ውዱ ነብዬ

የዐቀባ ቃል ኪዳኖች

የመጀመሪያው የዐቀባ ቃል ኪዳን

በቢዕሳ በአሥራ አንደኛው ዓመት በዙልሒጃ ወር አስዐድ ኢብኑ ዙራራና አሥራ አንድ ጓደኞቻቸው በሐጅ ወቅት እንደገና ወደ መካ መጡ። ከዓለማት ሰይድ ጋር ካደረጉት ቀዳሚ ግንኙነት ወዲህ ልክ አንድ ዓመት አልፎ ነበር። በዚያ ዓመት አጋሪዎቹ በሙስሊሞች ላይ ከቀደሙት ዓመታት ሁሉ ይበልጥ ስቃይና መከራ ያደርሱ ነበር። ክቡር ረሱሉላህን ያለማቋረጥ ይከታተሉ ነበር፤ ከእርሳቸው ጋር የሚነጋገረውንም ሰው ሁሉ ያሰቃዩ ነበር። ይህን ያወቁት የመዲና ሰዎች ከነብያችን ጋር በሌሊት በዐቀባ ለመገናኘት ቀጠሮ ያዙ። ሌሊት በሆነ ጊዜ ተገናኙ። ታማኝነታቸውን ገልጸው ለትእዛዞቻቸውና ለፍላጎቶቻቸው ሁሉ እንደሚገዙ ቃል በመግባት ቃል ኪዳን ፈጸሙ። በዚህ ስምምነትም «በአላሁ ተዓላ ላለማጋራት፣ ዝሙት ላለመፈጸም፣ ላለመስረቅ፣ ከሐሰተኛ ውንጀላ ለመራቅ፣ ነውርንና የሲሳይን እጦት ፈርተው ልጆቻቸውን ላለመግደል» ቃል ገቡ።1

ውዱ ነብያችን ሁለቱ የአውስ ጎሳ፣ ሌሎቹ ደግሞ የኸዝረጅ ጎሳ አባላት የሆኑትን እነዚህን 12 ሰዎች የጎሳዎቻቸው ተወካዮች አደረጓቸው። እነርሱም ለጎሳዎቻቸው እስልምናን ያስረዱና በእነርሱ ስም ለክቡር ረሱሉላህ ዋስ ይሆኑ ነበር። አስዐድ ኢብኑ ዙራራም በሁሉም ስም ተወካይ ሆነው ተሾሙ። ባለፈው ዓመት በዐቀባው ግንኙነት ላይ የተገኙት 5ቱና እስልምናን አዲስ የተቀበሉት 7ቱ እነዚህ ነበሩ፦ ከማሊክ ኢብኑ ነጃር ልጆች አስዐድ ኢብኑ ዙራራ፣ ዐውፍ ኢብኑል ሐሪስና ሙዓዝ ኢብኑል ሐሪስ፤ ከዙረይቅ ኢብኑ ዓሚር ልጆች ራፊዕ ኢብኑ ማሊክና ዘክዋን ኢብኑ ዐብዱ ቀይስ፤ ከገንም ኢብኑ ዐውፍ ልጆች ዑባዳ ኢብኑ ሷሚት፤ ከጉሰይና ልጆች የዚድ ኢብኑ ሰዕለባ፤ ከዐጅላን ኢብኑ ዘይድ ልጆች ዐባስ ኢብኑ ዑባዳ፤ ከሐራም ኢብኑ ከዕብ ልጆች ዑቅባ ኢብኑ ዓሚር፤ ከሰዋድ ኢብኑ ገንም ልጆች ቁጥባ ኢብኑ ዓሚር፤ ከዐብዱልአሽሀል ኢብኑ ጁሸም ልጆች አቡል ሀይሰም ማሊክ ኢብኑ ተዪሃን፤ ከዐምር ኢብኑ ዐውፍ ልጆች ደግሞ ዑወይም ኢብኑ ሳዒዳ።

በመዲና የወጣችው ፀሐይ

ከመጀመሪያው የዐቀባ ቃል ኪዳን (ስምምነት) በኋላ ወደ መዲና የተመለሱት ሰይዲና አስዐድ ኢብኑ ዙራራና ጓደኞቻቸው ለጎሳዎቻቸው ሌት ተቀን እስልምናን እያስረዱ ወደ እውነተኛው ሃይማኖት ጠሩ። በዚህ ጥሪ ምክንያት እስልምና በመዲና በፍጥነት መስፋፋት ጀመረ። ከዚህ ቀደም እርስ በርሳቸው ጠላቶች የነበሩት የአውስና የኸዝረጅ ጎሳዎች እንኳ አንድ ላይ ተሰባስበው እስልምናን በተሻለ ለመማር ከክቡር ረሱሉላህ አስተማሪ ጠየቁ። ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ቁርኣን ከሪምንና እስልምናን እንዲያስተምሩ በመካ ከነበሩት ሶሓቦቻቸው መካከል ሰይዲና ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይርን አስተማሪ አድርገው ወደ መዲና ላኩ። ሰይዲና ሙስዐብ በሰይዲና አስዐድ ቤት ተቀመጡ። ከእርሳቸው ጋር ቤት ለቤት እየዞሩ እስልምናን ለሁሉም አሳወቁ። ሰዎች ረሱሉላህን እንዲወዱና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እርሳቸውን ለመጠበቅ በሙሉ ልባቸው እንደሚተጉ ቃል እንዲገቡ ጠየቁ። ከረሱሉላህ ጋር ለሚደረገው ቃል ኪዳንም አዘጋጇቸው። የሰይዲና አስዐድ ኢብኑ ዙራራ ጎሳ መሪ ደግሞ ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ነበር፤ እርስ በርሳቸውም ዘመዳሞች ነበሩ። በዚያን ጊዜ በዓረቦች ዘንድ ዘመድን ከማዋረድ መቆጠብ ልማድ ስለነበር ገና ያላመነው ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ይህን ጉዳይ ለማደናቀፍ ወደ ሰይዲና አስዐድ ኢብኑ ዙራራ ቤት አልሄደም። የጎሳ መሪ እንደመሆኑ በዚህ ጉዳይ ራሱ ጣልቃ መግባት አልፈለገም። ስለዚህ ከጎሳው ታላላቆች አንዱ ለሆነው ለኡሰይድ ኢብኑ ሑደይር፦ «ወደ መንደራችን ሂድ፤ የመጣውን ያንን ሰው እይ፤ የምታደርገውንም አድርግ። አስዐድ የእናቴ እህት ልጅ ባይሆን ኖሮ ይህን ለአንተ አልተውልህም ነበር» አለ።

በዚህም ኡሰይድ ኢብኑ ሑደይር ጦሩን ይዞ ሰይዲና ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር ወደተቀመጡበት ቤት ሄደ። እዚያ ሲደርስ በቁጣ መናገር ጀመረ፦ «ወደ እኛ ለምን መጣችሁ? ሰዎችን ታታልላላችሁ! ሕይወታችሁን ማጣት ካልፈለጋችሁ ከዚህ ወዲያውኑ ውጡ!» አለ። ይህን የቁጣ ሁኔታውን ያዩት ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር፦ «እስኪ ትንሽ ተቀመጥና ቃላችንን አዳምጥ! ዓላማችንን ተረዳ፤ ከወደድከው ትቀበለዋለህ። ካልሆነ ደግሞ ታግደናለህ…» ብለው እጅግ በለዘበና በትሕትና መለሱለት። ኡሰይድ ተረጋግቶ፦ «እውነት ተናገርክ» አለ፤ ጦሩንም መሬት ላይ ተክሎ ተቀመጠ። የሰይዲና ሙስዐብን ጣፋጭ አነጋገር፣ ወደ ሰው ልብ ዘልቆ የሚገባ ቃላቸውንና በሚያምር ድምፃቸው ያነበቧቸውን የቁርኣን ከሪም አንቀጾች አዳመጠ። ራሱን ስቶ፦ «ይህ እንዴት ያለ ያማረ ነገር ነው!» አለ። ከዚያም፦ «ወደዚህ ሃይማኖት ለመግባት ምን ማድረግ ያስፈልጋል?» ብሎ ጠየቀ። አስረዱት፤ ኡሰይድ ኢብኑ ሑደይርም የሸሃዳን ቃል ተናግረው ሙስሊም ሆኑ። ከደስታቸው የተነሣ በቦታቸው መቀመጥ ያቃታቸው ሰይዲና ኡሰይድ፦ «እኔ ሄጄ አንድ ሰው ወደ እናንተ ልላክ። እርሱ ሙስሊም ከሆነ በመዲና ከወገኑ ያላመነ አንድም ሰው አይቀርም…» ብለው በፍጥነት ተነሥተው ሄዱ። በቀጥታ ወደ ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ዘንድ ደረሱ። ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ባያቸው ጊዜ፦ «እምላለሁ፤ ኡሰይድ ከዚህ በሄደበት ፊት አልተመለሰም» አለ። ከዚያም፦ «ኡሰይድ ሆይ! ምን አደረግህ?» ብሎ ጠየቀ። ሰይዲና ኡሰይድ ኢብኑ ሑደይር ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ሙስሊም እንዲሆን እጅግ ይመኙ ስለነበር፦ «ያንን ሰው (ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይርን) አነጋገርኩት፤ በእነርሱ ዘንድ ምንም ክፋት አላየሁም። ነገር ግን የበኑ ሐሪሳ ሰዎች የእናትህ እህት ልጅ አስዐድ እንዲህ ያለን ሰው በቤቱ ማስጠለሉን ተጠራጥረው ሊገድሉት መነሣታቸውን ሰማን» አሉ። እነዚህ ቃላት ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝን እጅግ ነኩት። ምክንያቱም ከጥቂት ዓመታት በፊት በተደረገ ጦርነት በኑ ሐሪሳን አሸንፈው ወደ ኸይበር እንዲጠለሉ አስገድደዋቸው ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላም ምሕረት አድርገውላቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቅደውላቸው ነበር። ይህ ሆኖ ሳለ እንዲህ ያለ አቋም ይይዛሉ የሚለው ሐሳብ ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝን እጅግ አስቆጣው። በእውነቱ ግን እንዲህ ያለ ነገር አልነበረም። ኡሰይድ ኢብኑ ሑደይር ይህን ብልሃት የተጠቀሙት ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ በእናቱ እህትና በልጃቸው በአስዐድ ኢብኑ ዙራራ፣ በዚህም ምክንያት በሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ነበር። በዚህም ወደ እነርሱ ወገን እንዲያዘነብልና በመጨረሻም ሙስሊም እንዲሆን መንገዱን አዘጋጁ። ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ በእነዚህ የኡሰይድ ኢብኑ ሑደይር ቃላት ከቦታው ዘሎ ተነሥቶ ወደ ሰይዲና አስዐድ ኢብኑ ዙራራ ዘንድ ሄደ። እዚያ ሲደርስ አስዐድና ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር እጅግ በሰላምና በእርጋታ ተቀምጠው ሲጨዋወቱ አያቸው። ወደ እነርሱ ቀርቦ፦ «አስዐድ ሆይ! በመካከላችን ዝምድና ባይኖር ኖሮ እነዚህን ማድረግ ባልቻልክ ነበር…» አለ። ለእነዚህ ቃላት ሰይዲና ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር እንዲህ ብለው መለሱ፦ «ሰዕድ ሆይ! ትንሽ ቆይ፤ ተቀመጥ፤ አዳምጠን፤ ተረዳንም… ቃላችን ከተስማማህ መልካም ነው፤ ካልወደድከው ግን አናቀርብልህም፤ አንተም ተነሥተህ ትሄዳለህ!» ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ በእነዚህ የለዘቡና ጣፋጭ ቃላት ተረጋግቶ በአንድ ጥግ ተቀመጠ፤ እነርሱንም ማዳመጥ ጀመረ። ሰይዲና ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር ለሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ በመጀመሪያ እስልምናን አስረዱት። የእስልምናን መሠረቶች ገለጹለት። ከዚያም በጣፋጭና በሚያምር ድምፃቸው ከቁርኣን ከሪም የተወሰነ ክፍል አነበቡ። ባነበቡ ቁጥር የሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ሁኔታ ይለወጥ ነበር፤ ራሱንም ይስት ነበር። አቻ በሌለው የቁርኣን ከሪም የአነጋገር ጥበብ ፊት ልቡ ለሰለሰ፤ በታላቅ ተጽዕኖ ሥርም ወደቀ። ራሱን መቆጣጠር አቅቶት፦ «እናንተ ወደዚህ ሃይማኖት ለመግባት ምን ታደርጋላችሁ?» ብሎ ጠየቀ። ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር ወዲያውኑ የሸሃዳን ቃል አስተማሩት። እርሱም፦ «አሽሀዱ አን ላ ኢላሀ ኢለላህ ወአሽሀዱ አነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ» ብለው ሙስሊም ሆኑ። ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ሙስሊም በመሆናቸው ከተሰማቸው ሰላምና ደስታ የተነሣ በቦታቸው መቀመጥ አልቻሉም። ወዲያውኑ ወደ ቤታቸው ሄደው እንደተማሩት ጉሱል አደረጉ። ከዚያም ወገናቸው እንዲሰበሰብ ጠየቁ። ኡሰይድ ኢብኑ ሑደይርን ይዘው ሕዝቡ ወደነበረበት ስፍራ ደረሱ። የዐብዱልአሽሀልን ልጆች እንዲህ ብለው ጠየቁ፦ «የዐብዱልአሽሀል ልጆች ሆይ! እኔን እንዴት ታውቁኛላችሁ?» እነርሱም በአንድ አፍ፦ «እርስዎ መሪያችንና ታላቃችን ነዎት፤ እኛም እርስዎን እንከተላለን!» ብለው መለሱ። ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ በዚህ ቃላቸው ላይ እንዲህ አሉ፦ «እንግዲያውስ ለሁላችሁም አሳውቃለሁ፦ እኔ ሙስሊም በመሆን ተከብሬያለሁ። እናንተም በአላሁ ተዓላና በመልዕክተኛው እንድታምኑ እፈልጋለሁ። ካላመናችሁ ከእናንተ ከአንዳችሁም ጋር አልነጋገርም፤ አልገናኝምም!…»

«እንግዲያውስ ለሁላችሁም አሳውቃለሁ፦ እኔ ሙስሊም በመሆን ተከብሬያለሁ። እናንተም በአላሁ ተዓላና በመልዕክተኛው እንድታምኑ እፈልጋለሁ» ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ (ረዲየላሁ ዐንሁ)

ሰነቱ ሱሩር (የደስታ ዓመት)

የዐብዱልአሽሀል ልጆች መሪያቸው ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ ሙስሊም መሆናቸውንና እነርሱንም ወደ እስልምና መጥራታቸውን እንደሰሙ ሁሉም በአንድነት ሙስሊም ሆኑ። በዚያን ቀን እስከ ምሽት ድረስ የመዲናን ሰማያት በሸሃዳ ቃልና በተክቢር ድምፆች አስተጋቡ።2 የዐብዱልአሽሀል ልጆች በአንድነት ሙስሊም ከሆኑ ብዙም ሳይቆይ መላው የመዲና ሕዝብና የአውስና የኸዝረጅ ጎሳዎችም እስልምናን ተቀበሉ። እያንዳንዱ ቤት በእስልምና ኑር በራ። ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝና ኡሰይድ ኢብኑ ሑደይር የጎሳዎቻቸው የሆኑትን ጣዖቶች ሁሉ ሰባበሩ። ይህ ሁኔታ ለውዱ ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በተነገረ ጊዜ እጅግ ተደሰቱ። የመካ ሙስሊሞች በደስታ ተሞልተው ነበር። በዚህ ምክንያት ይህ ዓመት (621 እ.ኤ.አ.) «ሰነቱ ሱሩር» (የደስታ ዓመት) ተባለ።

አስ-ሶላቱ ወሰላሙ ዐለይከ ያ ረሱለላህ!
አስ-ሶላቱ ወሰላሙ ዐለይከ ያ ሐቢበላህ!
አስ-ሶላቱ ወሰላሙ ዐለይከ ያ ሰይደል አወሊነ ወል አኺሪን።

ሁለተኛው የዐቀባ ቃል ኪዳን

በቢዕሳ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት የመካ አጋሪዎች በሙስሊሞች ላይ የሚያደርሱት ግፍ የመጨረሻ ደረጃው ላይ ደርሶ የማይታገሡት ሆኖ ነበር። በመዲና ግን በአስዐድ ኢብኑ ዙራራና በሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር አገልግሎት ምክንያት የአውስና የኸዝረጅ ሰዎች ሙስሊሞችን እጃቸውን ዘርግተው ለመቀበል፣ በደረታቸው ለማቀፍና ለእነርሱ ሲሉ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል በፍቅርና በጉጉት ተሞልተው ነበር። ክቡር ረሱሉላህ መዲናን በመምጣታቸው በተቻለ ፍጥነት እንዲያከብሩም ይመኙ ነበር፤ ለእርሳቸው ሲሉ ገንዘባቸውንና ሕይወታቸውን እንደማይሰስቱም ቃል ይገቡ ነበር። የሐጅ ጊዜ ደረሰ። በዙልሒጃ ወር ከሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር ጋር 73 ወንዶችና 2 ሴቶች የመዲና ሙስሊሞች ወደ መካ መጡ። ከሐጅ በኋላ ሁሉም እንደገና በዐቀባ ከነብያችን ጋር ተገናኙ። አስዐድ ኢብኑ ዙራራን ጨምሮ 12ቱ ተወካዮች በጎሳዎቻቸው ስም ነብያችን ወደ መዲና ሂጅራ እንዲያደርጉ ለመኑ፤ ሐሳብም አቀረቡ። ክቡር ረሱሉላህ ከቁርኣን ከሪም አንዳንድ ክቡር አንቀጾችን ካነበቡላቸው በኋላ ራሳቸውን፣ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን እንደሚጠብቁትና እንደሚንከባከቡት እርሳቸውንም እንዲሁ እንደሚጠብቁ ለማረጋገጥ ከእነርሱ ጽኑ ቃል ጠየቁ። ገና ሙስሊም ያልሆኑት የክቡር ረሱሉላህ አጎት ሰይዲና ዐባስም በዚያ ነበሩ። ቃል ኪዳን ለመግባት ለመጣው ለዚህ ጉባኤ እንዲህ ብለው ተናገሩ፦ «የመዲና ሰዎች ሆይ! እኚህ የወንድሜ ልጅ ናቸው። ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ የምወደው እርሳቸውን ነው። በእርሳቸው የምታምኑ፣ ከአላህ ዘንድ ያመጡትንም የምትቀበሉና ከእናንተ ጋር ይዛችኋቸው ለመሄድ የምትፈልጉ ከሆነ እኔን የሚያሳምን ጽኑ ቃል ልትሰጡኝ ይገባል። እንደምታውቁት ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ከእኛ ናቸው። በእርሳቸው ከማያምኑት ሰዎች ጠብቀናቸዋል። በመካከላችን በክብርና በልዕልና ተጠብቀው ይኖራሉ። ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ ከሁሉም ፊታቸውን አዙረው ከእናንተ ጋር ለመቀላቀልና አብረዋችሁ ለመሄድ ወስነዋል። የዓረብ ጎሳዎች ሁሉ ተባብረው በእናንተ ላይ በዘመቱ ጊዜ እነርሱን ለመቋቋም የሚበቃ የጦር ኃይል ካላችሁ ወደዚህ ጉዳይ ግቡ። ይህንንም ጉዳይ በመካከላችሁ በሚገባ ተወያዩበት፤ ተመካከሩበትም፤ በኋላ እንዳትከፋፈሉ። በሰጣችሁት ቃል ጸንታችሁ ከጠላቶቻቸው ልትጠብቋቸው ትችላላችሁን? ይህን እንደሚገባ ማድረግ ከቻላችሁ መልካም ነው። ከመካ ከወጡ በኋላ ብቻቸውን የምትተዋቸው ከሆነ ግን በአገራቸው በክብር ተጠብቀው እንዲኖሩ ከአሁኑ ተዉት።» ሰይዲና ዐባስ በተናገሩት በዚህ ንግግር የመዲና ሙስሊሞች አዘኑ። ክቡር ረሱሉላህን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ወደ አገራቸው ቢወስዷቸው ከአጋሪዎች ሊጠብቋቸው እንደማይችሉና በጭንቅ ጊዜ እንደሚተዋቸው የሚገልጽ ቃል የተነገራቸው ያህል ሆነባቸው። ከመዲና ሶሓቦች አንዱ የሆኑት ሰይዲና አስዐድ ኢብኑ ዙራራ ወደ ክቡር ነብያችን ዞረው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከፈቀዱልኝ ጥቂት የምናገረው አለኝ። ለእርስዎ ላቅርበው» አሉ። የፍጥረተ ዓለሙ ኩራት በፈቀዱላቸው ጊዜ ሰይዲና አስዐድ እንዲህ አሉ፦ «እናቴና አባቴ ለእርስዎ መሥዋዕት ይሁኑ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እያንዳንዱ ጥሪ የለዘበ ወይም የጠነከረ መንገድና ሥርዓት አለው። አሁን እርስዎ ሰዎች ለመቀበል እጅግ የሚከብዳቸውን ነገር እንድንቀበል እየጠሩን ነው። ምክንያቱም ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ሲያመልኳቸው የኖሩትን ጣዖቶች ትተው እስልምናን መቀበል እጅግ ከባድ ነው። ይህ ሆኖ ሳለ እኛ እስልምናን በሙሉ ልባችን ተቀበልን። ደግሞም አጋሪ ከሆኑት ዘመዶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት እንድንቆርጥ አዘዙን፤ እርሱንም በቅንነት ተቀበልን። ይህንንም መቀበል እጅግ ከባድ እንደሆነ ያውቃሉ። አጎቶችዎ እንኳ ጠላት ሆነው ያልጠበቁትን የላቀውን ማንነትዎን እጃችንን ዘርግተን ተቀበልን፤ ይህንንም የተከበረ ኃላፊነት በላያችን ላይ ግዴታና አስፈላጊ አድርገን ቆጠርነው። ሁላችንም በዚህ ቃላችን ተስማምተናል። በአንደበታችን የምንናገረውን በልባችን እናረጋግጠዋለን። የራሳችንን ሚስቶችና ልጆች እንደምንጠብቅ የተባረከ አካልዎንም እስከ መጨረሻው የደማችን ጠብታ ድረስ እንደምንጠብቅ እንምላለን። ይህን ቃል ኪዳናችንን ብናፈርስ ለአላሁ ተዓላ በሰጠነው ቃል ባለመጽናታችን ከመከረኞቹ ወገን እንሁን። የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኛ በዚህ ቃላችን ታማኞች ነን። አላሁ ተዓላ ያግዘን!» ከዚያም፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ለራስዎ የሚፈልጉትን ዋስትና ከእኛ ይውሰዱ፤ የሚሹትንም ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጡ» ብለው ቀጠሉ።

ክቡር ነብያችን ወደ እስልምና አበረታቷቸው፤ ከቁርኣን ከሪምም አነበቡ። ከዚያም እንዲህ አሉ፦ «ለጌታዬ ብዬ ከእናንተ የምጠይቀው ቅድመ ሁኔታ አላሁ ተዓላን እንድታመልኩና በእርሱ ምንም ነገር እንዳታጋሩ ነው። ለራሴና ለሶሓቦቼ ብዬ የምጠይቀው ቅድመ ሁኔታ ደግሞ እንድታስጠልሉን፣ እኔንና ሶሓቦቼን እንድትረዱ፣ ራሳችሁን ከምትከላከሉበትና ከምትጠብቁበት ነገር ሁሉ እኛንም እንድትጠብቁን ነው።»

በራእ ኢብኑ መዕሩር፦ «በእውነተኛው ሃይማኖትና በመጽሐፉ ነብይ አድርጎ በላከዎት በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ሚስቶቻችንንና ልጆቻችንን እንደምንከላከልና እንደምንጠብቅ እርስዎንም እንጠብቅዎታለን! የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ቃል ኪዳናችንን ይቀበሉን!» አሉ። ከመዲና ሙስሊሞች አንዱ የሆኑት ዐባስ ኢብኑ ዑባዳ ከክቡር ነብያችን ጋር የተደረገውን ስምምነት ለማጽናት ጓደኞቻቸውን፦ «የኸዝረጅ ሰዎች ሆይ! ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን ለምን እንደተቀበላችሁ ታውቃላችሁን?» አሏቸው። እነርሱም፦ «አዎ» ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ እንዲህ አሉ፦ «እናንተ እርሳቸውን በሰላም ጊዜም በጦርነት ጊዜም ተቀብላችሁ ትከተሏቸዋላችሁ። ገንዘባችሁ ጉዳት ሲደርስበትና ዘመዶቻችሁና ቤተ ዘመዶቻችሁ ሲጠፉ ነብያችንን ብቻቸውንና ያለ ረዳት የምትተዋቸው ከሆነ ይህን ከአሁኑ አድርጉ። ወላሂ! እንዲህ ያለ ነገር ብታደርጉ በዚህ ዓለምም በአኺራም ትጠፋላችሁ! ገንዘባችሁ ቢጠፋና የቅርብ ዘመዶቻችሁ ቢገደሉም እንኳ በሚጠሩበት ነገር ለእርሳቸው ታማኝ ለመሆን አእምሮአችሁ የሚያምን ከሆነ ያዟቸው። ወላሂ! ይህ ለዚህ ዓለማችሁም ለአኺራችሁም በላጭ ነው።» በዚህ ጊዜ ጓደኞቻቸው እንዲህ አሉ፦ «ገንዘባችን ቢጠፋም፣ የቅርብ ዘመዶቻችን ቢገደሉም ነብያችንን አንተዋቸውም። ከእርሳቸው ፈጽሞ አንለያይም። መሞት እንጂ መመለስ የለም!»

«ይህን ቃል ኪዳናችንን ብናፈርስ ለአላሁ ተዓላ በሰጠነው ቃል ባለመጽናታችን ከመከረኞቹ ወገን እንሁን። የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኛ በዚህ ቃላችን ታማኞች ነን። አላሁ ተዓላ ያግዘን!» አስዐድ ኢብኑ ዙራራ (ረዲየላሁ ዐንሁ)

ከዚያም ወደ ክቡር ነብያችን ዞረው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ይህን ቃል ኪዳናችንን ብንፈጽም ለእኛ ምን አለን?» ብለው ጠየቁ። በዚህ ጊዜ ውዱ ነብያችን፦ «የአላሁ ተዓላ ውዴታና ጀነት!» አሉ። ከእነርሱ እያንዳንዳቸው የወገናቸው ተወካዮችና ባለ ሙሉ ሥልጣኖች ሆነው ቃል ሰጡ። በመጀመሪያ ሰይዲና አስዐድ ኢብኑ ዙራራ፦ «ለአላሁ ተዓላና ለመልዕክተኛው የሰጠሁትን ቃል ለመፈጸምና በሕይወቴና በገንዘቤ እርሳቸውን ለመርዳት የገባሁትን ቃል እውን ለማድረግ ቃል ኪዳን እገባለሁ» ብለው እጅ ጨበጡ። ከእርሳቸው በኋላ እያንዳንዳቸው በዚሁ ሁኔታ ቃል ኪዳኑን ፈጽመው፦ «የአላሁ ተዓላንና የመልዕክተኛውን ጥሪ ተቀበልን፤ ሰማን፤ ታዘዝንም» በማለት እርካታቸውንና መገዛታቸውን ገለጹ። በዚህም ለረሱሉላህ ሲሉ ሕይወታቸውንና ገንዘባቸውን ያለ ማመንታት አቀረቡ። ከሴቶች ጋር የተደረገው ቃል ኪዳን በቃል ብቻ ነበር። ውዱ ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) «በአላሁ ተዓላ ምንም ነገር ላለማጋራት፣ ላለመስረቅ፣ ሐሰተኛ ውንጀላ ላለማቅረብ፣ ዝሙት ላለመፈጸም፣ ልጆቻቸውን ላለመግደል፣ ውሸት ላለመናገርና መልካም ሥራዎችን ላለመቃወም…» ከእነርሱ ቃል ተቀበሉ። የመዲና ሰዎች ለክቡር ነብያችን ቃል ኪዳን በሚገቡበት ጊዜ ከዐቀባ ኮረብታ አንድ ድምፅ፦ «በሚና የሰፈራችሁ ሰዎች ሆይ! ነብዩና የመዲና ሙስሊሞች እናንተን ለመዋጋት ተስማምተዋል!» ብሎ ጮኸ። ነብያችን ስለዚህ ድምፅ፦ «ይህ የዐቀባ ሰይጣን ነው» ካሉ በኋላ ለጠሪው፦ «የአላሁ ተዓላ ጠላት ሆይ! አንተንም እደርስብሃለሁ!» አሉ። ቃል ኪዳን የገቡትን የመዲና ሰዎችም፦ «ወዲያውኑ ወደ ማረፊያ ቦታዎቻችሁ ተመለሱ» አሏቸው። ዐባስ ኢብኑ ዑባዳ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እምላለሁ፤ እርስዎ ከፈለጉ ነገ ጠዋት በሚና ባሉት ከሓዲዎች ላይ ዘምተን ሁሉንም በሰይፍ እናጠፋቸዋለን» አሉ። ክቡር ነብያችን በዚህ ተደሰቱ፤ ነገር ግን፦ «እንዲህ እንድናደርግ ገና አልታዘዝንም። ለአሁኑ ወደ ቦታዎቻችሁ ተመለሱ» አሉ። ኢማም ነሳኢ ከዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ እንደዘገቡት፣ በዐቀባ ቃል ኪዳን ላይ የተገኙት አንሷሮች ወደ ረሱሉላህ በመምጣታቸው ከሙሃጂሮችም ሆነዋል።3

ጽዱ ለዋኖሷ ልመና ኩራቱን አይተውም፣
ጫፉን ይዞ እግሩ ሥር ወድቆ ካልለመነው ውኃ።
ጽጌረዳ የቡልቡልን ደም ልትጠጣ ትሻለች – በብልሃት
ወደ ቅርንጫፏ ባሕርይ ዘልቆ ካላዳነው ውኃ።
ንጹሕ ተፈጥሮውን ለዓለም ሰዎች አብርቶ አሳየ፤
የአሕመድ ሙኽታርን መንገድ ተከተለ ውኃ።
የሰው ዘር ሰይድ፣ የተመረጡ ዕንቁዎች ባሕር ናቸው፤
ለክፉዎች እሳት ተአምራታቸው ሆኑ ውኃ።
የነብይነትን የጽጌረዳ መስክ ውበት ለማደስ፣
በተአምራቸው ከጠንካራ ዓለት አፈለቁ ውኃ።
ተአምራቸው በዓለም ዳርቻ የሌለው ባሕር ነው፤
ከእርሱ እስከ ከሓዲዎች ሺህ የእሳት ቤቶች ደረሰ ውኃ።
የሰማ ሁሉ በመደነቅ ጣቱን ይነክሳል፤
በጭንቅ ቀን ለአንሷሮች ከጣቶቻቸው ሰጡ ውኃ።