ሂጅራ
የአውስና የኸዝረጅ ጎሳዎች በድንገት ሙስሊም መሆናቸውና የመካ ሙስሊሞች ከመዲና ሙስሊሞች ጋር ሊዋሐዱ መቻላቸው አጋሪዎቹን እጅግ አስደነገጣቸው፤ አሳበዳቸውም። ሁለተኛውን የዐቀባ ቃል ኪዳን የሰሙት የመካ አጋሪዎች አቋም እጅግ የከረረና እጅግ አደገኛ ሆነ። ለሙስሊሞች በመካ መቆየት ሊታገሡት በማይችሉት ደረጃ ላይ ደረሰ። በመጨረሻው የዐቀባ ቃል ኪዳን መዲና ለሙስሊሞች ሰላም የሚያገኙበትና የሚጠለሉበት ስፍራ ሆነች። አንድ መላ አግኝተው ከመካ ሂጅራ ለማድረግ፣ ትንሽ እፎይ ወደሚሉበትና ጥቂትም ቢሆን በነጻነት ወደሚኖሩበት ምድር ለመሄድ ይመኙ ነበር። ለክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሁኔታቸውን አቅርበው ሂጅራ ለማድረግ ፈቃድ ጠየቁ። እርሳቸውም ሶሓቦቻቸው እንዲታገሡ መከሯቸው፤ ምክንያቱም መካን ለመልቀቅ ገና ፈቃድ አልወረደም ነበር። በመጨረሻም ለሂጅራ የተጠበቀው የአላህ ፈቃድ መጣ። በዚያን ቀን ውዱ ነብያችን በደስታ ሆነው ወደ ሶሓቦች መጥተው እንዲህ አሉ፦ «ሂጅራ የምታደርጉበት ስፍራ ተነገረኝ። እርሱም የስሪብ (መዲና) ነው። ወደዚያ ሂጅራ አድርጉ። በዚያ ከሙስሊም ወንድሞቻችሁ ጋር ተቀላቀሉ። አላሁ ተዓላ እነርሱን ወንድሞቻችሁ አደረጋቸው። የስሪብን (መዲናን) ደኅንነትና ሰላም የምታገኙባት አገር አደረጋት።» በክቡር ረሱሉላህ ፈቃድና ምክር ሙስሊሞች አንዱ ከሌላው በኋላ በቡድን በቡድን ሆነው ወደ መዲና ሂጅራ ማድረግ ጀመሩ።1 ክቡር ነብያችን ሂጅራ የሚያደርጉትን እጅግ ጠንቃቆችና ጥንቁቆች እንዲሆኑ አጥብቀው ያሳስቡ ነበር። ሙስሊሞች የአጋሪዎቹን ትኩረት ላለመሳብ በትናንሽ ቅፍለቶች ሆነው ይጓዙ ነበር፤ በተቻለ መጠንም በምሥጢር ይንቀሳቀሱ ነበር። ወደ መዲና በመጀመሪያ ሂጅራ ያደረጉት አቡ ሰለማ ከአጋሪዎቹ ብዙ ስቃይ ደርሶባቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ነገሩን የተረዱት አጋሪዎች ለሂጅራ ከተነሡት ሙስሊሞች ያገኟቸውን ከመንገድ መመለስ፣ ሴቶችን ከባሎቻቸው መለየትና አቅማቸው የቻሉትን ወደ እስር ቤት መጣል ጀመሩ፤ ለልዩ ልዩ መከራዎችም ዳረጓቸው። ከሃይማኖታቸው ሊመልሷቸውም ማንኛውንም ዓይነት ስቃይ አደረሱባቸው። ነገር ግን የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይፈነዳ ስለፈሩ ለመግደል አልደፈሩም። ሙስሊሞች ግን ይህ ሁሉ ሆኖ እያንዳንዱን አጋጣሚ እየተጠቀሙ የመዲናን መንገዶች ያዙ። አንድ ቀን ሰይዲና ዑመርም ሰይፋቸውን ታጠቁ። ፍላጾቻቸውንና ጦራቸውን ይዘው በሁሉም ፊት ካዕባን ሰባት ጊዜ ጠዋፍ አደረጉ። በዚያ ለነበሩት አጋሪዎችም በታላቅ ድምፅ እንዲህ አሉ፦ «እነሆ እኔም ሃይማኖቴን ለመጠበቅ በአላሁ ተዓላ መንገድ ሂጅራ አደርጋለሁ። ሚስቱን ባልቴት፣ ልጆቹን ወላጅ አልባ ማድረግና እናቱን ማስለቀስ የሚፈልግ ካለ ከዚያ ሸለቆ ጀርባ ይጋፈጠኝ!…» በዚህም ሰይዲና ዑመርና ሃያ ያህል ሙስሊሞች በጠራራ ፀሐይ ያለ አንዳች ፍርሃት ወደ መዲና ጉዞ ጀመሩ። እርሳቸውን ከመፍራት የተነሣ ማንም ይህን ቅፍለት ሊነካው አልቻለም። ከዚያ በኋላ የስደቱ ፍሰት አልተቋረጠም፤ ሶሓቦችም በቡድን በቡድን መዲና ይደርሱ ነበር።
«ሂጅራ የምታደርጉበት ስፍራ ተነገረኝ። እርሱም የስሪብ (መዲና) ነው። ወደዚያ ሂጅራ አድርጉ» እና «በዚያ ከሙስሊም ወንድሞቻችሁ ጋር ተቀላቀሉ። አላሁ ተዓላ እነርሱን ወንድሞቻችሁ አደረጋቸው። የስሪብን (መዲናን) ደኅንነትና ሰላም የምታገኙባት አገር አደረጋት» ሐዲስ ሸሪፍ
የሂጅራ መንገድ
በዚህ መካከል ሰይዲና አቡበክርም ሂጅራ ለማድረግ ፈቃድ ጠየቁ። ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን)፦ «ታገሥ። አላሁ ተዓላ ለእኔም ፈቃድ ይሰጠኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አብረን ሂጅራ እናደርጋለን» አሉ። ሰይዲና አቡበክር፦ «እናቴና አባቴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ! እንዲህ ያለ ዕድል ይኖራልን?» ብለው በጠየቁ ጊዜ ነብያችን፦ «አዎ፣ ይኖራል» ብለው አስደሰቷቸው። ሰይዲና አቡበክር በስምንት መቶ ዲርሀም ሁለት ግመሎችን ገዝተው ያንን ቀን መጠባበቅ ጀመሩ። ከእንግዲህ በመካ የቀሩት ውዱ ነብያችንና ሰይዲና አቡበክር፣ ሰይዲና ዐሊይ፣ ድሆች፣ በሽተኞች፣ ሽማግሌዎችና አጋሪዎቹ ወደ እስር ቤት የጣሏቸው ምእመናን ብቻ ነበሩ።
በሌላ በኩል የመዲና ሰዎች (አንሷሮች) ሂጅራ ያደረጉትን የመካ ሰዎች (ሙሃጂሮችን) እጅግ በመልካም ሁኔታ ተቀብለው በእንግድነት አስተናገዷቸው። በመካከላቸውም ጠንካራ አንድነት ተፈጠረ።
ረሱሉላህም ሂጅራ አድርገው የሙስሊሞች መሪ ይሆናሉ በሚለው ሐሳብ የመካ አጋሪዎች ተሸበሩ። ታላላቅ ጉዳዮችን ለመመካከር በሚሰበሰቡበት በዳሩ ነድዋ ተሰብስበው ምን እንደሚያደርጉ መነጋገር ጀመሩ። ሰይጣን ሸይኹ ነጅዲ በሚል መልክ ማለትም ከነጅድ የመጣ ሽማግሌ መስሎ ወደ አጋሪዎቹ መጣ። ንግግራቸውን አዳመጠ። የተለያዩ ሐሳቦች ቀረቡ፤ ነገር ግን አንዱም ተቀባይነት አላገኘም። ከዚያም ሰይጣን በንግግሩ ውስጥ ገብቶ፦ «ካሰባችሁት አንዱም መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ፈገግታ የሞላበት ፊቱና ጣፋጭ አንደበቱ ማንኛውንም ዘዴ ያፈርሳል። ሌላ መላ አስቡ» ብሎ ሐሳቡን ተናገረ።
የቁረይሽ መሪ የነበረው አቡ ጀህል፦ «ከእያንዳንዱ ጎሳ አንድ ብርቱ ሰው እንምረጥ። ሰይፎቻቸውን በእጃቸው ይዘው በሙሐመድ ላይ ይረባረቡ። በሰይፍ መትተው ደሙን ያፍስሱ። ማን እንደገደለው አይታወቅም። በዚህም ሳይወዱ በግድ በደም ካሳው (በዲያ) ይስማማሉ። እኛም የደም ካሳውን ከፍለን ከዚህ ችግር እንገላገላለን» አለ። ሰይጣንም ይህን ሐሳብ ወደደው፤ በብርቱም አበረታታው፤ መከረውም።2
አጋሪዎቹ በዚህ ዝግጅት ላይ ሳሉ ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም መጥተው የአጋሪዎቹን ውሳኔ ለረሱሉል አክረም ነገሯቸው፤ በዚያች ሌሊት በአልጋቸው ላይ እንዳይተኙም አሳሰቧቸው፤ የአላሁ ተዓላን የሂጅራ ትእዛዝም አሳወቋቸው። በዚህ የአላህ ትእዛዝ ውዱ ነብያችን ሰይዲና ዐሊይን በአልጋቸው ላይ እንዲተኙና በአደራ የተሰጧቸውን ንብረቶች ለባለቤቶቻቸው እንዲመልሱ ነገሯቸው፤ እንዲህም አሉ፦ «ዛሬ ሌሊት በአልጋዬ ላይ ተኛ፤ ይህን ኺርቃዬንም ደርበህ ተሸፈን! አትፍራ፤ ምንም ጉዳት አይደርስብህም።»
ሰይዲና ዐሊይ ክቡር ነብያችን ባዘዙት መሠረት ተኙ። በዚያን ጊዜ ዕድሜያቸው ሃያ ሦስት ዓመት ነበር። በሐቢቡላህ ቦታ ያለ አንዳች ፍርሃት የራሳቸውን ሕይወት ለመሠዋት ዝግጁ ነበሩ።
በሂጅራው ሌሊት ከሓዲዎቹ የክቡር ረሱሉላህን የተባረከ ቤት ዙሪያውን ከበው ነበር። በዚያች ሌሊት የሱረቱ ያሲን የመጀመሪያዎቹ አንቀጾች ወረዱ። ክቡር ነብያችን ከተባረከው ቤታቸው ሲወጡ ትርጓሜው «ከፊታቸው ግርዶሽ፣ ከኋላቸውም ግርዶሽ አደረግን፤ ሸፈንናቸውም፤ ስለዚህ አያዩም» የሆነውን የሱረቱ ያሲንን ዘጠነኛውን ክቡር አንቀጽ በእነርሱ ላይ አነበቡ፤ ከዚያም ከመሬት አንድ እፍኝ አፈር አንሥተው በከሓዲዎቹ ራስ ላይ በተኑ። (ከዚህ አፈር ራሱ ላይ ያረፈበት ሰው ሁሉ በበድር ጦርነት እንደተገደለ ተዘግቧል።) ክቡር ረሱሉላህ በጤናና በሰላም በመካከላቸው አልፈው ወደ ሰይዲና አቡበክር ቤት ደረሱ። ከአጋሪዎቹ አንዱም ሊያያቸው አልቻለም ነበር።
«አቡበክር ሆይ! ታገሥ። አላሁ ተዓላ ለእኔም ፈቃድ ይሰጠኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አብረን ሂጅራ እናደርጋለን» ሐዲስ ሸሪፍ
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሰው ወደ አጋሪዎቹ መጥቶ፦ «እዚህ ምን ትጠብቃላችሁ?» ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፦ «ሙሐመድ ከቤቱ እስኪወጣ» ብለው መለሱ። ያ የመጣው ሰውም፦ «እምላለሁ፤ ሙሐመድ በመካከላችሁ አልፎ ሄዷል፤ በራሳችሁም ላይ አፈር በትኗል» አለ። አጋሪዎቹ እጆቻቸውን ወደ ራሳቸው ሰደዱ። በእርግጥም በራሳቸው ላይ አፈር አገኙ። ከፊታቸውና ከራሳቸው ላይ አፈሩን ጠረጉ። ወዲያውኑ ወደ በሩ ተረባርበው ወደ ውስጥ ገቡ። ሰይዲና ዐሊይን በመልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም አልጋ ላይ ባዩአቸው ጊዜ ረሱሉል አክረም የት እንዳሉ ጠየቁ።
ሰይዲና ዐሊይ፦ «አላውቅም! እርሳቸውን እንድጠብቅ ሾማችሁኛልን?» አሉ። በዚህ ጊዜ ሰይዲና ዐሊይን ገፈታተሯቸው። ከሓዲዎቹ ክቡር ረሱሉላህን ለማግኘት ወደ ውጭ ወጥተው መፈለግ ጀመሩ። ሰይዲና ዐሊይንም በካዕባ አጠገብ ለተወሰነ ጊዜ አስረው ከዚያ ለቀቋቸው።3
ከዚያም ወደ ሰይዲና አቡበክር ቤት ሄደው የሰይዲና አቡበክርን ልጅ አስማን ጠየቁ። መልስ ባልሰጧቸው ጊዜ ደበደቧቸው። ሁሉንም ቦታ ቢፈልጉም ሊያገኟቸው አልቻሉም፤ በዚህም አበዱ። ከእነርሱ እጅግ ጨካኙ የነበረው አቡ ጀህል በመካና በአካባቢዋ አዋጅ ነጋሪዎችን አስጮኸ፤ ውዱ ነብያችንንና ሰይዲና አቡበክርን አግኝቶ ለሚያመጣና ያሉበትን ቦታ ለሚያሳውቅ 100 ግመሎችን እንደሚሰጥ ቃል ገባ። ይህን ቃሉን የሰሙና ገንዘብን የሚጎመጁ አንዳንድ ሰዎች ጦር መሣሪያ ታጥቀው ፈረሶቻቸውን ተቀምጠው መፈለግ ጀመሩ።
ክቡር ረሱሉላህ ወደ ሰይዲና አቡበክር ቤት በመምጣታቸው አክብረው፦ «ሂጅራ እንዳደርግ ተፈቀደልኝ» ባሉ ጊዜ ሰይዲና አቡበክር ሲዲቅ በታላቅ ስሜት፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ፊቴን በተባረኩ እግሮችዎ አቧራ ላይ ላሽ!… እኔም አብሬዎት እሆናለሁን?» ብለው ጠየቁ። ሰይዳችንም፦ «አዎ…» ብለው መለሱ። ሰይዲና ሲዲቅ ከደስታቸው የተነሣ አለቀሱ። በእንባቸው መካከልም፦ «እናቴ፣ አባቴና ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ግመሎቹ ተዘጋጅተዋል። የፈለጉትን ይቀበሉ» አሉ። የዓለማት ሱልጣን፦ «የእኔ ያልሆነ ግመል ላይ አልቀመጥም። በዋጋው (ብቻ) እወስደዋለሁ» አሉ። በዚህ ቁርጥ ትእዛዝ ፊት ምርጫ ያጡት ሰይዲና ሲዲቅ የግመሉን ዋጋ ተናገሩ። ሰይዲና አቡበክር በመንገድ መሪነቱ የታወቀውን ዐብዱላህ ኢብኑ ኡረይቂጥ የተባለውን ሰው ጠርተው መንገዱን እንዲያሳያቸው በክፍያ ቀጠሩት፤ ግመሎቹንም ከሦስት ቀን በኋላ በሰውር ተራራ ወዳለው ዋሻ እንዲያመጣ አዘዙት።
በቢዕሳ በአሥራ ሦስተኛው ዓመት በሰፈር ወር 27ኛው ቀን ሐሙስ ዕለት ክቡር ነብያችንና አቡበክር ሲዲቅ ጥቂት ስንቅ ይዘው ጉዞ ጀመሩ።
ሰይዲና አቡበክር በረሱሉላህ ዙሪያ አንዳንዴ በቀኝ፣ አንዳንዴ በግራ፣ አንዳንዴ ከፊት፣ አንዳንዴ ደግሞ ከኋላ ይሄዱ ነበር። ነብያችን ለምን እንዲህ እንደሚያደርጉ በጠየቋቸው ጊዜ፦ «ከዙሪያው የሚመጣን አደጋ ለመከላከል ነው። ጉዳት ቢመጣ መጀመሪያ በእኔ ላይ ይድረስ። ነፍሴ ለላቀው ማንነትዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!» አሉ።
የዓለም መሪ እንዲህ አሉ፦ «አቡበክር ሆይ! በእኔ ላይ የሚደርስ መከራ በእኔ ፈንታ በአንተ ላይ እንዲደርስ ትፈልጋለህን?» ሰይዲና ሲዲቅም፦ «አዎ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! በእውነተኛው ሃይማኖት እውነተኛ ነብይ አድርጎ በላከዎት በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ የሚመጣ መከራ በእርስዎ ፈንታ በእኔ ላይ እንዲደርስ እፈልጋለሁ» አሉ።4
የውዱ ነብያችን ነጠላ ጫማ ጠባብ ስለነበር በመንገድ ላይ ተበጣጠሰ፤ የተባረኩ እግሮቻቸውም ቆሰሉ፤ የሚራመዱበት አቅም አልቀረላቸውም። በብዙ ችግር ተራራውን ወጥተው ወደ ዋሻው ደረሱ። ወደ መግቢያው በደረሱ ጊዜ ሰይዲና አቡበክር፦ «ለአላህ ብለው፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ወደ ውስጥ አይግቡ! እኔ ልግባ፤ በዚያ ጎጂ ነገር ካለ በእኔ ላይ ይድረስ፤ በተባረከው ማንነትዎ ላይ አንዳች ሐዘን፣ አንዳች ሕመም አይንካ» ብለው ወደ ውስጥ ገቡ። ውስጡን ጠርገው አጸዱ። በቀኝና በግራ በኩል ትልቅና ትንሽ የሆኑ ብዙ ቀዳዳዎች ነበሩ። ኺርቃቸውን ቀዳደው ቀዳዳዎቹን ደፈኑ፤ ነገር ግን አንዱ ክፍት ቀረ። እርሱንም በተረከዛቸው ደፍነው ረሱሉላህን ወደ ውስጥ ጋበዙ። ክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ወደ ውስጥ ገቡ፤ የተባረከ ራሳቸውንም በአቡበክር ጭን ላይ አድርገው ተኙ።
በዚያን ጊዜ እባብ የሰይዲና ሲዲቅን እግር ነደፋቸው። ረሱሉላህ እንዳይነቁ ታግሠው ምንም አልተንቀሳቀሱም። ነገር ግን እንባቸው በረሱሉላህ የተባረከ ፊት ላይ በወደቀ ጊዜ እርሳቸው፦ «አቡበክር ሆይ! ምን ሆንክ?» ብለው ጠየቁ። ሰይዲና አቡበክርም፦ «በእግሬ ከደፈንኩት ቀዳዳ አንድ እባብ እግሬን ነደፈኝ» አሉ። ክቡር ረሱሉላህ ቁስሉ እንዲድን ከተባረከ አፋቸው ምራቅ በአቡበክር ቁስል ላይ በቀቡ ጊዜ ሕመሙ ወዲያውኑ ጠፋ፤ ዳኑም።
ክቡር ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እና አቡበክር ሲዲቅ በውስጥ ሳሉ አጋሪዎቹ ዱካውን እየተከተሉ ወደ ዋሻው መግቢያ ደረሱ። የዋሻውን አፍ አንዲት ሸረሪት ድራ እንደሸፈነችውና ሁለት ርግቦችም ጎጆ እንደሠሩበት አዩ። ዱካ ተከታዩ ኩርዝ ኢብኑ ዐልቀማ፦ «እነሆ ዱካው እዚህ ተቋረጠ» አለ። ከሓዲዎቹም፦ «እነርሱ ወደዚህ ገብተው ቢሆን ኖሮ በበሩ ላይ ያለው የሸረሪት ድር መቀደድ ነበረበት» አሉ።
አንዳንዶቹ፦ «እዚህ ድረስ መጥተናል፤ ከእናንተ አንዱ ወደ ዋሻው ገብቶ ይመልከት!..» ባሉ ጊዜ ከሓዲው ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ፦ «በጭራሽ አእምሮ የላችሁምን? ተደራራቢ የሸረሪት ድር ባለበት በዚህ ዋሻ ውስጥ ምን ጉዳይ አላችሁ? እምላለሁ፤ ይህች ሸረሪት ድሯን ያደራችው ሙሐመድ ከመወለዱ በፊት ነው» አለ።
አጋሪዎቹ በበሩ ፊት ለፊት ሲከራከሩ ሰይዲና አቡበክር በውስጥ ሆነው በጭንቀት ተያዙና፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ወላሂ ለራሴ አልጨነቅም። ነገር ግን በላቀው ማንነትዎ ላይ አንዳች ነገር እንዳይደርስ እፈራለሁ። እኔ ብገደል አንድ ሰው ብቻ ነኝ፤ ምንም ነገር አይለወጥም። በእርስዎ ላይ ጉዳት ቢደርስ ግን መላው ኡማ ይጠፋል፤ ሃይማኖቱም ይፈርሳል» አሉ። የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን፦ «አቡበክር ሆይ! አትዘን!.. አላሁ ተዓላ በእርግጥ ከእኛ ጋር ነው» አሉ።
አቡበክር ሲዲቅ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን! ከእነርሱ አንዱ ራሱን ዝቅ አድርጎ ቢመለከት ያየናል!» ባሉ ጊዜ ሰይዳችን፦ «አቡበክር ሆይ! እኛ ሁለት ነን፤ ሦስተኛችን አላሁ ተዓላ ነው። አትዘን!.. ሐቅ ተዓላ በእርግጥ ከእኛ ጋር ነው» አሉ። አጋሪዎቹም ወደ ውስጥ ሳይመለከቱ ተመለሱ።5
አላሁ ተዓላ ስለዚህ ሁኔታ በቁርኣን ከሪም በትርጓሜ እንዲህ አለ፦ «እናንተ እርሱን (ሐቢቤን) ባትረዱት፣ (ያንን ጊዜ አስታውሱ፦) ከሓዲዎቹ እርሱን (ከመካ) ከሁለቱ ሁለተኛ ሆኖ (ከሰይዲና አቡበክር ጋር) ባወጡት ጊዜ፣ ሁለቱም (በሰውር ተራራ አናት ላይ ባለው) ዋሻ ውስጥ ሳሉ አላሁ ተዓላ እርሱን (ረሱሉላህን) ረድቶታል። ያን ጊዜ ለጓደኛው (ለአቡበክር ሲዲቅ)፦ ‹አትዘን፤ የአላሁ ተዓላ እርዳታና ድጋፍ በእርግጥ ከእኛ ጋር ነው› ብሎ ነበር። አላሁ ተዓላ ልቦችን የሚያረጋጋውን ሰኪናውን በእርሱ ላይ አወረደ፤ እርሱንም (ሐቢቡን) ባላያችኋቸው (መንፈሳዊ) ሠራዊት አበረታው (በመላእክት ጠበቀው)፤ የከሓዲዎቹንም ቃል እጅግ አዋረደ። የአላሁ ተዓላ (የተውሒድ) ቃል ግን እጅግ የላቀ ነው (የአላህን ስም በዓለም ሁሉ አሰራጨ፤ የበላይም አደረገው)። አላሁ ተዓላ ፍጹም አሸናፊ ነው። ብቸኛው የፍርድና የጥበብ ባለቤት ነው።»6
«ለአላህ ብለው፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ወደ ውስጥ አይግቡ! እኔ ልግባ፤ በዚያ ጎጂ ነገር ካለ በእኔ ላይ ይድረስ፤ በተባረከው ማንነትዎ ላይ አንዳች ሐዘን፣ አንዳች ሕመም አይንካ» አቡበክር ሲዲቅ (ረዲየላሁ ዐንሁ)
ውዱ ነብያችንና ሰይዲና አቡበክር በዚህ ዋሻ ሌት ተቀን ሦስት ቀን ቆዩ። የሰይዲና አቡበክር ልጅ ዐብዱላህ በመካ የሰሙትን በሌሊት ወደ ዋሻው መጥተው ይነግሯቸው ነበር፤ ነጻ የወጡ ባሪያቸውና የመንጎቻቸው እረኛ ዓሚር ኢብኑ ፉሀይራ ደግሞ በሌሊት ወተት እያመጡላቸው ዱካዎቹን ያጠፉ ነበር።
በአራተኛው ቀን እሑድ ሌሊት ለሰኞ አጥቢያ በንጋት ጊዜ ከሰውር ዋሻ የወጡት ውዱ ነብያችን ቀስዋ የተባለችውን ግመላቸውን ተቀመጡ። በአንድ ዘገባ መሠረት ሰይዲና አቡበክርን ከኋላቸው አፈናጠጧቸው። በሌላኛው ግመል ላይ ደግሞ ሰይዲና ዓሚር ኢብኑ ፉሀይራና መንገዶቹን በሚገባ የሚያውቀው ዐብዱላህ ኢብኑ ኡረይቂጥ ተቀመጡ።
የዓለማት ሰይድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አላሁ ተዓላ ካወደሳት፣ ከከተሞች ሁሉ እጅግ ውድ ከሆነችው ከአገራቸው ከመካ አል-ሙከረማ እየተለዩ ነበር። ግመላቸውን ወደ ሐረም ሸሪፍ አዙረው በሐዘን እንዲህ አሉ፦ «ወላሂ! አንቺ አላሁ ተዓላ ከፈጠራቸው ስፍራዎች ሁሉ በላጯ፣ በጌታዬ ዘንድም እጅግ ተወዳጇ ነሽ! ከአንቺ ባልተባረርኩ ኖሮ አልወጣም ነበር። ለእኔ ከአንቺ ይበልጥ ያማረ፣ ይበልጥ ተወዳጅ አገር የለም። ወገኖቼ ከአንቺ ባያስወጡኝ ኖሮ አልወጣም ነበር፤ ከአንቺ ሌላ በየትኛውም ስፍራ አገርና መኖሪያ አልይዝም ነበር።»
በዚያን ጊዜ ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም ወርደው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! አገርዎን ይናፍቃሉን? ናፈቅዎትን?» አሉ። ሰይዳችንም፦ «አዎ፣ እናፍቃለሁ!» አሉ። ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም በመጨረሻ ወደ መካ እንደሚመለሱ የሚያበሥረውን የሱረቱ አል-ቀሶስን ሰማንያ አምስተኛውን ክቡር አንቀጽ አንብበው የተባረከ ልባቸውን አጽናኑ።
ጉዞው በእርጋታ ቀጠለ። አጋሪዎቹ ሁሉንም ስፍራ ቢፈልጉም ሊያገኟቸው አልቻሉም፤ ክብሩ የላቀው አላህ ሐቢቡን ከክፋታቸው ይጠብቅ ነበር። ክቡር ረሱሉላህ ቁደይድ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜ በቸርነታቸው የታወቁ፣ አስተዋይና ጨዋ ሴት በሆኑት ኡሙ መዕበድ በተባሉት እመቤት ድንኳን ፊት ቆሙ። በዋጋ ምግብ፣ ተምርና ሥጋ ለመግዛት ፈለጉ። ኡሙ መዕበድ፦ «ቢኖረኝ ኖሮ በገንዘብ ሳይሆን ግብዣ አዘጋጅቼ አስተናግዳችሁ ነበር። በድርቅና በኑሮ ችግር ምክንያት በእጃችን ምንም ነገር አልቀረም» አሉ። «ወተት አለን?» ብለው በጠየቁ ጊዜ፦ «የለም። ከብቶቹ ደርቀዋል» ብለው መለሱ። የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከድንኳኑ አጠገብ የቆመችን አንዲት የከሳች በግ እያመለከቱ እንዲህ አሉ፦ «ኡሙ መዕበድ ሆይ! ይህች በግ ለምን እዚህ ታስራ ቆማለች?» እርሳቸውም፦ «እጅግ የታመመችና የደከመች ስለሆነች ከመንጋው ቀረች። አቅም ስላልነበራት መሄድ አልቻለችም» አሉ። «ምንም ወተት አላትን? ይህችን በግ እንዳልባት ትፈቅጅልኛለሽን?» ባሉ ጊዜ፦ «እናቴና አባቴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ! ወተት የላትም፤ ነገር ግን እርሷን እንዳያልቡ የሚከለክልዎት ምንም ነገር የለም» አሉ።
ክቡር ረሱሉላህ ወደ በጊቱ ቀርበው የአላሁ ተዓላን ስም አወሱ። በረከት እንዲሰጥ ዱዓ ካደረጉ በኋላ የተባረከ እጃቸውን በበጊቱ ጡት ላይ አሳለፉ። በዚያው ቅጽበት ጡቱ በወተት ተሞላ፤ መፍሰስም ጀመረ። ወዲያውኑ ዕቃ አምጥተው ሞሉት። በመጀመሪያ ለኡሙ መዕበድ ሰጧቸው። እርሳቸው ከጠጡ በኋላ ለሰይዲና አቡበክርና ለሌሎቹ ሰጥተው እስኪጠግቡ ድረስ እንዲጠጡ አደረጉ። በመጨረሻም እርሳቸው ራሳቸው ጠጡ። ዳግመኛ የተባረከ እጃቸውን በበጊቱ ጡት ላይ አድርገው አለቧት፤ በድንኳኑ ውስጥ ያለውንም ትልቁን ዕቃ ጠየቁ። እርሱንም ሞልተው ለኡሙ መዕበድ አስረከቡ። በዘገባው መሠረት ያቺ በግ አሥራ ስምንት ዓመት ኖረች፤ በዓለም ኩራት በረከትም ጠዋትና ማታ በወተቷ ይኖሩ ነበር። ከዚያ ከሄዱ በኋላ የኡሙ መዕበድ ባል መጥቶ ወተቱን አየ። በደስታም፦ «ይህ ወተት ከየት መጣ?» ብሎ በጠየቀ ጊዜ ኡሙ መዕበድ፦ «አንድ የተባረኩ ሰው መጥተው ቤታችንን አከበሩ። ያየኸው የእርሳቸው ሂማና በረከት ነው» አሉ። እርሱም፦ «ልትገልጭልኝ ትችያለሽን? ባሕርያቸውና መልካቸው እንዴት ነው?» ብሎ ጠየቀ።
ኡሙ መዕበድም እንዲህ አሉ፦ «ያየኋቸው እኚያ የተባረኩ ሰው እጅግ የተስተካከለ ቁመና ያላቸውና ፈገግታ የሞላበት ፊት የነበራቸው ናቸው። በዓይኖቻቸው ውስጥ ትንሽ ቅላት፣ በድምፃቸውም ልስላሴ ነበር። የተባረኩ ሽፋሽፍቶቻቸው ረጃጅም ነበሩ። የዓይናቸው ነጭ እጅግ ነጭ፣ ጥቁሩም እጅግ ጥቁር ሲሆን በተፈጥሮ ኩል የተኳሉ ይመስሉ ነበር። ጸጉራቸው ጥቁር፣ ጢማቸውም ጥቅጥቅ ያለ ነበር። ዝም ሲሉ ግርማና ክብደት ይታይባቸው ነበር። ሲናገሩ ፈገግ ይሉ ነበር፤ ቃላቸውም እንደ ተሰደሩ ዕንቁዎች ከአፋቸው በጣፋጭነት ይወርድ ነበር። ከሩቅ ሲታዩ እጅግ ግርማ ሞገስ ያላቸው ነበሩ፤ ሲቀርቡ ደግሞ እጅግ ተወዳጅና ማራኪ ይሆኑ ነበር። ከእርሳቸው ጋር የነበሩት ትእዛዛቸውን ለመፈጸም በሙሉ ልባቸው ይጣደፉ ነበር።» በዚህ ሁኔታ ሌሎች ብዙ መልካም ባሕርያቸውን ዘረዘሩ። ይህን በመደነቅ ያዳመጠው ባላቸው፦ «እምላለሁ፤ እኚህ ሰው ቁረይሾች የሚፈልጓቸው ሰው ናቸው። ባገኘኋቸው ኖሮ እርሳቸውን የማገልገል ክብር አገኝ ነበር፤ ከአጠገባቸውም አልለይም ነበር» አለ። የኡሙ መዕበድ ባል ክቡር ረሱሉላህን ተከትሎ ሄዶ በሪም ሸለቆ ደረሰባቸው፤ ሙስሊምም ሆኑ። ሶሓቢይ የመሆንን ክብር አገኙ። ከዚያም ኡሙ መዕበድም ሙስሊም ሆኑ።7
ሱራቃ ኢብኑ ማሊክ
አጋሪዎቹ ወደ መዲና ጉዞ የጀመሩትን ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምንና ሰይዲና አቡበክርን ያለማቋረጥ ይፈልጉ ነበር። ካላገኟቸው በእነርሱ ላይ እጅግ ታላቅ አደጋ ይከሰትባቸው ነበር። ምክንያቱም ሙስሊሞች «የእስልምና መንግሥት» መሥርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ እነርሱን ሊያጠፉ እንደሚችሉ ያስቡ ነበር። ስለዚህ አጋሪዎቹ ያላቸውን ሁሉ አወጡ። ክቡር ነብያችንንና ሰይዲና አቡበክርን ለሚገድል ወይም ለሚማርክ ከመቶ ግመሎች በተጨማሪ ቁጥር የሌለው ንብረትና ገንዘብ እንደሚሰጡ ቃል ገቡ። ይህ ወሬ ሱራቃ ኢብኑ ማሊክ አባል በሆነበት በሙድሊጅ ልጆች መካከልም ተሰራጨ።
ሱራቃ ኢብኑ ማሊክ ጎበዝ ዱካ ተከታይ ነበር። ስለዚህ የሚሆነውን ሁሉ በቅርብ ይከታተል ነበር።
አንድ ማክሰኞ ቀን የሙድሊጅ ልጆች ሱራቃ ኢብኑ ማሊክ በሚኖርበት አካባቢ በቁደይድ ተሰብስበው ነበር። በስብሰባውም ሱራቃ ኢብኑ ማሊክ ነበረ። በዚያን ጊዜ ከቁረይሽ ሰዎች አንዱ መጥቶ ሱራቃን፦ «ሱራቃ ሆይ! ወላሂ አሁን ወደ ባሕሩ ዳርቻ የሚሄድ የሦስት ወይም የአራት ሰዎች ትንሽ ቅፍለት አየሁ። እነርሱ ምናልባት ሙሐመድና ጓደኞቹ ናቸው» አለው። ሱራቃ ሁኔታውን ተረዳ። ነገር ግን የተዘጋጀው ሽልማት እጅግ ብዙ ስለነበር ብቻውን ሊያገኘው ፈለገ። ስለዚህ ሌላ ሰው እንዲያውቅ አልፈለገም። «አይደለም፤ ያየሃቸው ሰዎች እገሌና እገሌ ናቸው። ትንሽ ቀደም ብለው አልፈዋል። እኛም አይተናቸዋል» ብሎ ምንም ልዩ ነገር እንደሌለ አስመስሎ ተናገረ።
ሱራቃ ኢብኑ ማሊክ ትንሽ ጠበቀ። ትኩረት ሳይስብ ወደ ቤቱ መጣ። አገልጋዩን ፈረሱንና መሣሪያውን ይዞ ከሸለቆው ጀርባ እንዲጠብቀው ነገረው። እርሱ ራሱ ደግሞ ጦሩን ይዞ አንጸባራቂነቱ ትኩረት እንዳይስብ ጫፉን ወደ ታች አዞረው። ፈረሱን ማስጋለብ ጀመረ። ጉዞውን ቀጥሎ በመጨረሻ ዱካቸውን አገኘ። ክቡር ነብያችን የሚያነቡትን ቁርኣን ከሪም እንኳ እስኪሰማ ድረስ ቀረበ። ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ግን ወደ ኋላ ፈጽሞ አልተመለከቱም። ሰይዲና አቡበክር ወደ ኋላ ዞር ብለው በተመለከቱ ጊዜ ሱራቃን አይተው ተደናገጡ። ክቡር ነብያችንም በዋሻው እንዳሉት ሁሉ፦ «አትዘን፤ አላሁ ተዓላ ከእኛ ጋር ነው» አሏቸው።
«(መካ አል-ሙከረማ ሆይ!) ለእኔ ከአንቺ ይበልጥ ያማረ፣ ይበልጥ ተወዳጅ አገር የለም። ወገኖቼ ከአንቺ ባያስወጡኝ ኖሮ አልወጣም ነበር፤ ከአንቺ ሌላ በየትኛውም ስፍራ አገርና መኖሪያ አልይዝም ነበር» ሐዲስ ሸሪፍ
ቡኻሪ እንደዘገቡት በዚህ ጊዜ ሰይዲና አቡበክር አንድ ፈረሰኛ እንደደረሰባቸው ለረሱሉል አክረም አቀረቡ፤ ክቡር ነብያችንም፦ «ጌታዬ ሆይ! ጣለው!» ብለው ዱዓ አደረጉ። በሌላ ዘገባ ደግሞ ሱራቃ እስከ አጠገባቸው በመጣ ጊዜ ሰይዲና አቡበክር ማልቀስ ጀመሩ። ረሱሉል አክረም ለምን እንደሚያለቅሱ በጠየቋቸው ጊዜ፦ «ወላሂ ለራሴ አላለቅስም። የማለቅሰው በእርስዎ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ስለምፈራ ነው» አሉ። ሱራቃ ክቡር ነብያችንን ሊያጠቃ እስከሚችልበት ድረስ ቀረበ። «ሙሐመድ ሆይ! ዛሬ ከእኔ ማን ይጠብቅሃል!» አለ። የዓለም መሪም፦ «ጀባርና ቀሃር የሆነው አላሁ ተዓላ ይጠብቀኛል» ብለው መለሱ። በዚያን ቅጽበት የሱራቃ ፈረስ ሁለቱ የፊት እግሮቹ እስከ ጉልበቶቹ ድረስ መሬት ውስጥ ሰጠሙ። ከዚህ ተላቅቆ እንደገና ለማጥቃት በሞከረ ጊዜ የፈረሱ እግሮች ዳግመኛ መሬት ውስጥ ተቀበሩ። ሱራቃ ፈረሱን የቱንም ያህል ቢያስገድደው በምንም መንገድ ሊያላቅቀው አልቻለም። ሌላ የሚያደርገው ምንም ነገር አልነበረም። መላ ባጣ ጊዜ የፍቅርና የርኅራኄ ባለቤት የሆኑትን ክቡር ረሱሉላህን መለመን ጀመረ። ፍጽምናዎችንና መልካም ስነ ምግባርን ሁሉ በራሳቸው ያሰባሰቡት፣ በላቀ ስነ ምግባርና በላቀ ተፈጥሮ ላይ የተፈጠሩት ነብያችን ይህን ልመናውን ተቀበሉት። ሱራቃ፦ «ሙሐመድ ሆይ! እንደምትጠበቅ ተረዳሁ። እንድድን ዱዓ አድርግልኝ። ከእንግዲህ በአንተ ላይ ፈጽሞ ጉዳት አላደርስም። አንተን ለሚያሳድዱትም ስለ አንተ ምንም አልናገርም» ይል ነበር። የፍጥረተ ዓለሙ ሰይድ፦ «ጌታዬ ሆይ! በቃሉ እውነተኛና ቅን ከሆነ ፈረሱን አድነው» ብለው ዱዓ ባደረጉ ጊዜ አላሁ ተዓላ ይህን ዱዓ ተቀበለ። የሱራቃ ኢብኑ ማሊክ ፈረስ ከጉድጓዱ መውጣት የቻለው ከዚህ ዱዓ በኋላ ብቻ ነበር። በዚህ ጊዜ የፈረሱ እግሮች ከሰጠሙበት ስፍራ እንደ ጭስ ያለ ነገር ወደ ሰማይ ይወጣ ነበር። ሱራቃ በታላቅ መደነቅ ውስጥ ወደቀ፤ ከተፈጸመው ሁሉ ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ሁልጊዜ እንደሚጠበቁ ተረዳ። ብዙ ነገሮችን አይቶ ነበር። በመጨረሻም፦ «ሙሐመድ ሆይ! እኔ ሱራቃ ኢብኑ ማሊክ ነኝ! በእኔ ላይ ፈጽሞ ጥርጣሬ አይኑርዎት። ቃል እገባልዎታለሁ፤ ከእንግዲህ የማይወዱትን ምንም ነገር አላደርግም። ወገንዎ እርስዎንና ጓደኞችዎን ለሚይዝ ብዙ ሽልማት እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል» አለ፤ የቁረይሽ አጋሪዎች ሊያደርጉ ያሰቡትንም አንድ በአንድ ነገራቸው። እንዲያውም ለመንገድ የሚሆን ስንቅና የሚቀመጡበት ግመል ሊሰጣቸው ፈለገ፤ ነገር ግን ውዱ ነብያችን አልተቀበሉም፤ እንዲህም አሉት፦ «ሱራቃ ሆይ! የእስልምናን ሃይማኖት እስካልተቀበልክ ድረስ እኔም ግመልህንም ከብትህንም አልሻም፤ አልፈልግምም። እኛን ማየትህን በምሥጢር ያዝ፤ ይበቃል።» ኢብኑ ሰዕድ ደግሞ እንዲህ ብለው ዘግበዋል፦ ሱራቃ ክቡር ነብያችንን፦ «የፈለጉትን ይዘዙኝ» ባለ ጊዜ ክቡር ረሱሉላህ፦ «በአገርህ ቆይ። ማንም እንዲደርስብን ዕድል አትስጥ» አሉ። አላሁ ተዓላ በሻ ጊዜ ሁሉም ነገር ይሆናል። በእርሱ በቅንነት ተመክቶ በውዴታው መንገድ በተሄደ ጊዜ አእምሮ የማይደርስባቸው ክስተቶች ይፈጸማሉ። ክቡር ረሱሉላህን ገድሎ ታላላቅ ሽልማቶችን ለማግኘት በመጎምጀት እንደሚያገሣ አንበሳ ሆኖ የተነሣው ሱራቃ አሁን እንደ ለዘበና እንደሚታዘዝ ሕፃን ሆነ። በሁሉም ነገር ላይ ቻይ የሆነው አላሁ ተዓላ ሐቢቡን እንዳይጎዳ የሱራቃን ልብ ወደ መልካም ነገር አዞረው። በእርግጥ አላሁ ተዓላ ሐቢቡን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ብቻቸውን አይተዋቸውም ነበር፤ ምክንያቱም እርሳቸው ሰዎች በዚህ ዓለምም በአኺራም ዘላለማዊ ደስታን እንዲያገኙ ለእዝነት የላካቸው ውዱ ነብዩ ነበሩና። ከዚያም ሱራቃ በዱካው ተመለሰ። የደረሰበትንም ላገኛቸው ሰዎች አልተናገረም።8
የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን እየመጡ ነው!
ክቡር ነብያችን፣ ሰይዲና አቡበክር፣ ዓሚር ኢብኑ ፉሀይራና መንገድ መሪያቸው ዐብዱላህ ኢብኑ ኡረይቂጥ ከአንድ ሳምንት ጉዞ በኋላ በቢዕሳ በአሥራ ሦስተኛው ዓመት (622 እ.ኤ.አ.) በሴፕቴምበር 20 ቀን፣ ማለትም በሂጅራ የመጀመሪያው ዓመት በረቢዑል አወል ወር 8ኛው ቀን ሰኞ ዕለት ረፋድ ላይ «ቁባ» መንደር ደረሱ። ኩልሱም ኢብኑ ሂድም በተባሉ አንድ ሙስሊም ቤት በእንግድነት ተቀመጡ። የመጀመሪያዎቹ ሙሃጂሮች ረሱሉል አክረም ገና መዲና ሳይደርሱ በቁባ የዐምር ኢብኑ ዐውፍ ልጆች ንብረት የነበረውን የተምር ማድረቂያ ቦታ የሶላት ቦታ አድርገውት ነበር። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ቁባ በደረሱ ጊዜ ይህን የሶላት ቦታ አስፍተው የመጀመሪያውን መስጊድ ሠሩ። ሶላቶቻቸውንም በመስጂደ ቁባ ሰገዱ። መስጂደ ቁባ በሱረቱ አት-ተውባ መቶ ስምንተኛው ክቡር አንቀጽ በትርጓሜ «… መሠረቱ በተቅዋ ላይ የተገነባው መስጊድ» ተብሎ ተወደሰ።9
ሌሊትና ቀን እኩል የሆኑበትን ሴፕቴምበር 23ንም በቁባ መንደር አሳልፈው በረቢዑል አወል 12ኛው ቀን ጁሙዓ ዕለት ወደ መዲና ተነሡ። በዙህር ሶላት ጊዜ በመዲናና በቁባ መካከል ባለው በራኑና ሸለቆ ቆሙ። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የመጀመሪያውን የጁሙዓ ሶላት በዚያ ሰገዱ፤ የመጀመሪያውን ኹጥባም በዚያ አደረጉ።10 በዚያው ቀንም መዲና ደረሱ። (በኋላ በዚያ ስፍራ የመጀመሪያውን የጁሙዓ ሶላት ለማስታወስ «መስጂደል ጁሙዓ» በሚል ስም መስጊድ ተሠራ።) በዚህ መካከል በመካ የቀሩት ሰይዲና ዐሊይ ክቡር ረሱሉላህ በካዕባ አሽ-ሸሪፋ ዘወትር ይቀመጡበት በነበረው ስፍራ ተቀመጡ። «በረሱሉል አክረም ዘንድ ንብረት ያለው ሰው መጥቶ ይውሰድ» ብለው አስጮኹ። ሁሉም መጥቶ የንብረቱን ምልክት እየተናገረ አደራውን ተቀበለ። በዚህም አደራዎቹ ለባለቤቶቻቸው ተመለሱ። የአላህ አንበሳ ሰይዲና ዐሊይ የቁረይሽ ከሓዲዎች ወደተሰበሰቡበት ስፍራ ሄደው፦ «ኢንሻአላሁ ተዓላ ነገ ወደ መዲና አል-ሙነወራ እሄዳለሁ። የምትሉት ነገር አላችሁን? እዚህ እያለሁ ተናገሩ» አሉ። ሁሉም አንገታቸውን ደፍተው ምንም አልተናገሩም። በነጋ ጊዜ ሰይዲና ዐሊይ የረሱሉል አክረምን የግል ዕቃዎች ሰብስበው ጉዞ ጀመሩ። ከቁረይሽ 4 ወይም 5 ሰዎች መንገዳቸውን ቢዘጉም ከእነርሱ ጋር ተዋግተው አሸነፉ። ከዚያም በመንገድ ላይ ሚቅዳድ ኢብኑል አስወድ ፊት ለፊት ገጠማቸው። እርሱንም በአንድ ምት መሬት ላይ ጥለው ወደ ኢማን ጠሩት። እርሳቸውም ሙስሊም ሆኑ። ዳግመኛ ጉዞአቸውን ቀጥለው ካበጡ እግሮቻቸው ደም እየፈሰሰ ክቡር ረሱሉላህን በቁባ ደረሱባቸው። ቀን ቀን እየተደበቁ ሌሊት ሌሊት በእግራቸው በተጓዙበት በዚህ ጉዞ መጨረሻ ወደ ነብያችን ፊት መሄድ ወደማይችሉበት ሁኔታ ደርሰው ነበር። ረሱሉል አክረም ይህን በሰሙ ጊዜ እርሳቸው ራሳቸው ወደ ዐሊይ ሄዱ። ሰይዲና ዐሊይን ባዩአቸው ጊዜ በሁኔታቸው አዘኑላቸው፤ ውድና ራሳቸውን የሚሠዉትን የአጎታቸውን ልጅ አቀፉአቸው፤ በሐቅ መንገድ በሺዎች የሚቆጠሩ መከራዎችን የታገሡትን ለስላሳና ስስ እግሮቻቸውን በተባረኩ እጆቻቸው ዳበሱ፤ እንዲፈወሱም ዱዓ አደረጉላቸው። እንዲያውም በዚህ የሰይዲና ዐሊይ መሥዋዕትነት ምክንያት ትርጓሜው «ከሰዎች መካከል የአላሁ ተዓላን ውዴታ ለማግኘት ነፍሱን (ራሱን) የሚሠዋ አለ» የሆነው ክቡር አንቀጽ እንደወረደ ተዘግቧል።1112
«ሱራቃ ሆይ! የኪስራን አምባሮች ስታጠልቅ፣ ቀበቶውን ስትታጠቅና ዘውዱን ስትደፋ አሁን የማይህ ያህል ይሰማኛል!» ሐዲስ ሸሪፍ
ከዚህ ቀደም ወደ መዲና ሂጅራ ያደረጉት ሶሓቦችና የመዲና ሙስሊሞች የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን ሂጅራ ለማድረግ ከመካ መነሣታቸውን በሰሙ ጊዜ መምጣታቸውን በጉጉትና በስሜት ይጠባበቁ ነበር። ስለዚህ በመዲና አል-ሙነወራ ዳርቻዎች ጠባቂዎችን አስቀመጡ፤ ከተማቸውን በመምጣታቸው በሚያከብሩበት ቅጽበት ሰይዳችንን ለመቀበል ይጓጉ ነበር። በፍቅራቸው የሚቃጠሉት እነዚያ ሰዎች የሚያቃጥል በረሃ ውኃን እንደሚናፍቅ ዓይኖቻቸውን አድማሱ ላይ ተክለው ለብዙ ቀናት ጠበቁ።
በመጨረሻም በድንገት፦ «እየመጡ ነው! እየመጡ ነው!..» የሚል ድምፅ ተሰማ። ድምፁን የሰሙት ዓይኖቻቸውን ወደሚያቃጥለው በረሃ መሀል አማተሩ። አዎ!.. አዎ!.. እነርሱም ለብዙ ጊዜ ሲጠበቁ የነበሩት እንግዶች በሚያቃጥለው በረሃ ውስጥ የፀሐዩ ግለት ቢኖርም በታላቅ ግርማ ወደ እነርሱ ሲመጡ አዩ። በደስታም እርስ በርሳቸው፦ «የምሥራች!.. የምሥራች!.. ረሱሉላህ እየመጡ ነው!.. ነብያችን እየመጡ ነው!.. የመዲና ሰዎች ሆይ! ደስ ይበላችሁ! በዓል አድርጉ! ሐቢቡላህ እየመጡ ነው!.. የራሳችን ላይ ዘውድ እየመጡ ነው!..» እያሉ መጮኽ ጀመሩ። ይህ ወሬ በቅጽበት የመዲና አል-ሙነወራን ጎዳናዎች ሞላ። ከሰባት ዓመቱ እስከ ሰባ ዓመቱ፣ ከሽማግሌው እስከ በሽተኛው ድረስ ሁሉም ይህን አቻ የሌለውን አስደሳች ወሬ ይጠባበቅ ነበር።
የመዲና ሰዎች ሁሉ ያማሩ ልብሶቻቸውን ለብሰው የዓለማት ሰይድን ለመቀበል ተጣደፉ። የተክቢር ድምፆች ሰማዩን አስተጋቡ፤ የደስታ እንባዎችም እንደ ጎርፍ ፈሰሱ። በሐዘንና በደስታ የተሞላ አየር ነፈሰ፤ መዲናም በታሪኳ እጅግ ያማረውን ቀን አሳለፈች። በአንድ በኩል ሁሉም «አል-አሚን» በሚል ቅጽል ስም የሚያውቋቸውን የአላሁ ተዓላን ሐቢብ ለመግደል በራሳቸው ላይ ሽልማት ያስቀመጡ ነበሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እርሳቸውንና ጓደኞቻቸውን ለመጠበቅ፣ በደረታቸው ለማቀፍና በዚህም መንገድ ሕይወታቸውን ለመሠዋት የሚፈልጉ ነበሩ።
የመዲና ሰዎች የውዱ ነብያችንን ብሩህ ፊት በተቻለ ፍጥነት ለማየት ይፈልጉ ነበር። መዲና መዲና ከሆነች ጀምሮ እንዲህ ያለ አስደሳች፣ እንዲህ ያለ የተባረከ ቅጽበት አይታ አታውቅም ነበር። ይህ እስከዚያ ቀን ድረስ ያልታየ በዓል ነበር። አምሳያው ታይቶ በማያውቅና በማይታይ በዚህ በዓል ልጆች፣ ወጣቶች፣ ታላላቆች፣ እነዚያ ዕድለኛ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ጊዜ በአንድ አፍ ይህን ግጥም ዘመሩ፦13
ጦለዐል በድሩ ዐለይና፣
ሙሉ ጨረቃ በላያችን ወጣች
ሚን ሰኒያቲል ወዳዕ፣
ከወዳዕ ኮረብታዎች።
ወጀበሽ ሹክሩ ዐለይና፣
ምስጋና በእኛ ላይ ግዴታ ሆነ፣
ማ ደዓ ሊላሂ ዳዕ።
ወደ አላህ ጠሪ እስከጠራ ድረስ።
አዩሀል መብዑሱ ፊና፣
ወደ እኛ የተላኩት ሆይ፣
ጂእታ ቢል አምሪል ሙጧዕ፣
የአላህን ትእዛዝ አመጡ።
ጂእታ ሸረፍተል መዲና፣
መዲናን አከበሩ፣
መርሐበን ያ ኸይረ ዳዕ።
እንኳን ደኅና መጡ፣ ከጠሪዎች ሁሉ በላጩ ሆይ!
አንታ ሸምሱን፣ አንታ በድሩን፣
እርስዎ ፀሐይ ነዎት፣ እርስዎ ጨረቃ ነዎት፣
አንታ ኑሩን ዐላ ኑር፣
እርስዎ በኑር ላይ ኑር ነዎት፣
አንታ ሚስባሑ ሱረያ፣
እርስዎ የሱረያ ከዋክብት ብርሃን ነዎት፣
ያ ሐቢቢ፣ ያ ረሱል!
ውዴ ሆይ፣ መልዕክተኛ ሆይ!
ቀድ ለቢስና ሰውበ ዒዚን፣
ክብርና ልዕልና ለበስን፣
በዕደ አስዋቢር ሪቃዕ፣
ከተቀዳደደ ልብሳችን ተላቀቅን፣
ወረዲዕና ሰድየ መጅዲን፣
ታላቅነትን አገኘን፣ ጠገብንም፣
በዕደ አያሚድ ዲያዕ።
በኪሳራ ነበርን፣ ትርፍ አገኘን።
ቃለት አሕማሩድ ደያጂ፣
ጨለማን የምታስወግደው ጨረቃ እንዲህ ትላለች፦
ቁል ሊ አርባቢል ኢስላም፣
«ለእስልምና ሰዎች እንዲህ በሉ፦
ኩሉ መን የትበዕ ሙሐመድ፣
ሙሐመድን (ዐለይሂ ሰላም) የሚከተለውን
የንበጊ አን ላ ዩዷም።
ፈጽሞ አትበድሉት።»
ወተዓሀድና ጀሚዐን፣
ሁላችንም በአንድነት ቃል ገባን
የውመ አቅሰምነል የሚን፣
መሐላ በተፈጸመበት ቀን፦
ለን ነኹነል ዐህደ የውመን፣
እውነተኛነት መንገዳችን ነው፣
ወተኸዝነ ሲድቀ ዲን።
በሃይማኖት ውስጥ ከዳተኝነት የለም።
ለስቱ ወላሂ ነሲየን፣
ወላሂ! ፈጽሞ አልረሳም፦
ማ ዩቃሲሂል ዒባድ፣
ሕመም የሌለበት ቀን አልነበረም።
መሽሀደን ያ ነጅመ አምኒን፣
የደኅንነት ኮከብ ሆይ! እርስዎ ምስክር ነዎት፦
ዙ ወፋኢን ወዊዳድ።
ታማኝነትዎና ፍቅርዎ ታላቅ ነው።
በየስፍራው፦ «እንኳን ደኅና መጡ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!» እና «ወደ እኛ ይግቡ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!» የሚሉ ልመናዎች አስተጋቡ። ከመዲና ታላላቅ ሰዎች አንዳንዶቹ የቀስዋን ልጓም ይዘው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ወደ እኛ ይግቡ…» ብለው ለመኑ። እርሳቸውም፦ «የግመሌን ልጓም ልቀቁ፤ እርሷ ታዝዛለች። በማን ቤት ፊት ብትንበረከክ በዚያ እንግዳ እሆናለሁ!» አሏቸው።
«ከሰዎች መካከል የአላሁ ተዓላን ውዴታ ለማግኘት ነፍሱን የሚሠዋ አለ» በቀራ: 207
ሁሉም በታላቅ ስሜትና ጉጉት ተያዘ። ቀስዋ የት ትንበረከክ ይሆን? ቀስዋ ወደ መዲና ውስጥ ገፋች፤ በእያንዳንዱ በር ፊት ስታልፍም የቤቱ ባለቤቶች፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ወደ እኛ በመምጣት ያክብሩን፤ ያክብሩን!» እያሉ ይለምኑ ነበር። ክቡር ነብያችንም ፈገግ ብለው፦ «ለግመሏ መንገድ ልቀቁ! የት እንደምትንበረከክ ታዝዛለች» ይሏቸው ነበር።
በመጨረሻም ቀስዋ የክቡር ነብያችን የአሁኑ የተባረከ መስጊድ በር ባለበት ስፍራ ተንበረከከች። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከግመላቸው አልወረዱም። እንስሳዋ እንደገና ተነሥታ መሄድ ጀመረች። ከዚያም በመጀመሪያው ስፍራ ተንበረከከች፤ ዳግመኛም አልተነሣችም። በዚህ ጊዜ ሰይዳችን ከቀስዋ ላይ ወርደው፦ «ኢንሻአላህ መኖሪያችን ይህ ነው» አሉ፤ ከዚያም፦ «ይህ ስፍራ የማን ነው?» ብለው ጠየቁ። «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! የዐምር ልጆች የሱሀይልና የሰህል ነው» ብለው መለሱ። እነዚህ ልጆች ወላጅ አልባዎች ነበሩ። ነብያችንም፦ «ከዘመዶቻችን የማን ቤት ለዚህ ስፍራ ይበልጥ ቅርብ ነው?» ብለው ጠየቁ። ምክንያቱም የክቡር ረሱሉላህ አያት የዐብዱልሙጠሊብ እናት ከነጃር ልጆች ነበሩ። ሰይዲና ኻሊድ ኢብኑ ዘይድ አቡ አዩብ አል-አንሷሪ በደስታ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! የእኔ ቤት ይበልጥ ቅርብ ነው። ይኸው ቤቴ፣ ይኸውም በሩ» ብለው በታላቅ ስሜት አሳዩ። የቀስዋን ጭነት አውርደው ክቡር ረሱሉላህን ወደ ቤታቸው ጋበዙ።14
የመዲና ሙስሊሞችና ሙሃጂሮች በሰይዳችን ሂጅራ እጅግ ተደሰቱ። ይህ ዓመት «ሰነቱል ኢዝን» ይባላል።
በሂጅራ ጊዜ የልቦች መድኃኒት፣ የሰው ልጆች ዘውድ፣ የአላሁ ተዓላ ሐቢብ ክቡር ነብያችን ሃምሳ ሦስት ዓመታቸው ነበር።
ሁኔታዬ ምን ይሆናል?
ሁኔታዬ ምን ይሆናል፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ?
ነፍሴና ገላዬ ይነዳሉ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ።
እንደሚርገበገብ ነበልባል፣ እንደ ዕጣን ማጨሻ
በፍቅርዎ እጨሳለሁ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ።
ከእርስዎ ተለይቼ በናፍቆት ለብዙ ዘመን
ቀልጬ አልቃለሁ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ።
ዓለም ለእርስዎ የተፈጠረልዎ መሪ ነዎት፤ በላቀው ደጅዎ
አንገቴን አቀረቅራለሁ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ።
በረገጡት አፈር ላይ ጽጌረዳዎች አበቡ፤
እኔም በዚያ እሾህ ነኝ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ።
አቡ አዩብ አል-አንሷሪ ረዲየላሁ ዐንሁ
