ውዱ ነብዬ

የበድር ጦርነት

ይህ ዘመቻ ሁለተኛው በድር፣ በድሩል ቂታል እና በድሩል ኩብራ ተብሎም ይጠራል። ሶሓቦች በሰሪያዎቹ ያገኙት ስኬት ከሓዲዎችን ማስፈራራት ጀመረ። ከዚያ ወዲህ ቅፍለቶቻቸው በቡድን በቡድን ሆነውና ወታደሮችን አስከትለው ለጉዞ ይወጡ ነበር። በሂጅራ ሁለተኛው ዓመት የመካ አጋሪዎች ከየቤተሰቡ ገንዘብ ሰብስበው አንድ ሺህ ግመሎች ያሉት ቅፍለት ወደ ደማስቆ ላኩ። በመሪነቱም ከመካ ታላላቅ ሰዎች አንዱ የሆነው አቡ ሱፍያን ነበር፤ እርሱም ገና ሙስሊም አልሆነም ነበር።1 ቅፍለቱን ለመጠበቅ አርባ ያህል ጠባቂዎችም ተመድበው ነበር… ሸቀጦቹ ከተሸጡ በኋላ በገንዘቡ በሙሉ መሣሪያ ሊገዙ ነበር፤ እነዚህም ከሙስሊሞች ጋር በሚደረገው ጦርነት ሊውሉ ነበር።

ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አጋሪዎች ታላቅ ቅፍለትን ለንግድ ወደ ደማስቆ እንደላኩ በሰሙ ጊዜ ሁኔታቸውን እንዲያጣሩ ከሙሃጂሮች ጥቂት ሰዎችን መደቡ። እነርሱም ዙል ዑሸይራ ወደሚባለው ቦታ በደረሱ ጊዜ ቅፍለቱ ማለፉን ተረድተው ወደ መዲና ተመለሱ። የክህደት ሰዎች መሣሪያቸውና ንብረታቸው ከእጃቸው ቢወሰድ በእስልምና ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረስ አይችሉም ነበር፤ ተቃውሟቸውም ይሰበር ነበር። ስለዚህ ክቡር ረሱሉላህ ሁኔታውን ገምግመው ወዲያውኑ የጦርነት ዝግጅት ጀመሩ።

በእርሳቸው ፈንታ ሶላትን እንዲያሰግዱ ዐብዱላህ ኢብኑ ኡሙ መክቱምን ተዉ።2 ሰይዲና ጦልሐ ኢብኑ ዑበይዲላህንና ሰይዲና ሰዒድ ኢብኑ ዘይድን ደግሞ የቅፍለቱን መመለስ እንዲያጣሩ ሰላዮች አድርገው ላኳቸው።3 የሰይዲና ዑስማን ባለቤት ክፉኛ ታመው ስለነበር እርሳቸው በመዲና እንዲቆዩ አዘዙ። ከዚያም ለአራት ተጨማሪ ሰዎች ተልእኮ ሰጡ። በዚህም ተልእኮ የተሰጣቸው ሰዎች ስምንት ሆኑ።

ይህ አጋጣሚ የሚያመልጥ አልነበረም። ክቡር ነብያችን ወዲያውኑ ተዘጋጅተው ከሙሃጂሮችና ከአንሷሮች ሦስት መቶ አምስት ሶሓቦችን ይዘው በተከበረው የረመዳን ወር በአሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ በድር ተጓዙ። ተልእኮ ከተሰጣቸው ጋር ቁጥራቸው 313 ደረሰ።4 ከእነርሱም ስልሳ አራቱ ሙሃጂሮች ነበሩ።

በድር ወደ መካ፣ ወደ መዲናና ወደ ሶሪያ የሚሄዱ መንገዶች የሚገናኙበት ቦታ ነበር።

በዚህ የጦር ጉዞ ለመሳተፍ ገና ያደጉ ወጣቶች፣ ሴቶችም ጭምር ክቡር ነብያችንን ይማጸኑ ነበር። ኡሙ ወረቃ ወደ ክቡር ረሱሉላህ ዘንድ መጥተው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! አባቴና እናቴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ! ከፈቀዱልኝ ከእርስዎ ጋር መሄድ እፈልጋለሁ። የቆሰሉትን ቁስል እጠግናለሁ፤ የታመሙትንም አገለግላለሁ። ምናልባት አላሁ ተዓላ ለእኔም ሸሂድነትን ይለግሰኝ ይሆናል!» ባሉ ጊዜ ሐቢቡል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን)፦ «አንቺ በቤትሽ ተቀመጪ፤ ቁርኣን ከሪምን አንብቢ። ያለ ጥርጥር አላሁ ተዓላ ሸሂድነትን ይለግስሻል» አሉ።

«አንቺ (ኡሙ ወረቃ) በቤትሽ ተቀመጪ፤ ቁርኣን ከሪምን አንብቢ። ያለ ጥርጥር አላሁ ተዓላ ሸሂድነትን ይለግስሻል» ሐዲስ ሸሪፍ

ወደ በድር ጦርነት የተደረገው ጉዞ

ሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስ እንዲህ ብለው ተረኩ፦ «ክቡር ረሱሉላህ ከእኛ ጋር ለዘመቻ መሄድ የፈለጉትን ልጆች ለመመለስ በፈለጉ ጊዜ ወንድሜ ዑመይር እንዳይታይ በአንድ ጥግ ለመደበቅ ሲሞክር አየሁት። በዚያን ጊዜ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ነበር። ‹ምን ሆንክ፣ እንዲህ የምትደበቀው?› አልኩት። ‹ክቡር ረሱሉላህ እኔንም ልጅ ነህ ብለው እንዳይመልሱኝ እፈራለሁ! እኔ ግን በዘመቻው ተሳትፌ አላሁ ተዓላ ሸሂድነትን እንዲለግሰኝ እመኛለሁ› አለ። ስለ እርሱ ለክቡር ረሱሉላህ በነገሯቸው ጊዜ ወንድሜን፦ ‹አንተ ተመለስ› አሉት። ያን ጊዜ ወንድሜ ዑመይር ማልቀስ ጀመረ። የእዝነት ባሕር የሆኑት ሐቢቡል አክረም እንባውን መቋቋም አቅቷቸው ፈቀዱለት። ወንድሜ ሰይፉን ራሱ መታጠቅ ስላልቻለ በወገቡ ያሰርኩለት እኔ ነበርኩ።»5 የዓለማት ሰይድ የሆኑት የውዱ ነብያችንን ሰንደቅ ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር፣ ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝና ሰይዲና ዐሊይ ይዘው ነበር።6 ሶሓቦች ከእነርሱ ጋር ሦስት ፈረሶችና ሰባ ግመሎች ብቻ ነበሯቸው። ከፈረሶቹ አንዱ የሚቅዳድ፣ አንዱ የዙበይር፣ አንዱ ደግሞ የመርሰድ ኢብኑ አቢ መርሰድ ነበር። ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በአንድ ግመል እየተፈራረቁ ይጋልቡ ነበር። ክቡር ረሱሉላህ ከሰይዲና ዐሊይ፣ ከአቡ ሉባባና ከመርሰድ ኢብኑ አቢ መርሰድ ጋር እየተፈራረቁ ይጋልቡ ነበር። ነገር ግን ሁሉም መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም በእግራቸው እንዳይሄዱና ሁልጊዜ በግመሉ ላይ እንዲጓዙ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ነፍሳችን ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን! ከግመሉ አይውረዱ። በላቀው ማንነትዎ ፈንታ እኛ በእግራችን እንሄዳለን» እያሉ ይማጸኑ ነበር። የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን ግን ራሳቸውን ከእነርሱ የተለዩ አድርገው ሳይቆጥሩ፦ «እናንተ በእግር በመሄድ ከእኔ የበለጠ ብርቱዎች እንዳልሆናችሁ ሁሉ እኔም በምንዳና በሽልማት ረገድ ከእናንተ የተብቃቃሁና ምንም የማያስፈልገኝ አይደለሁም» አሉ። ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እና የላቁት ሶሓቦቻቸው በበረሃ በሚያቃጥል ሙቀት ሥር ይጓዙ ነበር። ከዚህም በላይ ጾመኞች ነበሩ። ሶሓቦች እስልምናን ለማስፋፋት ብዙ መከራዎችን ታግሠው ክቡር ነብያችንን በፍቅርና በጉጉት ይከተሉ ነበር። ምክንያቱም በመጨረሻው የአላሁ ተዓላና የመልዕክተኛው ውዴታ፣ እጅግ የሚናፍቁት ሸሂድነትና ጀነት ነበሩ… ውዱ ነብያችን የሶሓቦቻቸውን ሁኔታ ተመልክተው፦ «አላህ ሆይ! እነርሱ እግረኞች ናቸው፤ የሚጋልቡት እንስሳ ስጣቸው! አላህ ሆይ! እነርሱ የተራቆቱና እርቃናቸውን ናቸው፤ አልብሳቸው! አላህ ሆይ! እነርሱ ተርበዋል፤ አጥግባቸው! ድሆች ናቸው፤ በችሮታህና በልግስናህ ሀብታም አድርጋቸው!» ብለው ዱዓ አደረጉ።

ክቡር ነብያችንና የተባረከው ሠራዊታቸው በዚህ ኃይለኛ ሙቀት ሥር ወደ በድር ሲገሰግሱ ከደማስቆ የሚመጣው የአጋሪዎች ቅፍለትም ወደ በድር ቀርቦ ነበር። ክቡር ነብያችን ስለ ቅፍለቱ ወሬ እንዲያመጡ የላኳቸው ሁለት ሶሓቦች ቅፍለቱ በአንድ ወይም በሁለት ቀን ውስጥ በድር ሊደርስ እንደሚችል ተረድተው በፍጥነት ተመለሱ። የቅፍለቱ ሰዎች እነዚያ ሁለቱ ወሬውን ወደሰሙበት መንደር በደረሱ ጊዜ የመንደሩን ሰዎች፦ «ስለ ሙስሊሞች ሰላዮች የምታውቁት ነገር አለ?» ብለው ጠየቁ። እነርሱም፦ «አናውቅም። ነገር ግን ሁለት ሰዎች መጥተው እዚያ ትንሽ ተቀመጡ፤ ከዚያም ተነሥተው ሄዱ» አሉ።

አቡ ሱፍያን ወደተገለጸው ቦታ ሄዶ ሲመረምር መሬት ላይ የነበረውን የግመል ፋንድያ ፈጭቶ በውስጡ የመኖ ፍሬዎችን አየ፤ እንዲህም አለ፦ «ይህ የመዲና መኖ ነው፤ እነዚያ ሁለት ሰዎች የሙሐመድ (ዐለይሂ ሰላም) ሰላዮች ናቸው ብዬ እገምታለሁ።» ሙስሊሞች በጣም ቅርብ እንዳሉ ገምቶ በታላቅ ፍርሃት ተያዘ። ስለ ቅፍለቱ ዕጣ ፈንታ ተጨንቆ ሌሊትና ቀን እየተጓዘ ጊዜ ሳያጠፋ በቀይ ባሕር ዳርቻ በኩል በፍጥነት ወደ መካ ለመሄድ ወሰነ። በተጨማሪም ሁኔታውን እንዲያሳውቅ ደምደም ኢብኑ ዐምር አል-ጊፋሪ የተባለውን ሰው መልዕክተኛ አድርጎ ወደ መካ ላከ።7

«አላህ ሆይ! እነርሱ (ሶሓቦቼ) እግረኞች ናቸው፤ የሚጋልቡት እንስሳ ስጣቸው! አላህ ሆይ! እነርሱ የተራቆቱና እርቃናቸውን ናቸው፤ አልብሳቸው! አላህ ሆይ! እነርሱ ተርበዋል፤ አጥግባቸው! ድሆች ናቸው፤ በችሮታህና በልግስናህ ሀብታም አድርጋቸው!» ሐዲስ ሸሪፍ

ይህ ሰው መካ በደረሰ ጊዜ ሸሚዙን ከፊትና ከኋላ ቀደደ። የግመሉን ኮርቻ ገለበጠ። በሚያስገርም ሁኔታ፦ «ድረሱልኝ! ድረሱ!… የቁረይሽ ሰዎች ሆይ! ድረሱ!… ቅፍለታችሁን፣ ከአቡ ሱፍያን ጋር ያለውን ንብረታችሁን ሙሐመድና ሶሓቦቹ አጠቁ። መድረስ ከቻላችሁ ቅፍለታችሁን ልታድኑ ትችላላችሁ!…» እያለ ዋይታና ጩኸት ያሰማ ጀመር።

ይህን የሰሙት የመካ ሰዎች ወዲያውኑ ተሰባስበው ዝግጅታቸውን አደረጉ። ሰባት መቶ ግመለኞችን፣ መቶ ፈረሰኞችንና መቶ ሃምሳ እግረኞችን አሰባሰቡ። አቡ ለሀብን፦ «ና፣ አንተም ተቀላቀል!» ባሉት ጊዜ ከፍርሃቱ የተነሣ ሕመሙን ሰበብ አደረገ። በእርሱ ፈንታ ዓስ ኢብኑ ሂሻምን ተክቶ ላከ። ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ የተባለው አጋሪ ለጦርነቱ በመዘጋጀት እጅግ ይዳተት ነበር። ምክንያቱም ክቡር ነብያችን፦ «ሶሓቦቼ ኡመያን ይገድሉታል» ማለታቸውን ሰምቶ ነበር። እርሳቸው ፈጽሞ ከእውነት እንደማይወጡ ያውቅ ስለነበር ፈራ። ስለዚህ የአቡ ጀህልን ውትወታ በመቃወም ያረጀና እጅግ የወፈረ መሆኑን ምክንያት አድርጎ አቀረበ። ነገር ግን አቡ ጀህል በፈሪነት ስለከሰሰው ለመሄድ ተገደደ።

የአጋሪዎቹ ሠራዊት አንድ ሺህ ያህል ነበር። ሁሉም የብረት ጥሩር ለብሰው ነበር። ከእነርሱም ጋር ድምፀ መልካም ሴቶች ነበሩ። የሙዚቃ መሣሪያዎችንና መጠጥ መያዝንም አልዘነጉም። በዚህ ያህል ብርቱ ሠራዊት ሦስት መቶ ሰዎችን ይቅርና አንድ ሺህ ሰዎች ያሉትን ሠራዊት እንኳ በቅጽበት እናሸንፋለን ብለው ያስቡ ነበር። ገና ከመነሣታቸው በፊት የሚገድሏቸውን ሰዎችና የሚወስዱትን ምርኮ የሚያሰሉ እንኳ ነበሩ። ነገር ግን የሁሉም ታላቁ ምኞት እስልምናን ማጥፋት ነበር። ይህ ልቅ የአጋሪዎች መንጋ ሴቶቹ በሚመቱት ከበሮና በሚዘፍኑት ዘፈን ታጅቦ ጉዞ ጀመረ።

በዚህ መሀል አቡ ሱፍያን ከበድር በእጅጉ ርቆ ወደ መካ ብዙ መንገድ ተጉዞ ነበር። አደጋው እንደተወገደ እርግጠኛ በሆነ ጊዜ ቀይስ ኢብኑ ኢምሪኢል ቀይስ የተባለውን ሰውዬውን ወደ ቁረይሽ ልኮ፦ «የቁረይሽ ማኅበረሰብ ሆይ! እናንተ ከመካ የወጣችሁት ቅፍለታችሁን፣ ሰዎቻችሁንና ንብረታችሁን ለመጠበቅ ነበር። እኛ ከአደጋው ተርፈናል። አሁን ተመለሱ!…» አለ። በተጨማሪም፦ «ከሙስሊሞች ጋር ለመዋጋት ወደ መዲና ከመሄድ ተጠንቀቁ!» ብሎ መከረ።

ቀይስ ወሬውን ለአጋሪዎቹ ሠራዊት ባደረሰ ጊዜ አቡ ጀህል እንዲህ አለ፦ «እምላለሁ፤ ወደ በድር ሄደን ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንፈነጥዛለን፣ ግመሎችን እናርዳለን፣ ወይን እንጠጣለን። በዙሪያው ያሉ ጎሳዎች እኛን እያዩ በሁኔታችን ይቀናሉ፤ ማንንም እንደማንፈራም ያያሉ። ከዚህ በኋላ ከግርማችን የተነሣ ማንም ሊያጠቃን አይደፍርም። የማይሸነፍ የቁረይሽ ሠራዊት ሆይ! ወደፊት!…» ቀይስ አቡ ጀህል ምክር የሚሰማ ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ አይቶ ተመለሰና ሁኔታውን ለአቡ ሱፍያን አሳወቀ። አርቆ አሳቢና ጠንቃቃ ሰው የነበረው አቡ ሱፍያን፦ «ወዮ! ለቁረይሽ ምንኛ ያሳዝናል!… ይህ የዐምር ኢብኑ ሂሻም (የአቡ ጀህል) ዕቅድ ነው። ይህን ያደረገው በእርግጥ የሰዎች አለቃ የመሆን ምኞት አድሮበት ነው። ነገር ግን እንዲህ ያለ ትዕቢት ሁልጊዜ ታላቅ ጉድለትና መጥፎ ገድ ነው። ሙስሊሞች ቢያገኟቸው ወዮላቸው ለቁረይሾች!..» ከማለት ራሱን መግታት አልቻለም።

አቡ ሱፍያን ቅፍለቱን በፍጥነት መካ አድርሶ ሠራዊቱን ተቀላቀለ። በዚህ ጊዜ የፍጥረተ ዓለሙ መሪ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከሶሓቦቻቸው ጋር ወደ በድር እየቀረቡ ነበር። በአንድ ወቅት ከመዲና አጋሪዎች መካከል ኹበይብ ኢብኑ የሳፍንና ቀይስ ኢብኑ ሙሐሪስን በእስልምና ሠራዊት መካከል አዩ። ኹበይብ በራሱ ላይ የብረት ቆብ ቢያደርግም አወቁትና ሰይዲና ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝን፦ «ይህ ኹበይብ አይደለምን?» አሉ። እርሳቸውም፦ «አዎን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!» አሉ። ኹበይብ የጦር ጥበብን የሚያውቅ ጀግና ታጋይ ነበር። ከቀይስ ጋር ወደ ክቡር ረሱሉላህ የተከበረ ፊት ቀረቡ። ነብያችንም፦ «ከእኛ ጋር ለምን ትመጣላችሁ?» አሏቸው። እነርሱም፦ «አንተ የእህታችን ልጅና ጎረቤታችን ነህ። እኛም ከሕዝባችን ጋር ምርኮ ለመሰብሰብ እየመጣን ነው!» አሉ። ሰይዳችን ኹበይብን፦ «አንተ በአላሁ ተዓላና በመልዕክተኛው አምነሃልን?» ባሉት ጊዜ፦ «አይ» አለ። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም፦ «እንግዲያው ተመለስ! ከሃይማኖታችን ያልሆነ ከእኛ ጋር ሊሆን አይችልም!» አሉ። ኹበይብም፦ «ጀግንነቴን፣ ብርታቴንና በጠላት ደረት ላይ ቁስል የምከፍት ታጋይ መሆኔን ሁሉም ያውቃል። ለምርኮ ስል ከአንተ ጎን ሆኜ ጠላትህን እዋጋለሁ» አለ። ክቡር ነብያችን እርዳታውን አልተቀበሉም።

ጥቂት ከተጓዙ በኋላ ኹበይብ ጥያቄውን ደገመ፤ ነገር ግን ነብያችን ሙስሊም እስካልሆነ ድረስ ፍላጎቱ ተቀባይነት እንደማያገኝ አሳወቁ። ረውሓ ወደሚባለው ቦታ በደረሱ ጊዜ ኹበይብ ወደ ክቡር ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ዘንድ መጥቶ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! አላሁ ተዓላ የዓለማት ጌታ መሆኑንና የእርስዎን ነብይነት አመንኩ፤ ኢማንም አመጣሁ» ባለ ጊዜ የፍጥረተ ዓለሙ መሪ እጅግ ተደሰቱ። ቀይስም ወደ መዲና ከተመለሱ በኋላ በኢማን ተከበሩ (ረዲየላሁ ዐንሁ)።

የእስልምና ሠራዊት ሶፍራ ሸለቆ በደረሰ ጊዜ የመካ ሰዎች ሠራዊት አቋቁመው ቅፍለታቸውን ለማዳን ወደ በድር እየገሠገሡ መሆናቸውን ሰማ። ክቡር ነብያችን ሶሓቦቻቸውን ሰብስበው በዚህ ሁኔታ ላይ ከእነርሱ ጋር ተመካከሩ። ምክንያቱም የመዲና ሙስሊሞች በዐቀባ ለክቡር ረሱሉላህ ቃል ኪዳን በገቡ ጊዜ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ወደ ከተማችን ይምጡ። እዚያ ሕይወታችንን ቢያስከፍለንም ከጠላትዎ እንጠብቅዎታለን፤ እንከተልዎታለንም» ብለው ቃል ገብተው ነበር። አሁን ግን ከመዲና ውጭ ወጥተው ነበር። ፊት ለፊታቸው ደግሞ በቁጥር፣ በመሣሪያና በንብረት ከእነርሱ እጥፍ ድርብ የሚበልጥ ታላቅ የጠላት ሠራዊት ነበር።

ክቡር ረሱሉላህ ሶሓቦቻቸውን ሐሳባቸውን በጠየቁ ጊዜ ከሙሃጂሮች አቡበክር ሲዲቅና ዑመር አል-ፋሩቅ እያንዳንዳቸው ተነሥተው ከጠላት ሠራዊት ጋር መዋጋት አስፈላጊ መሆኑን ገለጹ። እንዲሁም ከሙሃጂሮች ሚቅዳድ ኢብኑ አስወድ ተነሥተው እንዲህ አሉ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! የአላሁ ተዓላ ትእዛዝ ምንም ይሁን እርሱን ይፈጽሙ። በእርሱ ትእዛዝ ይጓዙ። በየቅጽበቱ ከእርስዎ ጋር ነን፤ ለአንዲት ቅጽበት እንኳ ከጎንዎ አንለይም። እኛ የኢስራኢል ልጆች ለሙሳ ዐለይሂ ሰላም፦ ‹ሙሳ ሆይ! የኃያላንና የበዳዮች ሕዝብ በዚያ ምድር እስካሉ ድረስ ወደዚያ አንሄድም፤ ወደዚያች ከተማም ፈጽሞ አንገባም። ስለዚህ አንተና ጌታህ ሂዱና ሁለታችሁ ተዋጓቸው። እኛ እዚህ ተቀምጠናል…›8 እንዳሉት ያለ ቃል አንናገርም። ነፍሳችንንና ራሳችንን በአላሁ ተዓላና በመልዕክተኛው መንገድ መሥዋዕት እናደርጋለን። እውነተኛ ነብይ አድርጎ በላከዎ በአላሁ ተዓላ እንምላለን፤ ከባሕር ማዶ ወዳለው ሐበሻ ቢልኩን እንኳ እንሄዳለን። በምንም መንገድ በትንሹ እንኳ አንቃወምዎትም። ፍላጎትዎን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁ ነን። አባቴ፣ እናቴና ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ…»

«ከሃይማኖታችን ያልሆነ ከእኛ ጋር ሊሆን አይችልም» ሐዲስ ሸሪፍ

የበድር ጦርነት

የሚቅዳድ ይህ ንግግር ውዱ ነብያችንን እጅግ አስደሰታቸው፤ ለእርሳቸውም መልካም ዱዓ አደረጉ።9

በዚህ ቦታ የመዲና ሙስሊሞች አስተያየት እጅግ አስፈላጊ ነበር። ምክንያቱም ቁጥራቸው ብዙ ነበር፤ ደግሞም ረሱሉላህን በመዲና ለመጠበቅ ቃል ገብተው ነበር። ከመዲና ውጭ ለመዋጋት ግን ቃል አልገቡም ነበር። ይህ ሐሳብ በታወቀ ጊዜ ከአንሷሮች ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ተነሥተው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከፈቀዱልኝ በአንሷሮች ስም ልናገር» አሉ። በተፈቀደላቸው ጊዜም እንዲህ አሉ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! በእርስዎ አምነናል፤ ነብይነትዎንም አረጋግጠናል። ያመጡት ሁሉ እውነትና ትክክል ነው። በዚህ ጉዳይ ለመስማትና ለመታዘዝ ጽኑ ቃል ገብተንልዎታል፤ ምለናልም። ከዚያ ቃላችን ፈጽሞ አንመለስም፤ ወደየትም ቢሄዱ በትእዛዝዎ ሥር ነን። ትእዛዝዎን በራሳችን ላይ እናደርጋለን። ነፍሳችንንና ራሳችንን በመንገድዎ መሥዋዕት እናደርጋለን። እውነተኛ ነብይ አድርጎ በላከዎ በአላሁ ተዓላ እንምላለን፤ ወደ ባሕር ቢገቡ እኛም ተከትለንዎ እንገባለን። ከእኛ ማንም ከዚህ አንዲት እርምጃ እንኳ ወደ ኋላ አይቀርም። በተከበረው ልብዎ ያለውን ሁሉ ይዘዙ፤ እኛም እንፈጽመዋለን። ንብረታችንም ከነፍሳችን ጋር መሥዋዕት ይሁን። ከጠላት ፈጽሞ ፊታችንን አናዞርም። በጦርነት ታጋሾች ነን። ተስፋችን እርስዎን ማስደሰትና ውዴታዎን ማግኘት ነው። የአላሁ ተዓላ እዝነት በእርስዎ ላይ ይሁን…» ይህን ንግግር የሰሙት ሶሓቦች እጅግ ተነቃቁ። ሁሉም በዚህ ቃል በሙሉ ልባቸው እንደሚስማሙ ገለጹ። ክቡር ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እጅግ ተደሰቱ። ለሰይዲና ሰዕድና ለሶሓቦቻቸው ዱዓ አደረጉ። አሁን ማመንታት ሁሉ ተወግዶ ነበር። ጠላት ምንም ያህል ብዙና ብርቱ ቢሆን ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች ዓይናቸውን ሳያርገበግቡ ውዱ ነብያችንን ተከትለው ወደ ሸሂድነት ይገሰግሱ፣ የአላሁ ተዓላንና የመልዕክተኛውን ውዴታ ያገኙ ነበር። የፍጥረተ ዓለሙ ሰይድ በፊታቸው እስካሉ ድረስ የማይሄዱበት ቦታ አልነበረም… የዓለም ኩራት የሶሓቦቻቸውን ታማኝነትና ጉጉት ባዩ ጊዜ እንዲህ በማለት አበሠሯቸው፦ «በሉ፣ ተጓዙ! በአላሁ ተዓላ ችሮታ ደስ ይበላችሁ። ወላሂ፣ አሁን የቁረይሽ ሰዎች በጦር ሜዳ ተመትተው የሚወድቁበትን ቦታ እየተመለከትኩ እነርሱንም እያየሁ ያለሁ ይመስለኛል!» ከዚህ የምሥራች በኋላ ሶሓቦች በፍቅር ክቡር ረሱሉላህን ተከተሉ።

የመላእክት ለእርዳታ መምጣት

የበድርን አካባቢ በደረሱ ጊዜ ሐሙስ ሌሊት ለጁሙዓ አጥቢያ ነበር። ውዱ ነብያችን ሶሓቦቻቸውን፦ «በዚያች ትንሽ ኮረብታ አጠገብ ካለው ጉድጓድ አንዳንድ መረጃዎችን እንደምታገኙ ተስፋ አደርጋለሁ» አሉ። የአላሁ ተዓላ አንበሳ የሆኑትን ሰይዲና ዐሊይን፣ ሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስን፣ ዙበይር ኢብኑል ዐዋምንና አንዳንድ ሶሓቦቻቸውን ወደዚያ ላኩ። ሰይዲና ዐሊይና ጓደኞቻቸው ወዲያውኑ ወደ ጉድጓዱ ሄዱ። እዚያም የቁረይሽን ግመል ነጂዎችና ውኃ ቀጂዎች አዩ። እነርሱም ሙስሊሞችን ባዩ ጊዜ ሸሹ። ነገር ግን ከእነርሱ ሁለቱ ተያዙ። ከእነዚህም አንዱ የሐጃጅ ልጆች ባሪያ አሽለም፣ ሌላው ደግሞ የዓስ ኢብኑ ሰዒድ ልጆች ባሪያ ዐሪድ አቡ የሳር ነበሩ።

ወደ ክቡር ነብያችን ባመጧቸው ጊዜ ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን)፦ «ቁረይሾች የት ናቸው?» ብለው ጠየቋቸው። እነርሱም፦ «ከዚያ ከሚታየው የአሸዋ ኮረብታ ጀርባ ሰፍረዋል» ብለው መለሱ። ሰይዳችን፦ «ቁረይሾች ስንት ናቸው?» አሉ። «አናውቅም» አሉ። «በቀን ስንት ግመሎችን ያርዳሉ?» ለሚለው ጥያቄ፦ «አንድ ቀን ዘጠኝ፣ አንድ ቀን አሥር» የሚል መልስ ባገኙ ጊዜ ክቡር ነብያችን፦ «ከአንድ ሺህ ያነሱ፣ ከዘጠኝ መቶ የሚበልጡ ናቸው» አሉ። ደግመውም፦ «ከቁረይሽ ታላላቅ ሰዎች እነማን አሉ?» ብለው ጠየቁ። እነርሱም፦ «ዑትባ፣ ሸይባ፣ ሐሪስ ኢብኑ ዐምር፣ አቡል በኽተሪ፣ ሐኪም ኢብኑ ሒዛም፣ አቡ ጀህል፣ ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ…» ባሉ ጊዜ ክቡር ረሱሉላህ ወደ ሶሓቦቻቸው ዞረው፦ «የመካ ሰዎች የአንጀታቸውን ቁራጮች አሳልፈው ሰጧችሁ» አሉ። ከዚያም እነዚያን ሁለት ሰዎች፦ «ስትመጡ ከቁረይሽ የተመለሰ አለ?» ባሉ ጊዜ፦ «አዎን። ከበኑ ዙህራ አኽነስ ኢብኑ አቢ ሸሪቅ ተመልሷል» ብለው መለሱ። ሰይዳችንም፦ «እርሱ ራሱ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ሳይሆን፣ አኺራን፣ አላሁ ተዓላንና መጽሐፍን ሳያውቅ ለበኑ ዙህራ ቀጥተኛውን መንገድ አሳያቸው… ከእነርሱ ሌላ የተመለሰ አለ?» ባሉ ጊዜ፦ «የዐዲይ ኢብኑ ከዕብ ልጆች ተመልሰዋል» የሚል መልስ አገኙ።10

«የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! የአላሁ ተዓላ ትእዛዝ ምንም ይሁን እርሱን ይፈጽሙ። በእርሱ ትእዛዝ ይጓዙ። በየቅጽበቱ ከእርስዎ ጋር ነን፤ ለአንዲት ቅጽበት እንኳ ከጎንዎ አንለይም» ሚቅዳድ ኢብኑ አስወድ (ረዲየላሁ ዐንሁ)

ክቡር ነብያችን ቁረይሾችን ለመጨረሻ ጊዜ ለማስጠንቀቅ ሰይዲና ዑመርን የስምምነት ሐሳብ አስይዘው ወደ እነርሱ ላኩ። ዑመር ኢብኑል ኸጧብም እንዲህ አሏቸው፦ «እናንተ ግትር ሕዝብ ሆይ! መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም እንዲህ ይላሉ፦ ‹ሁሉም ከዚህ ጉዳይ ይታቀብ፤ በሰላም ይመለስ። ምክንያቱም ከእናንተ ሌላ ካሉት ጋር መዋጋት ከእናንተ ጋር ከመዋጋት ይልቅ ለእኔ ተወዳጅ ነው!…›»

በዚህ ሐሳብ ፊት ከቁረይሽ አጋሪዎች ሐኪም ኢብኑ ሒዛም ወደፊት ወጥቶ፦ «የቁረይሽ ማኅበረሰብ ሆይ! ሙሐመድ ለእናንተ እጅግ ፍትሐዊ ሆኗል። የጠየቀውን ወዲያውኑ ተቀበሉ። ያለውን ካላደረጋችሁ፣ እምላለሁ፣ ከዚህ በኋላ ፈጽሞ ፍትሐዊ አይሆንላችሁም!…» አለ። አቡ ጀህል በዚህ የሐኪም ንግግር ተቆጥቶ፦ «ይህን ፈጽሞ አንቀበልም፤ ከዚህ በኋላ ማንም ቅፍለታችንን ለማጥቃት እንዳይደፍር ሙስሊሞችን እስካልተበቀልን ድረስ አንመለስም» ብሎ የሰላምን መንገዶች ዘጋ። ሰይዲና ዑመር ተመለሱ።

በዚያች ሌሊት ክቡር ነብያችንና ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦቻቸው ከአጋሪዎች ቀድመው በድር ደርሰው ከጉድጓዶቹ አጠገብ ሰፈሩ። ክቡር ነብያችን ከሶሓቦቻቸው ጋር ተመካክረው የጦር ሰፈሩ የት መመሥረት እንዳለበት አስተያየታቸውን ጠየቁ። ከእነርሱ መካከል ገና የሠላሳ ሦስት ዓመት ወጣት የነበሩት ሑባብ ኢብኑ ሙንዚር ተነሥተው ለመናገር ፈቃድ ጠየቁ። በተፈቀደላቸው ጊዜም፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ይህ ቦታ አላሁ ተዓላ የጦር ሰፈር እንዲመሠርቱበት ያዘዘዎትና በእርግጥ ልንቆይበት የሚገባ ቦታ ነውን? ወይስ በግል አስተያየትና እንደ ጦር ስልት ተመርጧል?» ብለው ጠየቁ። ክቡር ነብያችንም፦ «አይደለም! ይህ ቦታ የተመረጠው እንደ ጦር ስልት ነው» አሉ።

ይህን ጊዜ ሰይዲና ሑባብ እንዲህ አሉ፦ «አባቴ፣ እናቴና ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!

እኛ የጦርነት ሰዎች ነን። እነዚህንም ቦታዎች በደንብ እናውቃቸዋለን። ቁረይሾች ከሚሰፍሩበት ቦታ አጠገብ ባለው ጉድጓድ ጣፋጭና ብዙ ውኃ አለ። ከፈቀዱልን እዚያ እንስፈር። በዙሪያው ያሉትን ጉድጓዶች ሁሉ እንድፈን። ከዚያም ኩሬ ሠርተን በውኃ እንሙላው። ከጠላት ጋር ስንዋጋ በተጠማን ቁጥር ከኩሬያችን መጥተን እንጠጣለን። ጠላት ግን ውኃ አያገኝም፤ ይጎሳቆላልም።»11 በዚያን ቅጽበት ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም ይህ ሐሳብ ትክክል መሆኑን የሚያሳውቅ ወሕይ አመጡ። ክቡር ነብያችንም፦ «ሑባብ ሆይ! ትክክለኛው ሐሳብ አንተ ያመለከትከው ነው» ብለው ተነሡ። ሁሉም በአንድነት ወደተጠቀሰው ጉድጓድ መጡ። ጣፋጭ ውኃ ካለው ጉድጓድ በስተቀር ጉድጓዶቹን ሁሉ ደፍነው ታላቅ ኩሬ ሠሩ። በውኃ ሞልተው የመጠጫ ዕቃዎችን አኖሩበት።

በዚህ ጊዜ ሰይዲና ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ወደ ክቡር ነብያችን የተከበረ ፊት ቀርበው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! የሚቀመጡበት ጥላ ከተምር ዛፍ ቅርንጫፎች እንሥራልዎ?» ብለው ሐሳብ አቀረቡ። የዓለም ኩራት በዚህ የሰዕድ ሐሳብ ተደስተው ዱዓ አደረጉላቸው። ወዲያውኑ ጥላ ተሠራ። የነብያት ሱልጣን ከተከበሩት ሶሓቦቻቸው ጋር የጦር ሜዳውን ዞረው መረመሩ። አልፎ አልፎ እየቆሙ፦ «ኢንሻአላህ፣ ነገ ጠዋት እከሌ ተመትቶ የሚወድቅበት ቦታ ይህ ነው! ኢንሻአላህ፣ ነገ ጠዋት እከሌ ተመትቶ የሚወድቅበት ቦታ ይህ ነው! እነሆ ይህ ነው! ይህ ነው…» እያሉ የቁረይሽ አጋሪዎች የሚገደሉባቸውን ቦታዎች በተባረኩ እጆቻቸው አንድ በአንድ አሳዩ።

በኋላም ሰይዲና ዑመር ይህን እንዲህ ብለው ተረኩ፦ «ከእነርሱ እያንዳንዱ ረሱሉል አክረም የተባረከ እጃቸውን ባኖሩባቸው ቦታዎች ላይ በትክክል ተመትቶ ሲገደል አየሁ። ከእነርሱ አንዱም በጥቂት እንኳ ወደፊትም ሆነ ወደ ኋላ አልነበረም።»

የዓለማት ሰይድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሶሓቦችን በሦስት ቡድኖች ከፈሉ። የሙሃጂሮችን ሰንደቅ ለሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር፣ የአውስን ሰንደቅ ለሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ፣ የኸዝረጅን ሰንደቅ ደግሞ ለሑባብ ኢብኑ ሙንዚር ሰጡ። እያንዳንዳቸው በሰንደቃቸው ሥር ተሰበሰቡ።12 ሰይዳችን ሠራዊቱን በሰልፍ አቁመው በሥርዓት አደራጁ።

ሠራዊቱን ሲያደራጁ ከሰልፉ ወደፊት የወጡትን የሰዋድ ኢብኑ ገዚያን ደረት በተባረከ እጃቸው በያዙት በትር ነካ አድርገው፦ «ሰዋድ ሆይ! ወደ ሰልፉ ተመለስ!» አሉ። ሰዋድም፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! በእጅዎ ያለው በትር አመመኝ። በእውነተኛው ሃይማኖት፣ በመጽሐፍና በፍትሕ በላከዎ በአላሁ ተዓላ ይሁንብዎ፣ እኔም እርስዎን እንዲሁ በበትር መንካት እፈልጋለሁ» አሉ። በዚህ ንግግራቸው ሶሓቦች ሁሉ ተደነቁ። ከፍጥረተ ዓለሙ ሰይድ አጸፋ መጠየቅ ይቻል ነበርን? እንዲህ ያለ ነገር ሊደረግ ይችል ነበርን? ክቡር ረሱሉላህ ግን የተባረከ ሸሚዛቸውን ፊት ከፍተው፦ «በል፣ አጸፋህን መልስ፤ መብትህንም ውሰድ» አሉ። ሰይዲና ሰዋድ የሐቢቡል አክረምን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የተባረከ ደረት በታላቅ ደስታና ፍቅር ሳሙ።

ሁሉም አጸፋ ሲጠብቁ ባዩት ትዕይንት ወንድማቸውን ሰዋድን አደነቁ፤ በሁኔታቸውም ቀኑ። ውዱ ነብያችን፦ «ለምን እንዲህ አደረግህ?» ብለው በጠየቁ ጊዜ ሰዋድ፦ «አባቴ፣ እናቴና ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ዛሬ በአላሁ ተዓላ ትእዛዝ ቀኔ እንደደረሰ አያለሁ፤ ከላቀው ማንነትዎ መለየትንም እፈራለሁ። ስለዚህ በመካከላችን በሚያልፉት በእነዚህ የመጨረሻ ደቂቃዎች ከንፈሮቼ የተባረከ አካልዎን እንዲነኩ ተመኘሁ። ይህንንም በቂያማ ቀን ሸፋዐ እንዲያደርጉልኝና በዚህም ከቅጣት እንድድን ምክንያት ላደርገው ፈለግሁ» አሉ። በዚህ ፍቅራቸው ክቡር ነብያችንም እጅግ ተነኩ፤ ለሰይዲና ሰዋድም ዱዓ አደረጉ።

የተባረከው የእስልምና ሠራዊት ቀኝ ክንፍ በጀግናው ሙጃሂድ በዙበይር ኢብኑል ዐዋም፣ ግራ ክንፉ ደግሞ በሚቅዳድ ኢብኑ አስወድ ሊታዘዝ ነበር።13

ክቡር ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ጦርነቱ እንዴት እንደሚጀመር ከተከበሩት ሶሓቦቻቸው ጋር መመካከር ፈልገው፦ «እንዴት ትዋጋላችሁ?» አሉ። ዓሲም ኢብኑ ሳቢት ቀስታቸውንና ፍላጻቸውን በእጃቸው ይዘው ተነሥተው እንዲህ በማለት አስተያየታቸውን ገለጹ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ቁረይሾች መቶ ሜትር ያህል በቀረቡን ጊዜ በፍላጻ እንምታቸው። ከዚያም በእጅ የሚወረወር ድንጋይ በሚደርስበት ርቀት በመጡ ጊዜ ድንጋይ እንወርውር። ጦር በሚደርስበት ያህል በቀረቡ ጊዜ ደግሞ ጦሮቻችን እስኪሰበሩ ድረስ በጦሮቻችን እንዋጋ። ከዚያም ሰይፎቻችንን መዝዘን እንዋጋ!» ይህ ስልት ክቡር ነብያችንን አስደሰታቸው። ለሶሓቦቻቸውም የሚከተለውን መመሪያ ሰጡ፦ «መስመሮቻችሁን ትታችሁ አትለዩ። ሳትንቀሳቀሱ በቦታችሁ ጽኑ። እኔ ትእዛዝ እስካልሰጠሁ ድረስ ጦርነት አትጀምሩ። ጠላት ሳይቀርባችሁ ፍላጻዎቻችሁን ተጠቅማችሁ አታባክኑ። ጠላት ጋሻውን በከፈተ ጊዜ ፍላጻችሁን ወርውሩ። ጠላት በደንብ በቀረበ ጊዜ በእጃችሁ ድንጋይ ወርውሩ። ይበልጥ በቀረቡ ጊዜ ጦሮቻችሁን ተጠቀሙ። ከጠላት ጋር ደረት ለደረት በተገናኛችሁ ጊዜ ደግሞ በሰይፎቻችሁ ተዋጉ…»

«ኢንሻአላህ፣ ነገ ጠዋት እከሌ ተመትቶ የሚወድቅበት ቦታ ይህ ነው! ኢንሻአላህ፣ ነገ ጠዋት እከሌ ተመትቶ የሚወድቅበት ቦታ ይህ ነው! እነሆ ይህ ነው! ይህ ነው…» ሐዲስ ሸሪፍ

ከዚያም ዘቦች ተመድበው ሶሓቦች ዕረፍት እንዲያደርጉ ተደረገ። በአላሁ ተዓላ ጥበብ የዓይን ሽፋኖቻቸውን ማንሣት እስኪያቅታቸው ድረስ ጥልቅ እንቅልፍ ወሰዳቸው። ክቡር ነብያችንም ከተምር ዛፍ ቅርንጫፎች ወደተሠራው ጥላ በገቡ ጊዜ ሰይዲና አቡበክር፣ ከዚያም ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ሰይፎቻቸውን መዝዘው በጥላው በር ላይ ዘብ ቆሙ። ውዱ ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የተባረኩ እጆቻቸውን አንሥተው በታላቅ ሐዘን አላሁ ተዓላን፦ «ጌታዬ ሆይ! ይህችን አንድ እፍኝ ጀማዐ ብታጠፋ ከዚህ በኋላ በምድር ላይ ፈጽሞ አትመለክም…» እያሉ መማጸን ጀመሩ። ይህ አሳዛኝ ዱዓ እስከ ንጋት ቀጠለ።

የተባረከው የእስልምና ሠራዊት የሰፈረበት ቦታ አሸዋማ ነበር። በዚህ ምክንያት መራመድ አስቸጋሪ ነበር፤ እግሮችም በአሸዋ ውስጥ ይሰምጡ ነበር። በአላሁ ተዓላ ችሮታና በክቡር ረሱሉላህ ዱዓ በረከት በዚያች ሌሊት እየጠነከረ የሚሄድ ዝናብ መዝነብ ጀመረ፤ ጎርፉም ወንዞችን እስኪያጥለቀልቅ ድረስ ይጎርፍ ነበር። የውኃ ዕቃዎች ተሞሉ፤ መሬቱም እግሮች እስከማይሰምጡ ድረስ ጠነከረ።

አጋሪዎች ግን በጭቃና በጎርፍ ውስጥ ቀሩ።

ጎህ ከቀደደ በኋላ ክቡር ረሱሉላህ ሶሓቦቻቸውን ለሶላት ቀሰቀሱ።

የሱብሒን ሶላት ካሰገዱ በኋላ ጠላትን በጂሃድ የመዋጋትንና የሸሂድነትን ብልጫ ተናግረው ለውጊያ አበረታቷቸው። እንዲህም አሉ፦ «በእርግጥ አላሁ ተዓላ እውነትና ትክክል የሆነውን ያዛል። ለውዴታው ያልተሠራን የማንንም ሥራ አይቀበልም… ጌታችን በእነዚህ ቦታዎች እዝነቱንና ምሕረቱን ቃል የገባላችሁን ትእዛዝ ለመፈጸም ጣሩ፤ ፈተናውንም አልፉ! ምክንያቱም ቃል ኪዳኑ እውነት፣ ንግግሩ ሐቅ፣ ቅጣቱም ብርቱ ነው። እኔም እናንተም ሐዩና ቀዩም ከሆነው ከአላሁ ተዓላ ጋር የተሳሰርን ነን። በእርሱ ተጠለልን፣ እርሱን ያዝን፣ በእርሱ ላይ ተመካን። የመጨረሻ መመለሻችንም ወደ እርሱ ነው። አላሁ ተዓላ እኔንና ሙስሊሞችን ሁሉ ይማረን!…»

በተከበረው የረመዳን ወር በአሥራ ሰባተኛው ቀን የጁሙዓ ቀን ፀሐይ ወጣች። ብዙም ሳይቆይ በታሪክ እጅግ ርኅራኄ የለሹ፣ እጅግ ያልተመጣጠነው፣ እጅግ አስፈላጊውና ታላቁ ጦርነት ሊጀመር ነበር…

በአንድ በኩል የዓለም ኩራት (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እና ሕይወታቸውን መሥዋዕት ከማድረግ በቅንጣት ታህል የማያመነቱ አንድ እፍኝ የተከበሩ ሶሓቦቻቸው ነበሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እስልምናን በአንድ ማንኪያ ውኃ ለማስጠም፣ የአላሁ ተዓላ ሐቢብ በመሆን የተከበሩትን ነብይ ለማጥፋት የተሰበሰበ ልቅና ገደብ የለሽ የከሓዲዎች ጭፍራ ነበር። የሚያሳዝነው ከእነርሱ መካከል የረሱሉል አክረም ዘመዶችም ይገኙ ነበር። እነርሱም ከውድ የወንድማቸው ልጅ ጋር ለመዋጋት ወደ በድር መጥተው ነበር።

ክቡር ነብያችን የሠራዊታቸውን ሥርዓት እንደገና ተመልክተው የሰጡትን መመሪያ ደገሙ። በዚህ ጊዜ የቁረይሽ አጋሪዎች ከሰፈራቸው ወጥተው ወደ በድር ሸለቆ መጉረፍ ጀመሩ። አብዛኞቻቸው በጥሩር ተሸፍነው ነበር። በታላቅ ኩራትና ትዕቢት በእስልምና ሠራዊት ላይ ጥቃት ጀምረው ነበር። ክቡር ረሱሉላህ የአጋሪዎችን ይህን ሁኔታ ባዩ ጊዜ ከሰይዲና አቡበክር ጋር ወደ ድንኳኑ ገቡ፤ የተባረኩ እጆቻቸውን አንሥተውም ክብሩ የላቀውን አላህ እንዲህ እያሉ መማጸን ጀመሩ፦ «ጌታዬ ሆይ! እነሆ የቁረይሽ አጋሪዎች በኩራታቸውና በትዕቢታቸው ሁሉ እየመጡ ነው!… አንተን ይገዳደራሉ፤ ነብይህንም ያስተባብላሉ። አላህ ሆይ! የገባህልኝን የእርዳታና የድል ቃል እንድትፈጽምልኝ እለምንሃለሁ!… አላህ ሆይ! የእነዚህን አንድ እፍኝ ሙስሊሞች ጥፋት ብትሻ ከዚህ በኋላ የሚያመልክህ አይገኝም!…»

በዚህ ሁኔታ ያለማቋረጥ፣ ደጋግመው እርዳታ እየለመኑ አላሁ ተዓላን ይማጸኑ ነበር። ይህ የክቡር ነብያችን እጅግ አሳዛኝና አንጀት የሚበላ ልመና ራሳቸውን ስተው መጎናጸፊያቸው ከተባረከው ትከሻቸው እስኪወድቅ ድረስ ቀጠለ። ይህን ከልብ የመነጨ ልመና መቋቋም ያልቻሉት ሰይዲና አቡበክር የተባረከውን መጎናጸፊያ በታላቅ አክብሮት ከመሬት አንሥተው በሰይዳችን የተባረከ ትከሻ ላይ እያደረጉ፦ «ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ይህን ያህል መማጸንዎ ይበቃል!… ወደ ጌታዎ አጥብቀው ዱዓ አድርገዋል! በእርግጥ አላሁ ተዓላ ቃል የገባልዎትን ድል በቅርቡ ይሰጥዎታል» ብለው አጽናኗቸው። በዚያን ቅጽበት የዓለማት ሰይድ በትርጓሜ እንዲህ የሚሉትን ክቡር አንቀጾች እያነበቡ ከድንኳኑ ወጡ፦ «ይህ ጭፍራ (በበድር ያለው) በቅርቡ በእርግጥ ይበታተናል፤ ይሸነፋልም፤ ጀርባቸውንም አዙረው ይሸሻሉ። እንዲያውም የቅጣታቸው ትክክለኛ ጊዜ ቂያማ ነው። የዚያ ጊዜ ቅጣት ደግሞ ይበልጥ አስፈሪና ይበልጥ መራራ ነው።»14

ውዱ ነብያችን ወደ ሠራዊታቸው ፊት መጡ። ለክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦቻቸውም የሚከተሉትን ክቡር አንቀጾች አነበቡላቸው፦ «እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የጠላትን ጭፍራ በተገናኛችሁ ጊዜ ጽኑ፤ ትድኑም ዘንድ አላሁ ተዓላን በብዛት አውሱ… በዚህም ስኬትን ታገኙ ዘንድ ይከጀላል። አላህንና መልዕክተኛውን ታዘዙ። እርስ በርሳችሁ አትጨቃጨቁ፤ አለበለዚያ ትከሽፋላችሁ፤ በእጃችሁ ያለው ኃይል (ብርታት፣ ጥንካሬ) ይሄዳል። ታገሡ፤ ምክንያቱም አላሁ ተዓላ ከታጋሾች ጋር ነው።»15

በጠላት ላይ በአንድነት የሚደረገው የመጀመሪያው ጦርነት ይህ ሊሆን ነበር። ጦርነቱ ሊጀመር ተቃርቦ ነበር። ስሜቱ ጣራ ደርሶ ነበር። ረሱሉል አክረም ትርጓሜው «አላሁ ተዓላን በብዛት አውሱ…» የሆነውን ክቡር አንቀጽ ባነበቡ ጊዜ ሶሓቦች ሁሉ በአንድነት «አላሁ አክበር!… አላሁ አክበር!…» ማለትና ድልን እንዲለግሳቸው ክብሩ የላቀውን አላህ መማጸን ጀመሩ። አሁን የክቡር ነብያችንን አንድ ምልክት ብቻ ይጠብቁ ነበር። በዚያን ዘመን ልማድ መሠረት ሁለት ሠራዊቶች ከመጋጠማቸው በፊት ከሁለቱም ወገን ጀግኖች ወደ ሜዳው ወጥተው እርስ በርሳቸው ይዋጉ ነበር። በዚህ ፍልሚያ የሁለቱም ወገኖች የውጊያ ቁጣና ፍላጎት ይጨምር፣ ለጦርነቱም ይሟሟቁ ነበር። ከአጋሪዎች ዓሚር ኢብኑል ሐድረሚ ይህን ደንብ ሳያከብር ረግጦ በእስልምና ሠራዊት ላይ ፍላጻ ወረወረ። ፍላጻው ከሙሃጂሮች ሚሕጃዕን መታ፤ እርሳቸውም ሸሂድ ሆኑ፤ የተባረከች ነፍሳቸውም ወደ ጀነት ዐረገች። የነብያት ሰይድ ስለዚህ የመጀመሪያው ሸሂድ፦ «ሚሕጃዕ የሸሂዶች ሰይድ ነው» ብለው አበሠሩ። ሶሓቦች በቦታቸው መቆም እስኪያቅታቸው ድረስ ተነሣሡ። ነገር ግን ከሰይዳችን ትእዛዝ ሳይመጣ ትንሽ እንቅስቃሴ እንኳ ማድረግ አይችሉም ነበር።

«ጌታዬ ሆይ! እነሆ የቁረይሽ አጋሪዎች በኩራታቸውና በትዕቢታቸው ሁሉ እየመጡ ነው!… አንተን ይገዳደራሉ፤ ነብይህንም ያስተባብላሉ። አላህ ሆይ! የገባህልኝን የእርዳታና የድል ቃል እንድትፈጽምልኝ እለምንሃለሁ!…» ሐዲስ ሸሪፍ

የእያንዳንዳቸው ውስጥ እንደ እሳተ ገሞራ መፍላት ጀመረ!…

በዚህ ጊዜ ከአጋሪዎቹ ሠራዊት ሦስት ሰዎች ዘለው ወደፊት ሲወጡ ታዩ። እነርሱም ከረቢዓ ልጆች የሆኑ የእስልምና መራር ጠላቶች፦ ዑትባ፣ ወንድሙ ሸይባና ልጁ ወሊድ ነበሩ። ወደ ሙጃሂዶቹ፦ «ከእናንተ መካከል ከእኛ ጋር መዋጋት የሚችል አለን?» ብለው ጮኹ። ከሶሓቦች መካከል መጀመሪያ ሰይዲና አቡ ሑዘይፋ አባታቸውን ዑትባን ለመዋጋት ወደፊት በወጡ ጊዜ የዓለማት ሱልጣን፦ «አንተ ቁም!» አሏቸው። ከመዲና ሙጃሂዶች የእመቤት ዐፍራእ ልጆች ሙዓዝና ሙዐዊዝ እንዲሁም ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሓ ወደፊት ወጡ። በዑትባ፣ በሸይባና በወሊድ ፊት ቆሙ። ሰይፋቸውን በእጃቸው ይዘው ተዘጋጅተው ይጠብቁ ነበር።

አጋሪዎቹ ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ ፈልገው፦ «እናንተ እነማን ናችሁ?» አሉ። እነርሱም፦ «ከመዲና ሙስሊሞች ነን» ባሉ ጊዜ አጋሪዎቹ፦ «ከእናንተ ጋር ጉዳይ የለንም! የሚያስፈልጉን የዐብዱልሙጠሊብ ልጆች ናቸው። ከእነርሱ ጋር መዋጋት እንፈልጋለን» አሉ፤ ወደ እስልምና ሠራዊትም ዞረው፦ «ሙሐመድ ሆይ! ከራሳችን ሕዝብ አቻዎቻችን የሆኑትን በፊታችን አውጣ!» ብለው ጮኹ።

ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በሜዳው ለነበሩት ለእነዚህ ሦስት ጀግና ሶሓቦቻቸው ዱዓ ካደረጉላቸው በኋላ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ አዘዙ። ከዚያም ዓይናቸውን በሶሓቦቻቸው መካከል አዟዙረው፦ «የሀሺም ልጆች ሆይ! ተነሡ! የአላሁ ተዓላን ኑር በከንቱ ሃይማኖቶቻቸው ለማጥፋት በመጡት ላይ በሐቅ መንገድ ተዋጉ፤ አላሁ ተዓላ ነብያችሁንም የላከው ለዚሁ ነውና። ዑበይዳ ሆይ፣ ተነሣ! ሐምዛ ሆይ፣ ተነሣ! ዐሊይ ሆይ፣ ተነሣ!» አሉ።

የአላሁ ተዓላ አንበሶች ሰይዲና ሐምዛ፣ ሰይዲና ዐሊይና ሰይዲና ዑበይዳ የራስ ቁሮቻቸውን አድርገው ወደ ሜዳው ወጡ። በፊታቸው በቆሙ ጊዜ አጋሪዎቹ፦ «እናንተ እነማን ናችሁ? አቻዎቻችን ከሆናችሁ ከእናንተ ጋር እንዋጋለን» አሉ። እነርሱም፦ «እኔ ሐምዛ ነኝ! እኔ ዐሊይ ነኝ! እኔ ዑበይዳ ነኝ!» ብለው በመለሱ ጊዜ አጋሪዎቹ፦ «እናንተም እንደ እኛ የተከበራችሁ ሰዎች ናችሁ። ከእናንተ ጋር መዋጋትን ተቀብለናል» አሉ። ጀግኖቹ የእስልምና ሙጃሂዶች አጋሪዎቹን በመጀመሪያ ወደ ኢማን ጠሩ፤ እነርሱ ግን አልተቀበሉም። ይህን ጊዜ ሦስቱም በአንድነት ሰይፎቻቸውን መዝዘው በአጋሪዎቹ ላይ ተሰነዘሩ። ሰይዲና ሐምዛና ሰይዲና ዐሊይ ከሓዲዎቹን ዑትባንና ወሊድን በአንድ ምት ገደሏቸው። ሰይዲና ዑበይዳ ሸይባን አቆሰሉ። ሸይባም ዑበይዳን አቆሰለ። ሰይዲና ሐምዛና ሰይዲና ዐሊይ ለዑበይዳ እርዳታ ደርሰው ሸይባን እዚያው ገደሉት። ሰይዲና ዑበይዳን አቅፈው ወደ ክቡር ረሱሉላህ ዘንድ አመጧቸው።16 ከሰይዲና ዑበይዳ ኢብኑ ሐሪስ የተባረከ ቁርጭምጭሚት ደምና መቅኒ ይፈስ ነበር። እርሳቸው ግን ለዚህ ሁኔታቸው ምንም ሳይጨነቁ፦ «ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! በዚህ ሁኔታዬ ብሞት ሸሂድ አይደለሁምን?» ብለው ጠየቁ። ክቡር ነብያችንም፦ «አዎን፣ አንተ ሸሂድ ነህ» ብለው የጀነት ሰው መሆናቸውን አበሠሯቸው። (ሰይዲና ዑበይዳ ረዲየላሁ ዐንሁ ከጦርነቱ ሲመለሱ ሶፍራ በሚባለው ቦታ አረፉ።) በዚህ ፍልሚያ ሦስት ታላላቅ ሰዎቻቸውን ያጡት አጋሪዎች ግራ ተጋቡ። ቢሆንም አቡ ጀህል የሠራዊቱን ሞራል ለማስተካከል፦ «የዑትባን፣ የሸይባንና የወሊድን መሞት አትመልከቱ፤ እነርሱ በውጊያው ቸኩለው በከንቱ ሞቱ! እምላለሁ፤ ሙስሊሞችን ይዘን በገመድ ሳናስር አንመለስም!…» እያለ ሊያጽናናቸው ይሞክር ነበር። ጀግኖቹ ሶሓቦች ግን ይህን የአጋሪዎች ጭፍራ በተቻለ ፍጥነት በሰይፎቻቸው ለመቅጣት ትዕግሥት አጥተው ነበር። ክቡር ነብያችንም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከተባረከ አንደበታቸው ያልተለየውን ይህን ዱዓ ይደጋግሙ ነበር፦ «አላህ ሆይ! የገባህልኝን ቃል ፈጽምልኝ!.. አላህ ሆይ! ይህችን አንድ እፍኝ ሙስሊሞች ብታጠፋ ከዚህ በኋላ በምድር ላይ የሚያመልክህ አይገኝም!…»

በዚህ ጊዜ ከአጋሪዎቹ ሰልፍ ከቁረይሽ እጅግ ደፋርና ስል ቀስተኞች አንዱ የሆነው፣ ገና ሙስሊም ያልሆነው የሰይዲና አቡበክር ልጅ ዐብዱረሕማን ወደ ሜዳ ወጥቶ ተፋላሚ ጠየቀ። በዚህ የጁላይ ወር የቀትር ሙቀት ከሙጃሂዶቹ ሰልፍም አንድ ሰው ወዲያውኑ ሰይፉን ይዞ ወደፊት ሲወጣ ታየ። ይህ ሰው በመጀመሪያ ሙስሊም በመሆንና በሲዲቅነት ማዕረግ የተከበሩት፣ ከነብያት ቀጥሎ ከሰዎች ሁሉ የላቁት ጀግናው ሰይዲና አቡበክር ነበሩ… ልጃቸውን ለመዋጋት ወደፊት ተሰንዝረው ነበር። ነገር ግን የዓለማት ሰይድ፦ «አቡበክር ሆይ! አንተ ለእኔ የሚያይ ዓይኔና የሚሰማ ጆሮዬ መሆንህን አታውቅምን? ከጎኔ አትለይ! በአካሌና በልቤ ላይ የሚደርስ ጭንቀት ሁሉ የተባረከ ፊትህን በማየት ይቀልላል። በአንተ ልቤ ይበረታል» አሏቸው።

በዚህም ከመዋጋት ከለከሏቸው። አቡበክር ሲዲቅ ልጃቸውን፦ «አንተ ርኩስ! ከእኔ ጋር ያለህ ዝምድና ወዴት ቀረ?» ከማለት ራሳቸውን መግታት አልቻሉም።

ከዚያም የነብያት ሱልጣን ሐቢቡል አክረም ወደ መሬት ጎንበስ ብለው አንድ እፍኝ አሸዋ ሲያነሡ ታዩ። ይህን አሸዋ ወደ ጠላት እየበተኑ፦ «ፊቶቻቸው ይጥቆሩ!… አላህ ሆይ! በልቦቻቸው ፍርሃትን ጣል፤ እግሮቻቸውንም አንቀጥቅጥ!» አሉ፤ ወደ ሶሓቦቻቸውም ዞረው፦ «ለጥቃት ተነሡ!.. አጥቁ!» የሚል ትእዛዝ ሰጡ። ምልክት ብቻ ይጠብቁ የነበሩት ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች ቀደም ሲል በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት መንቀሳቀስ ጀመሩ። «አላሁ አክበር!… አላሁ አክበር!…» በሚሉ ድምፆች መካከል ፍላጻዎች መፏጨት፣ ድንጋዮች ዒላማቸውን መምታት፣ ጦሮችም ጥሩሮችን መምታት ጀመሩ… የአላሁ ተዓላ አንበሶች፦ ሰይዲና ሐምዛ በሁለት እጆቻቸው በያዟቸው ሁለት ሰይፎች ይዋጉ ነበር፤ ሰይዲና ዐሊይ፣ ሰይዲና ዑመር፣ ዙበይር ኢብኑል ዐዋም፣ ሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስ፣ አቡ ዱጃና17 እና ዐብዱላህ ኢብኑ ጀሕሽ በአጋሪዎቹ ሰልፍ በአንዱ ጫፍ ገብተው በሌላው ጫፍ ይወጡ ነበር፤ ከሓዲዎቹንም ግራ ያጋቡ ነበር። እያንዳንዳቸው የማይደፈር ምሽግ ሆነው ነበር። «አላሁ አክበር!… አላሁ አክበር!…» የሚሉ ድምፆች ዓለምን ሞሉ፤ የአላሁ ተዓላ የክብሩ ታላቅነት በከሓዲዎቹ አናት ላይ እንደ መዶሻ ወረደ። ክቡር ነብያችን፦ «ሐዩ ሆይ! ቀዩም ሆይ! ሐዩ ሆይ! ቀዩም ሆይ!» እያሉ አላሁ ተዓላን ይማጸኑ ነበር። ሰይዲና ዐሊይ፦ «በበድር ከሁላችንም እጅግ ደፋሩና ጀግናው መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ነበሩ። ወደ አጋሪዎቹ ሰልፍ እጅግ የቀረቡትም እርሳቸው ነበሩ። በተጨነቅን ጊዜ ወደ እርሳቸው እንጠለል ነበር» ብለዋል።

አጋሪዎቹ መሪያቸውን አቡ ጀህልን በመካከላቸው አደረጉት። ከእነርሱ አንዱን እንደ አቡ ጀህል አልብሰው አስመሰሉት። የዚህ ዕድለ ቢስ ስም ዐብዱላህ ኢብኑ ሙንዚር ነበር። ሰይዲና ዐሊይ በዐብዱላህ ላይ ተሰንዝረው በአቡ ጀህል ዓይን ፊት ራሱን ቆረጡት። ከዚያም አቡ ቀይስን እንዲሁ አለበሱት። እርሱንም ሰይዲና ሐምዛ ገደሉት።

ሰይዲና ዐሊይ ከአንድ አጋሪ ጋር ይዋጉ ነበር። አጋሪው ሰይፉን በሰይዲና ዐሊይ ላይ ሰንዝሮ ሰይፉ በጋሻው ውስጥ ተሰክቶ ቀርቶ ነበር። ሰይዲና ዐሊይ ዙልፊቃራቸውን በአጋሪው ጥሩር የለበሰ አካል ላይ አሳርፈው ከትከሻው እስከ ደረቱ ከጥሩሩ ጋር በሰነጠቁት ጊዜ ከራሳቸው በላይ አንድ ሰይፍ ሲያብረቀርቅ አዩ። በፍጥነት ራሳቸውን ዝቅ አደረጉ። ሰይፉን ያብረቀረቁት፦ «ይኸው! ይህቺ ደግሞ ከሐምዛ ኢብኑ ዐብዱልሙጠሊብ ናት!» ባሉ ጊዜ የአጋሪው ራስ ከራስ ቁሩ ጋር መሬት ላይ ወደቀ። ሰይዲና ዐሊይ ዞረው ሲመለከቱ አጎታቸው ሰይዲና ሐምዛ በሁለት ሰይፎች ሲዋጉ አዩ። ነብያችን ሶሓቦቻቸው እንዲህ በጀግንነት ሲዋጉ ባዩ ቁጥር፦ «እነርሱ በምድር ላይ ያሉ የአላሁ ተዓላ አንበሶች ናቸው» እያሉ ያደንቋቸው ነበር።

«አላህ ሆይ! የገባህልኝን ቃል ፈጽምልኝ!.. አላህ ሆይ! ይህችን አንድ እፍኝ ሙስሊሞች ብታጠፋ ከዚህ በኋላ በምድር ላይ የሚያመልክህ አይገኝም!…» ሐዲስ ሸሪፍ

በአንድ ወቅት ከክቡር ረሱሉላህ አጠገብ ይዋጉ የነበሩት የሰይዲና ዑካሻ ሰይፍ ተሰበረ። ይህን ያዩት ውዱ ነብያችን መሬት ላይ ያዩትን አንድ በትር አንሥተው ሰጧቸውና፦ «ዑካሻ ሆይ! በዚህ ተዋጋ!..» አሉ። ዑካሻ በትሩን እንደተቀበሉ በትሩ የነብያችን ተአምር ሆኖ ረጅም፣ የሚያብረቀርቅ፣ ጀርባው ጠንካራና ስል ሰይፍ ሆነ። በዚህ ሰይፍ እስከ ጦርነቱ ፍጻሜ ድረስ ብዙ አጋሪዎችን ገደሉ።

የዓለማት ሰይድ ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በአንድ በኩል እየተዋጉ በሌላ በኩል ሶሓቦቻቸውን የሚያነሣሣውን ይህን የተባረከ ሐዲስ ሸሪፍ ይናገሩ ነበር፦ «ሕልውናዬ በኃይሉ እጅ ባለው በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ዛሬ የክብሩ የላቀው አላህ ውዴታ ተስፋ በማድረግ በትዕግሥትና በጽናት የሚዋጉትን፣ ጀርባቸውን ሳያዞሩ ወደፊት እየገሠገሡ የሚገደሉትን ሐቅ ተዓላ በእርግጥ ጀነቱ ያስገባቸዋል።» ዑመይር ኢብኑ ሑማም ይህን የተባረከ ቃል በሰሙ ጊዜ፦ «ምንኛ ያምራል! ምንኛ ያምራል! እንግዲያውስ ጀነት ለመግባት ሸሂድ ከመሆኔ በቀር ሌላ ነገር አያስፈልገኝም ማለት ነው» ብለው ጥቃታቸውን ይበልጥ አፋፋሙ። በአንድ በኩል ከጠላት ጋር እየተዋጉ በሌላ በኩል፦ «ወደ አላሁ ተዓላ የሚኬደው በቁሳዊ ስንቅ ሳይሆን በሐቅ ተዓላ ፍርሃት፣ በአኺራ ሥራና በጂሃድ በሚደረግ ትዕግሥትና ጽናት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው ስንቅ ሁሉ ያለ ጥርጥር ያልቃል፣ ይጠፋልም!…» ይሉ ነበር። በዚህ ሁኔታ ሸሂድ እስኪሆኑ ድረስ ተዋጉ።

ውጊያው እጅግ ተፋፍሞ ነበር!… በአንድ ሶሓቢይ ላይ ቢያንስ ሦስት አጋሪዎች በአንድነት ይሰነዘሩ ነበር። እያንዳንዳቸውን በሰይፍ ለመድረስ የሚጥሩትን ክብረ ገናናዎቹን ሶሓቦች ምንም ነገር ተስፋ ሊያስቆርጣቸው አልቻለም። «አላሁ አክበር! አላሁ አክበር!..» ባሉ ቁጥር እንደገና ይበረቱ ነበር፤ ደጋግመው ከማጥቃትም አይሰለቹም ነበር። በአንድ ወቅት የአጋሪዎች ጥቃት በረታ፤ ሶሓቦችም ተጨነቁ። በዚያን ጊዜ ክቡር ረሱሉላህ ከሰይዲና አቡበክር ጋር ከተምር ዛፍ ቅርንጫፎች ወደተሠራው ድንኳናቸው ገቡ። ነብያችን እንደገና አላሁ ተዓላን መማጸን ጀመሩ። «ጌታዬ ሆይ! ቃል የገባህልኝን እርዳታ ለግሰኝ!…» እያሉ ይለምኑ ነበር። በዚያን ቅጽበት ወሕይ መጣ። በትርጓሜ እንዲህ ተባለ፦ «ያን ጊዜ ከጌታችሁ እርዳታንና ድልን ትለምኑ ነበር፤ እርሱም፦ ‹በእርግጥ እኔ እርስ በርሳቸው የሚከታተሉ አንድ ሺህ መላእክትን ይዤ ለእርዳታችሁ እደርሳለሁ› ብሎ ጥያቄያችሁን መልሶ ዱዓችሁን ተቀበለ።»18 ክቡር ነብያችን ወዲያውኑ ተነሥተው፦ «አቡበክር ሆይ! የምሥራች! የአላሁ ተዓላ እርዳታ ደረሰልህ! እነሆ እኚያ ጂብሪል ናቸው። በአሸዋ ኮረብታዎች ላይ የፈረሳቸውን ልጓም ይዘው፣ ታጥቀው ትእዛዝ ይጠብቃሉ» አሉ። በሱረቱ አል-አንፋል እንደተገለጸው ክብሩ የላቀው አላህ ለመላእክት በትርጓሜ እንዲህ ብሎ ነበር፦ «ያን ጊዜ ጌታህ ለመላእክት እንዲህ ሲል ወሕይ አወረደ፦ ‹እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ (ለሙስሊሞች ድልና እርዳታ በመስጠት ረገድ)። በሉ፣ ምእመናንን (በድል የምሥራች) አበርቷቸው፤ ኃይልና ብርታትም ስጧቸው። እኔ አሁን በከሓዲዎች ልብ ውስጥ ድንጋጤንና ፍርሃትን እጥላለሁ። አንገቶቻቸውን ከላይ ምቱ፤ የእጆቻቸውንና የእግሮቻቸውን ጣቶች መገጣጠሚያዎች፣ አንጓዎቻቸውን ስበሩ!› ምክንያቱም እነርሱ አላሁ ተዓላንና መልዕክተኛውን ተቃወሙ። አላሁ ተዓላንና መልዕክተኛውን የሚቃወም ሰው (በቅጣቱ ይያዛል)፤ የአላሁ ተዓላ ቅጣት እጅግ ብርቱ ነው!»19

በዚህ ትእዛዝ ጂብሪል፣ ሚካኢልና ኢስራፊል ዐለይሂሙ ሰላም እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ መላእክትን ይዘው በተራ በውዱ ነብያችን አጠገብ፣ በቀኛቸውና በግራቸው ቦታቸውን ያዙ።20

ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም በራሳቸው ላይ ቢጫ ጥምጣም ጠምጥመው ነበር። የሌሎቹ መላእክት ራሶች ላይ ደግሞ ነጭ ጥምጣሞች ነበሩ። የጥምጣሞቻቸውን ጫፎች ወደ ጀርባቸው አንጠልጥለው ነጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ነበር። የዓለም መሪ ለሶሓቦቻቸው፦ «መላእክት ምልክትና መለያ አላቸው። እናንተም ለራሳችሁ ምልክትና መለያ አድርጉ!» አሉ።

ዙበይር ኢብኑል ዐዋም ቢጫ፣ አቡ ዱጃና ደግሞ ቀይ ጨርቅ እንደ ጥምጣም በራሳቸው ላይ ጠመጠሙ። ሰይዲና ዐሊይ ነጭ ላባ፣ ሰይዲና ሐምዛም በደረታቸው ላይ የሰጎን ላባ አደረጉ። መላእክት ወደ ጦርነቱ በገቡ ጊዜ ሁኔታው በቅጽበት ተለወጠ። ሶሓቦች በፊታቸው ባለው ከሓዲ ላይ ገና ሰይፋቸውን ሳይሰነዝሩ የእርሱ ራስ ከአካሉ ተለይቶ መሬት ላይ ይወድቅ ነበር። በክቡር ነብያችን ቀኝና ግራ፣ ፊትና ኋላ የማይታወቁ ሰዎች ከአጋሪዎች ጋር ሲዋጉ ይታዩ ነበር።

ሰይዲና ሰህል እንዲህ ብለው ተረኩ፦ «በበድር ጦርነት ከእኛ እያንዳንዳችን በአንድ አጋሪ ራስ ላይ ሰይፋችንን በሰነዘርን ጊዜ ሰይፉ ዒላማውን ገና ሳይደርስ ራሱ ከአካሉ ተለይቶ መሬት ላይ ሲንከባለል እናይ ነበር!…»

የአቡ ጀህል መገደል

የአጋሪዎቹ ሰንደቅ ያዥ አቡ ዐዚዝ ኢብኑ ዑመይር ተማረከ። አዛዣቸው አቡ ጀህል ግን ቁረይሾችን ለማደፋፈር ያለማቋረጥ ግጥሞችን እየተናገረ የወታደሮቹን ሞራል ለማስተካከል ይጥር ነበር። እንደ ወጣት ጎረምሳ እየተሰነዘረ፦ «እናቴ የወለደችኝ ለእንዲህ ያሉ ቀናት ነው!…» እያለ ይመካ፣ ወጣቶቹንም ያነሣሣ ነበር። ከአጋሪዎች ዑበይዳ ኢብኑ ሰዒድ ከራሱ እስከ እግሩ ጥሩር ለብሶ ነበር። የሚታዩት ዓይኖቹ ብቻ ነበሩ። በፈረሱ ላይ ሆኖ አንድ ጊዜ ወደዚያ፣ አንድ ጊዜ ወደዚህ እየዞረ፦ «እኔ አቡ ዛቲል ከሪሽ ነኝ! እኔ አቡ ዛቲል ከሪሽ ነኝ!»፣ ማለትም እኔ ትልቅ ሆድ ያለኝ፣ የሆድ አባት ነኝ እያለ በራሱ መንገድ ይገዳደር ነበር። ጀግናው ሙጃሂድ ሰይዲና ዙበይር ኢብኑል ዐዋም ወደ እርሱ ቀርበው ጦራቸውን በትክክል ዓይኑ ላይ አነጣጥረው፦ «አላሁ አክበር!» ብለው ወረወሩት። ዒላማውን ያገኘው ጦር ከፈረሱ ላይ ጣለው። ሰይዲና ዙበይር እየሮጡ ወደ እርሱ በደረሱ ጊዜ ዑበይዳ ሞቶ ነበር። እግራቸውን በጉንጩ ላይ ረግጠው በሙሉ ኃይላቸው ቢጎትቱትም ጦሩ በችግር ወጣ፤ ተጣምሞም ነበር። ሰይዲና ዙበይር በበድር ጦርነት ያሳዩት ጀግንነት እጅግ ታላቅ ነበር። በአካላቸው ላይ ያልቆሰለ ቦታ አልቀረም ነበር። ይህን ሁኔታ ልጃቸው ዑርዋ እንዲህ ብለው ተርከው ነበር፦ «አባቴ ሦስት ከባድ የሰይፍ ምቶች ደርሰውባቸው ነበር። ከእነዚህም አንዱ በአንገታቸው ላይ ነበር። ቁስሉ ጣቴን ማስገባት እስክችል ድረስ ጥልቅ ጠባሳ ትቶ ነበር።» ዐብዱረሕማን ኢብኑ ዐውፍም ከቁረይሾች ጋር ያለ ርኅራኄ ይዋጉ ነበር፤ ከቁስሎቻቸው የሚፈሰውን ደም ከቁብ ሳይቆጥሩ ያገኙትን ሁሉ ይጥሉ ነበር። ሰይዲና ዐብዱረሕማን የተመለከቱትን አንድ ክስተት እንዲህ ብለው ተረኩ፦ «በአንድ ወቅት ፊቴ ማንም አልቀረም ነበር። ወደ ቀኜና ወደ ግራዬ ስመለከት ከአንሷሮች ሁለት ወጣቶች ዓይኔ ውስጥ ገቡ። ከእነርሱ ይበልጥ ብርቱና ጠንካራ ምት ካለው ጋር መሆን ፈለግሁ። ከእነዚህ ሁለት ወጣቶች አንዱ በዓይኑ ገመገመኝ፤ ከዚያም ወደ እኔ ዞሮ፦ ‹አጎቴ ሆይ! አቡ ጀህልን ያውቁታልን?› ብሎ ጠየቀኝ። እኔም፦ ‹አዎን፣ አውቀዋለሁ› አልኩ፤ ‹የወንድሜ ልጅ ሆይ! አቡ ጀህልን ምን ልታደርገው ነው?› ብዬም ጠየቅሁት። እርሱም፦ ‹ረሱሉላህን እንደሚሰድብ ተነግሮኛል። በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ባየሁት ጊዜ እስክገድለው ወይም እኔ ራሴ እስክሞት ድረስ ፈጽሞ ከእርሱ አልለይም› አለ። አንድ ወጣት በስሜት ተሞልቶ የተናገረው ይህ ቁርጥና ጽኑ ቃል በእውነቱ አስደነቀኝ።

«አቡበክር ሆይ! አንተ ለእኔ የሚያይ ዓይኔና የሚሰማ ጆሮዬ መሆንህን አታውቅምን? ከጎኔ አትለይ! በአካሌና በልቤ ላይ የሚደርስ ጭንቀት ሁሉ የተባረከ ፊትህን በማየት ይቀልላል። በአንተ ልቤ ይበረታል» ሐዲስ ሸሪፍ

ሁለተኛው ወጣትም ገምግሞኝ የመጀመሪያው ያለውን አለ። በዚህ ጊዜ አቡ ጀህልን አየሁት! እርሱ በቁረይሽ ሠራዊት መካከል ያለማቋረጥ ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር። እኔም፦ ‹እናንተ ወጣቶች ሆይ! ያ ወዲያና ወዲህ በችኮላ የሚሄደው ሰው አቡ ጀህል ነው› ባልኩ ጊዜ ወዲያውኑ ሰይፎቻቸውን ይዘው ወደ አቡ ጀህል ሄዱ።

ከእርሱም ጋር መዋጋት ጀመሩ። እነዚህ ወጣቶች የእመቤት ዐፍራእ ልጆች ወንድማማቾቹ ሙዓዝና ሙዐዊዝ ነበሩ።» በዚህ መሀል ከሶሓቦች ጀግኖች አንዱ የሆኑት ሙዓዝ ኢብኑ ዐምር ወደ አቡ ጀህል አጠገብ የመድረስ ዕድል አገኙ። ረጅም ጭራ ባለው ፈረስ ላይ በነበረው በአቡ ጀህል ላይ ተሰንዝረው በሙሉ ኃይላቸው እግሩን በሰይፋቸው መቱት። የአቡ ጀህል እግር መሬት ላይ ወደቀ። በዚያን ጊዜ ለአባቱ እርዳታ የደረሰውና ገና ሙስሊም ያልሆነው ዒክሪማ ከሰይዲና ሙዓዝ ኢብኑ ዐምር ጋር መዋጋት ጀመረ።

በዚያ ቅጽበት ወንድማማቾቹ ሙዓዝና ሙዐዊዝ እንደ ጭልፊት ወደፊት ተወረወሩ። ያገኙትን ሁሉ እየጣሉ አቡ ጀህል ዘንድ ደረሱ። የሞተ እስኪመስላቸው ድረስ በሰይፎቻቸው መቱት።

ሰይዲና ሙዓዝ ኢብኑ ዐምር ግን ከዒክሪማ ጋር ባደረጉት ውጊያ በእጃቸውና በክንዳቸው ቆስለው ነበር። የተባረከ እጃቸው ከአንጓው ተቆርጦ በቆዳ ላይ ተንጠልጥሎ ቀርቶ ነበር። ራሳቸውን ለውጊያው አሳልፈው የሰጡት ሙዓዝ ኢብኑ ዐምር በእጃቸው የሚቆዩበትና ለማከም የሚያስሩበት ጊዜ አልነበራቸውም። የተቆረጠ እጃቸው በቆዳ ላይ እየተንጠለጠለ እንኳ በጀግንነት ይዋጉ ነበር።

አላሁ አክበር!… ምንኛ ብርቱ ኢማን ነው!… ምንኛ የሚታይ ትዕይንት ነበር!… ሰይዲና ሙዓዝ ለተወሰነ ጊዜ እንዲህ ከተዋጉ በኋላ የመንቀሳቀስ ችሎታቸው እንደቀነሰ አዩ። ምክንያቱ የተቆረጠው እጃቸው ነበር። ወዲያውኑ በእግራቸው ሥር አድርገው ቆርጠው ጣሉት…21

ከእስልምና መራር ጠላቶች አንዱ የሆነው ነውፈል ኢብኑ ኹወይሊድ ከቁረይሽ እጅግ የተወደሱ ታጋዮች አንዱ ነበር። ያለማቋረጥ እየጮኸ የአጋሪዎችን መንጋ ለማነሣሣትና ለማስቆጣት ይጥር ነበር። ክቡር ነብያችን ይህን ሁኔታውን ባዩ ጊዜ፦ «አላህ ሆይ! በነውፈል ኢብኑ ኹወይሊድ ላይ ረዳቴ ሁን። እርሱን አስወግድልኝ» ብለው ዱዓ አድርገው ነበር። የአላሁ ተዓላ አንበሳ ሰይዲና ዐሊይ አጋሪውን ነውፈልን ባዩ ጊዜ ወዲያውኑ ተሰነዘሩበት። ሰይፋቸውን በኃይል አወረዱ፤ እግሮቹ በጥሩር የተሸፈኑ ቢሆኑም ሁለቱንም በአንድነት እስኪቆርጡ ድረስ መቱት። ከዚያም ሰይፋቸውን በአንገቱ ላይ አሳርፈው ራሱን ከአካሉ ለዩት።22

ቢላል አል-ሐበሺን በሚያቃጥል አሸዋ ላይ አጋድሞ በደረታቸው ላይ ግዙፍ ቋጥኞችን ያኖረው ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ ከአጋሪዎች እጅግ መራሮቹ አንዱ ነበር። ክቡር ረሱሉላህን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ለማሰቃየት እያንዳንዱን አጋጣሚ የሚጠቀመው ይህ ታላቅ የእስልምና ጠላት በበድር ሸለቆም አጋሪዎችን ለማሰባሰብ ይጥር፣ የእስልምናን ኑር ለማጥፋት ይታገል ነበር። ይህን ሁኔታውን ያዩት ሰይዲና ቢላል ሰይፋቸውን መዝዘው ወደ እርሱ ቀርበው ፊቱ ቆሙና፦ «የክህደት አለቃ ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ ሆይ!… አንተ ከዳንክ እኔ አልዳን!» ብለው ተሰነዘሩበት። በሌላ በኩልም፦ «የአንሷር ወንድሞች ሆይ! ድረሱ፤ የክህደት አለቃ እዚህ አለ!» እንዳሉ ሶሓቦች ኡመያን ከበው ወዲያውኑ ገደሉት።23

በአጋሪዎቹ ሠራዊት ውስጥ ከዚህ በኋላ መሪ አልቀረም ነበር። እያንዳንዳቸው ምን እንደሚያደርጉ አያውቁም ነበር፤ በዘፈቀደ ለመሸሽ ይሞክሩ ነበር። የክህደት ምሽግ ፈርሶ ነበር። ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች ማሳደዱን ቀጠሉ። ከአጋሪዎች ከፊሉ ተማረኩ። የውዱ ነብያችን አጎት ዐባስም ከምርኮኞቹ መካከል ነበሩ።24

ድሉ የምእመናን ሆነ

ክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ክብረ ገናናዎቹን ሶሓቦቻቸውን፦ «ስለ ነውፈል ኢብኑ ኹወይሊድ የሚያውቅ አለ?» ብለው ጠየቁ። ሰይዲና ዐሊይ ወደፊት ወጥተው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኔ ገደልኩት» አሉ። በዚህ ወሬ እጅግ የተደሰቱት ውዱ ነብያችን «አላሁ አክበር!» ብለው ተክቢር አደረጉ፤ «አላሁ ተዓላ ስለ እርሱ ያደረግኩትን ዱዓ ተቀበለ» አሉም።

ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ መገደሉን በነገሯቸው ጊዜም እጅግ ተደሰቱና፦ «አልሐምዱሊላህ! ለአላሁ ተዓላ ምስጋና ይገባው። ጌታዬ ባሪያውን አረጋገጠ፤ ሃይማኖቱንም የበላይ አደረገ» አሉ።

ረሱሉል አክረም ስለ አቡ ጀህል፦ «አቡ ጀህል ምን አደረገ ይሆን? ምን ሆነ? ሄዶ የሚያይ ማነው?» ብለው በሙታን መካከል እንዲፈለግ አዘዙ። ፈለጉት፤ ግን አላገኙትም። ክቡር ነብያችንም፦ «ፈልጉት፤ ስለ እርሱ የተናገርኩት ቃል አለ። ካላወቃችሁት በጉልበቱ ላይ ያለውን የቁስል ጠባሳ ተመልከቱ። አንድ ቀን እኔና እርሱ በዐብዱላህ ኢብኑ ጁድዓን ግብዣ ላይ ነበርን። ሁለታችንም ወጣቶች ነበርን። እኔ ከእርሱ ትንሽ እበልጥ ነበር። በተጨናነቅን ጊዜ ገፋሁት። በጉልበቶቹ ላይ ወደቀ። ከጉልበቶቹ አንዱ ቆሰለ፤ የዚያም ቁስል ጠባሳ ከጉልበቱ አልጠፋም» አሉ።

ይህን ጊዜ ዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ አቡ ጀህልን ለመፈለግ ሄዱ። ቆስሎ አገኙትና አወቁት። «አቡ ጀህል አንተ ነህን?» አሉት። በአንገቱ ላይ እግራቸውን ረገጡ። ጢሙን ይዘው ጎተቱትና፦ «የአላሁ ተዓላ ጠላት ሆይ! በመጨረሻ አላሁ ተዓላ አዋረደህ፣ አሳነሰህም አይደለምን?» አሉ። አቡ ጀህልም፦ «ለምን ያዋርደኛል፣ ያሳንሰኛል! አንተ የበግ እረኛ! አላህ አንተን ያዋርድህ፣ ያሳንስህ። አንተ ለመውጣት እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ቦታ ላይ ወጥተሃል! ይልቅ ዛሬ ድልና አሸናፊነት በየትኛው ወገን እንደሆነ ንገረኝ» አለ። ሰይዲና ኢብኑ መስዑድ፦ «ድሉ በአላህና በመልዕክተኛው ወገን ነው» አሉ። የአቡ ጀህልን የራስ ቁር ከራሱ ላይ እያወለቁ፦ «አቡ ጀህል ሆይ! እገድልሃለሁ» አሉ። አቡ ጀህልም፦ «የሕዝቡን አለቃ የገደልክ የመጀመሪያው አይደለህም። ነገር ግን በእውነቱ አንተ እኔን መግደልህ በጣም ይከብደኛል። ቢያንስ ራሴ ግርማ ያለው እንዲመስል አንገቴን ከደረቴ አጠገብ ቁረጥ!» ብሎ ክህደቱ፣ ኩራቱና ትዕቢቱ ምን ያህል ደረጃ ላይ እንደደረሰ አሳየ።

ኢብኑ መስዑድ የአቡ ጀህልን ራስ በራሳቸው ሰይፍ መቁረጥ ስላልቻሉ በአቡ ጀህል ሰይፍ ቆረጡት፤ መሣሪያውን፣ ጥሩሩን፣ የራስ ቁሩንና ራሱን አምጥተው በክቡር ነብያችን ፊት አኖሩና፦ «አባቴና እናቴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ይህ የአላሁ ተዓላ ጠላት የአቡ ጀህል ራስ ነው» አሉ። ውዱ ነብያችንም፦ «ከእርሱ በስተቀር አምላክ የሌለ አላህ እርሱ ነው» አሉ። ከዚያም ተነሥተው ከሶሓቦቻቸው ጋር የአቡ ጀህል ሬሳ ወዳለበት ሄዱ። እዚያም፦ «አንተን ያዋረደህና ያሳነሰህ አላሁ ተዓላ ምስጋና ይገባው።

የአላህ ጠላት ሆይ! አንተ የዚህ ኡማ ፊርዐውን ነበርክ» አሉ። ከዚያም፦ «ጌታዬ ሆይ! ለእኔ የገባኸውን ቃል ፈጸምክ» ብለው አላሁ ተዓላን አመሰገኑ። ክቡር ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የቆሰሉትን ሶሓቦች ቁስል አሳሰሩ። ሸሂድ የሆኑትን አስቆጠሩ። ከሙሃጂሮች ስድስት፣ ከአንሷሮች ስምንት በድምሩ አሥራ አራት ሸሂዶች ወድቀው ነበር። የሁሉም የተባረኩ ነፍሳት ወደ ጀነት ሲበሩ የእስልምናን ኑር ለማጥፋት ከሚታገሉት አጋሪዎች ሰባ ሰዎች ተገደሉ፤ ሰባ ሰዎችም ተማረኩ። ክቡር ረሱሉላህ ድሉን እንዲያበሥሩ ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሓንና ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳን ወደ መዲና ላኩ። ክቡር ነብያችን ለሸሂዶቹ የጀናዛ25 ሶላት አሰግደው በቀብሮቻቸው አስቀበሯቸው። ከአጋሪዎቹ ሬሳዎች ሃያ አራቱን ወደ አንድ ደረቅ ጉድጓድ፣ ሌሎቹን ደግሞ በአንድነት ወደ ጉድጓዶች ጥለው በአፈር ሸፈኗቸው። የዓለማት ሰይድ ከተከበሩት ሶሓቦቻቸው ጋር ወደ ጉድጓዱ አፋፍ መጥተው፦ «ወደ ጉድጓድ የተጣላችሁ ሆይ!» አሉ። ከዚያም የተገደሉትን አጋሪዎች ስሞች ከአባቶቻቸው ስሞች ጋር እየቆጠሩ፦ «ዑትባ ኢብኑ ረቢዓ ሆይ! ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ ሆይ! አቡ ጀህል ኢብኑ ሂሻም ሆይ!.. ለነብያችሁ ምንኛ መጥፎ ሕዝብ ነበራችሁ! እናንተ አስተባበላችሁኝ፤ ሌሎች ግን አመኑኝ፤ እውነተኛነቴንም አረጋገጡ። እናንተ ከከተማዬና ከአገሬ አስወጣችሁኝ፤ ሌሎች ግን በሮቻቸውን ከፍተውልኝ በደረታቸው አቀፉኝ። እናንተ ተዋጋችሁኝ፤ ሌሎች ግን ረዱኝ። ጌታዬ ቃል የገባላችሁን አገኛችሁትን? እኔ ጌታዬ ቃል የገባልኝን ድል አገኘሁ» አሉ።

«(ሶሓቦቼ ሆይ!) መላእክት ምልክትና መለያ አላቸው። እናንተም ለራሳችሁ ምልክትና መለያ አድርጉ!» ሐዲስ ሸሪፍ

ሰይዲና ዑመር፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ሬሳ ለሆኑ ሰዎች ነው የሚናገሩት?» ብለው ጠየቁ። ይህን ጊዜ ረሱሉል አክረም፦ «በእውነተኛ ነብይነት በላከኝ በጌታዬ እምላለሁ፤ እናንተ ከእነርሱ የበለጠ አትሰሙኝም። ነገር ግን መልስ መስጠት አይችሉም» አሉ።

አጋሪዎች ሕይወታቸውን ለማዳን ከጦር ሜዳው በፍጥነት ሲሸሹ ያመጡትን ምንም ነገር ይዘው መሄድ አልቻሉም ነበር። ሁሉም በሙስሊሞች እጅ ገባ። ክቡር ነብያችን የጦር ምርኮውን በበድር ጦርነት ለተሳተፉትና ተልእኮ ለነበራቸው ሶሓቦቻቸው ሁሉ አከፋፈሉ። በበድር ሦስት ሌሊት ተጨማሪ ቆይተው ከአሥራ ዘጠኝ ቀናት በኋላ ወደ መዲና ተመለሱ። በዚህ መሀል የምሥራች መልዕክተኞች ሆነው የተላኩት ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሓና ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳ መዲና ቀርበው ነበር። እሑድ ቀን ረፋድ ላይ ዐቂቅ ወደሚባለው ቦታ በደረሱ ጊዜ ተለያዩ። ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሓ ከአንድ በኩል፣ ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳ ደግሞ ከሌላ አቅጣጫ ወደ መዲና ገቡ። ቤት ለቤት እየዞሩ ድሉን አበሠሩ። የክቡር ረሱሉላህ ገጣሚ ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሓ ድሉን በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያሉ አበሠሩ፦

የአንሷር ማኅበረሰብ ሆይ! የምሥራች እነግራችኋለሁ፦
የአላህ ነብይ በጤናና በሰላም አሉ።
አጋሪዎች ተገደሉ፣ ተማረኩም፤
ከምርኮኞቹም መካከል እጅግ ዝነኛ ሰዎች አሉ።
የረቢዓና የሐጃጅ ልጆች ሁሉም በአንድነት
በበድር ተገደሉ፤ አቡ ጀህል ዐምር ኢብኑ ሂሻምም።

ሰይዲና ዓሲም ኢብኑ ዐዲይ፦ «ኢብኑ ረዋሓ ሆይ! የምትናገረው እውነት ነውን?» ብለው ጠየቁ። ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሓም፦ «አዎን፣ ወላሂ እውነት ነው! ኢንሻአላህ ነገ ረሱሉላህም እጆቻቸው ከታሰሩ ምርኮኞች ጋር ይመጣሉ!» አሉ።

የሰይደቲና ሩቀያ ዕረፍት

በዚያ ቀን የውዱ ነብያችን ልጅ ሰይደቲና ሩቀያ (ረዲየላሁ ዐንሃ) አርፈው ነበር። ባለቤታቸው ሰይዲና ዑስማን የጀናዛ ሶላታቸውን አሰግደው ነበር። በዚህ ሐዘን ላይ የመጣው የድል ወሬ ጥቂት አጽናናቸው።

ክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከሶሓቦቻቸው ጋር የበድርን ድል ለለገሳቸው ለአላሁ ተዓላ ምስጋና አቅርበው የምስጋና ሱጁድ ካደረጉ በኋላ ከምርኮኞቹ ጋር ወደ መዲና አል-ሙነወራ ጉዞ ጀመሩ።

ቀደም ብለው የምሥራቹን ያደረሱት ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሓና ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳ በበድር ጦርነት የተከሰተውንና እነማን ሸሂድ እንደሆኑ ተርከው ነበር። በመዲና የቀሩት ልጆች፣ ሴቶችና ተልእኮ የነበራቸው ሰዎች በድሉ እጅግ ተደስተው ነበር። ክቡር ነብያችንን ለመቀበል ወጡ። ሸሂድ ከሆኑት መካከል ሐሪሳ ኢብኑ ሱራቃም ነበሩ። የሰይዲና ሐሪሳ እናት ሩበይዕ ልጃቸው ከኩሬው ውኃ ሲጠጡ በጠላት ፍላጻ ተመትተው ሸሂድ መሆናቸውን ሰምተው ነበር። እናታችን ሩበይዕ ይህን ወሬ በሰሙ ጊዜ፦ «መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም እስካልመጡ ድረስ ለልጄ አላለቅስም። መዲናን በመምጣታቸው ባከበሩ ጊዜ እጠይቃቸዋለሁ። ልጄ በጀነት ከሆነ ፈጽሞ አላለቅስም። በጀሀነም ከሆነ ግን ከዓይኖቼ በእንባ ፈንታ ደም አፈስሳለሁ» ብለው ነበር።

ውዱ ነብያችን ከተባረኩት ሶሓቦቻቸው ጋር መዲናን በመምጣታቸው ባከበሩ ጊዜ ሩበይዕ ወደ እርሳቸው ቀርበው፦ «አባቴና እናቴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ለልጄ ለሐሪሳ ያለኝን ፍቅር ያውቃሉ። ሸሂድ ሆኖ ጀነት ገብቷልን? እንዲህ ከሆነ እታገሣለሁ። ካልሆነ ግን ከዓይኔ የደም እንባ አፈስሳለሁ» አሉ። ሐቢቡል አክረምም፦ «የሐሪሳ እናት ሆይ! ልጅሽ በአንድ ሳይሆን ከአንድ በላይ በሆኑ ጀነቶች ውስጥ ነው። ቦታው ፊርደውስ ነው» ብለው አበሠሯቸው። ይህን ጊዜ ሩበይዕ፦ «ከእንግዲህ ለልጄ አላለቅስም» አሉ። የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን በዕቃ ውኃ እንዲመጣ ጠየቁ። በእዝነታቸው የተባረከ እጃቸውን በውኃው ውስጥ አስገብተው አወጡ። ይህን ውኃ ለሰይዲና ሐሪሳ እናትና እህት አጠጧቸው። በተጨማሪም ይህን ውኃ በራሶቻቸውና በፊቶቻቸው ላይ አሻሹላቸው። ከዚያን ቀን ጀምሮ የሩበይዕና የልጃቸው ፊቶች በኑር የተሞሉ ነበሩ። ዕድሜያቸውም እጅግ ረጅም ሆነ። የፍጥረተ ዓለሙ አስተማሪ (ዐለይሂ አፍደሉ ሶለዋት) ወደ መዲና የመጡትን ሰባ ምርኮኞች በሶሓቦቻቸው መካከል አከፋፍለው መልካም አያያዝ እንዲደረግላቸው አዘዙ። ስለ ምርኮኞቹ ዕጣ ፈንታ ከአላሁ ተዓላ ገና ወሕይ አልመጣም ነበር። ክቡር ረሱሉላህ ከሶሓቦቻቸው ጋር ከተመካከሩ በኋላ ምርኮኞቹ በቤዛ እንዲለቀቁ ወሰኑ።

የቤዛው መጠን በእያንዳንዱ ምርኮኛ ሀብት መሠረት ተወሰነ። ገንዘብ ከሌላቸው መካከል ማንበብና መጻፍ የሚችሉት በመዲና ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ አሥር ሰዎች ማንበብና መጻፍ ያስተምራሉ፤ ከዚያ በኋላ ወደ መካ መሄድ ይችላሉ። ክቡር ነብያችን በምርኮኞቹ መካከል ለነበሩት ለአጎታቸው ለዐባስ፦ «ዐባስ ሆይ! ለራስህ፣ ለወንድምህ ልጅ ለዑቀይል (ዐቂል) ኢብኑ አቢ ጧሊብና ለነውፈል ኢብኑ ሐሪስ ማስለቀቂያ ገንዘብ ክፈል። ምክንያቱም አንተ ሀብታም ነህ» አሉ። ሰይዲና ዐባስም፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኔ ሙስሊም ነኝ። ቁረይሾች በግድ ወደ በድር አመጡኝ» አሉ። ረሱሉላህም፦ «ሙስሊምነትህን አላሁ ተዓላ ያውቃል። እውነት የምትናገር ከሆነ አላሁ ተዓላ በእርግጥ ምንዳውን ይሰጥሃል። ነገር ግን አንተ በውጫዊ ሁኔታ በእኛ ላይ ነህ። ስለዚህ ማስለቀቂያ ገንዘብህን መክፈል አለብህ» አሉ። ዐባስም፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እንደ ምርኮ ከወሰዱብኝ 800 ዲርሀም በስተቀር ሀብት የለኝም» ባሉ ጊዜ ክቡር ነብያችን፦ «ዐባስ ሆይ! እነዚያን የወርቅ ሳንቲሞች ለምን አትናገርም?» አሉ። እርሳቸውም፦ «የትኞቹን ወርቆች?» አሉ። ውዱ ነብያችንም፦ «ከመካ በምትወጣበት ቀን ለባለቤትህ ለሐሪስ ልጅ ለኡሙል ፈድል የሰጠሃቸው ወርቆች! እነርሱን በሰጠህ ጊዜ ከእናንተ በስተቀር ማንም አጠገባችሁ አልነበረም። ለኡሙል ፈድል፦ ‹በዚህ ጉዞ ምን እንደሚገጥመኝ አላውቅም። መከራ ደርሶብኝ ባልመለስ ይህን ያህሉ የአንቺ ነው፤ ይህን ያህሉ ለፈድል፣ ይህን ያህሉ ለዐብዱላህ፣ ይህን ያህሉ ለዑበይዱላህ፣ ይህን ያህሉ ደግሞ ለቁሰም ነው› ብለህ የሰጠሃቸው ወርቆች» ባሉ ጊዜ ሰይዲና ዐባስ ተደነቁና፦ «እምላለሁ፤ እነዚህን ወርቆች ለባለቤቴ በሰጠሁ ጊዜ አጠገባችን ማንም አልነበረም። ይህን ከየት አወቁ?» አሉ። ክቡር ነብያችንም፦ «አላሁ ተዓላ አሳወቀኝ» ባሉ ጊዜ ዐባስ፦ «እርስዎ የአላሁ ተዓላ መልዕክተኛ መሆንዎንና እውነት እንደሚናገሩ እመሰክራለሁ» ብለው የሸሃዳን ቃል ተናገሩ።26 ሙስሊም በሆኑ ጊዜ ክቡር ነብያችን ሰይዲና ዐባስን በመካ ተልእኮ ሰጧቸው። እዚያ ያሉትን ሙስሊሞች እንዲጠብቁና ከእስልምና ጋር ጠላት ስለሆኑት ሰዎች ወሬ እንዲልኩ አዘዟቸው።

«በእውነተኛ ነብይነት በላከኝ በጌታዬ እምላለሁ፤ እናንተ ከእነርሱ (ከአጋሪዎቹ ሬሳዎች) የበለጠ አትሰሙኝም። ነገር ግን መልስ መስጠት አይችሉም» ሐዲስ ሸሪፍ

በበድር ጦርነት ለተሸነፉት ቁረይሾች ምርኮኞቻቸውን በቤዛ መውሰድ እንደሚችሉ ወሬ ተላከ። ነገር ግን ከሂጅራ በፊት በነብያት ሰይድ ላይ እጅግ ብዙ ስቃይና ግፍ ያደረሰው ነድር ኢብኑል ሐሪስ አንገቱ ተቀላ። እንዲሁም መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም በካዕባ ሶላት ሲሰግዱ በተባረከ ጀርባቸው ላይ የግመል ሆድ ዕቃ የማድረግ ክፋት ያሳየው ወራዳው ዑቅባ ኢብኑ አቢ ሙዐይጥ ተገደለ። የዚህ መራር የእስልምና ጠላት ራስ ከአካሉ በተለየ ጊዜ ክቡር ረሱሉላህ አላሁ ተዓላን አመሰገኑ። ወደ እርሱ ቀርበው፦ «ወላሂ፣ አላሁ ተዓላን፣ መልዕክተኛውንና ቁርኣን ከሪምን የካደ፣ ነብዩን ከስቃይ ወደ ስቃይ የዳረገ እንዳንተ ያለ ክፉ ሰው አላውቅም» አሉ።

ምርኮኞቹ ዘመዶቻቸው በቤዛ እስኪወስዷቸው ድረስ ከሶሓቦች (ዐለይሂሙ ሪድዋን) ዘንድ ቆዩ። ሶሓቦች ሁሉ ለምርኮኞቹ እጅግ መልካም አያያዝ አደረጉላቸው፤ በምግባቸውም አካፈሏቸው።

የሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር ወንድም አቡ ዐዚዝ ከምርኮኞቹ መካከል ነበር። እርሱም እንዲህ ብሎ ተረከ፦ «እኔም በአንድ የመዲና ሙስሊም ቤት ምርኮኛ ነበርኩ። እጅግ መልካም ያደርጉልኝ ነበር፤ ጠዋትና ማታ የሚበሉትን ዳቦ ለእኔ ይሰጡኝ ነበር፤ እነርሱ ራሳቸው ተምር ብቻ ለመብላት ይገደዱ ነበር። ከእነርሱ የአንዱ እጅ ቁራሽ ዳቦ ቢገባ በቀጥታ አምጥቶ ይሰጠኝ ነበር። ከኀፍረቴ የተነሣ ዳቦውን ላመጣው መልሼ እሰጠው ነበር። እርሱ ግን ዳቦውን እንደገና ይመልስልኝ ነበር።»

ከምርኮኞቹ መካከል የዚድ የተባለ አንድ የቁረይሽ ሰውም እንዲህ ብሎ ተረከ፦ «ሙስሊሞች ከበድር ወደ መዲና ሲመጡ እኛን ምርኮኞቹን በእንስሶች ላይ አስቀመጡን፤ እነርሱ ራሳቸው ግን በእግር ሄዱ።»

ከምርኮኞቹ መካከል የኸዲጃ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እህት ልጅ፣ የክቡር ነብያችን አማች የሆነው አቡል ዓስ ኢብኑ ረቢዕም ነበር። አቡል ዓስ ከመካ ነጋዴዎች አንዱ ሲሆን ብዙ ሀብት ነበረው። በታማኝነቱና በሃይማኖተኛነቱ ይታወቅ ነበር። ከመካ የምርኮኞቹ ቤዛ በተላከ ጊዜ ሰይደቲና ዘይነብ ቤዛውን ለማሟላት እናታቸው በሠርጋቸው ላይ በስጦታ የሰጧቸውን የአንገት ሐብልም ልከው ነበር። ቤዛዎቹ በመጡ ጊዜ ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የአንገት ሐብሉን አወቁት፤ እንዲህም አሉ፦ «ሶሓቦቼ ሆይ! ተገቢ ሆኖ ካገኛችሁት የልጄን የዘይነብን ምርኮኛ ከቤዛዋ ጋር ወደ እርሷ መልሱት።» ሶሓቦችም፦ «እሺ» አሉ። ዘይነብን ወደ መዲና እንዲልክ በሚል ቅድመ ሁኔታ አቡል ዓስ ከንብረቱ ጋር ወደ መካ እንዲሄድ ተፈቀደለት። አቡል ዓስም ዘይነብንና አብረዋቸው ያሉትን ከወንድሙ ኪናና ጋር ሸኘ። ይህን የሰሙት አጋሪዎች ተቆጥተው ከሰዎቻቸው ጥቂቶቹን ከኋላቸው ላኩ። በዙ ጡዋ ደረሱባቸው። ሀባር ኢብኑል አስወድ ጦሩን በወረወረ ጊዜ ግመሉ ደንብሮ ሰይደቲና ዘይነብን ከላዩ ወርውሮ መሬት ላይ ጣላቸው። ኪናና ፍላጻዎቹን ከፊቱ አፍስሶ በዘይነብ ላይ ክፉ ለማድረግ የሚያስብን ሁሉ በፍላጻ እንደሚገድል ተናገረ። ዘይነብን ከመካ አውጥቶ ማረፊያው ድረስ አደረሳቸው። ሰይደቲና ዘይነብ በደረሰባቸው ቁስል ታመሙ። ነፍሰ ጡር ነበሩ፤ መዲና በደረሱ ጊዜ ጽንሳቸው ወረደ። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ።

አጋሪዎች በበድር ተሸንፈው በተጎሳቆለ ሁኔታ ከጦር ሜዳው መሸሻቸው በመካ ታላቅ ድንጋጤ ፈጠረ። ይህ ፈጽሞ ያልጠበቁትና በአእምሯቸውም ጭራሽ ያልመጣ ውጤት ነበር። የመጀመሪያው ወሬ አምጪ የተናገረውን አቡ ለሀብና ሌሎቹ አጋሪዎች አላመኑም። ከጦር ሜዳው የሸሸው አቡ ሱፍያን መካ በደረሰ ጊዜ ወዲያውኑ ወደ እነርሱ ጠሩት። አቡ ለሀብም፦ «የወንድሜ ልጅ ሆይ! እስኪ ንገረን፤ እንዴት ሆነ?» ብሎ ጠየቀው። አቡ ሱፍያን እዚያ አንድ ቦታ ተቀመጠ። ብዙ ሰዎችም ቆመው ያዳምጡ ነበር። አቡ ሱፍያን እንዲህ ብሎ ተረከ፦

«አትጠይቁኝ፤ ከሙስሊሞች ጋር በተገናኘን ጊዜ እጆቻችንና ክንዶቻችን የታሰሩ ይመስሉ ነበር። እንደፈለጉ አደረጉብን። ከፊላችንን ገደሉ፤ ከፊላችንን ማረኩ። እምላለሁ፤ ከወገኖቻችን ማንንም አልወቅስም፣ አላነውርም። ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በሰማይና በምድር መካከል ግራጫ ፈረሶች ላይ የተቀመጡ ነጭ የለበሱ ሰዎችን አገኘን። ምንም ነገር ሊቋቋማቸው አይችልም ነበር፤ ማንም ሊገጥማቸው አይችልም ነበር!»

በእስልምና የመጀመሪያ ዘመን ሙስሊም ቢሆኑም ከአጋሪዎች ክፋት በመፍራት ሙስሊምነታቸውን ይፋ ያላደረጉት የዐባስ ባሪያ ሰይዲና አቡ ራፊዕ እዚያ ነበሩ። በዝምታ ሲያዳምጡ የነበሩት አቡ ራፊዕ ከደስታቸው የተነሣ ሁሉን ረስተው፦ «ወላሂ እነርሱ መላእክት ናቸው!» ብለው ተናገሩ።

አቡ ለሀብ በኃይል በጥፊ መታቸው፤ አንሥቶም መሬት ላይ ፈጠፈጣቸው። ብዙም ደበደባቸው። ይህን ጊዜ እዚያ የነበሩት የሰይዲና ዐባስ ባለቤት ኡሙል ፈድል መቋቋም አልቻሉም። ምክንያቱም እርሳቸውም ቀደም ብለው ሙስሊም ሆነው ነበር። ኡሙል ፈድል በክፍሉ ካሉት ምሰሶዎች አንዱን ይዘው፦ «ማንም የለውም ብለህ ደካማ አድርገህ ቆጠርከው አይደል?» እያሉ አቡ ለሀብን በኃይል መቱት። የአቡ ለሀብ ራስ ተፈነከተ። ደሙ እየፈሰሰ ተዋርዶና ተንቆ ዞሮ ሄደ። ከሰባት ቀን በኋላ አላሁ ተዓላ ‹ጥቁር ቁስል› የሚባል በሽታ ሰጠው። በዚህ በሽታ ሞተ። ልጆቹ ሁለት ወይም ሦስት ሌሊት ሳይቀብሩት ተዉት። በመጨረሻ መሽተት ጀመረ። ሁሉም ሰው አቡ ለሀብ ከተያዘበት በሽታ ከቸነፈር እንደሚሸሽ ይሸሽ፣ ይጸየፍም ነበር። ይህን ጊዜ ከቁረይሽ አንድ ሰው ለአቡ ለሀብ ልጆች፦ «ወዮላችሁ! አታፍሩም? አባታችሁን እስኪሸት ድረስ በቤት ተዋችሁት። ቢያንስ አንድ ቦታ ቀብራችሁ ከዓይን አርቁት» አለ። ልጆቹም ለዚያ ሰው፦ «እኛ በእርሱ ላይ ካለው በሽታ እንፈራለን!» ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ ሰውዬው፦ «እናንተ ሂዱ፤ እኔም እመጣለሁ፤ እረዳችኋለሁ» አላቸው። ከዚያም ሦስቱ ተሰበሰቡ። ተሸክመው ወደ ሩቅ ቦታ ወስደው ተዉት። እስከማይታይ ድረስ በላዩ ላይ ድንጋይ ወረወሩ። አቡ ለሀብ በዚህ ሁኔታ ለዘላለም በቅጣትና በእሳት ውስጥ ወደሚቆይበት መኖሪያው፣ ጨለማና የጀሀነም ጉድጓድ ወደሆነው ቀብሩ ገባ።

በበድር ከተማረኩት ቁረይሾች መካከል ወሊድ ኢብኑል ወሊድም ነበር። እርሱን የማረኩት ዐብዱላህ ኢብኑ ጀሕሽ ነበሩ። የወሊድ ወንድሞች ሂሻምና ገና ሙስሊም ያልሆነው ኻሊድ ኢብኑል ወሊድ ወደ መዲና መጡ። ዐብዱላህ ኢብኑ ጀሕሽ ፊድየቱ ነጃት፣ ማለትም የነጻነት ቤዛ እስካልተከፈለ ድረስ ሊለቁት አልፈለጉም። ከወንድሞቹ ኻሊድ ቢስማማም፣ አባቱ አንድ እናቱ የተለየ ወንድሙ ሂሻም አልተቀበለም። ክቡር ረሱሉላህ የአባታቸው መሣሪያና ትጥቅ እንዲሰጥ ሐሳብ አቀረቡ። ሂሻም በዚህ ቢስማማም ኻሊድ አልተቀበለም። በመጨረሻ ግን መቶ ዲናር በሚያወጣው የአባታቸው ሰይፍ፣ ጥሩርና የራስ ቁር ተስማሙ። ወሊድን ከምርኮ አስለቅቀው ወደ መካ ጉዞ ጀመሩ። ነገር ግን ወሊድ በመካ መንገድ ላይ ከመዲና አራት ማይል ርቀት ላይ በምትገኘው በዙል ሑለይፋ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ክቡር ነብያችን መጡ፤ አምነውም ከሶሓቦች አንዱ ሆኑ። ሙስሊም ከሆኑ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ መካ ወደ ወንድሞቻቸው ሄዱ። ያን ጊዜ ኻሊድ ኢብኑል ወሊድ፦ «ሙስሊም ልትሆን ከነበርክ የነጻነት ቤዛው ሳይከፈል ለምን አልሆንክም? ከአባታችን የቀረልንን ማስታወሻ ከእጃችን አስወጣህ። ለምን እንዲህ አደረግህ?» ብሎ በጠየቀ ጊዜ፦ «ቁረይሾች ‹ምርኮን መቋቋም አቅቶት ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን ተከተለ› እንዳይሉ ፈራሁ» ብለው መለሱ።

«ዐባስ ሆይ! ሙስሊምነትህን አላሁ ተዓላ ያውቃል። እውነት የምትናገር ከሆነ አላሁ ተዓላ በእርግጥ ምንዳውን ይሰጥሃል። ነገር ግን አንተ በውጫዊ ሁኔታ በእኛ ላይ ነህ። ስለዚህ ማስለቀቂያ ገንዘብህን መክፈል አለብህ» ሐዲስ ሸሪፍ

ወንድሞቻቸው በዚህ መልስ እጅግ ተቆጥተው ከመኽዙም ልጆች ከሆኑ አንዳንድ ሙስሊሞች፣ ከዐያሽ ኢብኑ አቢ ረቢዓና ከሰለማ ኢብኑ ሂሻም (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ጋር አሰሯቸው። ወሊድ ኢብኑል ወሊድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በማመናቸው ምክንያት ለዓመታት ታስረው ቆዩ። ከእስልምና መራር ጠላቶች አንዱ ከሆነው ከአጎታቸው ከሂሻምና አጋሪ ከሆኑ ዘመዶቻቸው ብዙ ግፍና ስቃይ ደረሰባቸው። ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በአጋሪዎች ግፍ ሥር ለነበሩት ለዐያሽ ኢብኑ አቢ ረቢዓ፣ ለሰለማ ኢብኑ ሂሻምና ለወሊድ እንዲህ ብለው ዱዓ አደረጉ፦ «ጌታዬ ሆይ! ወሊድ ኢብኑል ወሊድን፣ ሰለማ ኢብኑ ሂሻምን፣ ዐያሽ ኢብኑ አቢ ረቢዓንና ደካማ ተደርገው የሚታዩትን (በከሓዲዎች እጅ ተጨንቀው አቅም ያጡትን) ሌሎች ምእመናን አድን። ጌታዬ ሆይ! ሙደርን (ቁረይሽን) ይበልጥ (እጅግ ክፉኛ) ረግጥ። እነዚህን ዓመታት (ለእነርሱ) የዩሱፍን ዓመታት አስመስላቸው።»

በክቡር ረሱሉላህ ዱዓ በረከት ሰይዲና ወሊድ አጋጣሚ አግኝተው ከታሰሩበት ቦታ አመለጡ። ወደ መዲና አል-ሙነወራ መጥተው ውዱ ነብያችንን አገኙ። ሐቢቡላህ ስለ ዐያሽ ኢብኑ አቢ ረቢዓና ስለ ሰለማ ኢብኑ ሂሻም ሁኔታ በጠየቁ ጊዜ እግሮቻቸው እርስ በርስ ታስረው በከባድ ቅጣትና ስቃይ ሥር እየተሰቃዩ መሆናቸውን ነገሯቸው።

የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን በሁኔታቸው እጅግ አዝነው የሚድኑበትን መንገድ ፈለጉ። ማን ሊያድናቸው እንደሚችል በጠየቁ ጊዜ ወሊድ ለዓመታት በስቃይ ሥር ቢቆዩም በታላቅ ድፍረትና ፍቅር፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኔ አድናቸዋለሁ፤ ወደ እርስዎም አመጣቸዋለሁ» ብለው መለሱ። እንደገና ወደ መካ ሄደው ምግብ የምታመጣላቸውን አንዲት ሴት በመከተል ስቃይ የሚደርስባቸው ሙስሊሞች ያሉበትን ቦታ አወቁ። ሁለቱም ጣሪያ በሌለው ሕንጻ ውስጥ ታስረው ነበር። ወሊድ በሌሊት ሞትን ተጋፍጠው በታላቅ ድፍረት በግድግዳው ወርደው ወደ ጓደኞቻቸው ደረሱ። ከማመን በቀር ሌላ ወንጀል የሌላቸው እነዚያ ሁለት የተበደሉ ሰዎች በአጋሪዎች ከድንጋይ ጋር ታስረው በዓረቢያ በረሃ በሚያቃጥል ሙቀት ውስጥ ለሁሉም ዓይነት ግፍ ይዳረጉ ነበር። ወሊድ እነዚህን የተባረኩ ወንድሞቻቸውን አድነው በግመላቸው ላይ አስቀመጧቸው። እርሳቸው ራሳቸው በእግር፣ ባዶ እግራቸውን እጅግ ወደሚወዷቸው ወደ ረሱሉላህ በተቻለ ፍጥነት ለመድረስ ወደ መዲና አል-ሙነወራ ጉዞ ጀመሩ። ያቃጥላቸው የነበረው የበረሃው ሙቀት ሳይሆን የዓለማት ሰይድን የማግኘት ፍቅር ነበር።

ተርበው፣ ተጠምተውና ባዶ እግራቸውን በሦስት ቀን መዲና ደረሱ። የእግር ጣቶቻቸው በድንጋዮቹ ጉዳት ተቦጫጭቀው ነበር። ወሊድ ኢብኑል ወሊድ በደም ተነክረው እጅግ የሚወዷቸውን ሐቢቡላህን አገኙ።

የበድር ድል ሙስሊሞችን በታላቅ ደስታ አጥለቀለቃቸው። አጋሪዎች ግን በታላቅ ሐዘንና ብስጭት ውስጥ ወደቁ። የሐበሻ ንጉሥ ነጃሺም ክቡር ረሱሉላህ ድል እንዳደረጉ በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ በአገራቸው ወደነበሩት ሶሓቦች ሄደው፦ «መልዕክተኛውን በበድር ባለ ድል ያደረገና ድልን የለገሰው አላሁ ተዓላ ምስጋና ይገባው» ብለው አበሠሩ።

ከበድር ጦርነት በኋላ የተከሰቱ ክስተቶች

ውዱ ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በመዲና ከአይሁዶችም፣ እንደ ዐብዱላህ ኢብኑ ኡበይ ካሉ ሙስሊም መስለው ከሚታዩ መናፍቃንም፣ በተጨማሪም ከአጋሪዎች ጋር ይታገሉ ነበር። ከዚህም በላይ ከመዲና ውጭ ያሉትን የአጋሪ ጎሳዎች ወደ እስልምና ይጠሩ ነበር፤ ሙስሊም በመሆን እንዲከበሩም ይጥሩ ነበር። እንደ ቀርቀራ፣ በኑ ቀይኑቃዕ፣ ሰዊቅ፣ ገጠፋን፣ በሕራን… ያሉት ዘመቻዎች ሁሉ የተካሄዱት ከበድር ጦርነት በኋላ ነበር።

በሂጅራ ሁለተኛው ዓመት የተከሰቱ አንዳንድ ክስተቶች

በዚህ ዓመት ዘካ ፈርድ መሆኑ፣ ሰደቀቱል ፊጥር መሰጠቱ፣ የዒድ ሶላቶች መሰገዳቸውና እርድ መታረዱ ትእዛዝ መጣ። ክቡር ረሱሉላህ ልጃቸውን ኡሙ ኩልሱምን ከሰይዲና ዑስማን ጋር አጋቡ። የሰይዲና ዑመርን ልጅ ሐፍሷንና ዘይነብ ቢንት ኹዘይማን (ረዲየላሁ ዐንሁማ) በኒካሕ አገቡ። የሰይዲና ዐሊይ ልጅ ሰይዲና ሐሰን ተወለዱ።

ከሰይደቲና ዓኢሻ ጋር መጋባታቸው

ክቡር ነብያችን በመካ ሳሉ ከሰይደቲና ዓኢሻ ጋር ታጭተው ነበር፤ ነገር ግን ሠርጋቸው ገና አልተደረገም ነበር። አንድ ቀን ሰይዲና አቡበክር የዓለም መሪን፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከባለቤትዎ ጋር ሠርግ ከማድረግ የከለከለዎ ምንድን ነው?» ብለው ጠየቁ። ረሱሉላህም፦ «መህሩ ነው» አሉ። ሰይዲና አቡበክር ለረሱሉላህ የመህር ገንዘብ ላኩ።27

በዚህም የእናታችን የሰይደቲና ዓኢሻ ሠርግ ተደረገ። በዚያን ጊዜ ክቡር ነብያችን የሃምሳ አምስት ዓመት ዕድሜ ነበራቸው።28 እናታችን ሰይደቲና ዓኢሻ እጅግ ብልህና ተሰጥኦ ያላቸው ሲሆኑ ክስተቶችን በቅጽበት በግጥም መልክ መናገር ይችሉ ነበር። የተማሩትንና በቃላቸው የያዙትን ነገር ፈጽሞ አይረሱም ነበር። እጅግ አስተዋይ፣ ብልህ፣ ዓሊማ፣ ሥነ ጽሑፍ አዋቂ፣ ጨዋና ጻድቅ ነበሩ። የማስታወስ ችሎታቸው እጅግ ጠንካራ ስለነበር ሶሓቦች ብዙ ነገሮችን ከእርሳቸው ጠይቀው ይማሩ ነበር። በክቡር አንቀጽ ተወደሱ።

የቀርቀረቱል ኩድር ዘመቻ

ከበኑ ሱለይምና ከገጠፋን አንድ ቡድን በቀርቀራ እንደተሰበሰበ ወሬ መጣ። ይህን ጊዜ ክቡር ነብያችን ከሙሃጂሮችና ከአንሷሮች ሁለት መቶ ሰዎችን ይዘው ከመዲና ወጡ። በመዲና ሰይዲና ኢብኑ ኡሙ መክቱም ምትክ ሆነው ቀርተው ነበር። ነጩን ሰንደቅ ሰይዲና ዐሊይ ይዘው ነበር። ወደዚያ ቦታ ደረሱ፤ ነገር ግን ማንንም አላገኙም፤ የእስልምና ሠራዊት እየመጣ መሆኑን የሰሙት አጋሪዎች ቦታውን ትተው ሄደው ነበር። በሸለቆው ውስጥ ሲጓዙ አንድ ግመል ጠባቂ አገኙ። የበኑ ሱለይምና የገጠፋን ሰዎች የት እንዳሉ ጠየቁት። ግመል ጠባቂውም፦ «እንስሶቻቸውን እንድጠብቅ ለአምስት ቀን ቀጥረውኝ ነበር። አሁን የት እንዳሉ አላውቅም» አለ። አምስት መቶ ግመሎች በምርኮ ተወሰዱ። እረኛው የሳርም ተማረከ። በቀርቀረቱል ኩድር ሸለቆ ሦስት ሌሊት ካደሩ በኋላ ግመሎቹን እየነዱ ወደ መዲና ተንቀሳቀሱ። ክቡር ነብያችን ዲራር በሚባለው ቦታ ከግመሎቹ አንድ አምስተኛውን ለይተው የቀረውን አከፋፈሉ። ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ሁለት ግመሎች ደረሱ። በማግሥቱ የሱብሒን ሶላት ሲሰግዱ የሳር የተባለው ይህ ግመል ጠባቂ ከእነርሱ ጋር ሲሰግድ አዩ። ክቡር ነብያችንም ያንን ባሪያ ነጻ አወጡ። ከዚያም በሰላም ወደ መዲና ተመለሱ።

«ወላሂ፣ አላሁ ተዓላን፣ መልዕክተኛውንና ቁርኣን ከሪምን የካደ፣ ነብዩን ከስቃይ ወደ ስቃይ የዳረገ እንዳንተ (ዑቅባ ኢብኑ አቢ ሙዐይጥ) ያለ ክፉ ሰው አላውቅም» ሐዲስ ሸሪፍ

ወሰን በሌለው የናፍቆት እሳት የሚቃጠል ነፍስ ሁሉ ኑር ይሆናል፤
በፍቅር ሕመም የፈረሰ ልብም ተመልሶ ይታነጻል።

የበኑ ቀይኑቃዕ ዘመቻ

አንድ ቀን የበኑ ቀይኑቃዕ አይሁዶች በአንዲት ሙስሊም ሴት ላይ ለማፌዝ ፈለጉ፤ ከሶሓቦች አንዱ ይህን አይተው ወዲያውኑ ሰይፋቸውን መዝዘው ያንን አይሁዳዊ ገደሉት። አይሁዶችም በበኩላቸው ተሰብስበው እኚያን የተባረኩ ሶሓቢይ ገደሏቸው፤ እርሳቸውም ሸሂድ ሆኑ። ክስተቱ ለክቡር ነብያችን ተነገረ። ረሱሉል አክረም አይሁዶችን በቀይኑቃዕ ገበያ ሰብስበው እንዲህ አሉ፦ «የአይሁድ ማኅበረሰብ ሆይ! አላሁ ተዓላ ቁረይሾችን እንደቀጣበት ያለ ቅጣት እንዳይደርስባችሁ ፍሩ፤ ሙስሊሞችም ሁኑ። እኔ በአላሁ ተዓላ የተላክሁ ነብይ መሆኔን በደንብ ታውቃላችሁ። ይህንንም፣ አላሁ ተዓላ ከእናንተ ጋር የገባውን ቃል ኪዳንም በመጽሐፋችሁ አንብባችኋል…»

«መልዕክተኛውን በበድር ባለ ድል ያደረገና ድልን የለገሰው አላሁ ተዓላ ምስጋና ይገባው» ነጃሺ አስሐማ (ረሕመቱላሂ ዐለይሂ)

የበኑ ቀይኑቃዕ ዘመቻ

ይህ እዝነት ቢደረግላቸውም አይሁዶች ያደረጉትን ስምምነት አፍርሰው የዓለማትን ሱልጣን፦ «ሙሐመድ ሆይ! ጦርነት ማካሄድ የማያውቅን ሕዝብ ማሸነፍህ አያታልህ! እንምላለን፤ እኛ ተዋጊዎች ነን! ከእኛ ጋር መዋጋት በጀመርክ ጊዜ ብቻ ምን ዓይነት ጀግኖች እንደሆንን ትረዳለህ!…» ብለው ተገዳደሩ። በዚህም የቀድሞውን ስምምነት አፍርሰው እንደሚገዳደሩ ገለጹ። ይህን ጊዜ ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም ወሕይ አመጡ፤ በእርሱም በትርጓሜ እንዲህ ተባለ፦ «(ሐቢቤ ሆይ!) ስምምነት (ከአንተ ጋር) ያደረገ ሕዝብ ክዳት (ከስምምነቱ ተቃራኒ ድርጊት) ቢያሰጋህ፣ (ጦርነት ከማወጅህ በፊት) ቃል ኪዳናቸውን በእውነትና በፍትሕ ላይ ሆነህ እንደሻርከው በቀጥታ አሳውቃቸው። ምክንያቱም አላሁ ተዓላ ከዳተኞችን አይወድም።»29

በሌላ ክቡር አንቀጽ ደግሞ በትርጓሜ እንዲህ ተባለ፦ «መልዕክተኛዬ ሆይ! ለእነዚያ ከሓዲ ለሆኑት አይሁዶች እንዲህ በላቸው፦ በእርግጥ ትሸነፋላችሁ፤ ተሰብስባችሁም ወደ ጀሀነም ትነዳላችሁ፤ ጀሀነምም ምንኛ የከፋ መኖሪያ ነው!»30

ሐቢቡል አክረም ወዲያውኑ በሸዋል ወር አጋማሽ ቅዳሜ ቀን ሠራዊት አቋቁመው የቀይኑቃዕ አይሁዶች ወዳሉበት ምሽግ ዘመቱ። ነጩን ሰንደቅ ሰይዲና ሐምዛ ይዘው ነበር፤ በመዲና ደግሞ አቡ ሉባባ ምትክ ሆነው ቀርተው ነበር።31

የተባረከው ሠራዊት የቀይኑቃዕን ምሽግ ከበበ። «እኛ ምንኛ ጀግኖች ተዋጊዎች ነን!..» ያሉት አይሁዶች መቋቋም ይቅርና ከምሽጋቸው አንዲት ፍላጻ እንኳ ለመወርወር አልደፈሩም። ክቡር ረሱሉላህ መግቢያና መውጫዎቹን ተቆጣጠሩ። ማንም መውጣት አልቻለም። ይህ ሁኔታ አሥራ አምስት ቀናት ቀጠለ።32

አይሁዶች በፍርሃት ተይዘው እጃቸውን ሰጡ። እያንዳንዳቸው መገደል የሚገባቸው ሆነው ሳለ ለዓለማት እዝነት ሆነው የተላኩት ውዱ ነብያችን ርኅራኄ አድርገው የቀይኑቃዕ አይሁዶች ወደ ሻም እንዲሄዱ ፈቀዱላቸው። ከእነርሱ ማንም በዚያ አካባቢ እንዲቆይ አልተፈቀደለትም። በዚህም ከመዲና ምድር ተባረሩ።33 በኑ ቀይኑቃዕ አገራቸውን ለቀው ሄዱ። ንብረታቸውና መሣሪያቸው ለሙስሊሞች ምርኮ ሆነ።

የሰዊቅ ዘመቻ

አቡ ሱፍያን ከበድር ጦርነት ሸሽቶ መካ በደረሰ ጊዜ ሙሐመድን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እስኪበቀል ድረስ «ራሱን ዘይት ላለመቀባትና ወደ ሚስቶቹ ላለመቅረብ» ተሳለ። በሂጅራ ሁለተኛው ዓመት በዙልሒጃ ወር አምስተኛው ቀን እሑድ ስለቱን ለመፈጸም ከሁለት መቶ ፈረሰኞች ጋር ወደ መዲና ተንቀሳቀሰ። አንድ ሌሊት በመዲና የአንድን ሰው ቤት ሄዶ ስለ ክቡር ነብያችን ጠየቀ። ያ ሰው ትኩረት አልሰጠውም።

በሩንም እንኳ አልከፈተለትም። አቡ ሱፍያን ከዚያ ተለይቶ የሰላም ኢብኑ ሚሽከም እንግዳ ሆነ። በማግሥቱ ከዚያ ተነሥቶ ዑረይድ ወደሚባለው አካባቢ መጣ። በዚያ አካባቢ ከአንሷሮች መዕበድ ኢብኑ ዐምርን ከአገልጋዩ ጋር አግኝቶ በሥራቸው ላይ ሳሉ ገደላቸው፤ እነርሱም ሸሂድ ሆኑ። አንድ የተምር እርሻን በእሳት አቃጠለ። «መሐላዬ ተፈጸመ» ብሎ ከዚያ ሄደ።

ይህ ክስተት ለክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በተነገረ ጊዜ አቡ ሉባባን በመዲና ምትክ አድርገው ከሁለት መቶ ሰዎች ጋር አቡ ሱፍያንን ማሳደድ ጀመሩ።

«በእርግጥ ትሸነፋላችሁ፤ ተሰብስባችሁም ወደ ጀሀነም ትነዳላችሁ፤ ጀሀነምም ምንኛ የከፋ መኖሪያ ነው!» ኣሊ ዒምራን: 12

አጋሪዎች ይህን በሰሙ ጊዜ መሸሽ ጀመሩ። ለመዳን ሲሉ ጓዛቸውንና «ሰዊቅ» የሚሉትን አንድ ዓይነት እህል ለማብሰል ካመጧቸው ድስቶች ጋር እዚያው ትተው ሸሹ። ሙስሊሞች እነዚህን ነገሮች አግኝተው በምርኮ ወሰዱ። ስለዚህ ይህ ዘመቻ የሰዊቅ ዘመቻ ይባላል።

የሰይዲና ዐሊይና የሰይደቲና ፋጢማ ጋብቻ

ጊዜው በሂጅራ ሁለተኛው ዓመት ነበር። የፍጥረተ ዓለሙ ኩራት (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ልጅ ሰይደቲና ፋጢማ አሥራ አምስት ዓመት ሞልቷቸው ነበር።

አንድ ቀን ሰይደቲና ፋጢማ ለአንድ አገልግሎት ወደ ረሱሉል አክረም ዘንድ ገብተው ነበር። ክቡር ረሱሉላህ ልጃቸው ለጋብቻ የደረሱ መሆናቸውን ተመለከቱ። ከዚያን ቀን ጀምሮ እናታችንን ፋጢመቱ ዘህራን እጅግ ብዙ ሰዎች ለጋብቻ ጠየቁ። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ለእነርሱ ትኩረት ሳይሰጡ፦ «ጉዳይዋ በሐቅ ተዓላ ትእዛዝ ላይ የተመሠረተ ነው» አሉ።

አንድ ቀን አቡበክር፣ ዑመርና ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ በመስጊድ ተቀምጠው፦ «ከሰይዲና ዐሊይ በስተቀር ሁሉም ሰይደቲና ፋጢማን ለጋብቻ ጠይቀዋል። ለማንም ትኩረት አልተሰጠም» እያሉ ተነጋገሩ። ሰይዲና ሲዲቅ፦ «ለዐሊይ የሚሰጡ ይመስለኛል። ኑ፣ ልንጠይቀው እንሂድና ይህን ጉዳይ እናንሣለት። ድህነቱን ምክንያት ቢያደርግ እንርዳው» አሉ። ሰዕድም፦ «አቡበክር ሆይ! አንተ ሁልጊዜ በጎ ነገር ታደርጋለህ። ተነሥ፤ እኛም አብረንህ እንሂድ» አሉ። ሦስቱም በአንድነት ከመስጊድ ወጥተው ሰይዲና ዐሊይን ለማግኘት ሄዱ። ሰይዲና ዐሊይ ግመላቸውን ይዘው ሄደው የአንድን የአንሷር ሰው የተምር እርሻ ውኃ ያጠጡ ነበር። እነርሱን ባዩ ጊዜ ተቀብለው ደኅንነታቸውን ጠየቁ። ሰይዲና አቡበክር፦ «ዐሊይ ሆይ! በእያንዳንዱ በጎ ሥራ አንተ ግንባር ቀደም ነህ፤ በረሱሉል አክረም ዘንድም ለማንም ያልተሰጠ ደረጃ አለህ። ሁሉም ሰይደቲና ፋጢማን ለጋብቻ ጠየቁ። ለማንም ትኩረት አልተሰጠም። ለአንተ እንደሚሰጡ እንገምታለን። ለምን ሙከራ አታደርግም?» ብለው ጠየቁ።

ሰይዲና ዐሊይ ይህን በሰሙ ጊዜ የተባረኩ ዓይኖቻቸው በእንባ ተሞሉ፤ እንዲህም አሉ፦ «አቡበክር ሆይ! እጅግ አቃጠልከኝ። ከእኔ የበለጠ እርሷን የሚመኝ የለም። ነገር ግን የእጄ ማጠር ለዚህ እንቅፋት ነው።» ሰይዲና አቡበክር፦ «እንዲህ አትበል። በአላሁ ተዓላና በመልዕክተኛው ዘንድ ይህ ዓለም ምንም አይደለም። ድህነት ለዚህ እንቅፋት ሊሆን አይችልም። ሂድና ጠይቅ» አሉ።

ሰይዲና ዐሊይ እንዲህ ይላሉ፦ «በኀፍረትና በመሸማቀቅ ወደ ረሱሉላህ ፊት ገባሁ። ረሱሉላህ በሙሉ ግርማና ክብር ተሞልተው ነበር። በፊታቸው ተቀመጥኩ፤ መናገርም አልቻልኩም። ክቡር ረሱሉላህ፦ ‹ለምን መጣህ? የምትፈልገው ነገር አለን?› አሉ። ዝም አልኩ። ‹ፋጢማን ለመጠየቅ መጥተሃል መሰለኝ› ባሉ ጊዜ፦ ‹አዎን› ማለት ብቻ ቻልኩ። (ክቡር ነብያችን ሰይዲና ዐሊይ እርሳቸውን እንደጠየቁ ለሰይደቲና ፋጢማ አሳወቁ። እርሳቸውም ዝም አሉ።) ክቡር ነብያችን፦ ‹ለፋጢማ መህር አድርገህ የምትሰጠው ምን አለህ?› አሉ። ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ለእርሷ የምሰጠው ምንም ነገር የለኝም› አልኩ።»

እንደገና፦ «የሰጠሁህ የሑጠሚ ጥሩር ሸሚዝ የት ነው? ምን ሆነ?» ብለው ጠየቁ። ሰይዲና ዐሊይ፦ «አጠገቤ ነው» ባሉ ጊዜ፦ «ሽጠውና ገንዘቡን አምጣልኝ። ለመህር እርሱ በቂ ነው» አሉ።34 በሌላ ዘገባ ደግሞ ክቡር ረሱሉላህ ሰይዲና ዐሊይን፦ «አጠገብህ ምን አለ?» ባሏቸው ጊዜ፦ «ፈረሴና ጥሩር ሸሚዜ አሉኝ» ብለው መለሱ፤ ክቡር ረሱሉላህም፦ «ፈረስህ ያስፈልግሃል፤ ጥሩርህን ግን ሽጥ» አሉ። በሌላ ዘገባ ደግሞ፦ «ዐሊይ ሆይ! ሂድ፣ ለራስህ ቤት ተከራይ» አሉ።

ሰይዲና ዐሊይ እስኪያገቡ ድረስ ከክቡር ነብያችን ጋር ይኖሩ ነበር። በክቡር ነብያችን ትእዛዝ በመስጂደ ነበዊ አቅራቢያ ከሰይደቲና ዓኢሻ ክፍል ፊት ለፊት የሚገኘውን የሐሪሳ ኢብኑ ኑዕማንን ቤት ተከራዩ። ጥሩራቸውንም ወደ ገበያ ላኩ። ሰይዲና ዑስማን (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) በገበያው ሲዘዋወሩ የሰይዲና ዐሊይን ጥሩር አወቁት። ደላላውን ጠርተው፦ «የዚህ ጥሩር ባለቤት ምን ያህል ዋጋ ይጠይቃል?» አሉ። ደላላውም፦ «አራት መቶ ዲርሀም ይጠይቃል» አለ። ዑስማን (ረዲየላሁ ዐንሁ)፦ «ና፣ ገንዘብህን ውሰድ» አሉ። ከዚያም ወደ ተባረከው ቤታቸው ሄዱ። ጥሩሩን ከደላላው ተቀብለው ገንዘቡን ሰጡት። «ይህ ጥሩር ከእርሱ በስተቀር ለማንም አይገባም። ይህንንም ገንዘብ ለሠርጉ ያውለው። ይቅርታችንንም ይቀበለን» አሉ። አራት መቶውን ዲርሀም ሰጥተው ጥሩሩንም ከላዩ አድርገው በስጦታ ለሰይዲና ዐሊይ ላኩ። ሰይዲና ዐሊይ ጥሩሩንና ዲርሀሞቹን ይዘው ወደ ነብያችን በመጡ ጊዜ ክቡር ነብያችን ለሰይዲና ዑስማን ብዙ መልካም ዱዓ አደረጉ፤ «ዑስማን በጀነት ጓደኛዬ ነው» አሉም። ከዚያም ቢላል አል-ሐበሺን ጠርተው ከገንዘቡ የተወሰነውን ሰጥተው እንዲህ ብለው አዘዙ፦ «ይህን ገንዘብ ውሰድና ወደ ገበያ ሂድ! ትንሽ የጽጌረዳ ውኃ፣ በቀረው ገንዘብ ደግሞ ማር ግዛ፤ በመስጊዱ አንድ ጥግ በንጹሕ ዕቃ ውስጥ ከውኃ ጋር በጥብጡት። ኒካሑ ከታሰረ በኋላ እንድንጠጣው የማር ሸርባት አዘጋጁ። ከአንሷርና ከሙሃጂሮች ያሉትን ሶሓቦቼን ወደ መስጊድ ጋብዝ፤ የፋጢማና የዐሊይ ኒካሕ እንደሚታሰርም ለሕዝቡ አውጅ።»

ቢላል አል-ሐበሺ ወጥተው የሰይዲና ዐሊይና የሰይደቲና ፋጢማ ኒካሕ እንደሚታሰር ለሕዝቡ አወጁ። ሶሓቦች ወደ መስጂደ ነበዊ መጥተው ውስጡንም ውጭውንም ሞሉት። ይህን ጊዜ ክቡር ነብያችን ተነሥተው የሚከተለውን ኹጥባ አደረጉ፦ «ምስጋናና ሹክር ሁሉ ለዓለማት ጌታ ብቻ የተገባ ነው። እርሱ በሚለግሳቸው ጸጋዎች የሚወደስ፣ ወሰን በሌለው ችሎታውና ኃይሉ የሚመለክ፣ ቅጣቱና ሒሳቡ የሚፈራ፣ ፍርዱና ትእዛዙ በምድርና በሰማያት የሚሠራ ነው። ፍጥረታትን በችሎታው የፈጠረ፣ በፍትሐዊ ፍርዶቹ እርስ በርሳቸው የለያቸው፣ ሰዎችን በ (እስልምና) ሃይማኖትና በነብዩ በሙሐመድ (ዐለይሂ ሰላም) ያከበረ እርሱ ነው… አላሁ ተዓላ ልጄን ፋጢማን ለዐሊይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ በኒካሕ እንድሰጥ አዘዘኝ። አሁን እናንተን ምስክሮች አደርጋለሁ፤ (በአላሁ ተዓላ ትእዛዝ) ፋጢማን በ400 ሚስቃል ብር መህር ለዐሊይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ በኒካሕ ሰጠሁ። ጌታዬ ሕልውናቸውን ያስተሳስር፤ ይህንንም ለእነርሱ የተባረከ ያድርግላቸው። ዘራቸውን ንጹሕ፣ የእዝነት ቁልፍ፣ የጥበብ ማዕድንና ለሙሐመድ ኡማ የደኅንነት ምንጭ ያድርገው።

የምናገረው ይህ ነው። ለራሴም ለእናንተም ከጌታዬ ምሕረትን እለምናለሁ።»

ከዚያም ሰይዲና ዐሊይም ተነሥተው የሚከተለውን አጭር ኹጥባ አደረጉ፦ «… በፊታቸው ባለንበት፣ የተባረከች ልጃቸውን ፋጢማን በ400 ሚስቃል ብር መህር በኒካሕ በሰጡኝ በሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ላይ ሶላትና ሰላም አወርዳለሁ። የሃይማኖት ወንድሞቼ ሆይ! ያለ ጥርጥር ክቡር ነብያችን ያሉትን ሰምታችኋል፤ ምስክሮችም ሆናችኋል። እኔም ለዚህ ምስክርና ተስማሚ ነኝ። እንዳለ እቀበላለሁ። አላሁ ተዓላ የሁላችንም ቃል ምስክር ነው፤ የሁላችንም ጠባቂ ነው።»35

«ዑስማን በጀነት ጓደኛዬ ነው» ሐዲስ ሸሪፍ

የጋብቻው ውል ከተፈጸመ በኋላ ክቡር ነብያችን ትኩስ ተምር አስመጥተው፦ «በሉ፣ ከዚህ ተምር ውሰዱና ብሉ» አሉ። ሁሉም ወስደው በሉ። ከዚያም ሰይዲና ቢላል የማር ሸርባቱን አከፋፈሉ፤ እርሱንም ጠጡ፤ ሶሓቦች ሁሉም፦ «ባረከላሁ ፊኩማ ወዐለይኩማ ወጀመዐ ሸምለኩማ» ብለው ዱዓ አደረጉ። ኒካሑ ሲታሰር ፋጢማ (ረዲየላሁ ዐንሃ) የአሥራ አምስት፣ ዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ደግሞ የሃያ አምስት ዓመት ዕድሜ ነበራቸው።

ከኒካሑ በኋላ ሰይደቲና ፋጢማ ያለቅሱ ነበር። ክቡር ነብያችን ወደ እርሳቸው መጥተው፦ «ፋጢማ ሆይ! ምን ሆነሽ ነው የምታለቅሺው? በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ከጠየቁሽ መካከል እጅግ አዋቂውን፣ በትዕግሥትና በአስተዋይነት እጅግ የላቀውንና ቀድሞ ሙስሊም የሆነውን አጋባሁሽ» አሉ። ሰይደቲና ፋጢማም፦ «አባዬ! የምታገባ ሴት ልጅ ሁሉ መህሯ በወርቅና በብር ይገመታል፣ ይወሰናል። የእኔም መህር እንዲሁ ከተወሰነ በእርስዎና በሌሎቹ መካከል ምን ልዩነት ይኖራል? በቂያማ ቀን እርስዎ ከምእመናን ኃጢአተኞች ለስንቶቹ ሸፋዐ ቢያደርጉ እኔም ለሚስቶቻቸው ሸፋዐ ማድረግ እፈልጋለሁ። ምኞቴ ይህ ነው» አሉ።

አላሁ ተዓላ የሰይደቲና ፋጢማ ይህ ምኞት ተቀባይነት ማግኘቱን ባሳወቀ ጊዜ ክቡር ረሱሉላህ፦ «ፋጢማ ሆይ! የነብይ ልጅ መሆንሽን አሳየሽ!» አሉ።

ሰይዲና ዐሊይ እንዲህ አሉ፦ «ከእነዚህ ነገሮች በኋላ ጥቂት ወራት አለፉ። በጉባኤው ስለዚህ ጉዳይ ምንም ቃል አልተነሣም። እኔም ከሒጃቤ፣ ማለትም ከኀፍረቴ የተነሣ አፌን መክፈት አልቻልኩም። ነገር ግን ክቡር ረሱሉላህ አንዳንድ ጊዜ ለብቻዬ ሲያገኙኝ፦ ‹ሚስትህ ምንኛ መልካም ሴት ናት! የምሥራች ለአንተ፤ እርሷ የዓለም ሴቶች ሰይዳ ናት› ይሉኝ ነበር።»

በእነዚያ ቀናት የሰይዲና ዐሊይ ወንድም ሰይዲና ዐቂል፦ «ዐሊይ ሆይ! በዚህ የጋብቻ ውል ተደስተናል። ነገር ግን ምኞቴ እነዚህ ሁለት ዕድለኞች አብረው እንዲኖሩ ነው» አሉ። ሰይዲና ዐሊይም፦ «እኔም ምኞቴ ይኸው ነው፤ ነገር ግን አፍራለሁ» ብለው መለሱ። ሰይዲና ዐቂል የሰይዲና ዐሊይን እጅ ይዘው ወደ ክቡር ነብያችን ቤት በደረሱ ጊዜ የረሱሉላህ አገልጋይ የሆኑትን ኡሙ አይመንን አገኙ። ጉዳዩን ነገሯቸው። ኡሙ አይመንም፦ «ለዚህ ጉዳይ እናንተ መምጣት አያስፈልጋችሁም። እኛ ከንጹሐት ሚስቶች ጋር ተስማምተን ወሬ እንልክላችኋለን። ምክንያቱም በዚህ ጉዳይ የሴቶች ቃል ይሰማል» አሉ።

ኡሙ አይመን ጉዳዩን ለረሱሉላህ ሚስቶች ነገሩ። ሌሎቹ ንጹሐት ሚስቶች ወደ ሰይደቲና ዓኢሻ ቤት መጡ። ሰይደቲና ኸዲጃን አስታውሰው፦ «እርሳቸው በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ ምንም ጭንቀት አይኖርብንም ነበር» አሉ። ክቡር ረሱሉላህ አለቀሱ፤ እንዲህም አሉ፦ «እንደ ኸዲጃ ያለች ሴት የት አለች? ሰዎች ሲያስተባብሉኝ እርሷ አመነችኝ፤ ንብረቷንም ሁሉ በመንገዴ አውላለች። ለእስልምና ሃይማኖት እጅግ ረድታለች። በሕይወት ሳለች ሐቅ ተዓላ፦ ‹ኸዲጃን አብሥራት፤ በጀነት ለእርሷ ከመረግድ የተሠራ ቤተ መንግሥት ተሠርቶላታል› ብሎ አዘዘኝ።» የክቡር ረሱሉላህ ሚስቶች የሰይዲና ዐሊይን ፍላጎት አቀረቡ። ይህን ጊዜ ክቡር ረሱሉላህ ኡሙ አይመን ሰይዲና ዐሊይን እንዲጠሩ አዘዟቸው። ዐሊይ በመጡ ጊዜ በጉባኤው የነበሩት ሴቶች ተነሥተው ሄዱ። ሰይዲና ዐሊይ ራሳቸውን አቀርቅረው ተቀመጡ። ረሱሉላህም፦ «ዐሊይ ሆይ! ሚስትህን ትፈልጋለህን?» አሉ።

ዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ)፦ «አዎን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! አባቴና እናቴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ» አሉ። ረሱሉል አክረም አስማ ቢንት ዑመይስን፦ «ሂጂና የፋጢማን ቤት አዘጋጂ» አሉ። አስማ ሰይደቲና ፋጢማ በሙሽርነት ወደሚሄዱበት ቤት ሄዱ። አንዱን ፍራሽ ከአዲስ ቆዳ፣ አንዱን ከተጣፈ ቆዳ፣ አንዱን ደግሞ ከሰሌን ሠርተው ውስጣቸውን በተምር ዛፍ ቃጫ ሞሉ። ክቡር ረሱሉላህ ከዒሻ ሶላት በኋላ ወደ ፋጢማ ቤት መጥተው የተዘጋጀውን ተመለከቱ።

ነብያችን ሰይዲና ዐሊይ ካመጡት ገንዘብ በሁለት ሦስተኛው እንደ ምግብ፣ ጌጣጌጥና ሽቶ ያሉ ነገሮች፣ በአንድ ሦስተኛው ደግሞ ልብስ እንዲገዛ አዘዙ፤ የቤት ዕቃዎቹንም አሟሉ። በሰይደቲና ፋጢማ ጥሎሽና የቤት ዕቃዎች ውስጥ የሚከተሉት ነበሩ፦ አስማ ቢንት ዑመይስ ያዘጋጇቸው ሦስት ፍራሾች፣ ዘርፍ ያለው ምንጣፍ፣ ውስጡ በተምር ዛፍ ቃጫ የተሞላ የራስ ትራስ፣ ሁለት የእጅ ወፍጮዎች፣ የውኃ አቁማዳ፣ ከሸክላ የተሠራ የውኃ እንስራ፣ ከቆዳ የተሠራ የውኃ መጠጫ፣ ፎጣ፣ ቀሚስ፣ የተለፋ የአውራ በግ ቆዳ፣ ያረጀና ጸጉሩ የረገፈ ዥንጉርጉር የየመን ምንጣፍ፣ ከተምር ዛፍ ቅጠል የተሠራ መደብ፣ የየመን ሥራ የሆኑ ሁለት ዥንጉርጉር ልብሶችና አንድ የቬልቬት ብርድ ልብስ። ከዚያም ክቡር ረሱሉላህ ለሰይዲና ዐሊይ የተወሰነ ገንዘብ ሰጥተው ተምርና ቅቤ እንዲገዙ ነገሯቸው። ሰይዲና ዐሊይ ከዚያ በኋላ የሆነውን እንዲህ ብለው ተረኩ፦

«በአምስት ዲርሀም ተምር፣ በአራት ዲርሀም ቅቤ ገዛሁ። ወደ ረሱሉላህ ፊት አመጣሁት። ከቆዳ የተሠራ ገበታ ጠየቁ። ተምሩን፣ ዱቄቱን፣ ቅቤውንና እርጎውን በተባረከ እጃቸው ቀላቅለው አንድ ዓይነት ምግብ ሠሩ፤ እንዲህም አሉ፦ ‹ዐሊይ ሆይ! ሂድና ያገኘኸውን ሁሉ አምጣ።› ወጣሁ፤ እጅግ ብዙ ሰዎችን አየሁ፤ ሁሉንም ጋበዝኩ፤ ገብቼም፦ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ሰዎቹ እጅግ ብዙ ናቸው› ብዬ አቀረብኩ።

የዓለማት ሰይድ የፍጥረተ ዓለሙ ኩራት፦ ‹ምግብ እንዲበሉ አሥር አሥር ሆነው ይግቡ› አሉ። እንዲሁ አደረግሁ። ሲቆጠር ወንዶችና ሴቶች ሰባት መቶ ሰዎች በልተው ጠግበው ነበር።»

የሰይዲና ዐሊይና የሰይደቲና ፋጢማ የሠርግ ግብዣ ከተበላ በኋላ ኡሙ አይመን እንዳሳወቁት ክቡር ነብያችን ሰይዲና ዐሊይን፦ «ዐሊይ ሆይ! ልጄ ፋጢማ ሙሽራ ሆና ወደ ቤታችሁ ሄዳለች። እኔም ከመግሪብ ሶላት በኋላ መጥቼ ዱዓ አደርጋለሁ። ጠብቁኝ» አሉ።

ሰይዲና ዐሊይ ወደ ቤት በመጡ ጊዜ በአንድ ጥግ ተቀመጡ። ሰይደቲና ፋጢማም በቤቱ ሌላ ጥግ ተቀመጡ። ከዚያም ክቡር ረሱሉላህ መጥተው በሩን አንኳኩ። ኡሙ አይመን በሩን ከፈቱ።

ረሱሉላህ፦ «ወንድሜ እዚህ አለን?» አሉ። ኡሙ አይመንም፦ «አባቴና እናቴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ወንድምዎ ማን ነው?» አሉ። ክቡር ረሱሉላህ፦ «ዐሊይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ ነው» ባሉ ጊዜ ኡሙ አይመን፦ «ልጅዎን ከወንድምዎ ጋር አጋቡን?» አሉ። ክቡር ረሱሉላህም፦ «አዎን» አሉ። ኡሙ አይመን ረሱሉላህ «ወንድሜ እዚህ አለን?» በማለታቸው ኒካሑ የተፈቀደ እንደማይሆን አሰቡ። ክቡር ረሱሉላህም «አዎን» በማለታቸው ለጋብቻ እንቅፋት የሚሆነው ከአንድ እናት መወለድ መሆኑን አመለከቱ።

ከዚያም ክቡር ረሱሉላህ ኡሙ አይመንን፦ «አስማ ቢንት ዑመይስም እዚህ አለች?» አሉ። «አዎን» ብለው በመለሱ ጊዜ፦ «እንግዲያው የረሱሉላህን ልጅ ለማገልገል መጥታለች» አሉ። ኡሙ አይመን፦ «አዎን» ባሉ ጊዜ፦ «መልካም ነገርን ታግኝ» ብለው ዱዓ አደረጉላት።

«ፋጢማ ሆይ! ምን ሆነሽ ነው የምታለቅሺው? በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ከጠየቁሽ መካከል እጅግ አዋቂውን፣ በትዕግሥትና በአስተዋይነት እጅግ የላቀውንና ቀድሞ ሙስሊም የሆነውን አጋባሁሽ» ሐዲስ ሸሪፍ

ከዚያም በዕቃ ውኃ አስመጡ። የተባረኩ እጆቻቸውን ታጠቡ፤ በውኃውም ውስጥ ጥቂት ሚስክ ጨመሩ። ከዚያም ሰይደቲና ፋጢማን ጠሩ። ሰይደቲና ፋጢማ ከኀፍረታቸው የተነሣ ልብሳቸውን ይመለከቱ ነበር። ክቡር ረሱሉላህ ከውኃው ጥቂት ወስደው በፋጢማ ደረት፣ ራስና ጀርባ ላይ ረጩ፤ እንዲህም ብለው ዱዓ አደረጉ፦ «አላሁመ ኢኒ ኡዒዙሃ ቢከ ወዙሪየተሃ ሚነሽ-ሸይጧኒር-ረጂም» (ጌታዬ ሆይ! እርሷንና ዘሯን ከተረገመውና በድንጋይ ከተወገረው ሰይጣን ክፋት እንድትጠብቃቸው በአንተ እጠበቃለሁ)። ከዚያም ለሰይዲና ዐሊይም እንዲሁ አድርገው፦ «አላሁመ ባሪክ ፊሂማ ወባሪክ ዐለይሂማ ወባሪክ ለሁማ ፊ ነስሊሂማ» ብለው ዱዓ አደረጉ። ሱረቱ አል-ኢኽላስንና ሙዐዊዘተይንን አንብበው፦ «በአላሁ ተዓላ ስምና በረከት ወደ ባለቤትህ ግባ» አሉ። ከዚያም የበሩን ሁለት መዝጊያዎች በተባረኩ እጆቻቸው ይዘው በበረከት ዱዓ አድርገው ከዚያ ሄዱ።36

ሰይዲና ዐሊይ እንዲህ አሉ፦ «ከሠርጋችን ከአራት ቀን በኋላ ክቡር ረሱሉላህ ቤታችንን በመምጣታቸው አከበሩ። ልብን በሚማርኩ፣ በጥበብ በተሞሉ ቃላት መከሩን፤ እንዲህም አሉ፦ ‹ዐሊይ ሆይ! ውኃ አምጣ!› ተነሥቼ ውኃ አመጣሁ። አንድ ክቡር አንቀጽ አንብበው፦ ‹ከዚህ ውኃ ትንሽ ጠጣ። ጥቂት ይቅር› አሉ። እንዲሁ አደረግሁ። የቀረውን ውኃ በራሴና በደረቴ ላይ ረጩ። እንደገና፦ ‹ውኃ አምጣ› አሉ። ዳግመኛ ውኃ አመጣሁ። ለእኔ እንዳደረጉት ለፋጢማም አደረጉ። ከዚያም ወደ ውጭ ላኩኝ።»

ሰይዲና ዐሊይ ከወጡ በኋላ ልጃቸውን ስለ እርሳቸው ጠየቁ። ፋጢማም፦ «አባዬ! የፍጹምነት ባሕርያት ሁሉ በእርሱ ዘንድ አሉ። ነገር ግን አንዳንድ የቁረይሽ ሴቶች፦ ‹ባልሽ ድሃ ነው› ይሉኛል» አሉ። ይህን ጊዜ ክቡር ረሱሉላህ እንዲህ አሉ፦ «ልጄ ሆይ! አባትሽም ባልሽም ድሆች አይደሉም። የምድርና የሰማይ ግምጃ ቤቶችና ሀብቶች ሁሉ ለእኔ ቀረቡልኝ። አልተቀበልኳቸውም። በአላሁ ተዓላ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ተቀበልኩ። ውዷ ልጄ ሆይ! እኔ የማውቀውን አንቺ ብታውቂ ኖሮ ይህ ዓለም በዓይንሽ የተናቀና የወረደ በሆነ ነበር። በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ባልሽ ከሶሓቦች የመጀመሪያው ነው። በእስልምናም ታላቅ ነው፤ በዕውቀትም እጅግ ጥልቁ ነው። ልጄ ሆይ! አላሁ ተዓላ ከአህለል በይት ሁለት ሰዎችን መረጠ። አንዱ አባትሽ፣ ሌላው ደግሞ ባልሽ ነው። እርሱን ከማመጽና ትእዛዙን ከመቃወም በጣም ተጠንቀቂ።»

የፍጥረተ ዓለሙ ኩራት (ዐለይሂ አፍደሉ ሶለዋት) ልጃቸውን ከመከሩ በኋላ ሰይዲና ዐሊይን ጠሩ። ለእርሳቸውም ፋጢማን እንዲህ ብለው በአደራ ሰጡ፦ «ዐሊይ ሆይ! የፋጢማን ስሜት ጠብቅ። እርሷ የእኔ ቁራጭ ናት። በመልካም ያዛት። ብታሳዝናት እኔን አሳዘንክ።» ሁለቱንም ለአላሁ ተዓላ በአደራ ሰጡ። ከዚያም ተነሥተው ሊሄዱ በተዘጋጁ ጊዜ ሰይደቲና ፋጢማ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! የቤቱን ውስጥ ሥራ እኔ እሠራለሁ። የውጭውን ሥራ ደግሞ ዐሊይ ይሠራል። አንዲት ሠራተኛ ቢለግሱኝ በአንዳንድ ሥራዎቼ ትረዳኛለች። ያስደስቱኛልም» አሉ። ክቡር ረሱሉላህም፦ «ፋጢማ ሆይ! ከሠራተኛ የሚበልጥ ነገር ልለግስሽ ወይስ ሠራተኛ?» አሉ።

እናታችን ፋጢማ፦ «ከሠራተኛ የሚበልጠውን ይለግሱኝ» አሉ። ይህን ጊዜ ክቡር ረሱሉላህ እንዲህ አሉ፦ «በየቀኑ ስትተኚ ሠላሳ ሦስት ጊዜ ‹ሱብሓነላህ›፣ ሠላሳ ሦስት ጊዜ ‹አልሐምዱሊላህ›፣ ሠላሳ ሦስት ጊዜ ‹አላሁ አክበር›፣ አንድ ጊዜ ደግሞ ‹ላ ኢላሀ ኢለላሁ ወሕደሁ ላ ሸሪከ ለህ፣ ለሁል ሙልኩ ወለሁል ሐምዱ ወሁወ ዐላ ኩሊ ሸይኢን ቀዲር› በዪ። ሁሉም መቶ ቃላት ናቸው። በቂያማ ቀን አንድ ሺህ ሐሰና (መልካም ሥራ) ታገኛለሽ። በሚዛን ላይ መልካም ሥራዎችሽ ይከብዳሉ።» ከዚያም ክቡር ነብያችን ከልጃቸው ቤት ወጥተው ወደ ተባረከው ቤታቸው ሄዱ።

የከዕብ ኢብኑል አሽረፍ መገደል

በበድር ድል ምክንያት በመዲና የሚገኙ አይሁዶችና ጣዖት አምላኪ አጋሪዎች ልብ ውስጥ ፍርሃት ገባ። አንዳንድ አይሁዶች ወደ ልቦናቸው ተመልሰው፦ «በመጻሕፍታችን ባሕርያቱን የምናነበው ሰው በእርግጥ ይህ ነው። ከእንግዲህ እርሱን መቃወም አይቻልም። ምክንያቱም እርሱ ሁልጊዜ ያሸንፋል» ብለው ሙስሊሞች ሆኑ። ሌሎቹ ግን፦ «ሙሐመድ ጦርነት ከማያውቁ ቁረይሾች ጋር ተዋጋ። ስለዚህ አሸነፈ። ከእኛ ጋር ቢዋጋ ኖሮ ጦርነት እንዴት እንደሚካሄድ፣ ድል እንዴት እንደሚገኝ እናሳየው ነበር» አሉ።

ከዕብ ኢብኑል አሽረፍ የተባለ አንድ አይሁዳዊም የእስልምና ሠራዊት በበድር ማሸነፉን በሰማ ጊዜ በሙስሊሞች ላይ ካለው ቂም የተነሣ ወደ መካ ሄደ። እዚያ ያሉትን አጋሪዎች ሰብስቦ መዲናን እንዲያጠቁ ግጥሞችን ተናገረ፤ አበረታታቸው፣ አነሣሣቸውም። ከክቡር ነብያችን ጋር ለመዋጋት ከእነርሱ ጋር ተስማማ። እንዲያውም በውዱ ነብያችን ላይ የግድያ ሴራ አደራጀ። አላሁ ተዓላ ይህን ሁኔታ ለክቡር ረሱሉላህ አሳወቀ፤ በትርጓሜም እንዲህ አለ፦ «እነርሱ አላሁ ተዓላ የረገማቸው (ከእዝነቱ ያራቃቸው) ሰዎች ናቸው…»37

ይህን ጊዜ ረሱሉል አክረም ለተከበሩት ሶሓቦቻቸው፦ «ከዕብ ኢብኑል አሽረፍን ማን ይገድለዋል? ምክንያቱም እርሱ አላሁ ተዓላንና መልዕክተኛውን አስቸግሯል» አሉ።

ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኔ እንድገድለው ይፈልጋሉን?» ብለው ጠየቁ። ክቡር ረሱሉላህም፦ «አዎን፣ እፈልጋለሁ» አሉ። ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ በዚህ ጉዳይ ላይ ለጥቂት ቀናት አስበው ዕቅድ አወጡ። ወደ ጓደኞቻቸው ወደ አቡ ናኢላ፣ ዐባድ ኢብኑ ቢሽር፣ ሐሪስ ኢብኑ አውስና አቡ ዐብስ ኢብኑ ጀብር ሄደው ጉዳዩን ገለጡላቸው። ሁሉም ተስማምተው፦ «አብረን እንገድለዋለን» አሉ። በአንድነት ወደ ክቡር ነብያችን መጥተው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከፈቀዱልን ከእርሱ ጋር ስንነጋገር ስለ እርስዎ ከዕብን የሚያስደስቱ አንዳንድ ቃላትን መናገር እንችላለንን?» አሉ። ክቡር ነብያችንም የፈለጉትን እንዲናገሩ ፈቀዱላቸው።

በዚህም ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ከዕብ ኢብኑል አሽረፍ ሄዱ። «ይህ ሙሐመድ ሰደቃ ጠየቀን። ብዙ ግብር ጫነብን። ስለዚህ ከአንተ አንድ ነገር ለመበደር መጣሁ» አሉ። ከዕብ ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ እንደ እርሱ የሚያስቡ መስሎት ተደስቶ፦ «እርሱ ገና ያሰለቻችኋል» አለ። ሙሐመድ ኢብኑ መስለማም፦ «እነሆ አንድ ጊዜ ተከተልነው። እርሱን መከተላችንን እንቀጥላለን። መጨረሻው ምን እንደሚሆን እስኪ እንይ። አሁን አንተ ትንሽ ተምር አበድረን» አሉ። ከዕብም፦ «እሺ አበድራችኋለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር መያዣ ልትሰጡኝ ይገባል!» አለ። ሙሐመድ ኢብኑ መስለማና አብረዋቸው ያሉት፦ «ምን ትፈልጋለህ?» አሉ። ከዕብ፦ «ሴቶቻችሁን መያዣ እፈልጋለሁ» ባለ ጊዜ አልተስማሙም። ከዕብ፦ «እንግዲያው ወንዶች ልጆቻችሁን መያዣ ስጡኝ» አለ። «እነርሱንም መያዣ ልንሰጥ አንችልም። ከእነርሱ ስለ አንዱ በአንድ ወይም በሁለት የግመል ጭነት ተምር ፈንታ መያዣ ሆነ ይባላል፤ ይህም ለእኛ የማንረሳው ነውር ይሆናል። ነገር ግን መሣሪያዎቻችንንና ጥሩሮቻችንን መያዣ ልንሰጥህ እንችላለን» አሉ። ከዕብ ይህን ሐሳብ ተቀበለ። መቼ እንደሚመጡም ነገራቸው።38

«ዐሊይ ሆይ! የፋጢማን ስሜት ጠብቅ። እርሷ የእኔ ቁራጭ ናት። በመልካም ያዛት። ብታሳዝናት እኔን አሳዘንክ» ሐዲስ ሸሪፍ

አንድ ሌሊት ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ ወደ ከዕብ ሄዱ። አቡ ናኢላም አብረዋቸው ነበሩ። ከዕብ ወደ ምሽጉ ጠራቸው፤ እርሱ ራሱም ሊቀበላቸው ወደ ታች ወረደ። የከዕብ ሚስት፦ «በዚህ ሰዓት ወዴት ትወጣለህ?» አለች። ከዕብም፦ «የመጡት ሙሐመድ ኢብኑ መስለማና ወንድሜ አቡ ናኢላ ናቸው» አለ። ሚስቱ፦ «የምሰማው ይህ ድምፅ ጭራሽ ደስ አላለኝም። ደም የሚንጠባጠብበት ይመስላል» አለች። ከዕብም፦ «አይ፣ እነርሱ ሙሐመድ ኢብኑ መስለማና የጡት ወንድሜ አቡ ናኢላ ናቸው። እርሱ መልካም ወጣት ነው። በሌሊት ለሰይፍ ፍልሚያ እንኳ ቢጠራ ሳያመነታ ይመጣል። እንዲህ ያለ ሰው ነው» አለ። ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ ከእርሳቸው ጋር ሁለት ሰዎችን፣ በአንድ ዘገባ ደግሞ ሦስት ሰዎችን ወደ ምሽጉ አስገቡ። እነርሱም አቡ ዐብስ ኢብኑ ጀብር፣ ሐሪስ ኢብኑ አውስና ዐባድ ኢብኑ ቢሽር ነበሩ።39 ሰይዲና ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ ለጓደኞቻቸው፦ «ከዕብ በመጣ ጊዜ ጸጉሩን ማሽተት እንደምፈልግ እነግረዋለሁ፤ ራሱን ይዤ አሸታለሁ። የከዕብን ራስ አጥብቄ እንደያዝኩ ባያችሁ ጊዜ በሰይፎቻችሁ ምቱ» አሉ። ከዕብ ኢብኑል አሽረፍ በሚያምር ልብስ ተውቦ መልካም መዓዛ እያወደ ወደ እነርሱ መጣ። ኢብኑ መስለማ፦ «እስከ ዛሬ እንዲህ ያለ መልካም መዓዛ አሽትቼ አላውቅም» እያሉ ወደ ከዕብ ቀረቡ። ከዕብም፦ «ከዓረቦች እጅግ መልካም መዓዛ ያላቸው ሴቶች በእኔ ዘንድ ናቸው» ብሎ ተመካ። ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ፦ «ራስህን እንዳሸት ትፈቅድልኛለህን?» አሉ። ከዕብ እንደሚፈቅድ ተናገረ። ኢብኑ መስለማ አሸተቱት። ጓደኞቻቸውንም እንዲያሸቱ አደረጉ። ከዚያም እንደገና ማሽተት እንደሚፈልጉ ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ ራሱን አጥብቀው ይዘው ጓደኞቻቸው በሰይፎቻቸው እንዲመቱት ምልክት ሰጡ።

በመጀመሪያው የሰይፍ ምት ከዕብ በኃይል ጮኸ፤ ነገር ግን አልሞተም። ይህን ጊዜ ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ በጩቤያቸው ገደሉት። ከዕብን የገደሉት ሙጃሂዶች ወዲያውኑ ቦታውን ትተው መዲና ደረሱ። ለክቡር ረሱሉላህ የምሥራቹን ባደረሱ ጊዜ ነብያችን አላሁ ተዓላን አመሰገኑ፤ ለሙጃሂዶቹም ዱዓ አደረጉ። የከሓዲው የከዕብ ኢብኑል አሽረፍ መገደል አይሁዶችን በታላቅ ፍርሃት ላይ ጣላቸው። ምክንያቱም እንደ ከዕብ ያለ ታዋቂ መሪ ከተገደለ በኋላ የእነርሱ መገደል የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነበር። ጠዋት ተሰብስበው ወደ ክቡር ነብያችን ፊት መጡ። በሌሊት ስለሆነው ነገር አቤቱታ አቀረቡ። ረሱሉል አክረምም፦ «እርሱ ሁልጊዜ ያስቸግረን፣ በእኛ ላይ ግጥሞችን ይናገር ነበር። ከእናንተ ማንም እንዲሁ ቢያደርግ ቅጣቱ ሰይፍ መሆኑን ይወቅ» አሉ። ከዚህ ማስጠንቀቂያ በኋላ አይሁዶች ከፍርሃታቸው የተነሣ ከክቡር ረሱሉላህ ጋር እንደገና ስምምነት አደረጉ።40

የገጠፋን ዘመቻ

ይህ ዘመቻ «የአንማር ዘመቻ» ተብሎ እንደሚጠራ ሁሉ «የዙ አምር ዘመቻ» ተብሎም ይጠራል። ከበኑ ሰዕለባና ከበኑ ሙሓሪብ አንድ ቡድን ዙ አምር በሚባለው ቦታ ተሰብስቦ በመዲና ዙሪያ ያገኘውን ሁሉ ለመዝረፍ ወስኖ ነበር። መሪያቸው ገውረስ የሚል ቅጽል ስም ያለው ዳዕሱር ኢብኑ ሐሪስ ኢብኑ ሙሓሪብ የተባለ ሰው ነበር። ክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ዑስማን ኢብኑ ዐፋንን (ረዲየላሁ ዐንሁ) በመዲና ምትክ አድርገው አራት መቶ ሃምሳ ሰዎች ባሉት ኃይል ከመዲና ተነሡ። በመንገድ ላይ ጀባር የተባለ ሰው አገኙ። ስለ ጠላት ጠየቁት። እርሱም፦ «እነርሱ ከእናንተ ጋር መዋጋት አይፈልጉም። እናንተን ባዩ ጊዜ ወደ ተራሮች ሸሹ» አለ። ረሱሉላህ እስልምናን አቀረቡለት። እርሱም ተቀብሎ ሙስሊም ሆነ።

የእስልምና ሠራዊት ወደ ሸለቆው እየገሠገሠ ሳለ ዝናብ መዝነብ ጀመረ። ዝናቡ ለተወሰነ ጊዜ በሙሉ ኃይሉ ቀጠለ፤ ከዚያም ቀስ በቀስ ቀንሶ አቆመ። ክቡር ነብያችንን ጨምሮ ሙጃሂዶቹ ከራስ እስከ እግር ውኃ በውኃ ሆነው ነበር። ሁሉም በአንድ በኩል ልብሱን ያደርቅ ነበር። ረሱሉላህም ገለል ባለ ስፍራ ልብሳቸውን ለማድረቅ አውልቀው በአንድ ዛፍ ላይ ዘረጉት። ከዛፉ ሥር ዕረፍት እያደረጉ ሳሉ የእስልምናን ሠራዊት ይሰልሉ የነበሩት ከሓዲዎች ረሱሉላህን ብቻቸውን ሆነው አዩአቸውና ለዳዕሱር ኢብኑ ሐሪስ ነገሩት። እርሱም ረሱሉላህን ለመግደል ዕረፍት ወደሚያደርጉበት ቦታ በጸጥታ ቀረበ። ሰይፉን መዝዞ፦ «ከእጄ ማን ሊያድንህ ይችላል?» አለ። ረሱሉላህም፦ «አላሁ ተዓላ ያድናል» አሉ። በዚያው ቅጽበት ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም መጥተው የዳዕሱርን ደረት መቱና መሬት ላይ ጣሉት፤ ሰይፉም ከእጁ ወደቀ። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የዳዕሱርን ሰይፍ አንሥተው፦ «ከእጄ ማን ያድንሃል?» አሉ። ዳዕሱርም፦ «ማንም ሊያድነኝ አይችልም» አለ። የሸሃዳን ቃል ተናግረው ሙስሊም ሆኑ። ለብዙ ሰዎች ኢማን ማምጣትም ምክንያት ሆኑ።41 ከእንግዲህ ለጦርነት ፈጽሞ ወታደር እንደማይሰበስቡ ቃል ገቡ። የጦር ግጭት ሳይኖር ወደ መዲና ተመለሱ። በዘመቻው አሥራ አንድ ቀን ቆዩ።

የበሕራን ዘመቻ

ይህ ዘመቻ «በኑ ሱለይም» ወይም «የነጅራን ዘመቻ» ተብሎም ይጠራል። በበኑ ሱለይም ዘንድ የተሰበሰቡ ብዙ አጋሪዎች መዲናን ሊያጠቁ መሆናቸው ወሬ መጣ። ሰይዲና ኢብኑ ኡሙ መክቱም በምትክነት ቀሩ። ረሱሉላህ ሦስት መቶ ሰዎች ባሉት ኃይል ወደ ጠላት ዘመቱ። የእስልምና ሠራዊት እየመጣ መሆኑን የሰማው ጠላት ወደ ተራሮች ሸሸ። ስለዚህም መገናኘት አልተቻለም። ዘመቻው አሥራ ሁለት ቀን ቆየ።

«እርሱ (ከዕብ ኢብኑል አሽረፍ) ሁልጊዜ ያስቸግረን፣ በእኛ ላይ ግጥሞችን ይናገር ነበር። ከእናንተ ማንም እንዲሁ ቢያደርግ ቅጣቱ ሰይፍ መሆኑን ይወቅ» ሐዲስ ሸሪፍ

ፍቅርህ ከራሴ ነጠቀኝ፤
ጌታዬ ሆይ! እወድሃለሁ!
የአንተ ውዴታ እንዴት ጣፋጭ ነው፤
ጌታዬ ሆይ! እወድሃለሁ!
በሀብት አልደሰትም፣
በድህነትም አልከፋም፤
በፍቅርህ ደስታ አገኛለሁ፤
ጌታዬ ሆይ! እወድሃለሁ!
ዒባዳዎችን አዘዝክ፣
መልካም ሁኔታዎችን አወደስክ፣
ማለቂያ የሌላቸውን ጸጋዎች ሰጠህ፤
ጌታዬ ሆይ! እወድሃለሁ!
ነፍሴ እንዴት ያለች ውለታ ቢስ ናት፤
ለደስታዋ ስትል ሁልጊዜ ትሠዋኛለች!
እኔ ግን እውነተኛውን ደስታ አገኘሁ፤
ጌታዬ ሆይ! እወድሃለሁ!
ዒባዳን አሳምሮ መፈጸም፣
ለዱንያም ደግሞ መሥራት –
ሌት ተቀን ሥራዬ ይህ ነው፤ ምክንያቱም
ጌታዬ ሆይ! እወድሃለሁ!
ሒልሚ ሆይ! መውደድ በቃል አይሆንም፤
ጌታህ «ሥሩ» ብሎ አዘዘ።
ከሁኔታህም ይታወቅ፦
ጌታዬ ሆይ! እወድሃለሁ!
ስንቱ የእስልምና ጠላት
ሃይማኖትን በስውር ያጠቃል፤
ዝም ብለህ ብትቀመጥ ትክክል ይሆናልን?
ጌታዬ ሆይ! እወድሃለሁ!
አፍቃሪ በስንፍና ይቀመጣልን?
በተወዳጁ ላይ አቧራ እንዲያርፍ ይፈቅዳልን?
ጠላትን ዝም አሰኝና እንዲህ በል፦
«ጌታዬ ሆይ! እወድሃለሁ!»