ልጅነታቸው
ለአጥቢ እናት መሰጠታቸው
እናታችን አሚና የሚያበሩትን ሕፃናቸውን በእቅፋቸው በያዙ ጊዜ በባለቤታቸው በዐብዱላህ ሞት የደረሰባቸውን ሐዘን የረሱ ያህል ሆኑ። እናታቸው ክቡር ነብያችንን ዘጠኝ ቀን ካጠቡ በኋላ የአቡ ለሀብ ጃሪያ የነበሩት እመቤት ሱወይባ ለጥቂት ቀናት የአጥቢ እናትነት አገልግሎት ሰጡ። እመቤት ሱወይባ ከዚህ ቀደም ሰይዲና ሐምዛን፣ በኋላም አቡ ሰለማን አጥብተው ነበር። ሐፊዝ ኢብኑል ጀዘሪ እንዲህ ይላሉ፦ «አቡ ለሀብ በሕልም ታየና በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ተጠየቀ። እንዲህ አለ፦ ‹የቀብር ቅጣት እየደረሰብኝ ነው። ነገር ግን በየዓመቱ በረቢዑል አወል ወር በ12ኛው ሌሊት ቅጣቴ ይቀልልኛል። ያን ጊዜ ከሁለት ጣቶቼ መካከል የሚወጣውን ቀዝቃዛ ውኃ እየመጠጥኩ እፎይ እላለሁ። ረሱሉላህ ወደ ዓለም በመጡበት ሌሊት ሱወይባ የምትባለው ጃሪያዬ ይህን የምሥራች አበሠረችኝ። እኔም ከደስታዬ የተነሣ ነጻ አወጣኋትና አጥቢያቸው እንድትሆን አዘዝኳት። ስለዚህ በእነዚያ ሌሊቶች ቅጣቴ ይቀልልኛል።›» በዚያ ዘመን የመካ ሰዎች ልጆቻቸውን ለአጥቢ እናት መስጠት ልማዳቸው ነበር። በአካባቢው ወደሚገኙና አየራቸው ጥሩ፣ ውኃቸውም ጣፋጭ ወደ ሆነ ደጋማ ቦታዎች የሚላኩት ልጆች ለተወሰነ ጊዜ በተሰጡአቸው አጥቢ እናቶች ዘንድ ይቆዩ ነበር። ለዚህም ምክንያቱ የመካ ሞቃት አየር ነበር። ስለዚህ በየዓመቱ ብዙ ሴቶች ወደ መካ ይመጡ ነበር። እያንዳንዳቸውም የሚያጠቡትን አንድ አንድ ልጅ ይዘው ይሄዱ ነበር። ልጆቹን አሳድገው ሲያስረክቡም ብዙ ክፍያና ስጦታዎች ይቀበሉ ነበር። ክቡር ነብያችን በተወለዱበት ዓመትም በደጋማ ቦታዎች ይኖሩ ከነበሩት ከበኑ ሰዕድ ጎሳ ብዙ ሴቶች አጥቢ እናት ለመሆን አስበው ወደ መካ መጡ። እያንዳንዳቸውም የሚያጠቡትን ልጅ አስቀድመው ተቀብለው ነበር። በኑ ሰዕድ ጎሳ በመካ ዙሪያ ከሚገኙ ጎሳዎች መካከል በክብር፣ በልግስና፣ በጀግንነትና በትሕትና እንዲሁም ዓረብኛን አጣርቶ በመናገር እጅግ የታወቀ ነበር። የቁረይሽ ጎሳ ታላላቆች ልጆቻቸውን ይበልጥ ለዚህ ጎሳ መስጠት ይፈልጉ ነበር። በዚያ ዓመት በበኑ ሰዕድ ጎሳ አገር ብርቱ ድርቅና ረሃብ ሰፍኖ ነበር። ከዚህ ጎሳ የሆኑት እመቤት ሐሊማ ይህን ሁኔታ እንዲህ ይተርካሉ፦ «በዚያ ዓመት በሜዳዎች እየዞርኩ ቅጠላ ቅጠል እለቅም ነበር፤ ስላገኘሁትም አላሁ ተዓላን አመሰግን ነበር። አንዳንዴ ሦስት ቀን ቢያልፍም ምንም ነገር ወደ አፌ አላስገባም ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ ልጅ ወለድኩ። በአንድ በኩል ረሃብ፣ በሌላ በኩል የወሊድ ችግር ነበር። ከረሃብ የተነሣ ምድርንና ሰማይን፣ ሌሊትንና ቀንን መለየት የማልችልባቸው ጊዜያትም ነበሩ። አንድ ሌሊት በበረሃ ውስጥ እንቅልፍ ወሰደኝ። በሕልሜ አንድ ሰው ከወተት በነጣ ውኃ ውስጥ ነከረኝና፦ ‹ከዚህ ውኃ ጠጪ› አለኝ። እስክረካ ድረስ ጠጣሁ። ከዚያም ተጨማሪ እንድጠጣ አጥብቆ ገፋፋኝ። ጠጣሁ፣ ደጋግሜ ጠጣሁ፤ ከማር የጣፈጠ ነበር። ‹ሐሊማ ሆይ! ወተትሽ ይብዛ! ታውቂኛለሽን?› ብሎ ጠየቀኝ። እንደማላውቀው በነገርኩት ጊዜ፦ ‹እኔ በችግርሽ ጊዜ ያደረግሽው ሐምድና ሹክር ነኝ። ሐሊማ ሆይ! ወደ መካ ሂጂ። እዚያ አንድ «ኑር» ጓደኛሽ ይሆናል፤ በበረከትም ትሞዪያለሽ። ይህን ሕልም ለማንም አትናገሪ!› አለኝ። ስነቃ ጡቶቼ በወተት ተሞልተው አገኘኋቸው፤ ችግሩና ረሃቡም እንደተለየኝ አየሁ።» በዚያ ዓመት በረሃቡ ምክንያት በክፍያ ልጆችን አጥብተው ችግራቸውን ለማቃለል ከሌሎቹ ዓመታት ይበልጥ ብዙ አጥቢ እናቶች ወደ መካ መጥተው ነበር።
«እኛ የተፈጠርነው ለጨዋታ አይደለም» ሐዲስ ሸሪፍ
የሰዕድ ልጆች በረሃ
ሁሉም የሀብታም ቤተሰቦችን ልጆች ለመውሰድ ይጣደፉ ነበር። የተቻኮሉት ሴቶች እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ልጅ ወስደው ነበር። ክቡር ነብያችን ግን የሙት ልጅ በመሆናቸው ብዙ ክፍያ አናገኝም ብለው በማሰብ ለእርሳቸው ፍላጎት አላሳዩም። ከእነዚህ ሴቶች መካከል በንጽሕናቸው፣ በጨዋነታቸው፣ በሒልማቸው፣ ማለትም በገርነታቸው፣ በዓይናፋርነታቸውና በመልካም ስነ ምግባራቸው የታወቁት እመቤት ሐሊማም ነበሩ። የተቀመጡበት እንስሳ ደካማ ስለነበር ወደ መካ ለመድረስ ዘግይተው ነበር። ነገር ግን ይህ መዘግየት ከፈለጉት በላይ ለማግኘት ምክንያት ሆነላቸው። ከባለቤታቸው ጋር በመካ ሲዘዋወሩ የሀብታም ቤተሰቦች ልጆች ተወስደው እንዳለቁ አዩ። ቢሆንም ባዶ እጃቸውን መመለስ አልፈለጉም። ልጅ ይዘው መመለስ ብቸኛ ምኞታቸው ሆኖ ነበር።
በመጨረሻም አክብሮትን የሚስቡና ፊታቸው እጅግ ተወዳጅ የሆነ አንድ ሰው አገኙ። እርሳቸውም የመካው መሪ ዐብዱልሙጠሊብ ነበሩ። ፍላጎታቸውን ካወቁ በኋላ የልጅ ልጃቸውን እንዲወስዱና በዚህም ታላቅ ዕድልና ደስታ እንደሚያገኙ ነገሯቸው። የዐብዱልሙጠሊብ ፍቅርና ቅርበት ወደ እርሳቸው ሳባቸው። ሐሳባቸውን ወዲያውኑ ተቀበሉ። ከዚያም አዛውንቱ አያት እመቤት ሐሊማን ወደ አሚና ቤት ወሰዷቸው።
እመቤት ሐሊማ እንዲህ ይተርካሉ፦ «ወደ ሕፃኑ በደረስኩ ጊዜ በመጠቅለያ ተጠቅልለው በአረንጓዴ ሐር ምንጣፍ ላይ ጭልጥ ብለው ተኝተው ነበር፤ በዙሪያቸውም የሚስክ መዓዛ ይሰራጭ ነበር። ተደንቄ በቅጽበት በእርሳቸው ፍቅር እንዲህ ተሳብኩ፤ ልቤ ሊቀሰቅሳቸው አልፈቀደም። እጄን በደረታቸው ላይ ባደረግሁ ጊዜ ነቅተው ተመለከቱኝና ፈገግ አሉ። እኔም በዚያ ፈገግታ ተማርኬ ራሴን ሳትኩ። ከዚያም እናታቸው እንዲህ ያለውን ውብና የተባረከ ልጅ አይሰጡኝም ብዬ በማሰብ ፊታቸውን ሸፍኜ ወዲያውኑ ታቀፍኳቸው። ቀኝ ጡቴን ሰጠኋቸው፤ መጥባት ጀመሩ። ግራ ጡቴን ሰጠኋቸው፤ አልጠቡም። ዐብዱልሙጠሊብ ወደ እኔ ዞረው፦ ‹የምሥራች ይሁንልሽ! ከሴቶች መካከል እንዳንቺ ያለ ጸጋ ያገኘ የለም!› አሉ።1
እመቤት አሚና ውድ ሕፃናቸውን ከሰጡኝ በኋላ እንዲህ አሉ፦ ‹ሐሊማ ሆይ! ከሦስት ቀን በፊት፦ «ልጅሽን የምታጠባው ሴት ከበኑ ሰዕድ ጎሳ፣ ከአቡ ዙአይብ ዘር ናት» የሚል ድምፅ ሰማሁ።› በዚህም፦ ‹እኔ ከበኑ ሰዕድ ጎሳ ነኝ፤ የአባቴ ኩንያም አቡ ዙአይብ ነው› ብዬ መለስኩ።»
እመቤት ሐሊማ ደግሞ እንዲህ ብለው ተረኩ፦ «እመቤት አሚና ሌሎች ብዙ ክስተቶችን ነገሩኝ፤ ምክራቸውንም ለገሱኝ። እኔም ወደ መካ ከመምጣቴ በፊት ያየሁትን ሕልምና በመንገድ ላይ ከቀኜም ከግራዬም፦ ‹ሐሊማ ሆይ! የምሥራች ይሁንልሽ! ዓይንን የሚያጥበረብረውንና ዓለማትን የሚያበራውን ያንን ኑር ማጥባት ዕድልሽ ይሆናል› የሚሉ ድምፆች እንደመጡ ነገርኳቸው።»
እመቤት ሐሊማ እንዲህ ይላሉ፦ «ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን ይዤ ከአሚና ቤት ወጣሁ። ወደ ባለቤቴ መጣሁ። እርሳቸውም በእቅፌ ያሉትን የሕፃኑን ፊት ተመልክተው ራሳቸውን ሳቱና፦ ‹ሐሊማ ሆይ! እስከ ዛሬ እንዲህ ያለ ውብ ፊት አይቼ አላውቅም!› አሉ። ወደ እኛ እንደወሰድናቸውም ያገኘነውን በረከት ባዩ ጊዜ፦ ‹ሐሊማ ሆይ! እጅግ የተባረከና ማዕረጉ ከፍ ያለ ልጅ እንደወሰድሽ እወቂ› አሉ። እኔም፦ ‹ወላሂ! የምመኘውም ይህንኑ ነበር፤ የፈለግሁትን አገኘሁ› ብዬ መለስኩ።»
እመቤት ሐሊማና ባለቤታቸው ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን ይዘው ከመካ ከተነሡበት ቅጽበት ጀምሮ በረከታቸውን ማግኘት ጀመሩ። ቀጭኑና በፍጥነት መሄድ የማይችለው አህያቸው እንደ ምርጥ ፈረስ ሆነ። አብሯቸው የመጣው ቅፍለት ቀድሞ ተነሥቶ እጅግ ርቆ የነበረ ቢሆንም ደርሰውበት ወደ ኋላ ተዉት። ወደ በኑ ሰዕድ አገር ከደረሱ በኋላ ታይቶ የማይታወቅ ብልጽግናና በረከት አገኙ። ቀድሞ ጥቂት ወተት ይሰጡ የነበሩት የእንስሶቻቸው ጡቶች ሞልተው ይትረፈረፉ ነበር። ይህን ያዩ ጎረቤቶቻቸው ተደነቁ፤ ይህም ሊያጠቧቸው በወሰዷቸው ሕፃን ምክንያት መሆኑን በግልጽ ተረዱ። ክቡር ነብያችን ከአጥቢ እናታቸው ከእመቤት ሐሊማ የሚጠቡት ቀኝ ጡታቸውን ብቻ ነበር።
«ከአያቶቼ መካከል አንዳቸውም ዝሙት አልፈጸመም። አላሁ ተዓላ እኔን ከንጹሐንና ከመልካም አባቶች፣ ከንጹሐት እናቶች አስገኘኝ» ሐዲስ ሸሪፍ
ግራውን ደግሞ ለወተት ወንድማቸው ይተዉ ነበር። የሁለት ወር ልጅ ሳሉ ዳኹ። በሦስት ወራቸው መቆም ቻሉ፤ በአራት ወራቸው ግድግዳ እየያዙ ይራመዱ ነበር። በአምስት ወራቸው ሄዱ፤ በስድስት ወራቸው በፍጥነት መራመድ ጀመሩ። በሰባት ወራቸው ወደ የትም ይሄዱ ነበር። በስምንት ወራቸው በሚገባ፣ በዘጠኝ ወራቸው ደግሞ እጅግ በግልጽ መናገር ጀመሩ። በአሥር ወራቸው በቀስት መወርወር ጀመሩ።
እመቤት ሐሊማ እንዲህ ብለው ተረኩ፦ «መናገር በጀመሩ ጊዜ የመጀመሪያ ቃላቸው፦ ‹ላ ኢላሀ ኢለላሁ ወላሁ አክበር። ወልሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን› የሚል ነበር። ከዚያች ቀን ጀምሮ የአላሁ ተዓላን ስም ሳያወሱ ወደ ምንም ነገር እጃቸውን አልዘረጉም። በግራ እጃቸው ምንም አይበሉም ነበር። መራመድ በጀመሩ ጊዜ ልጆች ከሚጫወቱበት ስፍራ ይርቁና፦ ‹እኛ የተፈጠርነው ለዚህ አይደለም› ይሏቸው ነበር። በየቀኑ እንደ ፀሐይ ብርሃን ያለ ኑር ይሸፍናቸውና እንደገና ይገለጥ ነበር። ከጨረቃ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ ወደ እርሷ በጠቆሙ ቁጥር ጨረቃ ትንቀሳቀስ ነበር።»
በድርቁ ምክንያት እጅግ ተቸገሩ፤ አንድ ጊዜም የዝናብ ዱዓ ለማድረግ ወጡ። ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን ይዘው ዱዓ አደረጉ፤ ለእርሳቸው ክብር ሲባልም ብዙ ዝናብና በረከት አገኙ። እመቤት ሐሊማ እንዲህ ይተርካሉ፦ «ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ሁለት ዓመት በሞላቸው ጊዜ ጡት አስጣልኳቸው። ከዚያም ለእናታቸው ለመመለስ ከባለቤቴ ጋር ወደ መካ ሄድን። ነገር ግን በእርሳቸው ምክንያት እጅግ ብዙ በረከት አግኝተን ስለነበር ከእርሳቸው መለየትና የተባረከ ፊታቸውን አለማየት እጅግ ከበደን። ሁኔታቸውን ለእናታቸው ነገርኳቸው። እመቤት አሚና፦ ‹ልጄ ታላቅ ክብር አላቸው› አሉ። እኔም፦ ‹ወላሂ! ከእርሳቸው የበለጠ የተባረከ ሰው አይቼ አላውቅም› አልኩ። ከዚያም ብዙ ምክንያቶችን እየደረደርኩ ትንሽ ተጨማሪ ጊዜ ከእኛ ጋር እንዲቆዩ እመቤት አሚናን ለመንኩ። እርሳቸውም ልባችንን አልሰበሩም፤ ከእኛ ጋር እንዲቆዩ ፈቀዱልን። ከእርሳቸው ጋር እንደገና ወደ ጎሳችን ተመለስን። በዚህም ቤታችን በበረከት ተሞላ፤ ሀብታችን፣ ንብረታችንና ዝናችን ጨመረ። ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጸጋዎችን አገኘን።»2
በተባረከ ራሳቸው ላይ ያለ ደመና
እመቤት ሐሊማ እንዲህ ብለው ተረኩ፦ «የዓለም መሪ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አንድ ቀን፦ ‹ቀን ቀን ወንድሞቼን አላያቸውም። ምክንያቱ ምንድን ነው?› ብለው ጠየቁ። እኔም፦ ‹በግ ሊጠብቁ ይሄዳሉ። ወደ ቤት የሚመጡት ማታ ብቻ ነው› አልኩ። በዚህም፦ ‹እኔንም ከእነርሱ ጋር ይላኩኝ። እኔም በግ ልጠብቅ› አሉ። ሰበብ እየፈለግሁ ብዙ ምክንያቶችን አቀረብኩ። በመጨረሻም ልባቸው እንዲደሰት፦ ‹እሺ› አልኩ።
በማግሥቱ የተባረከ ጸጉራቸውን አበጠርኩ፤ ልብሳቸውንም አልብሼ ከወተት ወንድሞቻቸው ጋር ላክኋቸው።
ለጥቂት ቀናት እየሄዱ ተመለሱ። አንድ ቀን የወተት እህታቸው ሸይማ ከሜዳ በመጣች ጊዜ፦ ‹የዓይኔ ብርሃን ልጄ ሙሐመድ የት ናቸው?› ብዬ ጠየቅኋት። ‹በበረሃ ናቸው› አለች። ‹የልቤ ቁራጭ ይህን ሙቀት እንዴት ይችሉታል?› ብዬ ስጠይቃት ሸይማ፦ ‹እማዬ ሆይ! ምንም ጉዳት ፈጽሞ አይደርስባቸውም። ምክንያቱም በተባረከ ራሳቸው ላይ አንድ ደመና ሁልጊዜ አብሯቸው ይንቀሳቀሳል፤ በዚህም ከፀሐይ ሙቀት ይጠበቃሉ› ብላ መለሰች። ‹ምን እያልሽ ነው? የምትናገሪው በእውነት እውነት ነውን?› ባልኳት ጊዜ ማለች። ያን ጊዜ ብቻ ተረጋጋሁ።
የተባረከ ደረታቸው መሰንጠቅ (ሸቅቁ ሶድር)
አንድ ቀን ቀትር ላይ የወተት ወንድማቸው ደምራ እንደገና ወደ እኔ መጥቶ እንዲህ አለ፦ ‹እማዬ! ፈጥነው ይምጡ!… ከቁረይሹ ወንድሜ ጋር በግ እየጠበቅን ነበር። በድንገት አረንጓዴ የለበሱ ሦስት ሰዎች መጡ። ወንድሜን ከአጠገባችን ወስደው ወደ ተራራው ጫፍ ወሰዷቸው። በጀርባቸው አስተኝተው በቢላዋ ሆዳቸውን ሰነጠቁ። ልነግርዎ ስመጣ እዚያው ነበሩ። ወንድሜ በሕይወት መኖራቸውን አለመኖራቸውን አላውቅም።› እመቤት ሐሊማ የቀረውን እንዲህ ተረኩ፦ በዚያች ቅጽበት በድንጋጤ ተዋጥኩ። በፍጥነት ወደዚያ ደረስን፤ አየናቸው። ወዲያውኑ የተባረከ ፊታቸውንና ራሳቸውን ስሜ፦ ‹የዓይኔ ብርሃን ሆይ! ለዓለማት እዝነት የሆንከው ልጄ ሆይ! ይህ ምንድን ነው? ምን ደረሰብህ? ማን አስቸገረህ?› ብዬ ጠየቅሁ።
እርሳቸውም እንዲህ አሉ፦ ‹ከቤት ከወጣሁ በኋላ አረንጓዴ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎችን አየሁ። የአንዱ እጅ ላይ የብር ማንቆርቆሪያ፣ የሌላው እጅ ላይ ከአረንጓዴ መረግድ የተሠራ ሳፋ ነበር። ሳፋው ከበረዶ በነጣ ነገር ተሞልቶ ነበር። ወደ ተራራው ጫፍ ወሰዱኝ። አንዱ በጀርባዬ አስተኛኝ። እያየሁ ደረቴን እስከ እምብርቴ ድረስ ሰነጠቀ። ምንም ሕመምም ሆነ ስቃይ አልተሰማኝም። እጃቸውን አስገብተው በውስጡ ያለውን ሁሉ አወጡ። በዚያ ነጭ ነገር አጥበው ወደ ቦታው መለሱት። አንዱ ሌላውን፦ «ተነሥ፤ እኔም አገልግሎቴን ልፈጽም» አለው። እጁን አስገብቶ ልቤን አወጣ። ለሁለት ከፈለው፤ ከውስጡም ጥቁር ነገር አውጥቶ ጣለው። እንዲህም አለ፦ «ይህ በአካልዎ ውስጥ የሰይጣን ድርሻ ነበር። አውጥተን ጣልነው። የአላሁ ተዓላ ተወዳጅ ሆይ! ከወስወሳ3 እና ከሰይጣን ተንኮል ጠበቅንዎ።» ከዚያም በእነርሱ ዘንድ በነበረ ረቂቅና ለስላሳ ነገር ልቤን ሞሉት። በኑር ማኅተም አተሙት። እስከ አሁን የዚያ ማኅተም ቅዝቃዜ በሰውነቴ ክፍሎች ሁሉ ውስጥ ይሰማኛል። ከእነርሱ አንዱ እጁን በተሰነጠቀው ቦታ ላይ ባደረገ ጊዜ ቁስሌ ዳነ። ከዚያም ከኡማዬ ከአሥር ሰዎች ጋር መዘኑኝ፤ እኔ በለጥኩ። ከአንድ ሺህ ሰዎች ጋር መዘኑኝ፤ አሁንም በለጥኩ። በዚህም ከእነርሱ አንዱ ሌላውን፦ «አሁን መመዘናቸውን ተው። ወላሂ! ከመላው ኡማቸው ጋር ብትመዝናቸውም ይበልጣሉ» አለው። ከዚያም እያንዳንዳቸው እጄንና ፊቴን ሳሙ፤ እዚህ ትተውኝ ሄዱ።› የተሰነጠቀው ቦታ በተባረከ ደረታቸው ላይ ይታይ ነበር።»4
በውዱ ነብያችን ላይ የደረሰውና በቁርኣን ከሪም በሱረቱ አሽ-ሸርሕ የመጀመሪያው አንቀጽ የተገለጸው ይህ ክስተት «ሸቅቁ ሶድር»፣ ማለትም የደረታቸው መሰንጠቅ ይባላል።
ለሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ነብይነታቸው ከተገለጸላቸው በኋላ ከሶሓቦች አንዳንዶቹ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ስለ ራስዎ ይንገሩን?» ባሉ ጊዜ እንዲህ አሉ፦ «እኔ የአያቴ የኢብራሂም ዱዓ ነኝ። የወንድሜ የዒሳ የምሥራች ነኝ!
የእናቴም ሕልም ነኝ። እኔን አርግዘው ሳሉ የሻምን ቤተ መንግሥቶች የሚያበራ ኑር ከእርሳቸው ሲወጣ አዩ… እኔ የጠባሁትና ያደግሁት በሰዕድ ኢብኑ በክር ልጆች ዘንድ ነው።»
አራት ዓመት በሞላቸው ጊዜ እመቤት ሐሊማ ወደ መካ ወስደው ለእናታቸው መለሷቸው። አያታቸው ዐብዱልሙጠሊብ ለእመቤት ሐሊማ እጅግ ታላላቅ ስጦታዎችን ሰጥተው ቸርነት አደረጉላቸው። እመቤት ሐሊማ በመካ ትተዋቸው ሲሄዱ የመለያየቱን ሐዘን፦ «ነፍሴና ልቤ ከእርሳቸው ጋር የቀሩ ያህል ነው» በሚሉ ቃላት ገለጹ።
«ሙሐመድን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እስካጠባሁ ድረስ በእርሳቸው እጅግ ረክቼ ነበር። ምንም ነገር ፈጽሞ አላቆሸሹም። በቀንና በሌሊት አንድ ጊዜ ይሸኑ ነበር፤ ከዚያም እስከዚያው ሰዓት ድረስ ዳግመኛ አይሸኑም ነበር» እመቤት ሐሊማ
የተከበሩት እናታቸው ማረፍ
ውዱ ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እስከ ስድስት ዓመታቸው ከእናታቸው ጋር አደጉ። ስድስት ዓመት ሲሞላቸው እናታቸው ከእርሳቸውና ኡሙ አይመን ከተባሉ ጃሪያ ጋር ዘመዶቻቸውንና የአባታቸውን የዐብዱላህን መቃብር ለመጎብኘት ወደ መዲና ሄዱ።
እዚያ አንድ ወር ቆዩ። ክቡር ነብያችን በመዲና የነጃር ልጆች ንብረት በሆነ የውኃ ገንዳ ውስጥ መዋኘትን ተማሩ። በዚያን ጊዜ አንድ የአይሁድ ዓሊም በእርሳቸው ላይ የነብይነት ምልክቶችን አየ። ቀርቦም ስማቸውን ጠየቀ። «አሕመድ» ባሉ ጊዜ ያ ዓሊም፦ «ይህ ልጅ የመጨረሻው ዘመን ነብይ ይሆናሉ!» ብሎ ጮኸ። በዚያ የነበሩ ሌሎች አንዳንድ የአይሁድ ዓሊሞችም በእርሳቸው ላይ የነብይነትን ምልክት አይተው ነብይ እንደሚሆኑ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።
የእነርሱን ይህን ንግግር የሰሙት ኡሙ አይመን ሁኔታውን ለእናታችን አሚና ነገሩ። የተባረኩት እናታቸው አንዳች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ፈርተው ይዘዋቸው ወደ መካ ለመመለስ ጉዞ ጀመሩ። አብዋ ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ እናታችን አሚና ታመሙ። ሕመማቸው እየጸና ሄዶ በተደጋጋሚ ራሳቸውን ይስቱ ነበር።
ራስጌያቸው ቆመው የነበሩትን ውድ ልጃቸውን ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን እየተመለከቱ እንዲህ አሉ፦ «በአላሁ ተዓላ ችሮታና እርዳታ በመቶ ግመሎች ምትክ ከአስፈሪው የሞት ፍላጻ የዳኑት ሰው ልጅ ሆይ! አላሁ ተዓላ የተባረክ ያድርግህ። በሕልሜ ያየሁት እውነት ሆኖ ከተገኘ፣ የግርማና የብዙ ልግስና ባለቤት በሆነው በአላሁ ተዓላ ለአደም ልጆች ሐላልንና ሐራምን እንድታሳውቅ ትላካለህ። ክብሩ የላቀው አላህ ከሕዝቦች ጋር ከጥንት ጀምሮ ከመጡት ጣዖታትና ከጣዖት አምልኮ ይጠብቅሃል፣ ይከልልሃልም።» እነዚህንም ስንኞች ተናገሩ፦
አዲሱ ያረጃል፣ ሕያው የሆነው ይሞታል፣
ብዙው ያልቃል፤ ወጣት ሆኖ የሚቀር ማን አለ?
እኔም እሞታለሁ፤ ብቸኛ ልዩነቴ ይህ ነው፦
አንተን ወለድኩ፤ ክብሬ ይህ ነው።
መልካም ልጅ ትቼ እሄዳለሁ፣
ዓይኖቼን በሰላም እከድናለሁ።
ስሜ ሁልጊዜ በአንደበቶች ላይ ይኖራል፣
ፍቅርህ ዘወትር በልቦች ውስጥ ይኖራል።
ከዚያም አረፉ። እዚያው ተቀበሩ። እናታችን አሚና ባረፉ ጊዜ የሃያ ዓመት ዕድሜ ነበራቸው። ኡሙ አይመን የዓለማትን ሰይድ ይዘው ለጥቂት ቀናት ከተጓዙ በኋላ ወደ መካ አምጥተው ለአያታቸው ለዐብዱልሙጠሊብ አስረከቧቸው።5
እናታቸውና አባታቸው ምእመናን ነበሩ
የሐቢቡል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አባትና እናት በኢብራሂም ዐለይሂ ሰላም ሃይማኖት ላይ ነበሩ።6 ማለትም ምእመናን ነበሩ። የእስልምና ዓሊሞች በኢብራሂም ዐለይሂ ሰላም ሃይማኖት ላይ እንደነበሩ፣ ለሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ነብይነታቸው ከተገለጸላቸው በኋላም ከኡማቸው እንዲሆኑ ዳግመኛ ሕያው ተደርገው የሸሃዳን ቃል እንደሰሙና እንደተናገሩ፣ በዚህም ከዚህ ኡማ ደግሞ እንደሆኑ አሳውቀዋል።7
ከተባረኩት አያታቸው ጋር
ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም እስከ ስምንት ዓመታቸው ከአያታቸው ጋር አደጉ። አያታቸው ዐብዱልሙጠሊብ በመካ የተወደዱና የተለያዩ ጉዳዮችን የሚያስተዳድሩ ሰው ነበሩ፤ ግርማ ያላቸው፣ ታጋሽ፣ መልካም ስነ ምግባር ያላቸው፣ እውነተኛ፣ ጀግናና ቸር ነበሩ። ድሆችን ያበሉ ነበር፤ የተራቡና የተጠሙ እንስሳትን እንኳ ይመግቡ ነበር።
በአላሁ ተዓላና በአኺራ ያምኑ ነበር። ከክፋት ይጠነቀቁ ነበር፤ ከጃሂሊያ (የድንቁርና ዘመን) መጥፎ ልማዶች ሁሉ ይርቁ ነበር። በመካ ግፍንና በደልን ይከለክሉ ነበር፤ የሚመጡትን እንግዶችም በክብር ያስተናግዱ ነበር። በረመዳን ወር በሒራ ተራራ ላይ ለብቻቸው መገለል ልማዳቸው ነበር። ልጆችን የሚወዱና ርኅራኄ የተሞሉት ዐብዱልሙጠሊብ ውድ የልጅ ልጃቸውን ወደ ደረታቸው አስጠግተው ቀንም ሌሊትም ከአጠገባቸው አይለዩአቸውም ነበር። ታላቅ ፍቅርና ርኅራኄ ያሳዩአቸው ነበር። በካዕባ ጥላ ሥር ለራሳቸው ብቻ በተዘጋጀው ፍራሽ ላይ የልጅ ልጃቸውን ይዘው ይቀመጡ ነበር፤ ሊከለክሉ ለሚፈልጉትም፦ «ልጄን ተዉት፤ ክብራቸው ከፍ ያለ ነው» ይሉ ነበር።8 የክቡር ነብያችንን ሞግዚት ኡሙ አይመንን በደንብ እንዲንከባከቧቸው አጥብቀው ያሳስቡ ነበር፤ እንዲህም ይሉ ነበር፦ «ልጄን በደንብ ተንከባከቢ። የመጽሐፉ ባለቤቶች ስለዚህ ልጄ የዚህ ኡማ ነብይ ይሆናሉ ይላሉ።» ኡሙ አይመን እንዲህ አሉ፦ «በልጅነታቸው ስለ ረሃብም ሆነ ስለ ጥማት ሲያማርሩ ሰምቼ አላውቅም። ጠዋት ጠዋት አንድ ጉንጭ የዘምዘም ውኃ ይጠጡ ነበር። ልናበላቸው በፈለግን ጊዜ፦ ‹አልፈልግም፤ ጠግቤአለሁ› ይሉ ነበር።»
ዐብዱልሙጠሊብ ሲተኙ ወይም በክፍላቸው ለብቻቸው ሲሆኑ ከሙሐመድ በስተቀር ማንም እንዲገባባቸው አይፈቅዱም ነበር። በርኅራኄ ወደ ደረታቸው አስጠግተው ይዳብሷቸው ነበር፤ በንግግራቸውና በእንቅስቃሴያቸውም እጅግ ይደሰቱ ነበር። በማዕድ ላይ ከጎናቸው ያስቀምጧቸው፣ በጉልበታቸው ላይ ያስቀምጧቸው፣ ከምግቡ እጅግ ጥሩውንና ጣፋጩን ያበሏቸው ነበር፤ እርሳቸው ሳይመጡም ወደ ማዕድ አይቀመጡም ነበር። ስለ እርሳቸው ብዙ ሕልሞችን አዩ፤ የብዙ ክስተቶችም ምስክር ሆኑ።
አንድ ጊዜ በመካ ድርቅና ረሃብ ሆነ። ዐብዱልሙጠሊብ ባዩት አንድ ሕልም መሠረት የሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን እጅ ይዘው ወደ አቡ ቁበይስ ተራራ ወጡና፦ «አላህ ሆይ! ለዚህ ልጅ ክብር ስትል በበረከት ዝናብ አስደስተን» ብለው ዱዓ አደረጉ። ዱዓቸው ተቀባይነት አገኘ፤ ብዙ ዝናብም ዘነበ። የዚያ ዘመን ገጣሚዎች ይህን ክስተት በግጥሞቻቸው ገለጹት።
የነጅራኑ መነኩሴ
አንድ ቀን ዐብዱልሙጠሊብ በካዕባ አጠገብ ተቀምጠው ሳሉ ከነጅራን የመጣ አንድ መነኩሴ ወደ እርሳቸው ቀርቦ መነጋገር ጀመረ። በመካከልም፦ «ከኢስማዒል ልጆች በመጨረሻ የሚመጡት ነብይ ባሕርያት በመጻሕፍት ውስጥ ተጽፈው እንዳሉ አንብበናል። ይህ ስፍራ፣ ማለትም መካ፣ የትውልድ ቦታቸው ነው። ባሕርያቸውም እንዲህና እንዲህ ናቸው!» ብሎ አንድ በአንድ መዘርዘር ጀመረ። በዚያን ጊዜ ውዱ ነብያችን ወደ እነርሱ መጡ። የነጅራኑ መነኩሴ በጥንቃቄ ይመለከታቸው ጀመር፤ ከዚያም ቀርቦ ዓይኖቻቸውን፣ ጀርባቸውንና እግሮቻቸውን ተመለከተና በከፍተኛ ስሜት እንዲህ አለ፦
«ክብሩ የላቀው አላህ ከሕዝቦች ጋር ከጥንት ጀምሮ ከመጡት ጣዖታትና ከጣዖት አምልኮ ይጠብቅሃል፣ ይከልልሃልም» እመቤት አሚና
«እነሆ እርሳቸው ናቸው። ይህ ልጅ ከዘርህ ነውን?» ዐብዱልሙጠሊብ፦ «ልጄ ናቸው!» ባሉ ጊዜ የነጅራኑ መነኩሴ፦ «በመጻሕፍት እንዳነበብነው ከሆነ አባታቸው በሕይወት መኖር የለባቸውም!» አለ። ዐብዱልሙጠሊብም፦ «እርሳቸው የልጄ ልጅ ናቸው። እናታቸው እርጉዝ ሳሉ፣ ገና ሳይወለዱ አባታቸው አረፉ» ብለው አስረዱ። በዚህም መነኩሴው፦ «አሁን እውነት ተናገርክ» አለ። ከዚያም ዐብዱልሙጠሊብ ልጆቻቸውን፦ «ስለ ወንድማችሁ ልጅ የሚባለውን ስሙ፤ ተከታተሏቸው፣ በደንብም ጠብቋቸው» አሉ።
የተባረኩት አያታቸው ማረፍ
ዐብዱልሙጠሊብ የሚያርፉበት ጊዜ በቀረበ ጊዜ ልጆቻቸውን ሰብስበው እንዲህ አሉ፦ «እንግዲህ ከዚህ ዓለም ወደ አኺራ የምሄድበት ጊዜ ደረሰ። ብቸኛ ጭንቀቴ ይህ የሙት ልጅ ነው። ምነው ዕድሜዬ ረጅም በሆነና ይህን አገልግሎት በፍቅር በቀጠልኩ! ነገር ግን ምን ይደረጋል? ዕድሜ አይበቃም። አሁን ልቤና አንደበቴ በዚህ የናፍቆት እሳት እየተቃጠሉ ነው። ይህን ዕንቁ ከእናንተ ለአንዳችሁ አደራ መስጠት እፈልጋለሁ። ከእናንተ መካከል ሐቃቸውን በሚገባ የሚጠብቅና በአገልግሎታቸው የማያጓድል ማን ነው?» አቡ ለሀብ በጉልበቱ ተንበርክኮ፦ «የዓረቦች አለቃ ሆይ! ይህን አደራ ሊያስረክቡት ያሰቡት ሰው ካለ መልካም ነው፤ ካልሆነ ግን ይህን አገልግሎት እኔ እፈጽማለሁ» አለ። ዐብዱልሙጠሊብም፦ «ሀብትህ ብዙ ነው። ነገር ግን አንተ ልበ ደረቅ ነህ፤ ርኅራኄህም ጥቂት ነው። የሙት ልጅ ልብ ደግሞ የቆሰለና ስስ ነው። ቶሎ ይሰበራል» አሉት። ሌሎች አንዳንድ ልጆቻቸውም ያንኑ ጥያቄ ደገሙ። ዐብዱልሙጠሊብ የእያንዳንዳቸውን ባሕርይ እየጠቀሱ አልተቀበሏቸውም። ተራው ለአቡ ጧሊብ በደረሰ ጊዜ እንዲህ አሉ፦ «እኔ ከሁሉም ይበልጥ ይህን እፈልጋለሁ። ነገር ግን ታላላቆቼ እያሉ ቀድሜ መግባት ተገቢ አልነበረም። ሀብቴ ጥቂት ነው፤ ታማኝነቴ ግን ከወንድሞቼ ይበልጣል።» ዐብዱልሙጠሊብም፦ «እውነት ተናገርክ። ለዚህ አገልግሎት የሚገባው አንተ ነህ። ነገር ግን እኔ በየጉዳዩ እርሳቸውን አማክራለሁ፤ እንደ ፍላጎታቸውም እሠራለሁ። ሁልጊዜም ትክክለኛ ውጤት ላይ እደርሳለሁ። በዚህ ጉዳይም እርሳቸውን ላማክር። ከእናንተ ማንን ቢመርጡ እኔም እቀበለዋለሁ» አሉ።
ከዚያም ወደ ውዱ ነብያችን ዞረው፦ «የዓይኖቼ ብርሃን ሆይ! አንተን እየናፈቅሁ ወደ አኺራ ልሄድ ነው። ከእነዚህ አጎቶችህ ማንን ትመርጣለህ?» ብለው ጠየቁ።
ክቡር ነብያችን ወዲያውኑ ተነሥተው የአቡ ጧሊብን አንገት አቀፉና በጉልበታቸው ላይ ተቀመጡ። ዐብዱልሙጠሊብ ያን ጊዜ እጅግ እፎይ አሉና፦ «ምስጋና ለአላሁ ተዓላ ይገባው። የእኔም ፍላጎት ይህ ነበር» አሉ። ከዚያም ወደ አቡ ጧሊብ ዞረው፦ «አቡ ጧሊብ ሆይ! ይህ ዕንቁ የአባትና የእናት ርኅራኄ አላገኙም። ስለዚህ እንደሚገባቸው ተንከባከባቸው፤ በሙሉ ልብህም ተጠንቀቅላቸው። ከሌሎቹ ልጆቼ አንተን አስበልጥሃለሁ። ይህን ታላቅና እጅግ ውድ አደራ ለአንተ ሰጥቻለሁ። ምክንያቱም አንተና አባታቸው ከአንድ እናት ናችሁ። እንደ ራስህ ጠብቃቸው። ይህን ኑዛዜዬን ተቀበልክን?» ብለው ጠየቁ።
እርሳቸውም፦ «ተቀብያለሁ» ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ ዐብዱልሙጠሊብ ውዱ ነብያችንን አቅፈው የተባረከ ራሳቸውንና ፊታቸውን ሳሙ፤ መዓዛቸውንም አሸተቱ። ከዚያም፦ «ከዚህ የበለጠ ደስ የሚል መዓዛ እንዳላሸተትኩና ከዚህ የበለጠ ውብ ፊት እንዳላየሁ ሁላችሁም መስክሩ» አሉ።9
በአቡ ጧሊብ ጥበቃ ሥር
አያታቸው ካረፉ በኋላ የፍጥረተ ዓለሙ ሰይድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከስምንት ዓመታቸው ጀምሮ ከአጎታቸው ከአቡ ጧሊብ ጋር መኖር ጀመሩ፤ በእርሳቸውም ጥበቃ ሥር አደጉ። በዚያን ጊዜ አቡ ጧሊብም እንደ አባታቸው እንደ ዐብዱልሙጠሊብ በመካ ከቁረይሽ ታላላቆች አንዱ ነበሩ፤ የተወደዱ፣ የተከበሩና ቃላቸው የሚሰማ ሰው ነበሩ። እርሳቸውም ለክቡር ነብያችን ታላቅ ፍቅርና ርኅራኄ አሳዩ። ከገዛ ልጆቻቸው አብልጠው ይወዷቸው ነበር፤ ከአጠገባቸው ሳያደርጓቸው አይተኙም፣ ወደ የትም አይሄዱም ነበር፤ «አንተ እጅግ መልካም፣ እጅግ የተባረክ ነህ!» ይሏቸው ነበር። ሙሐመድ እጃቸውን ሳይዘረጉ አቡ ጧሊብ መብላት አይጀምሩም ነበር፤ እርሳቸው ቀድመው እንዲጀምሩ ይፈልጉ ነበር። አንዳንዴም ለእርሳቸው የተለየ ማዕድ ያዘጋጁላቸው ነበር። ጠዋት ሲነቁ ፊታቸው እንደ ጨረቃ ሲያበራ፣ ጸጉራቸውም ተበጥሮ ያዩአቸው ነበር። አቡ ጧሊብ ብዙ ሀብት አልነበራቸውም፤ ቤተሰባቸውም ብዙ ነበር። ረሱሉል አክረምን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በጥበቃቸው ሥር ካደረጉ በኋላ ብልጽግናና በረከት አገኙ። በመካ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ሕዝቡ በተቸገረ ጊዜ አቡ ጧሊብ እርሳቸውን ይዘው ወደ ካዕባ ሄዱና ዱዓ አደረጉ። በበረከታቸው ብዙ ዝናብ ዘነበ። ከድርቅና ከረሃብ ዳኑ።10
ከጋሊብ ዘር አንድ ነብይ ይነሣሉ፣
በዘምዘምና በሐጀር መካከል ይቆማሉ።
ከመላው የከተማ ሕዝብ ጋር እርዷቸው፣
የዓሚር ልጆች ሆይ! ደስታ እርሳቸውን በመርዳት ውስጥ ነው።
«እንግዲህ ከዚህ ዓለም ወደ አኺራ የምሄድበት ጊዜ ደረሰ። ብቸኛ ጭንቀቴ ይህ የሙት ልጅ ነው። ምነው ዕድሜዬ ረጅም በሆነና ይህን አገልግሎት በፍቅር በቀጠልኩ! ነገር ግን ምን ይደረጋል? ዕድሜ አይበቃም። አሁን ልቤና አንደበቴ በዚህ የናፍቆት እሳት እየተቃጠሉ ነው» ዐብዱልሙጠሊብ
የመካ–ቡስራ ጉዞ
መነኩሴው በሒራ
ውዱ ነብያችን አሥራ ሁለት ዓመት ገደማ ሲሆናቸው አንድ ቀን አቡ ጧሊብ ለንግድ ጉዞ ሲዘጋጁ አዩ። ይዘዋቸው መሄድ እንደማይፈልጉ በተረዱ ጊዜ አዝነው አቡ ጧሊብን፦ «በዚህ ከተማ ለማን ትተውኝ ይሄዳሉ? አባት የለኝም፤ የሚያዝንልኝም የለኝም!…» አሉ። ይህ ቃል አቡ ጧሊብን እጅግ ነካቸው፤ እርሳቸውንም ይዘዋቸው ለመሄድ ወሰኑ። የንግዱ ቅፍለት ከረጅም ጉዞ በኋላ በቡስራ የክርስቲያኖች በሆነ አንድ ገዳም አጠገብ ሰፈረ።11
በዚህ ገዳም በሒራ የሚባል አንድ መነኩሴ ይኖር ነበር። ቀደም ሲል ከአይሁድ ዓሊሞች አንዱ የነበረውና በኋላ ክርስቲያን የሆነው ይህ አዋቂ መነኩሴ ከእጅ ወደ እጅ እየተላለፈ በምሥጢር የተጠበቀ አንድ መጽሐፍ ነበረው፤ ለሚጠየቃቸው ጥያቄዎችም ከዚያ መልስ ይሰጥ ነበር። የቁረይሽ ቅፍለት በቀደሙት ዓመታት በዚህ ስፍራ ብዙ ጊዜ ቢያልፍም ምንም ትኩረት አልሰጠውም ነበር። በየማለዳው የገዳሙ ጣሪያ ላይ ወጥቶ ቅፍለቶች ወደሚመጡበት አቅጣጫ ይመለከት ነበር፤ በፍለጋ ስሜት በጉጉት አንድ ነገር ይጠባበቅ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን በመነኩሴው በሒራ ላይ አንድ ሁኔታ ተፈጠረ፤ በስሜት ደንግጦ ከቦታው ዘለለ። ምክንያቱም የቁረይሽ ቅፍለት ከሩቅ በታየ ጊዜ በላዩ ላይ አንድ ደመና አብሯቸው እየተንሳፈፈ እንደሚመጣ አስተዋለ። ይህ ደመና ለክቡር ነብያችን ጥላ ይሆን ነበር። ቅፍለቱ በሰፈረ ጊዜ በሒራ ሐቢቡል አክረም ከሥሩ የተቀመጡበት ዛፍ ቅርንጫፎች በላያቸው ላይ ሲያዘነብሉም አይቶ ይበልጥ በስሜት ተሞላ። ወዲያውኑ ማዕድ አስዘረጋ። ከዚያም ሰው ልኮ በቁረይሽ ቅፍለት ውስጥ የነበሩትን ሁሉ ለምግብ ጋበዘ። የቅፍለቱ ሰዎች ውዱ ነብያችንን ከዕቃዎቻቸው አጠገብ ትተው ወደ መነኩሴው ሄዱ። በሒራ የመጡትን በጥንቃቄ ተመልክቶ፦ «የቁረይሽ ሰዎች ሆይ! ከእናንተ መካከል ወደ ምግቡ ያልመጣ ሰው አለን?» ብሎ ጠየቀ። «አዎ፣ አንድ ሰው አለ» አሉ። ምክንያቱም ቁረይሾች ቢመጡም ደመናው አሁንም እዚያው ነበር። ይህን ባየ ጊዜ በቅፍለቱ ዘንድ አንድ ሰው እንደቀረ ተረድቶ ነበር። መነኩሴው በሒራ እርሳቸውም እንዲመጡ አጥብቆ ጠየቀ። ልክ እንደመጡም በሒራ በጥንቃቄ ይመለከታቸውና ይመረምራቸው ጀመር። አቡ ጧሊብን፦ «ይህ ልጅ ከዘርህ ነውን?» ብሎ ጠየቀ። አቡ ጧሊብ፦ «ልጄ ናቸው» ባሉ ጊዜ በሒራ፦ «በመጻሕፍት የዚህ ልጅ አባት በሕይወት እንደማይኖሩ ተጽፏል፤ እርሳቸው ልጅህ አይደሉም» አለ። በዚህ ጊዜ አቡ ጧሊብ፦ «እርሳቸው የወንድሜ ልጅ ናቸው» ብለው መለሱ። በሒራ፦ «አባታቸው ምን ሆኑ?» ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ፦ «አባታቸው ሊወለዱ ሲቃረብ አረፉ» አሉ። በሒራም፦ «እውነት ተናገርክ። እናታቸውስ ምን ሆኑ?» ባለ ጊዜ አቡ ጧሊብ፦ «እርሳቸውም አረፉ» ብለው መለሱ። በዚህም በሒራ፦ «እውነት ተናገርክ» ብሎ ወደ ክቡር ነብያችን ዞረና በጣዖታት ስም እንዲምሉ ጠየቃቸው። ውዱ ነብያችን ግን በሒራን፦ «በጣዖታት ስም አያስምሉኝ። በዚህ ዓለም ከእነርሱ የሚበልጥ ጠላት የለኝም። እጠላቸዋለሁ።» አሉት።
ከዚያም በሒራ በአላሁ ተዓላ ስም አስምሏቸው፦ «ትተኛለህን?» ብሎ ጠየቀ። እርሳቸውም፦ «ዓይኖቼ ይተኛሉ፤ ልቤ ግን አይተኛም።» አሉ።
በሒራ ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችን ጠይቆ መልሶቻቸውን አገኘ። ያገኛቸው መልሶች ቀደም ሲል ካነበባቸው መጻሕፍት ጋር ፍጹም ይስማሙ ነበር። ከዚያም የውዱ ነብያችንን የተባረኩ ዓይኖች ተመልክቶ አቡ ጧሊብን እንዲህ ብሎ ጠየቀ፦
«አንተ የአላሁ ተዓላ መልዕክተኛ እንደሆንክ እመሰክራለሁ!… እነሆ የዓለማት ሰይድ… እነሆ የዓለማት ጌታ መልዕክተኛ… እነሆ አላሁ ተዓላ ለዓለማት እዝነት አድርጎ የላካቸው ታላቁ ነብይ!» መነኩሴው በሒራ
«ይህ መቅላት በተባረኩ ዓይኖቻቸው ውስጥ ሁልጊዜ ይኖራልን?»
«አዎ፣ ሲጠፋ አይተን አናውቅም» ብለው መለሱ።
በሒራ ይህ ምልክትም መገጣጠሙን ባየ ጊዜ ልቡ ሙሉ እርግጠኝነት እንዲያገኝ የነብይነትን ማኅተም ማየት ፈለገ። ክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ግን ከጨዋነታቸው የተነሣ የተባረከ ጀርባቸውን መግለጥ አልፈለጉም።
ያን ጊዜ አቡ ጧሊብ፦ «የዓይኔ ብርሃን ሆይ! ይህንንም ፍላጎቱን ፈጽምለት!» አሉ። በዚህም የተባረከ ጀርባቸውን ገለጡ፤ በሒራም የነብይነትን ማኅተም በሙሉ ውበቱ እስኪረካ ድረስ ተመለከተ። በስሜት ተሞልቶ ሳመው፤ ከዓይኖቹም እንባ እንደ ጎርፍ ፈሰሰ። ከዚያም እንዲህ አለ፦
«አንተ የአላሁ ተዓላ መልዕክተኛ እንደሆንክ እመሰክራለሁ!» ድምፁንም ይበልጥ ከፍ አድርጎ፦ «እነሆ የዓለማት ሰይድ… እነሆ የዓለማት ጌታ መልዕክተኛ… እነሆ አላሁ ተዓላ ለዓለማት እዝነት አድርጎ የላካቸው ታላቁ ነብይ…» አለ።
በዚያ የነበሩት ቁረይሾች ተደንቀው፦ «ሙሐመድ በዚህ መነኩሴ ዘንድ ያላቸው ዋጋ ምንኛ ታላቅ ነው!» አሉ።
ያን ጊዜ በሒራ ወደ አቡ ጧሊብ ዞሮ እንዲህ አለ፦
«እርሳቸው የነብያት የመጨረሻውና እጅግ የተከበሩት ናቸው። ሃይማኖታቸው በመላው ምድር ላይ ይሰራጫል፤ የቀደሙትን ሃይማኖቶችም ይሽራል። ይህን ልጅ ወደ ሻም አትውሰዳቸው። ምክንያቱም የኢስራኢል ልጆች ጠላቶቻቸው ናቸው። በተባረከ አካላቸው ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ እፈራለሁ። ስለ እርሳቸው ብዙ ቃል ኪዳንና መሐላ ተገብቷል።»
አቡ ጧሊብ እንዲህ ብለው ጠየቁ፦
«እነዚያ ቃል ኪዳንና መሐላ ምንድን ናቸው?» በሒራም እንዲህ ብሎ መለሰ፦
«አላሁ ተዓላ ከነብያት ሁሉ፣ በመጨረሻም ከዒሳ ዐለይሂ ሰላም፣ የመጨረሻው ዘመን ነብይ እንደሚመጡ ለኡማዎቻቸው እንዲያሳውቁ ቃል ኪዳን ወስዷል።»
አቡ ጧሊብ ከበሒራ ይህን ቃል በሰሙ ጊዜ ወደ ሻም ከመሄድ ተመለሱ። ዕቃዎቻቸውን በቡስራ ሸጠው ወደ መካ ተመለሱ።12 ከበሒራ የሰሙት ነገር በአቡ ጧሊብ ጆሮ ዕድሜ ልካቸውን ያስተጋባ ነበር። ክቡር ነብያችንን ይበልጥ ወደዷቸው። እስከ ሕልፈታቸው ድረስ ጠበቋቸው፤ በየጉዳያቸውም ረዷቸው።
ከአጎታቸው ከዙበይር ጋር ወደ የመን መሄዳቸው
በሁኔታቸው ሁሉ የብልጫዎችና የውበቶች ባለቤት፣ ልዩ ሰው የሆኑት ውዱ ነብያችን አድገው አሥራ ሰባት ዓመት ሞልቷቸው ነበር። በዚያን ጊዜ ለንግድ ወደ የመን ይሄዱ የነበሩት አጎታቸው ዙበይር ንግዳቸው በረከት እንዲያገኝ እርሳቸውንም ይዘዋቸው ሄዱ። በዚህ ጉዞም ብዙ ድንቅ ሁኔታዎች ታዩባቸው። ወደ መካ በተመለሱ ጊዜ እነዚህ ሁኔታዎቻቸው ተወሩ፤ በቁረይሽ ጎሳ መካከልም፦ «ክብራቸው እጅግ ከፍ ያለ ይሆናል» መባል ጀመረ።13
