ውዱ ነብዬ

ወደ ሐበሻ የተደረገው ሂጅራ

ወደ ሐበሻ የተደረገው የመጀመሪያው ሂጅራ

በክቡር ረሱሉላህ ነብይነት (ቢዕሳ) አምስተኛው ዓመት የአጋሪዎቹ ስቃይ ቢኖርም የሙስሊሞች ቁጥር መጨመሩን ቀጠለ። ነገር ግን አጋሪዎቹም ስቃያቸውን እያበዙ የቻሉትን ሁሉ ያደርጉ ነበር። ሶሓቦቻቸው የማይቻል ስቃይ መቀበላቸው፣ በእግሮቻቸው በገመድ ከግመሎች ጋር ታስረው ወደ ተቃራኒ አቅጣጫዎች እየተጎተቱ መገነጣጠላቸው ክቡር ነብያችንን እጅግ ያሳዝናቸው ነበር። እነዚህ ስቃዮች ቀን ባለፈ ቁጥር እየበረቱ ሄዱ፤ ርኅራኄ የሞላው ልባቸውም ሊሸከማቸው አልቻለም።

አንድ ቀን ሶሓቦችን ሰብስበው፦ «ሶሓቦቼ ሆይ! አሁን በምድር ላይ ተበተኑ። አላሁ ተዓላ በቅርቡ እንደገና ይሰበስባችኋል» አሉ።

እነርሱም፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ወዴት እንሂድ?» ብለው ጠየቁ። ነብያችን በተባረከ እጃቸው ወደ ሐበሻ (ኢትዮጵያ) ምድር እያመለከቱ፦ «ወደዚያ! ወደ ሐበሻ ምድር ሂዱ!1 ምክንያቱም በዚያ በአጠገቡ ካሉት በአንዱም ላይ ግፍ የማይፈጽም ንጉሥ አለ። ደግሞም ያ የእውነት ምድር ነው። አላሁ ተዓላ ካላችሁበት ጭንቅ መውጫና የመዳኛ መንገድ እስኪከፍትላችሁ ድረስ በዚያ ቆዩ» አሉ።

የዓለም መሪ ሙሐመድ ሙስጦፋ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በዚህ መልኩ ሶሓቦቻቸው ከስቃይ እንዲድኑና እርሳቸው ብቻቸውን ከመካ አጋሪዎች ጋር ትግላቸውን እንዲቀጥሉ ወስነው ነበር። በተወለዱ ጊዜ «ኡማዬ! ኡማዬ!» ያሉት ውዱ ነብያችን አሁን ደግሞ ለሶሓቦቻቸው መዳን ራሳቸውን መሥዋዕት ያደርጉ ነበር። በዚህ ፈቃዳቸው ከሶሓቦች ከፊሎቹ አገራቸውን ትተው ሂጅራ አደረጉ!.. ነገር ግን ከውዱ ነብያችን በመለየታቸው ሐዘናቸውም እጅግ ታላቅ ነበር።

በዚህ የመጀመሪያው ሂጅራ የተሳተፉት ሰይዲና ዑስማንና ባለቤታቸው ሰይደቲና ሩቀያ ቢንት ረሱሉላህ፣ አቡ ሑዘይፋና ባለቤታቸው ሰህላ ቢንት ሱሀይል፣ ዙበይር ኢብኑል ዐዋም፣ ሙስዐብ ኢብኑ ዑመይር፣ ዐብዱረሕማን ኢብኑ ዐውፍ፣ አቡ ሰለማ ኢብኑ ዐብዱልአሰድና ባለቤታቸው ኡሙ ሰለማ፣ ሐጢብ ኢብኑ ዐምር፣ ዓሚር ኢብኑ ረቢዓና ባለቤታቸው ለይላ ቢንት አቢ ሐስማ፣ ዑስማን ኢብኑ መዝዑን፣ አቡ ሰብራ ኢብኑ አቢ ሩህምና ባለቤታቸው ኡሙ ኩልሱም ቢንት ሱሀይል፣ ሱሀይል ኢብኑ በይዳ እና ዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁም) ነበሩ።2 ክቡር ነብያችን ስለ ሰይዲና ዑስማን፦ «ያለ ጥርጥር ዑስማን ከነብዩ ሉጥ በኋላ ከባለቤቱ ጋር ሂጅራ ያደረገ የመጀመሪያው ሰው ነው» አሉ።

ከሶሓቦች ከፊሎቹ በእንስሳ ተቀምጠው፣ ከፊሎቹም በእግር በምሥጢር መካን ለቀው ወጡ። ቅፍለቱ ሹዐይባ በደረሰ ጊዜ በላቀው አላህ ቸርነት ሁለት የንግድ መርከቦች መጥተው ነበር። ሶሓቦች ለነጋዴዎቹ እያንዳንዳቸው ግማሽ ወርቅ ከፍለው በመርከቦቹ ተሳፈሩ። በዚህ መሀል ይህን የሰሙት አጋሪዎች ሶሓቦችን ተከታተሉ። የባሕሩ ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ሙሃጂሮቹ በመርከብ ተሳፍረው ወደ ባሕር ገብተው ስለነበር ከእነርሱ አንዱንም ሊይዙ አልቻሉም። ድካማቸው ከንቱ ሆነ፤ ተስፋ ቆርጠውም ተመለሱ። ሶሓቦች በቀይ ባሕር በኩል በሰላም ሐበሻ ደረሱ።3 የሐበሻው ንጉሥ ነጃሺ ሙስሊሞችን በአገራቸው አሰፈሯቸው፤ እጅግ መልካምም አደረጉላቸው።

«ሶሓቦቼ ሆይ! አሁን በምድር ላይ ተበተኑ። አላሁ ተዓላ በቅርቡ እንደገና ይሰበስባችኋል» ሐዲስ ሸሪፍ

ሶሓቦች ወደ ሐበሻ ከሄዱ በኋላ ሱረቱ አን-ነጅም ወረደ። ረሱሉላህ ይህን ሱራ በመስጂደል ሐራም ለቁረይሾች እያነበቡ የአጋሪዎቹ ጣዖቶች የተጠቀሱበት አሥራ ዘጠነኛውና ሃያኛው ክቡር አንቀጽ በደረሱ ጊዜ የተረገመው ሰይጣን፦ «ጣዖቶቹ ታላላቅ ጣዖቶች ናቸው፤ ከእነርሱ ሸፋዐ ይጠበቃል» የሚሉ ቃላትን አስገባ። አጋሪዎቹ እነዚህን ቃላት ረሱሉላህ የተናገሯቸው መስሏቸው፦ «እርሱ ሃይማኖታችንን ስለተቀበለ እኛም ከእርሱ ጋር ታረቅን» አሉ። በዚያን ጊዜም ወሊድ ኢብኑል ሙጊራ ወደ ረሱሉላህ መጥቶ፦ «ከእንግዲህ አንነካህም» ባለ ጊዜ ክቡር ነብያችን ተደነቁ። ይህ የአጋሪዎቹ የ«ዕርቅ» ወሬ (!) በተባረከው የረመዳን ወር መጨረሻ ላይ በሐበሻ ወዳሉት ሶሓቦች ደረሰ። በሐበሻ የነበሩት ሙስሊሞች፦ «በመካ አጋሪዎቹና ሙስሊሞቹ ስምምነት አድርገዋል!» የሚል ወሬ ደረሳቸው። በዚህም እንዲህ ብለው አሰቡ፦ «ሂጅራችን፣ ስፍራችንንና አገራችንን መተዋችን የአጋሪዎቹ ጠላትነት ውጤት ነበር። አሁን ጠላትነታቸው ወደ ወዳጅነት ተለውጧል። ስለዚህ እንሂድና ረሱሉል አክረምን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በማገልገል እንከበር።» በዚህ መሀል ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም ይህን የሰይጣን ተንኮል ለረሱሉላህ አሳወቁ። እርሳቸውም በዚህ እጅግ አዘኑ። ክብሩ የላቀው አላህ ትርጓሜው «ከአንተ በፊት የላክናቸው ሸሪዓ ያላቸው ረሱሎችና እነርሱን የተከተሉ ነብያት ክቡር አንቀጽ ለማንበብ ወይም ከራሳቸው አንድ ነገር ለመናገር በፈለጉ ጊዜ ሰይጣን በሚያነቡት ወይም በሚናገሩት ውስጥ አንድ ነገር ይቀላቅላል። አላሁ ተዓላ ሰይጣን የቀላቀለውን ከእውነተኛው ይለያል። ከዚያም አንቀጾቹን ያጸናል። አላሁ ተዓላ የሰዎችን ሁኔታ አዋቂና ፍርዱን ፈጻሚ ነው።» የሆነውን የሱረቱ አል-ሐጅ ሃምሳ ሁለተኛውን ክቡር አንቀጽ አወረደ። አጋሪዎቹ ይህን አንቀጽ በሰሙ ጊዜ እንደገና ማንገላታትና ማሰቃየት ጀመሩ። ሙሃጂሮቹ ከሐበሻው ንጉሥ ፈቃድ ወስደው በሸዋል ወር ወደ መካ አል-ሙከረማ መጡ። ነገር ግን የደረሳቸው ወሬ ሐሰት መሆኑን አወቁ።4 የሆነውን በሰሙ ጊዜ ግራ ተጋቡ። ከዚያም ወደ ክቡር ነብያችን ዘንድ መጥተው ስለ ሐበሻ እንዲህ አሉ፦ «በዚያ መልካም ጉርብትናና ጥበቃ አገኘን። ሃይማኖታችንን የነካ የለም፤ አልተጎዳንም። የሚያስከፋንን አንድም ቃል አልሰማንም። በሰላም አላሁ ተዓላን አመለክን።»5 የሐበሻ ውኃ፣ አየርና ፍራፍሬ ብርታት እንደሚሰጥ፣ አራት የአምልኮ ቤቶች እንዳሉ፣ በእነዚያ ስፍራዎች በየቀኑ ግመሎችና በጎች እንደሚታረዱ፣ ድሆችና እንግዶች ተጋብዘው በመልካም እንደሚስተናገዱ፣ ንጉሣቸውም እየጎበኟቸው ጥበቃ እንደሰጧቸውና ችግራቸውን እንዳስወገዱላቸው በሰፊው ተርከው እርካታቸውን ገለጹ።6 በሐበሻ ከሁለት ወር በላይ ቆይተው ነበር።

ሰይዲና ሐምዛ ሙስሊም መሆናቸው

የቢዕሳ ስድስተኛው ዓመት… የእስልምና ድምፅ በየቀኑ ከአፍ ወደ ጆሮ እየተዛመተ ልቦች ውስጥ እየደረሰ ይበልጥ ወደ ሩቅ ይዘልቅ ነበር። ይህ ሁኔታ የቁረይሽን አጋሪዎች አሳበዳቸው፤ ምንም ያህል ቢጥሩም የእስልምናን መስፋፋት ሊያግዱ አልቻሉም። በ«ደላኢሉ ኑቡዋ» እና «መዓሪጁ ኑቡዋ» ውስጥ እንዲህ ተብሏል፦

ከአጋሪዎቹ መካከል ወሊድ የሚባል አንድ ሰው ጣዖት ነበረው። በሶፋ ኮረብታ ላይ ተሰብስበው ይህን ጣዖት ያመልኩ ነበር። አንድ ቀን ክቡር ነብያችን ወደ እነርሱ ሄደው አጋሪዎቹን ወደ ኢማን ጋበዙ። ከሓዲ የሆነ አንድ ጂን ወደዚያ ጣዖት ውስጥ ገብቶ ስለ ውዱ ነብያችን የማይገቡ ቃላትን ተናገረ። የዓለም ኩራት (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በዚህ አዘኑ። በሌላ ቀን ራሱ የማይታይ አንድ አካል ለክቡር ነብያችን ሰላምታ አቅርቦ እንዲህ አለ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከሓዲ የሆነ አንድ ጂን ስለ እርስዎ የማይገቡ ነገሮችን ተናግሯል። እኔ አግኝቼ ገደልኩት። ቢፈቅዱና ነገ ወደ ሶፋ ኮረብታ ቢመጡ? እርስዎ እንደገና ወደ እስልምና ይጋብዟቸዋል። እኔም ወደዚያ ጣዖት ውስጥ ገብቼ እርስዎን የሚያወድሱ ቃላትን እናገራለሁ።» ክቡር ነብያችንም ዐብዱላህ የሚባለውን የዚህን ጂን ሐሳብ ተቀበሉ።

በማግሥቱ ውዱ ነብያችን ወደዚያ ሄደው አጋሪዎቹን እንደገና ወደ ኢማን ጋበዙ።

አቡ ጀህልም በዚያ ነበር። ሙስሊሙ ጂን አጋሪዎቹ በእጃቸው ወደያዙት ጣዖት ውስጥ ገብቶ ስለ ውዱ ነብያችንና ስለ እስልምና ያማሩ ቃላትንና ግጥሞችን ተናገረ። አጋሪዎቹ እነዚህን ቃላት በሰሙ ጊዜ በእጃቸው ያለውን ጣዖት ሰባበሩት፤ በረሱሉላህም ላይ ተረባረቡ። የተባረከ ጸጉራቸው ፍጹም ተመሰቃቀለ። የተባረከ ፊታቸው በደም ተለወሰ። ግፋቸውንና ስቃያቸውን ታግሠው፦ «የቁረይሽ ሰዎች ሆይ! እኔን ትመታላችሁ። ነገር ግን እኔ ነብያችሁ ነኝ» አሉ። ከዚያም ከዚያ ተነሥተው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። አንዲት አገልጋይ ልጃገረድ ይህን ክስተት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አይታ ነበር። በዚህ ጊዜ ሰይዲና ሐምዛ በተራሮች ላይ እያደኑ ነበር። አንዲትን ሚዳቋ በቀስት ሊወጉ ሲሉ ሚዳቋዋ አንደበት አውጥታ፦ «ሐምዛ ሆይ! እኔን በቀስት ከምትወጋ የወንድምህን ልጅ ሊገድሉ የሚፈልጉትን ብትወጋ ይሻልሃል» አለች። ሰይዲና ሐምዛ በእነዚህ ቃላት ተደንቀው በፍጥነት ወደ ቤታቸው ተጓዙ። ከአደን ሲመለሱ መጀመሪያ ለጠዋፍ ወደ ሐረም ሸሪፍ ጎራ ብለው ከዚያ በኋላ ወደ ቤታቸው መሄድ ልማዳቸው ነበር። በዚያን ቀን ጠዋፍ በማድረግ ላይ ሳሉ አገልጋይቱ ወደ እርሳቸው መጥታ አቡ ጀህል በሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ላይ ያደረገውን ነገረቻቸው። ሰይዲና ሐምዛ ክቡር ነብያችን መሰደባቸውን በሰሙ ጊዜ የዝምድና ስሜታቸው ገነፈለ። መሣሪያቸውን ይዘው አጋሪዎቹ ወዳሉበት ስፍራ መጡ። «የወንድሜን ልጅ በክፉ ቃል የተናገርከውና ልቡን ያቆሰልከው አንተ ነህን? እነሆ የእኔም ሃይማኖት የእርሱ ሃይማኖት ነው። ኃይል ካለህ በእርሱ ላይ ያደረግኸውን በእኔም ላይ አድርግ እስኪ!» ብለው በአንገታቸው ባለው ቀስት የአቡ ጀህልን ራስ ፈነከቱ። በዚያ የነበሩት ከሓዲዎች በሰይዲና ሐምዛ ላይ ሊረባረቡ ፈለጉ። ነገር ግን አቡ ጀህል፦ «አትንኩት፤ ሐምዛ ትክክል ነው። የወንድሙን ልጅ ክፉ ቃል ተናገርኩት» አለ። ሰይዲና ሐምዛ ከዚያ ከሄዱ በኋላ አቡ ጀህል በዙሪያው ያሉትን፦ «ተጠንቀቁ፤ አትንኩት! ይቆጣብንና ሙስሊም ይሆናል። በዚህም ሙሐመድ ይጠናከራል» አለ። ምክንያቱም ሐምዛ የተከበሩ፣ ዋጋ ያላቸውና ብርቱ ሰው ነበሩ። አቡ ጀህል ሰይዲና ሐምዛ ሙስሊም እንዳይሆኑ ራሱ መፈንከቱን እንኳ ተቀብሎ ነበር። ሰይዲና ሐምዛ ወደ ክቡር ነብያችን ዘንድ መጥተው፦ «ሙሐመድ ሆይ! ከአቡ ጀህል ብቀላህን ተወጣሁልህ። በደም አጥለቀለቅሁት። አትዘን፤ ደስ ይበልህ!» አሉ። ውዱ ነብያችንም፦ «እኔ በእንደዚህ ዓይነት ነገሮች አልደሰትም» አሉ። ሰይዲና ሐምዛ፦ «አንተን ለማስደሰትና ከሐዘን ለማላቀቅ የፈለግከውን ሁሉ አደርጋለሁ!» ባሉ ጊዜ ክቡር ነብያችን፦ «እኔ የምደሰተው አንተ ስታምንና ውድ ሰውነትህን ከጀሀነም እሳት ስታድን ብቻ ነው» አሉ።

ሰይዲና ሐምዛ ወዲያውኑ ሙስሊም ሆኑ። ስለ እርሳቸውም ክቡር አንቀጽ ወረደ። እንደ ሰይዲና ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ አባባል፣ በቁርኣን ከሪም በሱረቱ አል-አንዓም መቶ ሃያ ሁለተኛው ክቡር አንቀጽ «ሕያው የተደረገውና ወደ ብርሃን የተወሰደው» ተብሎ የተገለጸው ሰው ሰይዲና ሐምዛ ሲሆኑ፣ «በጨለማዎች ውስጥ የሚዋልለው» የተባለው ደግሞ አቡ ጀህል ነው።

ሰይዲና ሐምዛ ወደ አጋሪዎቹ ሄደው ሙስሊም መሆናቸውንና የአላሁ ተዓላን ሐቢብ ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን ሕይወታቸውን ቢያስከፍላቸውም እንኳ እንደሚጠብቁ አሳውቀው አንድ ቀሲዳ አነበቡ። ባነበቡት ቀሲዳ እንዲህ አሉ፦ «ልቤን ወደ እስልምናና ወደ እውነት ስላዘነበለው ለአላሁ ተዓላ ምስጋና ይገባው። ይህ ሃይማኖት የባሮቹን ሥራ ሁሉ በሚያውቀው፣ ሁሉንም በችሮታው በሚይዘው፣ ኃይሉ ሁሉንም በሚያሸንፈው፣ የዓለማት ጌታ በሆነው በአላሁ ተዓላ የተላከ ነው። ቁርኣን ከሪም በሚነበብበት ጊዜ የልብና የአእምሮ ባለቤቶች ዓይኖች እንባ ያፈሳሉ። ቁርኣን ከሪም በጥሩ አንደበት በተብራሩ አንቀጾች መልክ ለሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ወርዷል። እርሳቸው ሙሐመድ ሙስጦፋ በመካከላችን ቃላቸው የሚሰማ፣ የሚታዘዙላቸው የተባረኩ ሰው ናቸው። እናንተ አጋሪዎች ሆይ! አእምሮአችሁን አጥታችሁ፣ ዓይናችሁ ጨልሞ ስለ እርሳቸው ኃይለኛ፣ ከባድና ሻካራ ቃላትን አትናገሩ። እንዲህ ባለ ሐሳብ ብትወሰዱ፣ በእኛ በሙስሊሞች ሬሳ ላይ ሳይረማመድ ማንም ሊነካቸው አይችልም።»

«የቁረይሽ ሰዎች ሆይ! እኔን ትመታላችሁ። ነገር ግን እኔ ነብያችሁ ነኝ» ውዱ ነብያችን ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም

ሰይዲና ሐምዛ ሙስሊም በመሆናቸው ውዱ ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እጅግ ተደሰቱ። እርሳቸውም ከእነርሱ ጋር በመቀላቀላቸው ሙስሊሞች እጅግ ተጠናከሩ። ሰይዲና ሐምዛ ሙስሊም በመሆናቸው ሁኔታው ተለወጠ። ምክንያቱም የመካ ሰዎች ሰይዲና ሐምዛ ተዋጊ፣ ደፋር፣ ጨዋ፣ ታጋይና ታላቅ ጀግና መሆናቸውን ያውቁ ነበር። ስለዚህ የቁረይሽ አጋሪዎች ከእንግዲህ ሙስሊሞችን ያለ ምንም ምክንያት ክፉ ማድረግ አልቻሉም፤ በተለይ የሰይዲና ሐምዛን ሰይፍ ብርታት ይፈሩ ነበር።7

በፍቅርዎ መንገድ ወጣሁ፣
ሸፋዐ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!
ኃጢአተኛ ነኝ፣ ፊቴ የጠቆረ፣
ሸፋዐ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!

ሰይዲና ዑመር ሙስሊም መሆናቸው

የእስልምና ሃይማኖት ቀን በቀን እየተስፋፋ የቁርኣን ከሪም ኑር ነፍሳትን ያበራ ነበር። ዕድሉ ያላቸው ሰዎች ከአላሁ ተዓላ በተሰጣቸው ችሮታ ያምኑ፣ ወደ ቅኑ መንገድም ይመሩ ነበር። ሶሓቦች (ረዲየላሁ ዐንሁም) የመሆንን ክብር ያገኙት እነዚህ የተባረኩ ሰዎች እጅ ለእጅና ልብ ለልብ ተያይዘው በክቡር ረሱሉላህ ዙሪያ በብርሃን ዙሪያ እንደሚዞሩ ቢራቢሮዎች ይዞሩ ነበር። የእርሳቸውን ትንሿን ፍላጎትና ምልክት እንደ ታላቅ ትእዛዝ ቆጥረው ለመፈጸም ይሽቀዳደሙ ነበር፤ ለዚህም ሕይወታቸውን እንኳ ከመሠዋት ወደ ኋላ አይሉም ነበር። የአጋሪዎቹ ጭንቀትና ስጋት ግን ጣሪያ ደርሶ ነበር። ምክንያቱም በጣት ከሚጠቆሙ ጀግኖች አንዱ የሆኑት ሰይዲና ሐምዛም ሙስሊም ሆነው በረሱሉላህ ሰልፍ ውስጥ ቦታቸውን ይዘው ነበር። ይህ ያልተጠበቀ ክስተት አጋሪዎቹን ፈጽሞ ከልክ በላይ አስቆጣቸው። በዚህም ምክንያት የኸጧብ ልጅ ዑመር (ገና ሙስሊም አልሆኑም ነበር) አንድ ቀን ክቡር ረሱሉላህን ባገኟቸው ስፍራ ሊገድሏቸው አስበው ከቤታቸው ወጡ።

ውዱ ነብያችንን በመስጂደል ሐራም ሶላት ሲሰግዱ አገኟቸው። ሶላቱ እስኪያልቅ ሲጠብቁ የሚያነቡት ነገር ትኩረታቸውን ሳበው፤ ዑመርም በጉጉት ማዳመጥ ጀመሩ። ሐቢቡል አክረም የተከበረውን ሱረቱ አል-ሓቃን ያነቡ ነበር። በትርጓሜ፦ «መምጣቷ እውነት የሆነችው ቂያማ!… መምጣቷ እውነት የሆነችው ቂያማ ምንድን ናት (ታውቃለህን)? መምጣቷ እውነት የሆነችው ቂያማ ምን እንደሆነች ምን አሳወቀህ? ሰሙድና ዓድ (ሕዝቦች) ልቦች ከድንጋጤዋ የሚንቀጠቀጡባትን ቂያማ አስተባበሉ። የሰሙድ ሕዝብ በአመፃቸው ምክንያት (በጂብሪል ዐለይሂ ሰላም ጩኸት) ጠፉ።

የዓድ ሕዝብ ደግሞ በሚያጠፋ፣ በሚያጓራ፣ ወሰን ባለፈና ኃይለኛ በሆነ ነፋስ (በአውሎ ነፋስ) ጠፉ። አላሁ ተዓላ ያንን አውሎ ነፋስ ሰባት ሌሊትና ስምንት ቀን ያለማቋረጥ በላያቸው ላይ አሰለጠነው። (እንዲህ ያለ ሁኔታ ላይ ደረሱ፤) በዚያን ጊዜ በዚያ ብትገኝ ኖሮ ከሥሩ ተነቅሎ መሬት ላይ እንደተዘረረ የተቦረቦረ የተምር ዛፍ ግንድ እንዴት ሞተው እንደወደቁ ባየህ ነበር! አሁን ከእነርሱ የቀረ ነገር (አንድ ሰው፣ አንድ ሕያው ፍጡር) ታያለህን? ፊርዐውንም፣ ከእርሱ በፊት የነበሩትም፣ የተገለበጡት ከተሞች ሰዎችም (የሉጥ ሕዝብ) ያንኑ ስሕተት (ሽርክንና አመፅን) ሁልጊዜ ፈጸሙ… በዚህም በጌታቸው ነብይ (በሉጥ ዐለይሂ ሰላምና በሌሎቹ) ላይ አመፁ። በዚህም በሌሎቹ ኡማዎች ላይ ከመጣው ቅጣት የበረታ ቅጣት ያዛቸው… በእርግጥ ውኃው ሁሉንም በሸፈነ ጊዜ (በኑሕ የጥፋት ውኃ) ለእናንተ ትምህርት እንዲሆንና የሚሰሙት ጆሮዎች እንዲጠብቁትና እንዲያስታውሱት እናንተን (ማለትም ለመኖራችሁ ምክንያት የሆኑትን አያቶቻችሁን) በመርከብ ውስጥ ተሸከምናችሁ።

ቀንዱ አንድ ጊዜ በተነፋ ጊዜ፣ ምድርና ተራሮች ከስፍራቸው ተነሥተው በኃይል እርስ በርሳቸው ተጋጭተው በተበታተኑ ጊዜ፣ በዚያ ቀን ቂያማ ትቆማለች። በዚያ ቀን ሰማይ ኃይሏንና ጽናቷን አጥታ ትሰነጠቃለች፤ ትበታተናለችም።

መላእክትም በሰማይ ዳርቻዎች ላይ ናቸው (የጌታቸውን ትእዛዝ ይጠባበቃሉ)። በዚያ ቀን የጌታህን ዐርሽ (በሰማይ ዙሪያ ካሉት) ስምንት መላእክት ይሸከማሉ። በዚያ ቀን (ለሒሳብ ወደ አላሁ ተዓላ) ትቀርባላችሁ፤ ከእናንተ ምንም ምሥጢር (በዓለም ሳላችሁ የደበቃችሁት የመሰላችሁ) የተሰወረ አይሆንም (ከአላሁ ተዓላ)። ያን ጊዜ መጽሐፉ በቀኙ የተሰጠው ሰው (እየተደሰተ) እንዲህ ይላል፦ ‹እነሆ፣ መጽሐፌን አንብቡ! እኔ ሒሳቤን እንደምገናኝ በእርግጠኝነት አውቄ ነበር።›

እርሱ በተወደደ ሕይወት ውስጥ ይሆናል፤ በከፍተኛ ጀነት ውስጥ ይሆናል… (ፍሬዎቿ) ለመልቀም የቀረቡ ናቸው። (ለእነርሱ እንዲህ ይባላል፦) ‹ባለፉት ቀናት (በዓለም) ላስቀደማችኋቸው መልካም ሥራዎች ምንዳ ብሉ፣ ጠጡ፤ መልካም ጤና ይሁንላችሁ።›

መጽሐፉ በግራው የተሰጠው ሰው ግን እንዲህ ይላል፦ ‹ወዮ! ምነው መጽሐፌ ባልተሰጠኝ… ሒሳቤም ምን እንደሆነ ባላወቅሁ! ወዮ! ምነው እርሱ (ሞት) ፍጹም ፍጻሜ በሆነ (ለሕይወቴ) (ዳግመኛም ባልተቀሰቀስኩ)! ገንዘቤ ምንም አልጠቀመኝም። ሥልጣኔ (ሁሉ) (ኃይሌ፣ ማስረጃዬ፣ ያለኝ ሁሉ) ከእኔ ተለይቶ ጠፋ!..› (አላሁ ተዓላ በጀሀነም ላይ የተመደቡትን መላእክት እንዲህ ይላል፦) ‹ያዙት፤ እሰሩትም (እጆቹን ከአንገቱ ጋር)!.. ከዚያም ጀሒም ውስጥ (የጀሀነም እጅግ ብርቱ የቅጣት ስፍራ) ጣሉት! ከዚያም ርዝመቷ ሰባ ክንድ በሆነች ሰንሰለት ውስጥ (እንደገና) አስገቡት!.. ምክንያቱም እርሱ በላቀው በአላሁ ተዓላ አያምንም ነበር። ድሃን ማብላትን (ራሱ ማብላቱ ቀርቶ ሌሎችንም) አያበረታታም ነበር። ስለዚህ ዛሬ በዚህ ምንም ዘመድ (የሚያዝንለት ወዳጅም) የለውም። ከጊስሊን (ከጀሀነም ሰዎች ከደም ጋር የተቀላቀለ መግል) በስተቀር ምግብም የለውም፤ እርሱን (አውቀው) ስሕተት ከሚሠሩት (ከከሓዲዎች) በስተቀር ማንም አይበላውም…›»8 ሰይዲና ዑመር ክቡር ነብያችን የሚያነቡትን በአድናቆት ያዳምጡ ነበር። በሕይወታቸው እንዲህ ያሉ ያማሩ ቃላትን ሰምተው አያውቁም ነበር። ይህን ራሳቸው በኋላ እንዲህ ብለው ተርከዋል፦ «የሰማኋቸው የእነዚህ ቃላት አንደበተ ርቱዕነት፣ ቅንብርና ጥቅልነት አስደንቆኝ ነበር። ለራሴም፦ ‹እምላለሁ፤ ይህ ቁረይሾች እንደሚሉት ገጣሚ መሆን አለበት!› አልኩ።» በዚህ ጊዜ ነብያችን ክቡር አንቀጾችን ማንበባቸውን ቀጠሉ፦ «በምታዩትና በማታዩት እምላለሁ፤ ያለ ጥርጥር እርሱ (ቁርኣን ከሪም) በአላሁ ተዓላ ዘንድ እጅግ የተከበረ መልዕክተኛ (ከጌታው) ያመጣው ቃል ነው። የገጣሚ ቃል አይደለም። እናንተ ምንኛ ጥቂት ታምናላችሁ!..»9 ሰይዲና ዑመር እንዲህ ብለው ተረኩ፦ «እንደገና ለራሴ፦ ‹ይህ ጠንቋይ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም በውስጤ ያሰብኩትን ተረድቷል!..› አልኩ።» ረሱሉላህ ሱራውን ማንበባቸውን ቀጠሉ፦ «የጠንቋይ ቃልም አይደለም። እናንተ ምንኛ ጥቂት ታስተውላላችሁ!.. እርሱ (ቁርኣን ከሪም) ከዓለማት ጌታ (ለሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም በጂብሪል ዐለይሂ ሰላም አማካይነት) የተወረደ ነው። እርሱ (ነብዩ) ያልተናገርናቸውን አንዳንድ ቃላት በእኛ ላይ ከራሱ ቢቀጥፍ ኖሮ በእርግጥ በኃይል በያዝነው፣ ከዚያም ያለ ጥርጥር የሕይወት ጅማቱን (የአንገት ደም ሥሩን) በቆረጥንና ባጠፋነው ነበር!

«(አጎቴ ሆይ!) እኔ የምደሰተው አንተ ስታምንና ውድ ሰውነትህን ከጀሀነም እሳት ስታድን ብቻ ነው» ሐዲስ ሸሪፍ

ከእናንተም ማንም ይህን ሊከለክል ባልቻለ ነበር! በእርግጥ እርሱ (ቁርኣን ከሪም) ለጥንቁቆቹ ግልጽ ምክር ነው። ከእናንተ መካከል (የሚያረጋግጡት እንዳሉ ሁሉ) የሚያስተባብሉት እንዳሉ በእርግጥ እናውቃለን። በእርግጥ እርሱ (ቁርኣን ከሪም) ለከሓዲዎች (በአኺራ ላረጋገጡት የሚሰጡትን ጸጋዎች ለሚያዩት) (የማይቀር) ቁጭትና ጸጸት ነው። በእርግጥ እርሱ (ቁርኣን ከሪም) እርግጠኛው እውነት ነው (ሐቁል የቂን) (በእርግጥ የእርግጠኛ ዕውቀት እውነታ ነው፤ ከእርግጠኛ ዕውቀት የተገኘ ነው)። ስለዚህ የላቀውን የጌታህን ስም አወድስ።»10

ሰይዲና ዑመር፦ «ረሱሉላህ ሱራውን በሙሉ ካነበቡ በኋላ በልቤ ወደ እስልምና ዝንባሌ ተፈጠረ» አሉ። ሰይዲና ሐምዛ ሙስሊም ከሆኑ ከሦስት ቀን በኋላ አቡ ጀህል አጋሪዎቹን ሰብስቦ እንዲህ አለ፦ «የቁረይሽ ሰዎች ሆይ! ሙሐመድ ጣዖቶቻችንን ሰደበ። ከእኛ በፊት የነበሩት አያቶቻችን በጀሀነም እንደሚቀጡና እኛም ወደዚያ እንደምንሄድ ተናገረ!..

እርሱን ከመግደል ሌላ መፍትሔ የለም!.. እርሱን ለሚገድል ሰው መቶ ቀይ ግመሎችንና ቁጥር የሌለው ወርቅ እሰጣለሁ!..» በቅጽበት ከኸጧብ ልጅ ከዑመር ልብ የእስልምና ዝንባሌ ጠፋ። ዘለው ተነሥተው፦ «ይህን ሥራ ከኸጧብ ልጅ በስተቀር የሚሠራ የለም» አሉ። «በል እንግዲህ የኸጧብ ልጅ! እስኪ እንይህ» እያሉ አጨበጨቡላቸው።

ሰይፋቸውን ታጥቀው መንገድ ጀመሩ። በመንገድ ላይ ኑዐይም ኢብኑ ዐብዱላህን አገኙ። እርሳቸውም፦ «እንዲህ በብርቱ ቁጣ ወዴት ነው፣ ዑመር ሆይ?» ብለው ጠየቁ። ዑመርም፦ «በሕዝቡ መካከል መለያየትን የዘራውን፣ ወንድምን ለወንድሙ ጠላት ያደረገውን ሙሐመድን ልገድል እሄዳለሁ» አሉ። ኑዐይም፦ «ዑመር ሆይ! ይህ ከባድ ሥራ ነው። ሶሓቦቻቸው እንደ ቢራቢሮ በዙሪያቸው እየዞሩ ምንም እንዳይደርስባቸው ይጠነቀቁላቸዋል። ወደ እነርሱ መቅረብ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ብትገድላቸው እንኳ ከዐብዱልሙጠሊብ ልጆች እጅ አታመልጥም» አሉ።

ሰይዲና ዑመር በዚህ ቃል እጅግ ተቆጡ። «ወይስ አንተም ከእነርሱ ነህ? በመጀመሪያ ጉዳይህን ልጨርስ!» ብለው ሰይፋቸውን ያዙ። «ዑመር ሆይ! ተወኝ! ይልቅ ወደ እህትህ ወደ ፋጢማና ወደ ባሏ ወደ ሰዒድ ኢብኑ ዘይድ ሂድ፤ እነርሱም ሙስሊም ሆነዋል» አሉ ኑዐይም። ሰይዲና ዑመር ይህን ቃል አላመኑም። «ካላመንክ ሂደህ ጠይቅ! ትረዳለህ» አሉ።

ሰይዲና ዑመር በዚህ ሐሳባቸው ቢሳካላቸው ኖሮ የሃይማኖት ልዩነት ይጠፋ ነበር፤ ነገር ግን የዓረቦች ልማድ የሆነው የደም በቀል ይነሣ ነበር፤ ቁረይሽም ለሁለት ተከፍሎ ማብቂያ በሌላቸው ግጭቶች ውስጥ ይገባ ነበር። በዚህም ዑመር ኢብኑል ኸጧብ ብቻ ሳይሆኑ የኸጧብ ልጆች ሁሉ ይገደሉ ነበር። ነገር ግን ዑመር ኢብኑል ኸጧብ እጅግ ብርቱ፣ ደፋርና ቁጡ ስለነበሩ እነዚህን ማሰብ አልቻሉም። ስለ እህታቸው ተጨንቀው ወዲያውኑ ወደ ቤታቸው ሄዱ።

በዚያን ጊዜ ሱረቱ ጣሀ ገና ወርዶ ነበር። ሰዒድና ፋጢማ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) አስጽፈውት ሰይዲና ኸባብ ኢብኑል አረት የሚባሉትን ሶሓቢይ ወደ ቤታቸው አምጥተው ያነቡት ነበር። ሰይዲና ዑመር በበሩ ላይ ድምፃቸውን ሰሙ። በሩን በጣም በኃይል አንኳኩ። በወገባቸው ሰይፍ ታጥቀው ተቆጥተው ባዩአቸው ጊዜ ጽሑፉን ደበቁ፤ ሰይዲና ኸባብንም ሰወሩ። ከዚያም በሩን ከፈቱ። ወደ ውስጥ በገቡ ጊዜ፦ «ምን እያነበባችሁ ነበር?» አሉ። «ምንም» አሉ።

ቁጣቸው ጨምሮ፦ «የሰማሁት እውነት ኖሯል፤ እናንተም በድግምቱ ተታለላችሁ!» ብለው ጮኹ። ሰይዲና ሰዒድን ከአንገትጌያቸው ይዘው መሬት ላይ ጣሏቸው። እህታቸው ባለቤታቸውን ለማዳን ሲሞክሩ በቁጣ ፊታቸውን በጥፊ መቷቸው። ከፊታቸው ደም መፍሰስ መጀመሩን ባዩ ጊዜ ለእህታቸው አዘኑ። ፋጢማ ተጎድተው በደም ተለውሰው ነበር። ነገር ግን የኢማን ኃይል አንቀሳቀሳቸው፤ ወደ አላሁ ተዓላ ተጠግተው እንዲህ አሉ፦ «ዑመር ሆይ! ለምን አላህን አታፍርም? በአንቀጾችና በተአምራት በላካቸው ነብዩ ለምን አታምንም? እነሆ እኔና ባለቤቴ በእስልምና ተከብረናል። ራሳችንን ብትቆርጥ እንኳ ከዚህ አንመለስም።» የሸሃዳንም ቃል አነበቡ።

ሰይዲና ዑመር በዚህ የእህታቸው ኢማን ፊት ድንገት ለሰለሱ፤ መሬት ላይም ተቀመጡ። በለስላሳ ድምፅ፦ «እስኪ ያንን የምታነቡትን መጽሐፍ አውጡልኝ» አሉ። ፋጢማ፦ «ንጹሕ እስካልሆንክ ድረስ አልሰጥህም» አሉ። ሰይዲና ዑመር ጉሱል አደረጉ።

ከዚያም ፋጢማ የቁርኣን ከሪሙን ገጽ አመጡ። ሰይዲና ዑመር በደንብ ያነቡ ነበር። ሱረቱ ጣሀን ማንበብ ጀመሩ። የቁርኣን ከሪም አንደበተ ርቱዕነት፣ ውበት፣ ትርጉሞቹና የላቁ ባሕርያቱ ልባቸውን ቀስ በቀስ አለሰለሱት። ትርጓሜው «በሰማያትና በምድር ያለው፣ በሁለቱም መካከል ያለውና ከአፈር በታች (በሰባቱ ንብርብሮች) ያለው ሁሉ የእርሱ ነው»11 የሆነውን ክቡር አንቀጽ ባነበቡ ጊዜ በጥልቅ ሐሳብ ተዋጡ። «ፋጢማ ሆይ! እነዚህ ማብቂያ የሌላቸው ፍጥረታት በሙሉ የምታመልኩት የአላህ ናቸውን?» አሉ። እህታቸውም፦ «አዎ፣ እንዴታ! ጥርጥር አለበት እንዴ?» ብለው መለሱ። መደነቃቸው እየጨመረ፦ «ፋጢማ ሆይ! እኛ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስና ከድንጋይ የተቀረጹና ያጌጡ አንድ ሺህ አምስት መቶ ያህል ሐውልቶች አሉን። ከእነርሱ አንዱም በምድር ላይ ምንም ነገር የለውም» አሉ። ጥቂት ቀጥለው አንብበው ትርጓሜው «ከአላሁ ተዓላ በስተቀር ሊመለክና ሊሰገድለት የሚገባ እውነተኛ አምላክ፣ መዕቡድ የለም። ያማሩ ስሞች የእርሱ ናቸው»12 የሆነውን ክቡር አንቀጽ አሰቡበት። «በእርግጥም ምንኛ እውነት ነው!» አሉ። ኸባብ ይህን በሰሙ ጊዜ ከተደበቁበት ዘለው ወጥተው ተክቢር አሉ። ከዚያም እንዲህ አሉ፦ «ዑመር ሆይ! የምሥራች! ረሱሉላህ አላሁ ተዓላን፦ ‹ጌታዬ ሆይ! ይህን ሃይማኖት በአቡ ጀህል ወይም በዑመር አጠንክር!› ብለው ለምነው ነበር። እነሆ ይህ ዕድል፣ ይህ ደስታ ለአንተ ተሰጠ።»

ይህ ክቡር አንቀጽና ይህ ዱዓ በሰይዲና ዑመር ልብ የነበረውን ጠላትነት አጠፋው፤ ጠርጎም አስወገደው። ወዲያውኑ፦ «ረሱሉላህ የት ናቸው?» አሉ። ልባቸው ቀድሞውንም ከረሱሉላህ ጋር ተቆራኝቶ ነበር። በዚያ ቀን ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በሰይዲና አርቀም ቤት ሶሓቦቻቸውን ይመክሩ ነበር። ሶሓቦች በዚያ ተሰብስበው ነበር፤ ብሩህ ፊታቸውን በማየትና ጣፋጭና ልብ የሚነኩ ቃላቸውን በመስማት ልባቸውን ያጸዱ ነበር፤ ማብቂያ በሌለው ደስታ፣ ሐሴትና ፌሽታ ውስጥ ከሁኔታ ወደ ሁኔታ እየተሸጋገሩ ነፍሳቸውን ያረኩ ነበር።

ሰይዲና ዑመር ሲመጡ ከአርቀም ቤት ታዩ። ሰይፋቸውም ከእርሳቸው ጋር ነበር። ግርማ ሞገስ ያላቸውና ብርቱ ስለነበሩ ሶሓቦች ረሱሉላህን ከበቡ። ሰይዲና ሐምዛ፦ «ዑመርን የሚያስፈራ ምን አለ? በመልካም ሐሳብ መጥቶ ከሆነ እንኳን ደኅና መጣ። ካልሆነ ግን ሰይፉን ሳይመዝዝ ራሱን እቆርጠዋለሁ!» ሲሉ ረሱሉላህ፦ «መንገድ ልቀቁለት፤ ይግባ!» አሉ።

«የጠንቋይ ቃልም አይደለም። እናንተ ምንኛ ጥቂት ታስተውላላችሁ!.. እርሱ (ቁርኣን ከሪም) ከዓለማት ጌታ (ለሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም በጂብሪል ዐለይሂ ሰላም አማካይነት) የተወረደ ነው» ሓቃ: 42–43

ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም ሰይዲና ዑመር ለማመን እንደመጡና በመንገድ ላይ እንዳሉ አስቀድመው አሳውቀው ነበር። ክቡር ረሱሉላህ ሰይዲና ዑመርን በፈገግታ ተቀብለው፦ «ተዉት፤ ከአጠገቡ ራቁ» አሉ። ሰይዲና ዑመር በረሱሉላህ ፊት ተንበረከኩ። ረሱሉላህ ሰይዲና ዑመርን ከክንዳቸው ይዘው፦ «ዑመር ሆይ! ወደ ኢማን ና!» አሉ። እርሳቸውም በንጹሕ ልብ የሸሃዳን ቃል ተናገሩ። ሶሓቦች ከደስታቸው የተነሣ የተክቢር ድምፃቸውን ወደ ሰማይ አስተጋቡ።

ሰይዲና ዑመር ሙስሊም ከሆኑ በኋላ ሁኔታቸውን እንዲህ ብለው ተረኩ፦

«ሙስሊም በሆንኩ ጊዜ ሶሓቦች ከአጋሪዎቹ ይደበቁ፣ ዒባዳቸውንም በምሥጢር ያደርጉ ነበር። በዚህ ሁኔታ እጅግ አዘንኩ፤ እንዲህም ብዬ ጠየቅሁ፦ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኛ በእውነት ላይ አይደለንምን?› ክቡር ነብያችንም፦ ‹አዎ። ሕልውናዬ በቁጥጥሩ ሥር በሆነው በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ሙታንም ሆናችሁ ሕያዋን በእርግጥ በእውነት ላይ ናችሁ› አሉ።

በዚህም፦ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኛ በእውነት ላይ፣ አጋሪዎቹ ደግሞ በሐሰት መንገድ ላይ ከሆኑ ታዲያ ሃይማኖታችንን ለምን እንደብቃለን? በአላህ እምላለሁ፤ እኛ የእስልምናን ሃይማኖት በክህደት ፊት በግልጽ ለማሳወቅ ይበልጥ መብት ያለንና የተገባን ነን። የአላሁ ተዓላ ሃይማኖት በመካ ያለ ጥርጥር ያሸንፋል። ወገናችን በፍትሕ ቢይዙን መልካም ነው፤ ወሰን ማለፍ ከፈለጉ ግን ከእነርሱ ጋር እንዋጋለን› አልኩ። ክቡር ረሱሉላህም፦ ‹እኛ በቁጥር እጅግ ጥቂት ነን!› አሉ።

እኔም፦ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እርስዎን እውነተኛ ነብይ አድርጎ በላከው በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ያለ ማመንታትና ያለ ፍርሃት ተቀምጬ እስልምናን ያላስረዳሁበት የአጋሪዎች ሸንጎ አይቀርም። ከእንግዲህ በግልጽ እንውጣ!› አልኩ። በተቀበሉ ጊዜ በሁለት ሰልፍ ወደ ውጭ ወጥተን ወደ ሐረም ሸሪፍ ተጓዝን። ከሰልፎቹ የአንዱ ፊት ላይ ሐምዛ፣ የሌላኛው ፊት ላይ ደግሞ እኔ ነበርኩ። መሬትን እንደ ዱቄት የምንፈጭ ይመስል በጠንካራ እርምጃና በግርማ ሞገስ በተሞላ አረማመድ ወደ መስጂደል ሐራም ገባን። የቁረይሽ አጋሪዎች አንዴ እኔን፣ አንዴ ደግሞ ሐምዛን ይመለከቱ ነበር። ምናልባት በሕይወታቸው አይተውት በማያውቁት ተስፋ መቁረጥ፣ ሐዘንና ትካዜ ተመቱ።» ሰይዲና ዑመር እንዲህ በመምጣታቸው አቡ ጀህል ወደ ፊት ወጥቶ፦ «ዑመር ሆይ! ይህ ምንድን ነው?» ብሎ ጠየቀ። ሰይዲና ዑመር ምንም ግድ ሳይሰጣቸው፦ «አሽሀዱ አን ላ ኢላሀ ኢለላህ ወአሽሀዱ አነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ» አሉ። አቡ ጀህል የሚለውን አጣ። ደርቆ ቀረ። ሰይዲና ዑመር ወደዚያ የአጋሪዎች ስብስብ ዞረው እንዲህ አሉ፦ «የቁረይሽ ሰዎች ሆይ!… የሚያውቀኝ ያውቀኛል! የማያውቀኝ ደግሞ እኔ የኸጧብ ልጅ ዑመር መሆኔን ይወቅ… ሚስቱን መበለት፣ ልጆቹን ወላጅ አልባ ሊያደርግ የሚፈልግ ከስፍራው ይንቀሳቀስ! የተንቀሳቀሰውን በሰይፌ ቆራርጬ መሬት ላይ እዘርረዋለሁ!…» በዚህም የቁረይሽ አጋሪዎች በቅጽበት ተበትነው ከዚያ ራቁ። ረሱሉላህና የላቁ ሶሓቦቻቸው ሰልፍ ሠርተው በታላቅ ድምፅ ተክቢር አሉ። የመካ ሰማያት በሶሓቦች፦ «አላሁ አክበር!… አላሁ አክበር!…» ጩኸት አስተጋቡ። ለመጀመሪያ ጊዜ በሐረም ሸሪፍ በግልጽ ሶላት ተሰገደ።13 ሰይዲና ዑመር ሙስሊም በሆኑ ጊዜ የሱረቱ አል-አንፋል ስልሳ አራተኛው ክቡር አንቀጽ ወረደ። በትርጓሜ፦ «ነብዬ ሆይ! ረዳት ሆኖ አላሁ ተዓላና ፈለግህን የሚከተሉ ምእመናን ይበቁሃል።» በጥርጣሬ ውስጥ ይዋልሉ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ሰይዲና ዑመር ሙስሊም መሆናቸውን ባዩ ጊዜ እስልምናን መረጡ፤ ሶሓቦች የመሆንንም ክብር አገኙ።

ከእንግዲህ የሙስሊሞች ቁጥር ቀን በቀን እንደ ናዳ ማደግ ጀመረ።

«ጌታዬ ሆይ! ይህን ሃይማኖት በአቡ ጀህል ወይም በዑመር አጠንክር!» ሐዲስ ሸሪፍ

በሥራው ሁሉ የረሕማንን ስም ያወሱ ነበር፣ ያ የቸርነት ምንጭ፣ ለውዳሴና ለምስጋና ማዕድን ነበሩ ነብዩ፣ ያ የቸርነት ምንጭ። የመለኮታዊ ችሮታዎች መገለጫ፣ የዕውቀትና የትዕግሥት ምንጭ ነበሩ፣ ነፍሳቸው በመልካም ስነ ምግባር ተሞልታ ነበር፣ ያ የቸርነት ምንጭ። ለአላህ ብለው ለሐቁ ፍጥረታት ገርነትንና ትሕትናን አሳዩ፣ ለሰዎች ሁሉ ችሮታንና በጎነትን ያደርጉ ነበር፣ ያ የቸርነት ምንጭ።

የካዕባ አል-ሙዐዘማ የቀድሞ ገጽታ መካ አል-ሙከረማ

ወደ ሐበሻ የተደረገው ሁለተኛው ሂጅራ

ሶሓቦች (ዐለይሂሙ ሪድዋን) ወደ መካ በተመለሱ ጊዜ አጋሪዎቹ እንደገና ያንገላቷቸውና ያሰቃዩአቸው ጀመር። ግፋቸው እየበዛ ሄደ። ማንኛውንም ዓይነት ስቃይ ያለ ምንም ማመንታት ይፈጽሙ ነበር። አንድ ቀን ሰይዲና ዑስማን እንዲህ አሉ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ሐበሻን ጥሩ የንግድ ስፍራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የአንድ ወር ንግድ ብዙ ትርፍ ያስገኛል። አላሁ ተዓላ የሂጅራን ስፍራ እስኪወስን ድረስ ለሙስሊሞች ከዚህ የተሻለ ስፍራ ሊኖር አይችልም። ቢያንስ ምእመናን ከቁረይሽ ግፍ ይድናሉ። ነጃሺ ብዙ ቸርነትና ብዙ በጎነት አድርገውልናል።» በዚህ ጊዜ ክቡር ነብያችን፦ «በአላሁ ተዓላ ስም እንድትጠበቁ እንደገና ወደ ሐበሻ ተመለሱ» አሉ። ሰይዲና ዑስማን፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እርስዎ ወደዚያ ቢሄዱ ምናልባት እነርሱ ሙስሊም ይሆኑ ነበር። የመጽሐፉ ባለቤቶች ስለሆኑ ቶሎ ወደ እስልምና ይመጣሉ፤ እርዳታቸውንም አይነፍጉም» ባሉ ጊዜ ውዱ ነብያችን፦ «እኔ ዕረፍትንና ምቾትን እንድፈልግ አልታዘዝኩም። በሂጅራ ጉዳይ የአላሁ ተዓላን የተባረከ ትእዛዝ እጠብቃለሁ። እንደታዘዝኩት እንዲሁ አደርጋለሁ» አሉ።

በቢዕሳ ስድስተኛው ዓመት፣ በአንድ ዘገባ መሠረት ከሶሓቦች (ረዲየላሁ ዐንሁም) 83 ወንዶችና 18 ሴቶች፣ መቶ አንድ ሰዎች ያሉበት ቅፍለት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሐበሻ ጉዞ ጀመረ። በዚህ ቅፍለት ራስ ላይ ሰይዲና ጀዕፈር ኢብኑ አቢ ጧሊብ ተሹመው ነበር። በሰላም ወደ ነጃሺ አገር ደረሱ። በሐበሻ ያጋጠማቸውን ሰይደቲና ኡሙ ሰለማ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ ብለው ተረኩ፦ «ሐበሻ በደረስን ጊዜ በዚያ እጅግ መልካም ጎረቤት አገኘን። ያ ጎረቤት ንጉሥ ነጃሺ ነበሩ። ፍላጎታችንን ሁሉ ፈጸሙልን። የሃይማኖታችንን ትእዛዛት እንደፈለግነው መፈጸም እንችል ነበር። አላሁ ተዓላን በነጻነት እናመልክ ነበር፤ ምንም ስቃይም አልደረሰብንም። አንድም ክፉ ቃል አልሰማንም።» የመካ አጋሪዎች ይህን ሁኔታ በሰሙ ጊዜ ወደ ሐበሻው ንጉሥ ሁለት ልዑካንን ለመላክ ወሰኑ። ለነጃሺ እጅግ ውድ ከሆኑ ዕቃዎች በተጨማሪ እጅግ ከሚወዱት ከመካ ቆዳ የተዘጋጁ ስጦታዎች ተዘጋጁ። ለካህናቱና ለመንግሥቱ ባለሥልጣናትም ስጦታዎች ታሰቡ። ለዚህ ተግባር ዐብዱላህ ኢብኑ አቢ ረቢዓና ዐምር ኢብኑል ዓስ ተመደቡ። ለእነዚህ ሁለት ልዑካን በነጃሺ ፊት ምን እንደሚናገሩ ተነገራቸው። እንዲህም ተባሉ፦ «ከንጉሡ ጋር ከመነጋገራችሁ በፊት ለፓትርያርኮቹና ለአዛዦቹ ለእያንዳንዳቸው ስጦታቸውን ስጡ። ከዚያም የነጃሺን አቅርቡ። ይህን ካደረጋችሁ በኋላ በዚያ ያሉት ሙስሊሞች ለእናንተ እንዲሰጡ ጠይቁ። ነጃሺ ከሙስሊሞቹ ጋር እንዲገናኝና እንዲነጋገር ዕድል አትስጡት።»14 ልዑካኑ ሐበሻ ደረሱ። የመንግሥቱን ባለሥልጣናት ጎብኝተው ስጦታዎቻቸውን ከሰጡ በኋላ ለእያንዳንዳቸው እንዲህ አሉ፦ «በመካከላችን አንዳንድ ሰዎች ተነሡ። እኛም እናንተም የማናውቀውን አዲስ ሃይማኖት ፈጠሩ። ወደዚህ የመጡትን እነዚህን ሰዎች ወደ አገራቸው ልንመልሳቸው እንፈልጋለን። ከንጉሣችሁ ጋር ስለ እነርሱ በምትነጋገሩበት ጊዜ ከእነርሱ ጋር ሳይነጋገሩ ለእኛ እንዲሰጡ ጥረት አድርጉ። ከእነዚህ ሰዎች ጋር በሚገባ መያዝ የሚችሉት የገዛ ወላጆቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ናቸው። እነርሱ በሚገባ ያውቋቸዋል።»15 ፓትርያርኮቹ ይህን ሐሳብ ተቀበሉ። ከዚያም የመካ ልዑካን የነጃሺን ስጦታዎች አቀረቡ። ነጃሺ ስጦታዎቹን ተቀብለው ወደ እርሳቸው ጋብዘው ለጥቂት ጊዜ አነጋገሯቸው።

«በአላሁ ተዓላ ስም እንድትጠበቁ እንደገና ወደ ሐበሻ ተመለሱ» ሐዲስ ሸሪፍ

ልዑካኑ ነጃሺን እንዲህ አሉ፦ «ንጉሥ ሆይ! ከእኛ መካከል አንዳንድ ሰዎች ወደ አገርዎ ተጠግተዋል። እነዚህ የመጡት የገዛ ሕዝባቸውን ሃይማኖት እንደተዉ ሁሉ ወደ እርስዎ ሃይማኖትም አልገቡም። እንደ ራሳቸው አስተሳሰብ የፈጠሩት ሃይማኖት አላቸው። እኛም እርስዎም ይህን ሃይማኖት አናውቅም። እነርሱ ከተወለዱበት ሕዝብ መሪዎች ወደ እርስዎ ላኩን። እነዚህ መሪዎች ወደ አገርዎ የተጠጉት ሰዎች አባቶችና የቅርብ ዘመዶች ናቸው። ፍላጎታቸው የመጡት እንዲመለሱ ነው። ምክንያቱም ሁኔታቸውን በቅርበት ያውቃሉ። እነዚህ ሰዎች በገዛ ሃይማኖታቸው ውስጥ የማይቀበሉትን በተሻለ ያውቃሉ…» ዐምር ኢብኑል ዓስም ሆነ ዐብዱላህ ኢብኑ አቢ ረቢዓ ከሁሉ አብልጠው የሚመኙት ነጃሺ እነዚህን ቃላት አዳምጠው እንደ ፍላጎታቸው እንዲያደርጉ ነበር። ልዑካኑ እነዚህን ቃላት ከተናገሩ በኋላ የነጃሺ ፓትርያርኮች ቃል ተቀብለው እንዲህ አሉ፦ «እነዚህ ፍጹም ትክክል ናቸው። ሕዝባቸው ከእነርሱ ጋር በተሻለ ሊያዝ ይችላል፤ ምን እንደሚቀበሉና እንደማይቀበሉም በተሻለ ሊመዝን ይችላል። ስለዚህ እነዚህን ሰዎች አሳልፈው ይስጡ፤ እነርሱም ወደ አገራቸውና ወደ ሕዝባቸው ይመልሷቸው።» ነጃሺ በዚህ እጅግ ተቆጥተው እንዲህ አሉ፦ «በአላህ እምላለሁ፤ አይሆንም! እነዚህን ሰዎች አሳልፌ አልሰጥም። ወደ እኔ የተጠጉትንና ወደ አገሬ የመጡትን ሰዎች ልከዳ አልችልም። እነርሱ ከሌሎች መርጠውኝ ወደ አገሬ መጥተዋል። ስለዚህ የመጡትን ሙሃጂሮች ወደ ቤተ መንግሥቴ ጋብዤ እነዚህ ሰዎች ለተናገሩት ቃል ምን እንደሚሉ እጠይቃቸዋለሁ፤ መልሳቸውንም አዳምጣለሁ። ሙሃጂሮቹ እነዚህ እንደሚሉት ከሆኑ ለመጡት ሰጥቼ ወደ ሕዝባቸው እመልሳቸዋለሁ። ካልሆኑ ግን በአገሬ እስካሉ ድረስ እጠብቃቸዋለሁ፤ በጎ አደርግላቸዋለሁም።» ነጃሺ ከዚህ ቀደም ሰማያዊ መጻሕፍትን አጥንተው ነበር። የሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም የሚመጡበት ጊዜ መቅረቡን፣ ወገናቸው ውሸታም ብለው እንደማያምኑባቸውና ከመካ እንደሚያስወጧቸው ያውቁ ነበር። ነጃሺ የመካ ልዑካንን፦ «የሚያምኑት በማን ነው?» ብለው ጠየቁ። እነርሱም፦ «በሙሐመድ» አሉ። ነጃሺ ይህን ስም በሰሙ ጊዜ ነብይ መሆናቸውን ተረዱ፤ ነገር ግን አላሳወቁም። እንደገና የመጡትን፦ «ሃይማኖቱና መንገዱ ምንድን ነው? ወደ ምንስ ይጠራል?» ብለው ጠየቁ። ዐምርም፦ «መንገድ የለውም» አለ። ነጃሺም፦ «መንገዳቸውንና ሃይማኖታቸውን ሳላውቅ ወደ እኔ የተጠጉትን ቡድን እንዴት አሳልፌ እሰጣለሁ? ሸንጎ እንሰብስብ። እነርሱንም እናምጣ። ከእናንተ ጋር ፊት ለፊት እናገናኛቸው። የሁላችሁም ሁኔታ ይታወቅ። የእነርሱንም ሃይማኖት ልወቅ» አሉ። ሙስሊሞቹን ወደ ቤተ መንግሥቱ ጋበዟቸው። ሙስሊሞቹ በመጀመሪያ በመካከላቸው ተመካከሩ፤ «የሐበሻን ንጉሥ የሚያስደስትና ከባሕርያቸው ጋር የሚስማማ ምን እንበል?» ብለው ተነጋገሩ። ሰይዲና ጀዕፈር፦ «በአላህ እምላለሁ፤ በዚህ ጉዳይ የምናውቀው ነብያችን ያዘዙን ብቻ ነው። ውጤቱ ምንም ቢሆን እንቀበላለን» አሉ። ሁሉም ተስማሙ፤ ሰይዲና ጀዕፈር ብቻ እንዲናገሩ ከተስማሙ በኋላ ወደ ነጃሺ ዘንድ መጡ። ንጉሥ ነጃሺም ሊቃውንቶቻቸውን ሰብስበው ነበር። ታላቅ ሸንጎ ተካሄደ። ከዚያም ሙሃጂሮቹን አስገቡ። ሙስሊሞቹ በገቡ ጊዜ ሰላምታ ሰጡ።

ነገር ግን ሱጁድ አላደረጉም። ነጃሺ፦ «ለምን ሱጁድ አላደረጋችሁም?» ብለው በጠየቋቸው ጊዜ እንዲህ አሉ፦ «እኛ ከአላሁ ተዓላ በስተቀር ለማንም ሱጁድ አናደርግም። ክቡር ነብያችን ከአላሁ ተዓላ በስተቀር ለሌላ ሱጁድ እንዳናደርግ ከልክለውናል፤ ‹ሱጁድ ለአላሁ ተዓላ ብቻ የተገባ ነው› ብለዋል።» ነጃሺ ሙሃጂሮቹን እንዲህ አሉ፦ «ወደ ፊቴ የመጣችሁ ቡድን ሆይ! ንገሩኝ። ወደ አገሬ ለምን መጣችሁ? ሁኔታችሁ ምንድን ነው? ነጋዴዎች አይደላችሁም፤ ምንም ጥያቄም የላችሁም። ያ የተነሣው ነብያችሁ ሁኔታው ምንድን ነው? ከአገራችሁ ሰዎች ወደዚህ የሚመጡት ሰላምታ እንደሚሰጡኝ ለምን ሰላምታ አትሰጡም?»

ጀዕፈር (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አሉ፦ «ንጉሥ ሆይ! በመጀመሪያ ሦስት ነገሮችን እናገራለሁ። እውነት ከተናገርኩ ያረጋግጡልኝ፤ ከዋሸሁ ያስተባብሉኝ። ከሁሉ በፊት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ብቻ እንዲናገር፣ ሌላው ዝም እንዲል ያዝዙ!»

ዐምር ኢብኑል ዓስ፦ «እኔ ልናገር» አለ። ነጃሺ፦ «ጀዕፈር ሆይ፣ በመጀመሪያ አንተ ተናገር» አሉ።

ሰይዲና ጀዕፈር እንዲህ አሉ፦ «የምናገራቸው ሦስት ነገሮች አሉኝ። ይህን ሰው ይጠይቁት፤ እኛ ተይዘን ለአሳዳሪዎቻችን የምንመለስ ባሪያዎች ነንን?» ነጃሺ፦ «ዐምር ሆይ! እነርሱ ባሪያዎች ናቸውን?» ብለው ጠየቁ። ዐምር፦ «አይደሉም! ባሪያዎች አይደሉም፤ ነጻ ሰዎች ናቸው!» አለ። ሰይዲና ጀዕፈር፦ «ምናልባት ያለ አግባብ የአንድን ሰው ደም አፍስሰን ደሙ ለፈሰሰው ሰዎች ተላልፈን የምንሰጥ ነንን?» አሉ። ነጃሺ ዐምርን፦ «እነዚህ ያለ አግባብ አንድን ሰው ገድለዋልን?» ብለው በጠየቁ ጊዜ ዐምር፦ «አይ፣ አንዲት ጠብታ ደም እንኳ አላፈሰሱም» አለ። ሰይዲና ጀዕፈር ነጃሺን፦ «ከሌሎች ንብረት ያለ አግባብ የወሰድነውና ልንመልሰው የሚገባን ገንዘብ አለብንን?» አሉ። ነጃሺም፦ «ዐምር ሆይ! እነዚህ ምስኪኖች የሚከፍሉት እጅግ ብዙ ወርቅ ቢኖርባቸው እንኳ፣ ዕዳ ካለባቸው እኔ እከፍላለሁ፤ ተናገር!» አሉ። ዐምር፦ «አይ፣ አንድ ቂራጥ (የገንዘብ መለኪያ) እንኳ የለባቸውም!» አለ። ነጃሺ፦ «ታዲያ ከእነዚህ ምን ትፈልጋላችሁ?» ብለው በጠየቁ ጊዜ ዐምር፦ «እነርሱና እኛ በአንድ ሃይማኖትና በአንድ መንገድ ላይ ነበርን። እነርሱ ይህን ተዉ። ሙሐመድንና ሃይማኖቱን ተከተሉ» አለ። ነጃሺ ጀዕፈርን፦ «የነበራችሁበትን ሃይማኖት ትታችሁ ሌላውን ለምን ተከተላችሁ? የሕዝባችሁን ሃይማኖት ትታችሁ በእኔም ሃይማኖት ላይ ካልሆናችሁ ታዲያ የምታምኑበት ይህ ሃይማኖት ምን ዓይነት ነው? ስለ እርሱ ልትነግረኝ ትችላለህን?» ብለው ጠየቁ።

ሰይዲና ጀዕፈር እንዲህ አሉ፦ «ንጉሥ ሆይ! እኛ መሃይም ሕዝብ ነበርን። ጣዖታትን እናመልክ ነበር። የሞቱ እንስሳትን ሬሳ እንበላ ነበር፤ ማንኛውንም ክፉ ሥራ እንሠራ ነበር። ከዘመዶቻችን ጋር ያለንን ዝምድና እንቆርጥ ነበር፤ ለጎረቤቶቻችንም መልካም አናደርግም ነበር። ብርቱዎቻችን ደካሞችን ይበድሉ ነበር፤ ርኅራኄ ምን እንደሆነም አያውቁም ነበር። አላሁ ተዓላ እውነተኛነታቸውን፣ ታማኝነታቸውን፣ ጨዋነታቸውንና ንጽሕናቸውን፣ የዘር ሐረጋቸውንም ንጽሕና የምናውቀውን ነብይ ከመካከላችን እስኪልክልን ድረስ በዚህ ሁኔታ ቆየን። ያ ነብይ በአላሁ ተዓላ መኖርና አንድነት እንድናምን፣ እርሱን እንድናመልክና እኛና አባቶቻችን ሲያመልኳቸው የኖሩትን ድንጋዮችና ጣዖታት እንድንተው ጋበዙን። እውነተኞች እንድንሆን፣ በአደራ ላይ ክህደት እንዳንፈጽም፣ የዝምድናን መብቶች እንድንጠብቅ፣ ከጎረቤቶች ጋር በመልካም እንድንኖርና ከኃጢአትና ደም ከማፍሰስ እንድንጠበቅ አዘዙን። ከማንኛውም ብልግና፣ ከውሸት፣ የየቲሞችን ገንዘብ ከመንካትና በጨዋ ሴቶች ላይ የሐሰት ክስ ከማቅረብ ከለከሉን። አላሁ ተዓላን አቻና ተጋሪ ሳናደርግለት እንድናመልከው አዘዙን። እኛም ተቀበልን፤ ከአላሁ ተዓላ ያመጡትን ሁሉ አመንን፤ የሚሉትንም ፈጸምን። አላሁ ተዓላን አመለክን። በእኛ ላይ ሐራም ያደረገውን ሐራም፣ ሐላል ያደረገውን ሐላል ብለን ተቀበልን፤ በዚሁም ሠራን። በዚህ ምክንያት ሕዝባችን ጠላታችን ሆኖ በደለን። ከሃይማኖታችን ሊመልሱን፣ አላሁ ተዓላን ከማምለክ እንድንተውና እንደገና ጣዖታትን እንድናመልክ ልዩ ልዩ ስቃዮችንና መከራዎችን አደረሱብን። በደሉን። ይበልጥ እያጣበቡን ሄዱ። በእኛና በሃይማኖታችን መካከል ገብተው ከሃይማኖታችን ሊለዩን ፈለጉ። እኛም አገራችንንና ቤታችንን ትተን ወደ እርስዎ አገር ተጠጋን። ከሌሎች ይልቅ እርስዎን መረጥን። ጥበቃዎንና ጉርብትናዎን አጥብቀን ተመኘን። በእርስዎ ዘንድ ጭቆናና በደል እንደማይደርስብን ተስፋ እናደርጋለን።» ሰይዲና ጀዕፈር ንግግራቸውን እንዲህ ብለው ቀጠሉ፦ «ሰላምታን በተመለከተ፣ በረሱሉላህ ሰላምታ ሰላም አልንዎ። እርስ በርሳችንም እንዲሁ ሰላምታ እንለዋወጣለን። የጀነት ሰዎች ሰላምታም እንዲሁ መሆኑን ክቡር ነብያችን አሳውቀውናል። ስለዚህ የላቀውን ማንነትዎን እንዲሁ ሰላም አልን። ክቡር ነብያችን ለሰዎች ሱጁድ እንደማይደረግ ስለተናገሩ ከአላሁ ተዓላ በስተቀር ለሌላ ሱጁድ ከማድረግ በአላሁ ተዓላ እንጠበቃለን።» ነጃሺ፦ «አላህ ካወረደው ከፊሉን ታውቃለህን?» ብለው ጠየቁ። ሰይዲና ጀዕፈር፦ «አዎ» ባሉ ጊዜ ነጃሺ፦ «አንብብልኝ» አሉ። ሰይዲና ጀዕፈርም የሱረቱ መርየምን የመጀመሪያ አንቀጾች ማንበብ ጀመሩ። (ከሱረቱ አል-ዐንከቡትና ከሱረቱ አር-ሩም እንዳነበቡም ተዘግቧል።) ነጃሺ አለቀሱ። ከዓይኖቻቸው የፈሰሰው እንባ ጢማቸውን አራሰው። መነኮሳቱም አለቀሱ። ነጃሺና መነኮሳቱ፦ «ጀዕፈር ሆይ! ከዚህ ጣፋጭና ውብ ቃል ጥቂት ጨምረህ አንብብ» አሉ። ሰይዲና ጀዕፈር ከሱረቱ አል-ከህፍ መጀመሪያ ጀምረው አነበቡ፤ በእርሱም በትርጓሜ እንዲህ ይባላል፦ «ምስጋና ለዚያ አላህ ይገባው፤ ለባሪያው (ለሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም) ቀጥተኛውን መጽሐፍ (ቁርኣን ከሪምን) ያወረደ፣ በቃሉ ውስጥ ጠማማነትን፣ በትርጉሙም ውስጥ ተቃርኖን ያላደረገበት (ከማጋነንና ከማጉደል የራቀ)፤ ይህም ከሓዲዎችን ከእርሱ (ከላቀው ዘንድ) በሚመነጭ እጅግ ብርቱ ቅጣት (በጀሀነም) ሊያስጠነቅቅ፣ መልካም ሥራዎችን የሚሠሩትን ምእመናን ለዘላለም በሚኖሩበት መልካም ምንዳ (በጀነት) ሊያበሥር፣ ‹አላሁ ተዓላ ልጅ ያዘ› የሚሉትንም ሊያስጠነቅቅ ነው። እነርሱም (‹አላሁ ተዓላ ልጅ ያዘ› የሚሉት) አባቶቻቸውም በዚህ (በዚያ ቃል) ላይ ምንም ዕውቀት (ወይም ግንዛቤ) የላቸውም። ከአፋቸው የሚወጣው ይህ ቃል (ከባድና) እጅግ አደገኛ ነው። ውሸትን እንጂ ሌላ አይናገሩም። (መልዕክተኛዬ ሆይ!) በዚህ ቁርኣን ከሪም ካላመኑ በእነርሱ ምክንያት በሐዘንና በቁጣ ራስህን ልታጠፋ ነውን? በምድር ላይ ያለውን (ደኖችን፣ ወንዞችን፣ ማዕድናትን፣ እንስሳትንና ዕፅዋትን…) ሰዎችን ከእነርሱ መካከል ሥራው መልካም የሆነው ማን እንደሆነ ልንፈትናቸው ጌጥ አደረግነው…»16

«ሱጁድ ለአላሁ ተዓላ ብቻ የተገባ ነው» ሐዲስ ሸሪፍ

ነጃሺ ራሳቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው እንዲህ አሉ፦ «በአላህ እምላለሁ፤ ይህ ከአንድ ፋኖስ የሚፈልቅ ኑር ነው። ሙሳና ዒሳም (ዐለይሂማ ሰላም) ይዘውት መጥተዋል።» ከዚያም ወደ ቁረይሽ ልዑካን ዘወር ብለው፦ «ሂዱ! በአላህ እምላለሁ፤ እነርሱን ለእናንተ አሳልፌ አልሰጥም፤ ስለ እነርሱም ምንም ክፉ ነገር አላስብም» አሉ። ዐብዱላህ ኢብኑ አቢ ረቢዓና ዐምር ኢብኑል ዓስ ከነጃሺ ፊት ወጡ።17 ዐምር ዐብዱላህን፦ «እምላለሁ፤ በነጃሺ ፊት የእነርሱን አንድ ጥፋት ገልጬ ከሥራቸው እንዲነቀሉ አደርጋለሁ፤ ታያለህ!» አለው። ጓደኛው ግን ዐምርን፦ «እነርሱ ቢቃወሙንም በክፉም በደጉም ዝምድና አለን፤ ይህን አታድርግ» አለው። ዐምርም፦ «ዒሳ ዐለይሂ ሰላምን የአላህ ባሪያ አድርገው እንደሚቆጥሩ ለነጃሺ እነግራለሁ» አለ። በማግሥቱ ወደ ነጃሺ ሄዶ እንዲህ አለ፦ «ንጉሥ ሆይ! እነርሱ ስለ መርየም ልጅ ስለ ዒሳ (ዐለይሂ ሰላም) ከባድ ቃላትን ይናገራሉ። ወደ እነርሱ ሰው ልከው ስለ ዒሳ ዐለይሂ ሰላም ምን እንደሚሉ እስኪ ይጠይቋቸው።» ነጃሺ ስለ ዒሳ ዐለይሂ ሰላም ያላቸውን አመለካከት እንዲጠይቅ ወደ ሙስሊሞቹ ሰው ላኩ። ሙስሊሞቹ እንደገና ተሰበሰቡ፤ እርስ በርሳቸውም፦ «ስለ ዒሳ ዐለይሂ ሰላም ቢጠይቁን ምን መልስ እንሰጣለን?» ተባባሉ። ሰይዲና ጀዕፈር፦ «በአላህ እምላለሁ፤ ስለ ዒሳ ዐለይሂ ሰላም አላሁ ተዓላ ያለውንና ክቡር ነብያችን ያመጡልንን እንናገራለን» አሉ። ወደ ነጃሺ ፊት በቀረቡ ጊዜ ነጃሺ፦ «ስለ መርየም ልጅ ስለ ዒሳ ዐለይሂ ሰላም ምን ትላላችሁ?» ብለው ጠየቁ። ሰይዲና ጀዕፈርም እንዲህ አሉ፦ «እኛ ስለ ዒሳ ዐለይሂ ሰላም ክቡር ነብያችን ከአላሁ ተዓላ አምጥተው ያደረሱልንን እንናገራለን። እርሳቸው የአላሁ ተዓላ ባሪያና መልዕክተኛ መሆናቸውን፣ ዓለምንና ወንዶችን ትተው ራሳቸውን ለሐቅ ተዓላ ለሰጡት ንጽሕት ሴት ለሰይደቲና መርየም አላሁ ተዓላ ያስተላለፈው ቃሉ መሆናቸውን እንቀበላለን። የመርየም ልጅ የዒሳ ሁኔታና ማዕረግ ይኸው ነው። አደም ዐለይሂ ሰላምን ከአፈር እንደፈጠረ ሁሉ ዒሳ ዐለይሂ ሰላምንም ያለ አባት ፈጠረ እንላለን።» በዚህ ጊዜ ነጃሺ እጃቸውን ወደ መሬት ዘርግተው ከመሬት አንዲት የገለባ ዘንግ አነሡና፦ «እምላለሁ፤ የመርየም ልጅ ዒሳም እናንተ ከተናገራችሁት ምንም አይበልጡም። በመካከሉ የዚህችን ገለባ ያህል እንኳ ልዩነት የለም» አሉ።

ነጃሺ ይህን በተናገሩ ጊዜ በዙሪያቸው የነበሩት የመንግሥቱ ባለሥልጣናትና አዛዦች እርስ በርሳቸው ማንሾካሾክና ማጉረምረም ጀመሩ።

ነጃሺ ይህን ባዩ ጊዜ እንዲህ አሏቸው፦ «እምላለሁ፤ እናንተ የፈለጋችሁትን ብትሉ እኔ ስለ እነዚህ ሰዎች መልካም ነገር አስባለሁ።» ከዚያም ወደ ሙስሊም ሙሃጂሮቹ ዘወር ብለው እንዲህ አሉ፦ «ለእናንተና ከእርሳቸው ዘንድ ለመጣችሁት ለዚያ ታላቅ ሰው ደስታዬን እገልጻለሁ! እርሳቸው የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን አመንኩ። ቀድሞውንም በኢንጂል አይተናቸው ነበር። የመርየም ልጅ ዒሳም ያንን መልዕክተኛ አብሥረዋል። በአላህ እምላለሁ፤ እርሳቸው እዚህ ቢኖሩ ኖሮ ሄጄ ጫማቸውን በተሸከምኩ፣ እግራቸውንም ባጠብኩ ነበር! ሂዱ! ማንም እጁን ባላሳረፈበት በአገሬ ክፍል፣ ከማንኛውም ጥቃት ርቃችሁ በሰላምና በጸጥታ ኑሩ። በእናንተ ላይ ክፉ የሚያደርገውን አጠፋዋለሁ። የተራራ ያህል ወርቅ ቢሰጡኝ እንኳ ከእናንተ አንዱን አላሳዝንም!»

ከዚያም ነጃሺ የቁረይሽ ልዑካን ስላመጧቸው ስጦታዎች፦ «እኔ እነዚህን አልፈልግም! ሌሎች የነጠቁኝን ይህን መንግሥቴን አላሁ ተዓላ ሲመልስልኝና ሕዝቡንም ሲያስገዛልኝ ከእኔ ጉቦ አልተቀበለም» ብለው ስጦታዎቻቸውን መለሱላቸው። የቁረይሽ ልዑካን ከነጃሺ ፊት ባዶ እጃቸውን ተመለሱ። ዕድለኛው ነጃሺም እስልምናን መርጠው ሶሓቦችን እጅግ አስደስተው ነበር።18

ሐቁ ዓለምን ፈጠረ
ሐቁ (አላህ) ዓለምን ፈጠረ ለሙሐመድ ፍቅር፣
ጨረቃንና ቀንን ፈጠረ ለሙሐመድ ናፍቆት።
«ሁን!» አለ – ዓለም ሆነ፤ ለውሕና ቀለም ተጻፉ፣
ቃሉ ከዳር እስከ ዳር ተነበበ ለሙሐመድ ክብር።
አውሊያ ሁሉ መጡ፣ በደጃፉ ፊታቸውን አሻሹ፣
የተውሒድን ዚክር አደረጉ ለሙሐመድ ኑር።
ኡወይስ አል-ቀረኒ አገኙ፣ ቢሆንም ደግሞ ጓጉ፤
ስምንቱ ጀነቶች አጌጡ ለሙሐመድ ፍቅር።
በአየር ላይ ወፎች ይበርራሉ፣ ተራሮችና ድንጋዮች ይለመልማሉ፣
ዛፎች ፍሬ ይሰጣሉ ለሙሐመድ ፍቅር።
ኢማን የሌላቸው መጡ፣ ከእርሳቸው ኢማንን ተቀበሉ፣
አምስቱን ወቅት ሶላት ሰገዱ ለሙሐመድ ፍቅር።
መላእክት መጡ፣ ሰፍ ሰፍ ሆነው ቆሙ፣
አምስቱን ወቅት ሶላት ሰገዱ ለሙሐመድ ፍቅር።
ዩኑስ ማን ነውና ያወድሳቸው? የቁርኣን አንቀጽ ያወድሳቸዋል፤
አስታውስ፣ ሶለዋትን አውርድ ለሙሐመድ ፍቅር።

«ለእናንተና ከእርሳቸው ዘንድ ለመጣችሁት ለዚያ ታላቅ ሰው ደስታዬን እገልጻለሁ! እርሳቸው የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን አመንኩ። ቀድሞውንም በኢንጂል አይተናቸው ነበር። የመርየም ልጅ ዒሳም ያንን መልዕክተኛ አብሥረዋል» ነጃሺ አስሐማ