂ አላሁ ተዓላ እንዳስፋፋው የላከኝን ይህን ሃይማኖት የበላይና ልዑል እስኪያደርገው ድረስ፣ ወይም ራሴ ከአካሌ እስኪለይ ድረስ ከእነርሱ ጋር ከመዋጋት ፈጽሞ ወደ ኋላ አልልም!» አሉ። ከዚያም ወደ ጀግኖቹ ሶሓቦቻቸው ዞረው በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸውንና አስተያየታቸውን ጠየቁ። በሙሉ ማንነታቸው ራሳቸውን ለረሱሉላህ የሰጡት ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች፦ «አላሁ ተዓላና መልዕክተኛው ይበልጥ ያውቃሉ። ነፍሳችን ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኛ በይቱላህን ጠዋፍ ለማድረግ ኒያ አድርገን ነው የተነሣነው። ማንንም ለመግደልም ሆነ ለመዋጋት አልመጣንም። ነገር ግን ካዕባን እንዳንጎበኝ ሊከለክሉን ከፈለጉ በእርግጥ ከእነርሱ ጋር እንዋጋለን፤ ግባችንንም እናሳካለን!…» አሉ። ይህ የክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች ቁርጠኝነት ውዱ ነብያችንን ደስ አሰኛቸው። «እንግዲያውስ በአላሁ ተዓላ የተከበረ ስም ገስግሱ!…» አሉ። ሶሓቦች በክቡር ነብያችን ዙሪያ ሆነው «ለበይክ፣ አላሁመ ለበይክ!…» እያሉ ተልቢያ፣ «አላሁ አክበር! አላሁ አክበር!…» እያሉ ደግሞ ተክቢር በማለት ወደ መካ መገስገስ ጀመሩ።
በአንድ የዙህር ሰዓት ቢላል አል-ሐበሺ በድምፃቸው ውበት ሁሉ ሙሐመዳዊውን አዛን አድርገው የሶላት ወቅት መግባቱን አሳወቁ። በዚህ ጊዜ ሁለት መቶ ሰዎች ያሉት የቁረይሽ የፈረሰኛ ጓድ እዚያ ደርሶ በመካና በሶሓቦች መካከል ገብቶ ለጥቃት ተዘጋጅቶ ቆሞ ነበር። ይህም ሆኖ የዓለማት ሰይድ ከላቁት ሶሓቦቻቸው ጋር ሰፍ ሠርተው ሶላት ጀመሩ። ከውዱ ነብያችን ኋላ አንድ ሺህ አራት መቶ ያህል ሶሓቦቻቸው በሰፍ ሆነው ሳይንቀሳቀሱ በቂያም መቆማቸውና ለሩኩዕ ማጎንበሳቸው የሚታይ ትዕይንት ነበር። ይልቁንም ሁሉም በአንድነት ወደ ሱጁድ ሲወርዱ ግርማ ያለው ተራራ ሲያጎነብስና ቀና ሲል ይመስል ነበር።
«በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ቁረይሽ ከእኔ ምንም ቢጠይቅ የተከበረው ቤት እንዲከበር በሚለው ቅድመ ሁኔታ እቀበላለሁ» ሐዲስ ሸሪፍ
ወደ ሑደይቢያ የተደረገው ጉዞ
በአላሁ ተዓላ ፊት የተከበሩ ግንባሮቻቸውን መሬት ላይ በማስደፋት ያሳዩት ትሕትና በአንዳንድ የቁረይሽ ፈረሰኞች ልብ ውስጥ የእስልምናን ፍቅር ጣለ። ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች አሰላምተው ከሶላት በወጡ ጊዜ የቁረይሽ ፈረሰኞች አዛዥ፦ «በሙስሊሞች በዚህ ሁኔታ ተጠቅመን ድንገተኛ ጥቃት ብንሰነዝር ኖሮ አብዛኞቻቸውን እንገድል ነበር!… በሶላት ላይ ሳሉ ለምን አላጠቃናቸውም?» ብሎ ተቆጨ፤ ከዚያም፦ «አትጨነቁ። ከነፍሳቸውና ከልጆቻቸው አብልጠው ወደሚወዱት ሌላ ሶላት መቆማቸው አይቀርም!…» ብሎ በዚህ ጊዜ አጋጣሚውን እንደማያሳልፉ ለጓደኞቹ አሳወቀ። አላሁ ተዓላ ይህን ቃላቸውን በጂብሪል ዐለይሂ ሰላም አማካይነት ወሕይ አውርዶ ለክቡር ነብያችን አሳወቀ። በወረደው ክቡር አንቀጽ በትርጓሜ እንዲህ ተባለ፦ «(ሐቢቤ ሆይ!) አንተም በመካከላቸው ሆነህ (በጠላት ፊት) ለእነርሱ (ለሶሓቦችህ) ሶላት በምታሰግድበት ጊዜ (ለሁለት ክፍል ክፈላቸው፤) ከፊላቸው ከአንተ ጋር (በሶላት፣ ሌላው ደግሞ በጠላት ፊት) ይቁሙ። የጦር መሣሪያዎቻቸውንም ይዘው ይቁሙ። ከአንተ ጋር በሶላት ሆነው አንድ ረከዓ የሰገዱት (ሶላትን ከሚያበላሹ ሥራዎች እየተጠነቀቁ) ወደ ጠላት ፊት ይሂዱ። ከዚያም ገና ሶላታቸውን ያልሰገዱት ሌላኛው ክፍል መጥተው ሁለተኛውን ረከዓ ከአንተ ጋር ይስገዱ፤ እነርሱም ጥሩሮቻቸውን፣ የመከላከያ ዕቃዎቻቸውንና የጦር መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ይሁኑ። (ተሸሁድን ከአንተ ጋር ያንብቡ። አንተ ባሰላመትክ ጊዜ እነርሱ ሳያሰላምቱ ወደ ጠላት ፊት ይሂዱ፤ አስቀድመው አንድ ረከዓ የሰገዱት ተመልሰው መጥተው ለብቻቸው አንድ ተጨማሪ ረከዓ ሰግደው ያሰላምቱ። ሁለተኛውን ረከዓ ከኢማሙ ጋር የሰገዱትም ተመልሰው መጥተው አንድ ተጨማሪ ረከዓ ሰግደው ሶላቱን አሟልተው ያሰላምቱ።) ከሓዲዎች ከጦር መሣሪያዎቻችሁና ከዕቃዎቻችሁ እንድትዘናጉና በድንገት ጥቃት እንዲሰነዝሩባችሁ ይመኛሉ… ከዝናብ የተነሣ ችግር ቢደርስባችሁ ወይም ብትታመሙ የጦር መሣሪያዎቻችሁን ብታስቀምጡ በእናንተ ላይ ኃጢአት የለም። ነገር ግን አሁንም የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሁሉ ውሰዱ። ጥርጥር የለም፤ አላሁ ተዓላ ለከሓዲዎች አዋራጅ ቅጣትን አዘጋጅቷል።»2 በዐስር ሰዓት ሰይዲና ቢላል አዛን ባደረጉ ጊዜ የቁረይሽ ፈረሰኞች እንደገና በመካና በክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች መካከል ለጥቃት ተዘጋጅተው ቆሙ። ክቡር ነብያችን ለሶሓቦቻቸው በክቡር አንቀጹ እንደተገለጸው ሶላታቸውን አሰገዱ። አጋሪዎች ሙስሊሞች በዚህ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ሶላት መስገዳቸው አስገረማቸው። አላሁ ተዓላ በልባቸው ፍርሃትን ጣለ። ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ አልደፈሩም። ወደ መካ ወሬ ለማድረስ ከዚያ ተለይተው ሄዱ። ክቡር ነብያችንና ሶሓቦቻቸውም ከዚህ ተነሥተው ወደ መካ አቅጣጫ ተንቀሳቀሱ። የተቀደሰችው መካ ወሰን በደረሱ ጊዜ የክቡር ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ግመል ቀስዋ ምንም የሚታይ ምክንያት ሳይኖር በድንገት ተንበረከከች። እንድትነሣ ብዙ ደከሙ፤ ነገር ግን አልተነሣችም። በዚህ ጊዜ የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን እንዲህ አሉ፦ «እርሷ እንዲህ የመንበርከክ ልማድ የላትም። ነገር ግን በአንድ ወቅት (የአብረሀን) ዝሆን ወደ መካ እንዳይገባ ይዞ ያስቀረው አላሁ ተዓላ አሁን ደግሞ ቀስዋን ይዞ አስቀራት። ሕልውናዬ በኃይሉ እጅ ባለው በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ቁረይሽ አላሁ ተዓላ በሐረም ውስጥ ሐራም ካደረጋቸው ነገሮች (ውጊያንና ደም ማፍሰስን መተው የመሳሰሉትን) ማንኛውንም ከእኔ ቢጠይቁ ይህን ጥያቄያቸውን በእርግጥ እፈጽምላቸዋለሁ!»
ከዚያም ቀስዋን ሊያስነሡ ፈለጉ። ግመሏ ዘላ ተነሣች። ከሐረም ወሰን ወደ ውስጥ አልገባችም፤ በትክክል በወሰኑ ላይ ባለው ሑደይቢያ በሚባለው ቦታ ቆመች። ክቡር ነብያችንና ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች ውኃው ጥቂት በሆነው በዚህ ቦታ ሰፈሩ።
«የቁረይሽ አጋሪዎች በራሳቸው ውስጥ ኃይል ያለ ይመስላቸዋልን? ወላሂ አላሁ ተዓላ እንዳስፋፋው የላከኝን ይህን ሃይማኖት የበላይና ልዑል እስኪያደርገው ድረስ፣ ወይም ራሴ ከአካሌ እስኪለይ ድረስ ከእነርሱ ጋር ከመዋጋት ፈጽሞ ወደ ኋላ አልልም!» ሐዲስ ሸሪፍ
ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ድንኳናቸውን ከተቀደሰችው መካ ወሰን ውጭ አስተከሉ። ከሶሓቦቻቸው ጋር በዚያ መጠበቅ ጀመሩ። የሶላት ወቅት በገባ ጊዜ ሶላቶቻቸውን በመካ አል-ሙከረማ ወሰን ውስጥ ይሰግዱ ነበር። በጉድጓዶቹ ውስጥ የሚጠጣና ለአገልግሎት የሚውል ውኃ አልቀረም ነበር። ውኃ የነበረው በክቡር ነብያችን ማንቆርቆሪያ ውስጥ ብቻ ነበር። በከባድ ሁኔታ ውስጥ የነበሩት ሶሓቦች፦ «ነፍሳችን ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከእኛ ጋር ውኃ ያለው በእርስዎ ማንቆርቆሪያ ውስጥ ብቻ ነው። ጠፋን» አሉ።
የዓለማት ሰይድም፦ «እኔ በመካከላችሁ እስካለሁ ድረስ አትጠፉም» አሉ። ከዚያም «ቢስሚላህ» ብለው የተባረከ እጃቸውን በማንቆርቆሪያው ላይ አኖሩ። ከዚያም አንሥተው «ውሰዱ!…» ባሉ ጊዜ ከተባረኩ ጣቶቻቸው መካከል ውኃ እንደ ምንጭ መፍሰስ ጀመረ። ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች እስኪረኩ ድረስ ውኃ ጠጡ፤ ውዱእ አደረጉ፤ የውኃ አቁማዳዎቻቸውን ሁሉ ሞሉ፤ ፈረሶቻቸውንና ግመሎቻቸውንም አጠጡ። ሶሓቦቻቸውን ፈገግ ብለው ይመለከቱ የነበሩት የእዝነት ውቅያኖስ ውዱ ነብያችን አላሁ ተዓላን አመሰገኑ። በዚያን ቀን እዚያ የነበሩት ሰይዲና ጃቢር ኢብኑ ዐብዱላህ፦ «እኛ አንድ ሺህ አራት መቶ ሰዎች ነበርን። መቶ ሺህ ሰዎች እንኳ ብንሆን ኖሮ ያ ውኃ ለሁላችንም ይበቃን ነበር» አሉ።
በይዐቱ ሪድዋን
ረሱሉል አክረም በሑደይቢያ ሳሉ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ከሙስሊሞች ጋር ወዳጅ የነበረው የኹዛዐ ጎሳ አለቃ ቡደይል ወደ እርሳቸው ፊት መጥቶ በአካባቢው ያሉ ጎሳዎችም የተቀላቀሉበት የቁረይሽ ሠራዊት በሑደይቢያ መስፈሩንና ሠራዊታቸው እስኪበተን ድረስ ለመዋጋት መማላቸውን አሳወቀ። በዚህ ጊዜ ክቡር ነብያችን እንዲህ አሉ፦ «እኛ ወደዚህ የመጣነው ከማንም ጋር ለመዋጋት አይደለም። የመጣነው ዑምራ ለማድረግ፣ ካዕባ አል-ሙዐዘማን ጠዋፍ ለማድረግና ለመጎብኘት ብቻ ነው። ይህም ሆኖ በይቱላህን እንዳንጎበኝ ሊከለክለን የሚነሣን ሁሉ እንዋጋዋለን። ያለ ጥርጥር ጦርነቶች ቁረይሽን እጅግ አድክመውታል፣ አቅም አሳጥተውታል፤ ብዙ ጉዳትም አድርሰውበታል። ከፈለጉ የዕርቅ ጊዜ ልወስንላቸው። በዚያ ጊዜ ውስጥ ከእኔ በኩል በደኅንነት ይሁኑ። በእኔና በሌሎች ጎሳዎች መካከል አይግቡ፤ ከእነርሱ ጋር ለብቻዬ ይተዉኝ። እኔ እነዚያን ጎሳዎች ባሸንፍና ክብሩ የላቀው አላህም ቅኑን መንገድ ለግሷቸው ሙስሊም ቢሆኑ የቁረይሽ አጋሪዎች ከፈለጉ እንደ እነርሱ ሙስሊም ሊሆኑ ይችላሉ። እነርሱ እንደሚያስቡት ሌሎቹን ማኅበረሰቦች ማሸነፍ ባልችል ደግሞ ያን ጊዜ እነርሱ ራሳቸው እፎይታ አግኝተው ኃይል ያገኛሉ። የቁረይሽ አጋሪዎች ይህን ሳይቀበሉ ከእኔ ጋር ለመዋጋት ቢነሡ ግን ሕልውናዬ በኃይሉ እጅ ባለው በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ለማስፋፋት በምጥረው በዚህ ሃይማኖት መንገድ ራሴ ከአካሌ እስኪለይ ድረስ ከእነርሱ ጋር እዋጋለሁ። ያን ጊዜ አላሁ ተዓላም እንደሚረዳኝ የገባውን ቃል ያለ ጥርጥር ይፈጽማል!»
የኹዛዐ ጎሳ አለቃ ቡደይል የክቡር ነብያችንን ቃል ወደ ቁረይሽ የጦር ሰፈር ለማድረስ ጉዞ ጀመረ። አጋሪዎች የክቡር ረሱሉላህን ቃል ከቡደይል ከሰሙ በኋላ ከታላላቅ ሰዎቻቸው አንዱን ዑርዋ ኢብኑ መስዑድን ለድርድር ወደ ክቡር ነብያችን ላኩ። ዑርዋ ቁረይሽ ማንንም ወደ መካ ላለማስገባት ቁርጥ ውሳኔ ላይ መሆኑን ባሳወቀ ጊዜ ሐቢቡል አክረም፦ «ዑርዋ ሆይ! ለአላህ ብለህ ተናገር! እነዚህ የእርድ ግመሎች እንዳይታረዱ፣ ይህች ካዕባ አል-ሙዐዘማም እንዳትጎበኝና ጠዋፍ እንዳይደረግባት መከልከል ይገባልን?» አሉ። ከዚያም ለኹዛዐ ጎሳ አለቃ የነገሩትን ለዑርዋም ነገሩት።
ዑርዋ በአንድ በኩል ክቡር ነብያችንን እያዳመጠ በሌላ በኩል የክብረ ገናናዎቹን ሶሓቦች ሁኔታና ጠባይ፣ እርስ በርሳቸውና ለዓለማት ሰይድ ያላቸውን አያያዝ፣ አክብሮታቸውንና ክብራቸውን በጥንቃቄ ይመለከት ነበር። የውዱ ነብያችንን ሐሳብ ካዳመጠ በኋላ ተነሥቶ ይህን ለቁረይሾች ለመንገር ሄደ። ወደ እነርሱ ዘንድ ደርሶ እንዲህ አለ፦ «የቁረይሽ ማኅበረሰብ ሆይ! እኔ እንደ ቄሳር፣ ነጃሺና ኪስራ ወዳሉ ወደ ብዙ ነገሥታት ፊት መልዕክተኛ ሆኜ እንደሄድኩ ታውቃላችሁ። እምላለሁ፤ ሙስሊሞች ለሙሐመድ የሚያሳዩትን ክብርና አክብሮት እስከ ዛሬ ድረስ ለአንድም ንጉሥ ሲደረግ አላየሁም። ከሶሓቦቹ አንዳቸውም ያለ እርሱ ፈቃድ አይናገሩም። ከራሱ አንዲት ጸጉር ብትወድቅ በረከት ለማግኘት ተሻምተው በጉያቸው ይደብቋታል። በፊቱ ሲናገሩ ድምፃቸውን እስከማይሰማ ድረስ ዝቅ ያደርጋሉ። ለእርሱ ካላቸው አክብሮት የተነሣ ፊቱን ማየት አይችሉም፤ ዓይኖቻቸውንም ወደ መሬት ዝቅ ያደርጋሉ። እርሱ ለሶሓቦቹ ምልክት ቢሰጥ ወይም ትእዛዝ ቢያዝ ሕይወታቸውን ቢያስከፍላቸውም እንኳ ለመፈጸም ይጥራሉ።
የቁረይሽ ማኅበረሰብ ሆይ! እጃችሁን ወደ ሰይፎቻችሁ ምንም ያህል ብትሰዱ፣ ዘዴዎችን ሁሉ ብትጠቀሙም እነርሱ የነብያቸውን አንዲት ጸጉር እንኳ አሳልፈው አይሰጧችሁም። እንዲያውም ምንም ጉዳት እንዲደርስበትና ማንም እንዲነካው እንኳ አይፈቅዱም። ሁኔታው ይህ ነው። ከዚህ በኋላ ያለውን በሚገባ አስቡበት! ነገሩ እንዲህ ሆኖ ሳለ ሙሐመድ መልካም የዕርቅ ስምምነት እያቀረበልን ነው፤ ተጠቀሙበት!»
የቁረይሽ አጋሪዎች ይህን ቃል አልተቀበሉም፤ በዑርዋ ላይ ሻካራ ጠባይ አሳይተው አስቀየሙት። ከቁረይሽ የጦር ሰፈር ምንም ወሬ ባልመጣ ጊዜ ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሐሳባቸውን እንዲደግሙ ኺራሽ ኢብኑ ኡመያን መልዕክተኛ አድርገው ላኩ። አጋሪዎች በእስልምና መልዕክተኛ ላይ እጅግ ሻካራ ጠባይ አሳዩ። ግመላቸውን አርደው በሉ፤ ራሳቸውንም ሊገድሏቸው ተነሡባቸው። ከእጃቸው በችግር ያመለጡት ኺራሽ ኢብኑ ኡመያ ክቡር ነብያችን ፊት መጥተው የሆነውን በተረኩ ጊዜ በመልዕክተኛቸው ላይ በደረሰው በዚህ ውርደት እጅግ አዘኑ። በዚህ ጊዜ ከአጋሪዎቹ የጦር ሰፈር የአሓቢሽ ጎሳ አለቃ ሑለይስ ታየ። ወደ ክቡር ነብያችን እየመጣ ነበር። አጋሪዎች መልዕክተኛ አድርገው መድበውት ነበር። ውዱ ነብያችን ሑለይስ ሲመጣ ባዩ ጊዜ፦ «ይህ የሚመጣው ሰው ለእርድ እንስሳት አክብሮት ከሚያሳዩ፣ የአላሁ ተዓላን ትእዛዛት ለመፈጸምና ዒባዳ ለማድረግ ከሚተጉ ሕዝቦች ነው። (ሶሓቦቼ ሆይ!) የእርድ ግመሎቹን ወደ እርሱ ንዷቸው፤ ይያቸው!» አሉ። ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች የእርድ ግመሎቹን ወደ እርሱ ለቀቁ፤ «ለበይክ፣ አላሁመ ለበይክ!» እያሉም ተልቢያ አሉ። ሑለይስ አንገታቸው የታሰረውንና ጆሮአቸው ምልክት የተደረገበትን የእርድ እንስሳት ባየ ጊዜ ለረጅም ጊዜ ተመለከታቸው። ዓይኖቹ እንባ አቀረሩ፤ ከነፍሱ ጥልቀት በሚወጣ በሐዘን ድምፅ፦ «ሙስሊሞች ካዕባን ጠዋፍ ከማድረግና ከመጎብኘት በቀር ሌላ ምንም ዓላማ የላቸውም። እነርሱን ከዚህ መከልከል ምንኛ መጥፎ ድርጊት ነው! በካዕባ ጌታ እምላለሁ፤ ቁረይሾች በዚህ የተሳሳተ ድርጊታቸው ምክንያት ይጠፋሉ!» ከማለት ራሱን መግታት አልቻለም። ይህን ቃል የሰሙት የዓለማት ሰይድ፦ «አዎን፣ እንዲሁ ነው፤ የኪናና ልጆች ወገን የሆንክ ወንድም ሆይ!» አሉ። ሑለይስ ከኀፍረቱ የተነሣ ክቡር ረሱሉላህ ፊት መምጣት እንዳልቻለ ሁሉ የተባረከ ፊታቸውንም እንኳ ማየት አልቻለም። ወደ ቁረይሽ የጦር ሰፈር ተመለሰ። ያየውን ተርኮ፦ «እርሳቸውን ካዕባን እንዳይጎበኙ መከልከላችሁን ትክክል ሆኖ አላገኘሁትም» ብሎ ሐሳቡን በግልጽ ተናገረ። የቁረይሽ አጋሪዎች እጅግ ተናደዱ፤ ሑለይስንም በድንቁርና ከሰሱት።
«ዑርዋ ሆይ! ለአላህ ብለህ ተናገር! እነዚህ የእርድ ግመሎች እንዳይታረዱ፣ ይህች ካዕባ አል-ሙዐዘማም እንዳትጎበኝና ጠዋፍ እንዳይደረግባት መከልከል ይገባልን?» ሐዲስ ሸሪፍ
በዚህ ጊዜ አጋሪዎች በጭካኔው የታወቀውን ሚክረዝ ኢብኑ ሐፍስን መልዕክተኛ አድርገው ላኩ። እርሱም መልሱን አግኝቶ ተመለሰ። ከሚክረዝ መልዕክተኝነት በኋላ አጋሪዎች ሙስሊሞች ድንገተኛ ጥቃት ይሰነዝሩብናል ብለው በፍርሃት ተያዙ።
ክቡር ነብያችን ጉዳዩን በግማሽ መንገድ ለመተው አልፈለጉም፤ በቁረይሾች ዘንድ ተሰሚነት ያላቸውን ከሶሓቦቻቸው አንዱን መላክ ፈለጉ። በመጨረሻም ሰይዲና ዑስማንን ለመላክ ተወሰነ። ውዱ ነብያችን ለዑስማን ኢብኑ ዐፋን፦ «‹እኛ ወደዚህ የመጣነው ከማንም ጋር ለመዋጋት አይደለም። የመጣነው ካዕባ አል-ሙዐዘማን ጠዋፍ ለማድረግና ለመጎብኘት ብቻ ነው። ከእኛ ጋር ያሉትን የእርድ ግመሎች አርደን እንመለሳለን› ብለህ ንገራቸው፤ ወደ እስልምናም ጥራቸው!» አሏቸው። በተጨማሪም በመካ ላሉ ሙስሊሞች መካ በቅርቡ እንደምትያዝ የምሥራች እንዲያደርሱ አሳሰቧቸው።3
ሰይዲና ዑስማን ወደ አጋሪዎች ሄደው የክቡር ነብያችንን ቃል በትክክል ነገሯቸው። እነርሱ ሰይዲና ዑስማን ላቀረቡትም ሐሳብ አሉታዊ መልስ ሰጡ። ከፈለጉ እርሳቸው ብቻ በይቱላህን ጠዋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ነገሯቸው። ሰይዲና ዑስማን ግን፦ «መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም በይቱላህን ጠዋፍ እስካላደረጉ ድረስ እኔም አላደርግም!» አሉ። በዚህ እጅግ የተናደዱት አጋሪዎች ያዟቸው። ይህ ወሬ ለሶሓቦች «ዑስማን ሸሂድ ሆኑ» በሚል መልክ ደረሰ። ሁኔታውን ለክቡር ነብያችን ባሳወቁ ጊዜ እጅግ አዘኑና፦ «ይህ ወሬ እውነት ከሆነ ከዚህ ሕዝብ ጋር ሳንዋጋ ከዚህ አንለይም» አሉ። ከዚያም እዚያ በነበረው ሰሙራ በሚባል ዛፍ ሥር ተቀምጠው፦ «አላሁ ተዓላ በይዐ እንድትገቡልኝ አዘዘኝ» ብለው ሶሓቦቻቸውን ወደ በይዐ ጠሩ። ጀግኖቹ ሶሓቦች እጃቸውን በክቡር ነብያችን የተባረከ እጅ ላይ አኑረው፦ «አላሁ ተዓላ ድልን እስኪለግስዎ ድረስ በፊትዎ እየተዋጋን ድሉን እውን ለማድረግ ወይም በዚህ መንገድ ሸሂድ ለመሆን በይዐ ገባን!» ብለው ቃል ሰጡ። ክቡር ነብያችን አንዱን እጃቸውን በሌላው እጃቸው ላይ አድርገው እዚያ በሌሉት በሰይዲና ዑስማን ስም ራሳቸው በይዐ ገቡ። ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በሶሓቦቻቸው በዚህ በይዐ እጅግ ተደስተው፦ «ከዛፉ ሥር በእውነት በይዐ ከገቡት አንዳቸውም ጀሀነም አይገቡም» አሉ። ይህ በይዐ በይዐቱ ሪድዋን ተባለ።4 ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች (ረዲየላሁ ዐንሁም) ሰይፎቻቸውን መዝዘው በቦታቸው መቆየት አቅቷቸው የመልዕክተኛውን ዐለይሂ ሰላም ምልክት ይጠብቁ ነበር። በዚህ ጊዜ የእስልምናን የጦር ሰፈር ይሰልሉ የነበሩት የቁረይሽ ሰላዮች ሙጃሂዶቹ በዚህ መንገድ የሸሂድነትን ሸርባት እስኪጠጡ ድረስ ለመዋጋት ለውዱ ነብያችን በይዐ መግባታቸውንና ዝግጅት ማድረጋቸውን አይተው ነበር። ወዲያውኑ ወደ ቁረይሽ የጦር ሰፈር ሄደው የሆነውን ሁሉ ተረኩ። ክቡር ነብያችን ለማንኛውም ጥንቃቄ ብለው በሌሊት ሶሓቦቻቸውን የሚጠብቁ ዘቦችን ያቆሙ ነበር። ሰይዲና ዑስማን ታስረው በነበሩባቸው ቀናት በአንዱ ሌሊት በሚክረዝ የሚመራ ሃምሳ ሰዎች ያሉት የአጋሪዎች ቡድን የእስልምናን ወታደሮች በእንቅልፋቸው ላይ ድንገት ለመምታት ጥቃት ሰነዘረ። በዚያ ሌሊት ሙሐመድ ኢብኑ መስለማና ጓደኞቻቸው ዘብ ይጠብቁ ነበር። የመጡትን ከሓዲዎች ከአጭር ግጭት በኋላ ጥፍር አድርገው ያዟቸው። ሚክረዝ ብቻ ማምለጥ ቻለ። ምርኮኞቹን ክቡር ረሱሉላህ ፊት አመጧቸው። ከፊሎቹ ታሰሩ፤ ከፊሎቹ ደግሞ ይቅርታ ተደረገላቸው። አጋሪዎች በማግሥቱ ሌሊትም ድንገተኛ ጥቃት ለመሰንዘር ፈለጉ፤ ነገር ግን እንደገና ተያዙ። ክቡር ነብያችን እነርሱንም ይቅር ብለው ለቀቋቸው።
የሑደይቢያ ስምምነት
የእስልምና ሠራዊት ቀንና ሌሊት ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ እንደቆመና በማንኛውም ጊዜ ጥቃት ሊሰነዝር እንደሚችል የተረዱት የከሓዲዎች ሠራዊት ልብ በፍርሃት ተሞላ። ከስምምነት ውጭ ሌላ መውጫ መንገድ እንደሌለ ሲያዩ በችኮላ የልዑካን ቡድን መረጡ። በሱሀይል ኢብኑ ዐምር መሪነት ለተመረጠው ለዚህ ቡድን፦ «ዘንድሮ ወደ መካ እንዳይገቡ በሚል ቅድመ ሁኔታ ስምምነት አድርጉ» ተባለ።
ውዱ ነብያችን የቁረይሽን ልዑካን ተቀበሉ። የልዑካኑ የመጀመሪያ ጥያቄ የታሰሩ ሰዎቻቸው እንዲለቀቁ ነበር። የዓለማት ሰይድም፦ «በመካ የያዛችኋቸውን ሶሓቦቼን እስካልፈታችሁ ድረስ እነዚህን ሰዎቻችሁን አልለቅም!» አሉ። ሱሀይል፦ «እውነቱን ለመናገር በእኛ ላይ ያሳየኸው አያያዝ እጅግ ፍትሐዊና ትክክለኛ ነበር» ብሎ በመካ ታስረው የነበሩት ሰይዲና ዑስማንና ቀደም ሲል ያሰሯቸው ወደ አሥር የሚሆኑ ሶሓቦች እንዲለቀቁ አደረገ። ከዚያም በጥቃቱ ጊዜ ተይዘው የታሰሩት አጋሪዎች ተለቀቁ።
ከረጅም ንግግር በኋላ ስምምነት ላይ ተደረሰ። አሁን የሚቀረው መጻፍ ነበር። ጸሐፊ ሆነው ሰይዲና ዐሊይ ተመረጡ። የዕርቅ ስምምነቱን ለመጻፍ ወረቀትና የቀለም ዕቃ ተዘጋጀ። ለዓለማት እዝነት ሆነው የተላኩት ሐቢቡላህ ለሰይዲና ዐሊይ፦ «ጻፍ፦
‹ቢስሚላሂ ረሕማኒ ረሒም!›» አሉ። ሱሀይል ወዲያውኑ ተቃወመ፦ «እምላለሁ፣ ‹ረሕማን› የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም። እንዲህ አትጻፍ፤ ‹ቢስሚከ አላሁመ› ብለህ ጻፍ! አለበለዚያ ወደ ዕርቁ አልቀርብም!» ክቡር ነብያችን በዕርቁ መደረግ እጅግ ታላቅ ጥበቦችን ያዩ ነበር። ስለዚህ፦ «‹ቢስሚከ አላሁመ› የሚለውም መልካም ነው» አሉ፤ ለሰይዲና ዐሊይም እንዲሁ እንዲጽፉ አዘዙ። ከተጻፈ በኋላ ክቡር ነብያችን፦ «ይህ ሙሐመድ ረሱሉላህ ከሱሀይል ኢብኑ ዐምር ጋር የተስማሙባቸው፣ የዕርቅ ስምምነት ያደረጉባቸውና ቅድመ ሁኔታዎቹ በሁለቱ ወገኖች እንዲፈጸሙ የፈረሙባቸው ድንጋጌዎች ናቸው» ባሉ ጊዜ ሱሀይል የሰይዲና ዐሊይን እጅ ሲይዝ ታየ። ወደ ክቡር ነብያችን ዘወር ብሎ፦ «እምላለን፣ አንተ ረሱሉላህ መሆንህን ብንቀበል ኖሮ አንቃወምህም ነበር፤ ካዕባን እንዳትጎበኝም አንከለክልህም ነበር። ስለዚህ ‹ረሱሉላህ› ከሚለው ፈንታ ‹የዐብዱላህ ልጅ ሙሐመድ› ብለህ ጻፍ!» አለ።
ክቡር ነብያችን ይህንንም ተቀብለው እንዲህ አሉ፦ «በአላህ እምላለሁ፣ ብታስተባብሉኝም እኔ ያለ ምንም ጥርጥር የአላሁ ተዓላ መልዕክተኛ ነኝ። ስሜንና የአባቴን ስም ማስጻፍ ነብይነቴን አያስወግድም። ዐሊይ ሆይ! ይህን ደምስሰው፤ ‹ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱላህ› ብለህ ጻፍ»።
ከክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች የአንዳቸውም ልብ «ረሱሉላህ» የሚለው ቃል መደምሰሱን አልተቀበለውም። በቅጽበት ሁሉን ረስተው፦ «ዐሊይ ሆይ! ‹ሙሐመድ ረሱሉላህ› ብለህ ጻፍ፤ አለበለዚያ በእኛና በእነዚህ አጋሪዎች መካከል ያለውን ጉዳይ የሚወስነው ሰይፍ ብቻ ነው!…» አሉ። ክቡር ነብያችን በሶሓቦቻቸው በዚህ ወኔ ተደሰቱ፤ ነገር ግን በተባረኩ እጆቻቸው ዝም እንዲሉ ጠቆሟቸው። ለሰይዲና ዐሊይ እንዲደመስሱት ባዘዟቸው ጊዜ እርሳቸው፦ «ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! የእርስዎን ይህን የተባረከ ማዕረግ ለመደምሰስ እጄ አይታዘዝልኝም!…» ብለው ይቅርታ ጠየቁ። ውዱ ነብያችን ቦታውን እንዲያሳዩ ጠየቁ። ባሳዩ ጊዜ ጽሑፉን ከእጃቸው ተቀብለው በራሳቸው የተባረከ ጣት ደመሰሱት፤ «የዐብዱላህ ልጅ» ብለውም አስጻፉ። ከዚያም ድንጋጌዎቹን መጻፍ ጀመሩ፦ 1) ስምምነቱ ለአሥር ዓመት የሚጸና ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁለቱ ወገኖች እርስ በርስ አይዋጉም።
«ከዛፉ ሥር በእውነት በይዐ ከገቡት አንዳቸውም ጀሀነም አይገቡም» ሐዲስ ሸሪፍ
ሙስሊሞች በዚህ ዓመት ካዕባን አይጎበኙም፤ ነገር ግን ከአንድ ዓመት በኋላ ሊጎበኙ ይችላሉ። 3) ካዕባን ለመጎብኘት የሚመጡ ሙስሊሞች ሦስት ቀን ይቆያሉ፤ ከመንገደኛ የጦር መሣሪያ በቀር ሌላ የጦር መሣሪያ አይዙም። 4) ሙስሊሞች ካዕባን ጠዋፍ በሚያደርጉበት ጊዜ የመካ አጋሪዎች ከካዕባ ወጥተው ሙስሊሞች በነጻነት ጠዋፍ እንዲያደርጉ ያስችላሉ።
ከቁረይሽ ሙስሊም የሆነ ሰው ያለ ሞግዚቱ ፈቃድ ወደ መዲና ቢሄድ ይመለሳል፤ ከሙስሊሞች አንዱ ወደ ቁረይሽ ወገን ተሻግሮ ወደ መካ ቢሄድ ግን አይመለስም። ሰይዲና ዑመር ስለዚህ ድንጋጌ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ይህን ቅድመ ሁኔታም ይቀበላሉን?» ብለው ሲጠይቁ ውዱ ነብያችን ፈገግ ብለው፦ «አዎ። ከእኛ ወደ እነርሱ የሚሄዱትን አላሁ ተዓላ ከእኛ ያርቃቸው!» አሉ።
ከሶሓቦች አንዱ ሐጅ ወይም ዑምራ የማድረግ ሐሳብ ይዞ ወደ መካ ቢመጣ ነፍሱና ንብረቱ አስተማማኝ ይሆናል።
ከአጋሪዎች አንዱ ወደ ሻም፣ ወደ ግብጽ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ሲሄድ መዲናን ቢያልፍ የእርሱም ነፍስና ንብረት አስተማማኝ ይሆናል።
ሌሎች የዓረብ ጎሳዎች የፈለጉትን ወገን ጥበቃ መግባት ይችላሉ፤ ከሙስሊሞችም ሆነ ከአጋሪዎች ጋር ለመተባበር ነጻ ይሆናሉ።5
የስምምነቱ መፈረም ተራ ደረሰ። በዚያን ጊዜ እግሮቹ ላይ ያሉትን ሰንሰለቶች እየጎተተ አንድ ሰው ወደ እስልምና ሠራዊት ሲመጣ ታየ። እየቀረበ ሄደና፦ «አድኑኝ!…» ብሎ ጮኸ። ይህን ድምፅ የሰማው የቁረይሽ ልዑካን መሪ ወዲያውኑ ከቦታው ዘለለ። በእጁ የያዘውን እሾሃማ የዛፍ ቅርንጫፍ በሰውየው ራስና ፊት ላይ መምታት ጀመረ። ሰውየው ያለውን ኃይል ሁሉ አሰባስቦ ራሱን በክቡር ረሱሉላህ የተባረኩ ጉልበቶች ሥር ወረወረና፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ያድኑኝ!» ብሎ ለመነ። ይህ በመካ በእስልምና ክብር በማግኘቱ ምክንያት በአባቱ በሰንሰለት የታሰረ አንድ ሙስሊም ነበር። በየቀኑ ከባድ ስቃይ ይደርስበት፣ ጣዖታትንም እንዲያመልክ ይገደድ ነበር። አጋሪዎች ወደ ሑደይቢያ መሄዳቸውን ተጠቅሞ ሰንሰለቶቹን በጥሶ ነበር፤ ማንም ሳያየው ከመካ ወጥቶ በሙስሊሞች መካከል ራሱን ጣለ። ቅኑን መንገድ ያገኙት እኚህ የተባረኩ ሰው የአጋሪዎች ልዑካን መሪ የሱሀይል ልጅ ሰይዲና አቡ ጀንደል ነበሩ። ሱሀይል ለክቡር ነብያችን ልጁን አቡ ጀንደልን እያመለከተ፦ «አሁን በጻፍነው ስምምነት መሠረት ልትመልስልኝ የሚገባህ የመጀመሪያው ሰው ይህ ነው!» አለ።
ክቡር ነብያችንም ሶሓቦችም እጅግ አዘኑ። ሁሉም ክቡር ረሱሉላህ ምን መልስ እንደሚሰጡ በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። በአንድ በኩል የዕርቅ ስምምነቱ፣ በሌላ በኩል በስቃይ ውስጥ ያለ አንድ ሶሓቢይ… የዓለማት ሰይድ ለሱሀይል፦ «እኛ ይህን የዕርቅ ስምምነት ገና አልፈረምንም!» አሉ። ሱሀይል በግትርነት፦ «ሙሐመድ ሆይ! የስምምነቱን ድንጋጌዎች ልጄ ወደዚህ ከመምጣቱ በፊት ጽፈን ጨርሰን ነበር። ልጄን የማትመልስ ከሆነ እኔ በፍጹም ይህን የዕርቅ ስምምነት አልፈርምም!» አለ። ክቡር ነብያችን፦ «ለእኔ ስትል እርሱን ከስምምነቱ ውጭ አድርገው» ቢሉም አጋሪዎች ይህን አልተቀበሉም። ሱሀይል ኢብኑ ዐምር ልጁን እየጎተተ ሲወስደው አቡ ጀንደል፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! የሙስሊም ወንድሞቼ ሆይ!… በእስልምና ክብር አግኝቼ ወደ እናንተ የተጠጋሁ ሆኜ ሳለሁ ለአጋሪዎች አሳልፋችሁ ትሰጡኛላችሁን? በየቀኑ የማይቻል ስቃይ እንዲደርስብኝ ትፈቅዳላችሁን? የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከሃይማኖቴ እንዲመልሱኝ ብለው ነው የሚመልሱኝ?!…» እያሉ ይጮኹ ነበር።
ይህን ልብ የሚሰብር ልመና መሸከም እጅግ ከባድ ነበር። ልባቸው የቆሰለ ሶሓቦች ማልቀስ ጀመሩ። የምሕረት ውቅያኖስ የሆኑት የውዱ ነብያችንም የተባረኩ ዓይኖች በእንባ ተሞሉ። ወደ ሱሀይል ሄደው፦ «እንዲህ አታድርግ! እርሱን ለእኔ ስጦታ አድርገህ ስጠኝ!» ብለው ጠየቁት። ሱሀይል ግን፦ «የማይቻል ነው፤ አልሰጥም!» ብሎ መለሰ። ከዚያም ውዱ ነብያችን አቡ ጀንደልን አጽናንተው፦ «አቡ ጀንደል ሆይ! ጥቂት ጊዜ ተጨማሪ ታገሥ! በአንተ ላይ የሚደረገውን ተሸከም! የዚህን ምንዳ ከአላሁ ተዓላ ጠይቅ። አላሁ ተዓላ ለአንተና ለአንተ ዓይነት ደካማና ረዳት ለሌላቸው ሙስሊሞች በእርግጥ ምቾትና መውጫ መንገድ ይሰጣል» አሉ፤ ከዚያም፦ «የሰጠነውን ቃል አለመጠበቅ ለእኛ አይገባንም» አሉ። አቡ ጀንደል፦ «መልካም፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ» ብለው እንደሚታገሡ አሳወቁ።
ይህን ልብ የሚሰብር ክስተት በልዑካኑ ቡድን ውስጥ የነበሩ አጋሪዎች እንኳ ሊሸከሙት አልቻሉም፤ እንዲህም አሉ፦ «ሙሐመድ ሆይ! ለአንተ ክብር ስንል አቡ ጀንደልን በጥበቃችን ሥር እናደርገዋለን። ሱሀይል እንዲያሰቃየው አንፈቅድም!»
ከዚያ በኋላ ክቡር ረሱሉላህና ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች ጥቂት ተረጋጉ። (ሱሀይል ኢብኑ ዐምር ከመካ ድል በኋላ ሙስሊም ሆነው ከክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች ሆኑ።) የዕርቅ ስምምነቱ በሁለት ቅጂ ተጻፈ፤ ሁለቱም ወገኖች ፈረሙበት። አጋሪዎች ወደ ሰፈራቸው ተመለሱ።6 የቁረይሽ ልዑካን ለሙስሊሞች የማይጠቅሙ በሚመስሉ በእነዚህ ድንጋጌዎች እጅግ ደስ ብሏቸው ነበር። ነገር ግን በተቃራኒው ይህ የዕርቅ ስምምነት ለምእመናን ታላቅ ድል ነበር፤ ድንጋጌዎቹም ለሙስሊሞች የሚጠቅሙ ነበሩ። ከሁሉ በፊት አጋሪዎች ሙስሊሞች መንግሥት መሆናቸውን ተቀበሉ። ከመካ የሆነ አጋሪ ለንግድም ሆነ ለሌላ ነገር ወደ ሻም ወይም ወደ ግብጽ ሲሄድ መዲናን ቢያልፍ ነፍሱና ንብረቱ አስተማማኝ ይሆን ነበር። በዚህ መንገድ አጋሪዎች የሙስሊሞችን አኗኗር ከቅርብ ያዩ፣ በእስልምና ፍትሕና በሶሓቦች እርስ በርስ ባላቸው መልካም ጠባይ ይደነቁ፣ እስልምናንም ይወዱ ነበር። በመጨረሻም ሙስሊም ሆነው በሶሓቦች ሰልፍ መካከል ይቀላቀሉ ነበር። ለአሥር ዓመት ሊቆይ በሚገባው በዚህ ስምምነት ሙስሊሞች ይበዙ፣ ይጠነክሩም ነበር። እስልምና በየአቅጣጫው ይሰፋ ነበር። ነገር ግን «ከቁረይሾች አንዱ ሙስሊም ሆኖ መዲና ለመጠለል ቢፈልግ ይመለሳል» የሚለው ድንጋጌ ክቡር ነብያችንን እጅግ አሳዘናቸው፤ እርሳቸውም፦ «አላሁ ተዓላ ለእነርሱ በእርግጥ ምቾትንና መውጫ መንገድን ይፈጥርላቸዋል» አሉ። ከአጋሪዎች ጋር የሚደረግ ሌላ ጉዳይ አልቀረም ነበር። ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ለክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች፦ «ተነሡ! የእርድ እንስሳዎቻችሁን እረዱ። ራሳችሁን ከተላጫችሁ በኋላ ከኢሕራም ውጡ» አሉ። ክቡር ነብያችን ከሁሉም በፊት የራሳቸውን የእርድ እንስሳ አረዱ። ከዚያም ጸጉር አስተካካያቸው ሰይዲና ኺራሽ ኢብኑ ኡመያ የእርሳቸውን ራስ ላጩ። ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች እነዚያን የተባረኩ ጸጉሮች መሬት ሳይነኩ በአየር ላይ ነጠቁ፤ ለበረከትም አስቀመጧቸው። ሶሓቦችም የእርድ እንስሳዎቻቸውን አረዱ፤ ከፊሎቹ ራሳቸውን ተላጩ፣ ከፊሎቹ አሳጠሩ።7
«አቡ ጀንደል ሆይ! ጥቂት ጊዜ ተጨማሪ ታገሥ! በአንተ ላይ የሚደረገውን ተሸከም! የዚህን ምንዳ ከአላሁ ተዓላ ጠይቅ። አላሁ ተዓላ ለአንተና ለአንተ ዓይነት ደካማና ረዳት ለሌላቸው ሙስሊሞች በእርግጥ ምቾትና መውጫ መንገድ ይሰጣል» ሐዲስ ሸሪፍ
በሑደይቢያ ወደ ሃያ ቀን ያህል ቆዩ። ክቡር ነብያችን ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ መዲና ለመመለስ ተነሡ። በመንገድ ላይ አላሁ ተዓላ ለክቡር ነብያችን ሱረቱ አል-ፈትሕን አወረደ፤ ጸጋውንና እርዳታውን እንደሚያሟላም የምሥራች አበሠረ። የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በድል አድራጊነት ወደ ብርሃናማዋ መዲና በመጡባቸው ቀናት ከቁረይሽ የሰቂፍ ጎሳ የሆኑት አቡ በሲር በእስልምና ተከበሩ። በአጋሪዎች መካከል መኖር እንደማይችሉ የተረዱት አቡ በሲር በእግራቸው ወደ መዲና መጡ። ነገር ግን የሑደይቢያ ስምምነት እንደሚያስፈልገው ከመዲና ወጥተው በቀይ ባሕር ዳርቻ ዒስ በሚባል ቦታ ተቀመጡ።8
ይህ ቦታ የቁረይሽ አጋሪዎች ወደ ሻም በሚሄዱበት የንግድ መንገድ ላይ ነበር። ከዚህ በኋላ ከቁረይሽ ሙስሊም የሆኑ ሰዎች መካን ትተው ወደ መዲና ሳይሆን ወደ ዒስ፣ ወደ አቡ በሲር ሄዱ። ከእነርሱ የመጀመሪያው ሰይዲና አቡ ጀንደል ነበሩ። ከዚያም ይህ አላቋረጠም። ሃምሳ፣ መቶ፣ ሁለት መቶ፣ ሦስት መቶ ሰዎች ሆኑ። የቁረይሽ የንግድ ተጓዥ ቡድን ወደ ሻም ሲሄድ ከዚህ ቦታ ማለፍ ግዴታው ነበር። ሰይዲና አቡ በሲርና ከእርሳቸው ጋር የነበሩት ሙስሊሞች ከዚህ የሚያልፉ አጋሪዎችን ይይዙና ሙስሊም እንዲሆኑ ይጠይቋቸው ነበር። ሙስሊም ያልሆኑትን ይዋጉና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይተዋቸው ነበር። የሻም የንግድ መንገዶች መቋረጣቸውን ያዩት የመካ አጋሪዎች ወደ መዲና የልዑካን ቡድን ላኩ። እነርሱም በሑደይቢያ የዕርቅ ስምምነት ውስጥ ያለው «ከቁረይሽ ሙስሊም የሆነ ሰው ያለ ሞግዚቱ ፈቃድ ወደ መዲና ቢሄድ ይመለሳል!…» የሚለው ድንጋጌ እንዲሰረዝ ለመኑ። ክቡር ነብያችን ራርተው ይህን ጥያቄያቸውን ተቀበሉ። በዚህ መንገድ ለቁረይሾች ወደ ሻም የሚወስደው የንግድ መንገድ እንደገና ተከፈተ። ሙስሊሞችም ለትዕግሥታቸው ምንዳ ሆኖ ወደ መዲና፣ ወደ ክቡር ነብያችን ዘንድ መጡ።
የውበት ሁሉ ውበት ሆይ!
የውበት ሁሉ ውበት ሆይ፣ በፍቅርዎ አቃጠሉኝ!
ዓይኔ ምንም አያይም፤ አእምሮዬ በየአፍታው በሐሳብዎ ተመስጧል!
እርስዎ የ‹ቃበ ቀውሰይን› መሪ ነዎት፣ እኔ ግን አመፀኛ ባሪያ፤
ይህ የተደነቀ ሰው «እንግዳዎ ነኝ» ብሎ እንዴት ይደፍር?
በአንዲት የምሕረት እይታ ሙት ልቦችን አስነሡ፤
ወደ ማያልቀው ምሕረትዎ ተጠግቼ በርዎን አንኳኳሁ!
እርስዎ የበጎነት ምንጭ፣ የፈውስ ውቅያኖስ ነዎት!
አንዲት ጠብታ ችሮታዎን ለግሱኝ፤ ለሕመሜ መድኃኒት አጣሁ!
ሰው ሁሉ ወደ መካ ይመጣል፤ ወደ ካዕባ፣ ወደ ሶፋና መርዋ፤
እኔ ግን ለእርስዎ ብዬ ተራሮችንና ኮረብቶችን ተሻገርኩ!
ትናንት ሌሊት በሕልም ራሴ ሰማያትን ነካ፤
በደጅዎ ያሉ አገልጋዮች አንገቴን የረገጡኝ መሰለኝ!
የውዴ ዘማሪ ወፍ ጃሚ ሆይ!
ከግጥሞችዎ መካከል ይህችን ስንኝ መረጥኩ፦
«ምላሳቸው የተንጠለጠለ እከካም ውሾች እንደሆኑ፣
አንዲት ጠብታ ተስፋ አድርጌ ወደ ችሮታዎ ውቅያኖስ መጣሁ።»
ማውላና ኻሊድ ባግዳዲ (ቁዲሰ ሲሩሁ)
«እኛ በእርግጥ ለአንተ ግልጽ ድልን ሰጠንህ» ፈትሕ: 1
የክቡር ረሱሉላህ የጥሪ ደብዳቤዎች
ፀሐይ ለዓለም ባልበራች ነበር፣
ያ ውድ ነፍስ ባይመጡ ኖሮ፤
ለዓለም ብርሃን ባልሰጠች ነበር፣
የተባረከው የልደት ሰዓት ባይደርስ ኖሮ።
የጽጌረዳ ፊታቸው በክሪስታልና በደስታ፣
ባልተቦካ ነበር፤
በልቦች ላይ በሚያንጸባርቅ ብርሃን፣
አካል ሆነው ባይገለጡ ኖሮ።
Eyyübî
