ውዱ ነብዬ

የክቡር ነብያችን ተአምራት

ውዱ ነብያችን ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም የአላሁ ተዓላ ነብይ መሆናቸውን የሚያሳዩ ምስክሮች ተቆጥረው የማያልቁ ያህል ብዙ ናቸው። አላሁ ተዓላ፦ «አንተ ባትኖር ኖሮ ዓለምን ባልፈጠርኩ ነበር!» አለ።1 ፍጥረታት ሁሉ የአላሁ ተዓላን መኖርና አንድነት እንደሚያሳዩ ሁሉ ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ነብይ መሆናቸውንና ብልጫቸውንም ያሳያሉ። በኡማቸው አውሊያ ዘንድ የሚገለጹት ከራማዎች ሁሉ የእርሳቸው ተአምራት ናቸው። ምክንያቱም ከራማዎች የሚገለጹት እርሳቸውን በሚከተሉና በፈለጋቸው በሚሄዱ ሰዎች ዘንድ ነው። እንዲያውም ነብያት ሁሉ ከኡማቸው መሆንን ስለተመኙ፣ ይበልጥ ትክክሉ ደግሞ ሁሉም ከእርሳቸው ኑር ስለተፈጠሩ፣ የእነርሱ ተአምራትም ከሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ተአምራት ይቆጠራሉ። የውዱ ነብያችን ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ተአምራት ከጊዜ አንጻር በሦስት ይከፈላሉ፦

የመጀመሪያዎቹ የተባረከች ነፍሳቸው ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ነብይነታቸው እስከተገለጸበት የቢዕሳ ዘመን ድረስ የሆኑት ናቸው። ሁለተኛዎቹ ከቢዕሳ እስከ ዕረፍታቸው ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሆኑት ናቸው።

ሦስተኛዎቹ ከዕረፍታቸው ጀምሮ እስከ ቂያማ ድረስ የሆኑትና የሚሆኑት ነገሮች ናቸው። ከእነዚህ የመጀመሪያዎቹ ኢርሃስ ይባላሉ። እያንዳንዳቸውም በተጨማሪ በዓይን የሚታዩና ሳይታዩ በአእምሮ የሚገነዘቡ ተአምራት ተብለው በሁለት ይከፈላሉ። ተአምራቱ ሁሉ እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ መወሰንም መቁጠርም አልተቻለም። የሁለተኛው ክፍል ተአምራት ሦስት ሺህ ገደማ እንደሆኑ ተገልጿል። ከእነርሱ መካከል የታወቁት ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል። 1. ከሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ተአምራት ሁሉ ታላቁ ቁርኣን ከሪም ነው። እስከ ዛሬ የመጡ ገጣሚዎችና የስነ ጽሑፍ ሰዎች ሁሉ በቁርኣን ከሪም አወቃቀርና ትርጉም ፊት አቅም አጥተው በመደነቅ ቆመዋል። የአንድን ክቡር አንቀጽ አምሳያ እንኳ መናገር አልቻሉም። ተአምራዊነቱና የንግግሩ ጥራት የሰውን ንግግር አይመስልም። ማለትም ከእርሱ አንድ ቃል ቢወጣ ወይም አንድ ቃል ቢጨመርበት የቃሉና የትርጉሙ ውበት ይበላሻል። በአንዱ ቃሉ ምትክ ለማስቀመጥ ሌላ ቃል የፈለጉ ሰዎች አላገኙም። አወቃቀሩ የዓረብ ገጣሚዎችን ግጥሞች አይመስልም። ባለፈው ዘመን የሆኑና ወደፊት የሚሆኑ ብዙ የተሰወሩ ነገሮችን ይነግራል። የሚሰሙትና የሚያነቡት ጣዕሙን አይጠግቡም፤ ቢደክሙም አይሰለቹም። ማንበቡና መስማቱ ጭንቀትን እንደሚያስወግድ በቁጥር በማይወሰኑ ልምዶች ታውቋል። በሰሙት ጊዜ ልባቸውን ድንጋጤና ፍርሃት የወረራቸው፣ በዚህም ምክንያት የሞቱ ሰዎች እንኳ ታይተዋል። ብዙ ጨካኝ የእስልምና ጠላቶች ቁርኣን ከሪምን በማዳመጣቸው ልባቸው ለስልሶ ወደ ኢማን መጥተዋል። ከእስልምና ጠላቶችና ሙዐጢላ፣ መላሒዳና ቀራሚጣ ከሚባሉት የሙስሊም ስም ከተሸከሙ ዚንዲቆች መካከል ቁርኣን ከሪምን ለመለወጥ፣ ለማበላሸትና አምሳያውን ለመናገር የሞከሩ ቢኖሩም አንዳቸውም ፍላጎታቸውን ማሳካት አልቻሉም። ተውራትና ኢንጂል ግን በሰዎች ሁልጊዜ ተለውጠዋል፤ አሁንም እየተለወጡ ነው። በየትኛውም ዕውቀትና ልምድ ሊገኙ የማይችሉ መልካም ነገሮች፣ መልካም ስነ ምግባር፣ ሰዎችን የሚያስበልጡ ትሩፋቶች፣ ወደ ዱንያና ወደ አኺራ ደስታ የሚያደርሱ መልካም ሥራዎች፣ ስለ ፍጥረታት መጀመሪያና መጨረሻ የሆኑ ዕውቀቶችና ለሰዎች ጠቃሚና ጎጂ የሆኑ ነገሮች ሁሉ በቁርኣን ከሪም ውስጥ በግልጽ ወይም በስውር ተገልጸዋል። በስውር የተገለጹትን የዘርፉ ባለሙያዎች ሊረዷቸው ይችላሉ። በሰማያዊ መጻሕፍት ሁሉ፣ በተውራት፣ በዘቡርና በኢንጂል ውስጥ የሚገኙ ዕውቀቶችና ምሥጢራት ሁሉ በቁርኣን ከሪም ተገልጸዋል። በቁርኣን ከሪም ውስጥ ያሉትን ዕውቀቶች ሁሉ የሚያውቀው አላሁ ተዓላ ብቻ ነው። አብዛኛዎቹን ለውድ ነብዩ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አሳውቋል። ዐሊይ እና ሑሰይን (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁማ) ከእነዚህ ዕውቀቶች ብዙዎቹን እንደሚያውቁ ተናግረዋል። ቁርኣን ከሪምን ማንበብ እጅግ ታላቅ ጸጋ ነው። አላሁ ተዓላ ይህን ጸጋ ለሐቢቡ ኡማ ለግሷል። መላእክት ከዚህ ጸጋ የተነፈጉ ናቸው። ስለዚህ ቁርኣን ከሪም በሚነበብበት ስፍራ ተሰብስበው ያዳምጣሉ። ተፍሲሮች ሁሉ በቁርኣን ከሪም ውስጥ ካሉት ዕውቀቶች እጅግ ጥቂቱን ብቻ ይገልጻሉ። በቂያማ ቀን ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ሚንበር ላይ ወጥተው ቁርኣን ከሪምን ባነበቡ ጊዜ የሚያዳምጡት ሰዎች ዕውቀቶቹን ሁሉ ይረዳሉ። 2. ከሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም የታወቁ ተአምራት ታላላቆቹ አንዱ ደግሞ ጨረቃን ለሁለት መክፈላቸው ነው። ይህ ተአምር ለሌላ ለየትኛውም ነብይ አልተሰጠም። ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም የሃምሳ ሁለት ዓመት ሰው ሳሉ በመካ የቁረይሽ ከሓዲዎች መሪዎች ወደ እርሳቸው መጥተው፦ «ነብይ ከሆንክ ጨረቃን ለሁለት ክፈል» አሉ። ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ሰው ሁሉ፣ በተለይም የሚያውቋቸውና ዘመዶቻቸው እንዲያምኑ እጅግ ይፈልጉ ነበር። እጆቻቸውን አንሥተው ዱዓ አደረጉ። አላሁ ተዓላ ዱዓቸውን ተቀብሎ ጨረቃን ለሁለት ከፈለ። ግማሹ በአንድ ተራራ ላይ፣ ሌላኛው ግማሽ ደግሞ በሌላ ተራራ ላይ ታየ። ከሓዲዎቹ፦ «ሙሐመድ ድግምት አደረገብን» አሉ፤ አላመኑም።

«ከሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም አንድ ሺህ ተአምራት ታዩ፤ ወዳጅም ጠላትም ሁሉም ይህን ተናገረ። ከእነዚህ ሁሉ ተአምራት እጅግ ውዱ የአደባቸው ጥራትና መልካም ጠባያቸው ነበር» ሪያዱን ናሲሒን

ግጥም፦
ውሻ ጨረቃን ባየ ጊዜ ይጮኻል፤
ጨረቃ ታዲያ በዚህ ምን ጥፋት አለባት?
ውሾች ምንጊዜም ይጮኻሉ፤
ሞኝ ከዚህ ምን ይገባዋል?
ቤት፦
የአፍ ጣዕም መጥፋት ሕመምን ያመለክታል፤
ከሁሉ የጣፈጠው ሸርባት እንኳ ለሕሙም መራራ ይሆናል።

3. ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም በአንዳንድ ዘመቻዎቻቸው ውኃ በጠፋ ጊዜ የተባረከ እጃቸውን በአንድ ዕቃ ውስጥ ባለ ውኃ አስገቡ፤ ውኃውም በጣቶቻቸው መካከል እየፈሰሰ ዕቃው ያለማቋረጥ ሞልቶ ይፈስስ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሰማንያ፣ አንዳንድ ጊዜ ሦስት መቶ፣ አንዳንድ ጊዜ አንድ ሺህ አምስት መቶ፣ በተቡክ ዘመቻ ደግሞ ሰባ ሺህ ሰዎች ሁሉም ከእንስሶቻቸው ጋር ከዚህ ውኃ ጠጡ፤ ተጠቀሙበትም። የተባረከ እጃቸውን ከውኃው ባወጡ ጊዜ መፍሰሱ ቆመ። 4. አንድ ቀን ወደ አጎታቸው ዐባስ ቤት ሄደው እርሳቸውንና ልጆቻቸውን አጠገባቸው አስቀመጡ። በኢሕራማቸው ሸፍነዋቸው፦ «ጌታዬ ሆይ! ይህን አጎቴንና አህለል በይቴን እንደሸፈንኩ አንተም ከጀሀነም እሳት ጠብቃቸው!» አሉ። ከግድግዳዎቹ ሦስት ጊዜ «አሚን» የሚል ድምፅ ተሰማ።2 5. አንድ ቀን ከእርሳቸው ተአምር ለጠየቁ ሰዎች ምላሽ እንዲሆን ሩቅ የነበረን አንድ ዛፍ ጠሩ። ዛፉ ሥሮቹን እየጎተተ መጥቶ ሰላምታ አቀረበና፦ «አሽሀዱ አን ላ ኢላሀ ኢለላህ ወአሽሀዱ አነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ» አለ። ከዚያም ተመልሶ በቦታው ተተከለ። 6. በኸይበር ዘመቻ መርዝ የተቀባ የበግ ጥብስ ባቀረቡላቸው ጊዜ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! አይብሉኝ፤ እኔ መርዝ ተጨምሮብኛል» የሚል ድምፅ ተሰማ።

7. አንድ ቀን በእጁ ጣዖት ለያዘ ሰው፦ «ጣዖቱ ቢያናግረኝ ታምናለህን?» አሉ። ሰውየውም፦ «እኔ ይህን ለሃምሳ ዓመት አምልኬዋለሁ። ለእኔ አንድም ነገር ተናግሮኝ አያውቅም። አንተን እንዴት ያናግርሃል?» አለ። ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም፦ «ጣዖት ሆይ! እኔ ማን ነኝ?» ባሉ ጊዜ፦ «እርስዎ የአላህ ነብይ ነዎት» የሚል ድምፅ ተሰማ። የጣዖቱ ባለቤት ወዲያውኑ ወደ ኢማን መጣ።

8. በመዲና በመስጂደ ነበዊ ውስጥ የተተከለ የተምር ዛፍ ግንድ ነበረ። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ኹጥባ ሲያደርጉ በዚህ ምሰሶ ላይ ይደገፉ ነበር። እርሱም ሐናና ይባል ነበር። ሚንበር በተሠራ ጊዜ ወደ ሐናና አጠገብ አልሄዱም። ጀማዐው ሁሉ ከእርሱ የለቅሶ ድምፅ ሰሙ። ከሚንበሩ ወርደው ሐናናን አቀፉት፤ ድምፁም ቆመ። «ባላቅፈው ኖሮ ከእኔ በመለየቱ እስከ ቂያማ ድረስ ያለቅስ ነበር» አሉ።

እንደዚህ ያሉ ተአምራት ብዙ ጊዜ ታይተዋል፤ ተወርተዋልም። 9. በእጃቸው የያዟቸው ጠጠሮችና የምግብ ቁርጥራጮች እንደ ንብ ድምፅ አላሁ ተዓላን ተስቢሕ ሲያደርጉ ብዙ ጊዜ ታይቷል።

10. አንድ ከሓዲ መጥቶ፦ «አንተ ነብይ መሆንህን እኔ ከየት አውቃለሁ?» አለ። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን)፦ «በዚያ የተምር ዛፍ ላይ ያለውን ዘለላ ብጠራውና ቢመጣ ታምናለህን?» አሉ። ከሓዲውም፦ «አዎ፣ አምናለሁ» አለ። ረሱሉላህ የተምሩን ዘለላ ጠሩት፤ እየዘለለም መጣ። ረሱሉላህ፦ «ወደ ቦታህ ሂድ!» አሉ። በዛፉ ላይ ወዳለው ቦታው ወጥቶ ተንጠለጠለ። ይህን ያየው ከሓዲ አመነ። 11. በመካ ጥቂት ተኩላዎች ከአንድ መንጋ በጎችን ነጥቀው ወሰዱ። እረኛው ተንደርድሮ በጎቹን ከተኩላዎቹ እጅ ባስጣለ ጊዜ ከተኩላዎቹ አንዱ፦ «አላሁ ተዓላ የላከልንን ሲሳያችንን ከእጃችን ስትወስድ አላሁ ተዓላን አትፈራምን?» አለ። እረኛው፦ «እጅግ ተደነቅሁ፤ ተኩላ ይናገራልን?» ባለ ጊዜ ተኩላው፦ «ከዚህ ይበልጥ የሚያስደንቅ ነገር ልንገርህን? በመዲና የአላሁ ተዓላ ነብይ የሆኑት ሙሐመድ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ተአምራትን እያሳዩ ነው» አለ። እረኛው መጥቶ ይህን ለረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ነገረ፤ ሙስሊምም ሆነ።

12. ሰይዳችን ሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በአንድ መስክ ሲሄዱ ሦስት ጊዜ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!» የሚል ድምፅ ሰሙ። ወደዚያ አቅጣጫ ተመልክተው የታሰረች አንዲት ሚዳቋ አዩ። አጠገቧ አንድ ሰው ተኝቶ ነበር። ሚዳቋዋን ምን እንደምትፈልግ በጠየቋት ጊዜ፦ «ይህ አዳኝ አድኖ ያዘኝ። በፊት ለፊት ባለው ኮረብታ ላይ ሁለት ግልገሎች አሉኝ። ይልቀቁኝ! ሄጄ አጥግቤያቸው ልመለስ» አለች። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም፦ «ቃልሽን ጠብቀሽ ትመለሻለሽን?» አሉ። ሚዳቋዋም፦ «ለአላህ ብዬ ቃል እገባለሁ፤ ባልመለስ የአላህ ቅጣት በእኔ ላይ ይሁን» አለች። ረሱሉላህ ሚዳቋዋን ለቀቋት። ብዙም ሳይቆይ ተመለሰች። ሰውየው ነቅቶ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ትእዛዝ አለዎትን?» አለ። ክቡር ነብያችንም፦ «ይህችን ሚዳቋ ነጻ ልቀቃት!» አሉ። ሰውየው የሚዳቋዋን ገመድ ፈትቶ ለቀቃት። ሚዳቋዋም፦ «አሽሀዱ አን ላ ኢላሀ ኢለላህ ወአነከ ረሱሉላህ» ብላ ሄደች።

13. አንድ ቀን አንድን የገጠር ሰው ወደ ኢማን ጠሩ። እርሱም፦ «የሞተችውን የአንድ ሙስሊም ጎረቤቴን ልጅ ሕያው ብታደርግ አምናለሁ» አለ። ወደ ቀብሯ ሄዱ። ስሟን ጠርተው ልጅቷን ጠሯት። መጀመሪያ ከቀብሩ ውስጥ ድምፅ ተሰማ፤ ልጅቷም ወጣች። ክቡር ረሱሉላህ፦ «ወደ ዱንያ መምጣት ትፈልጊያለሽን?» አሉ። ልጅቷም፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ወደ ዱንያ መምጣት አልፈልግም። እዚህ ከአባቴ ቤት ይበልጥ ምቾት አለኝ። የሙስሊም አኺራ ከዱንያው ይበልጣል» አለች። የገጠሩ ሰው ይህን ባየ ጊዜ ወዲያውኑ ወደ ኢማን መጣ። 14. ጃቢር ኢብኑ ዐብዱላህ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) አንድ በግ አበሰሉ። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከሶሓቦቻቸው ጋር በሉት። «አጥንቶቹን አትስበሩ!» አሉ። አጥንቶቹን ሰብስበው የተባረኩ እጆቻቸውን በላያቸው አድርገው ዱዓ አደረጉ። አላሁ ተዓላ በጉን ሕያው አደረገው። 15. ወደ ረሱሉላህ አድጎ ሳለ ፈጽሞ ተናግሮ የማያውቅ አንድ ልጅ አመጡ። «እኔ ማን ነኝ?» ብለው ጠየቁት። ልጁም፦ «እርስዎ ረሱሉላህ ነዎት» ብሎ መለሰ። ከዚያ እስኪሞት ድረስ ተናገረ።

«ጌታዬ ሆይ! ይህን አጎቴን (ዐባስን) እና አህለል በይቴን እንደሸፈንኩ አንተም ከጀሀነም እሳት ጠብቃቸው!» ሐዲስ ሸሪፍ

16. አንድ ሰው የእባብ እንቁላል ረግጦ ሁለቱም ዓይኖቹ ማየት አቆሙ። ወደ ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አመጡት። ከተባረከ ምራቃቸው ዓይኖቹ ላይ በመቀባታቸው ማየት ጀመረ። እንዲያውም ሰማንያ ዓመት ሆኖት ሳለ በመርፌ ቀዳዳ ክር ያስገባ ነበር።

17. ሙሐመድ ኢብኑ ሐጢብ እንዲህ ይላሉ፦ «ትንሽ ልጅ ነበርኩ። በላዬ ላይ የፈላ ውኃ ፈሰሰ፤ ሰውነቴ ተቃጠለ። አባቴ ወደ ረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ወሰደኝ። በተባረኩ እጆቻቸው ምራቃቸውን በተቃጠሉት ስፍራዎች ላይ ቀቡ፤ ዱዓም አደረጉ። ቃጠሎዎቹ ወዲያውኑ ዳኑ።»

18. አንዲት ሴት ራሰ መላጣ የሆነን ወንድ ልጇን አመጣች። ረሱሉላህ በተባረኩ እጆቻቸው ራሱን ዳበሱት። ፈውስ አገኘ፤ ጸጉሩም ማደግ ጀመረ።

19. ቲርሚዚና ነሳኢ «ሱነን» በተባሉት መጽሐፎቻቸው እንዲህ ይላሉ፦ ሁለቱም ዓይኖቹ የማያዩ (ዕውር) አንድ ሰው መጥቶ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ዓይኖቼ እንዲከፈቱ ዱዓ ያድርጉልኝ» አለ። ሰይዳችንም አዝነውለት እንከን የሌለበት ውዱእ እንዲያደርግና ከዚያም ይህን ዱዓ እንዲያነብ ነገሩት፦ «ጌታዬ ሆይ! ወደ አንተ እለምናለሁ። ውድ ነብይህን ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን መካከል አድርጌ ከአንተ እጠይቃለሁ። እጅግ የምወድዎ ነብዬ ሰይዲና ሙሐመድ ሆይ! እርስዎን ወሲላ አድርጌ ወደ ጌታዬ እለምናለሁ። ለእርስዎ ክብር ሲል እንዲቀበለኝ እጠይቃለሁ። ጌታዬ ሆይ! እኚህን የላቁ ነብይ አማላጅ አድርግልኝ! ለእርሳቸው ክብር ብለህ ዱዓዬን ተቀበል!» ሰውየው ውዱእ አድርጎ ዱዓ ባደረገ ጊዜ ዓይኖቹ ተከፈቱ። ሙስሊሞች ይህን ዱዓ ሁልጊዜ አንብበዋል፤ ምኞቶቻቸውንም አግኝተዋል። 20. ረሱሉላህ ከአቡ ጧሊብ ጋር በአንድ በረሃ ይጓዙ ነበር። አቡ ጧሊብ በጣም እንደተጠሙ ተናገሩ። ረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከእንስሳው ወርደው፦ «ተጠማህን?» አሉ፤ በተባረከ ተረከዛቸውም መሬቱን መቱ። ውኃ ፈልቆ ወጣ። «አጎቴ ሆይ! ከዚህ ውኃ ጠጣ!» አሉ። 21. ወደ ሑደይቢያ በተደረገው ጉዞ ውኃው ጥቂት በሆነ ጉድጓድ አጠገብ ሰፈሩ። ወታደሮቹ ስለ ውኃ ጥም አማረሩ። አንድ ባልዲ ውኃ አስመጡ፤ ከእርሱ ውዱእ አድርገውና ተፍተውበት ወደ ጉድጓዱ እንዲፈስ አደረጉ። አንድ ፍላጻ ወስደው ወደ ጉድጓዱ ወረወሩ። ጉድጓዱ እስከ አፉ ድረስ በውኃ ሲሞላ አዩ።

22. በአንድ ዘመቻ ወታደሮቹ ስለ ውኃ ጥም አማረሩ። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ሁለት ወታደሮችን ውኃ እንዲፈልጉ ላኩ። በግመል ላይ ሁለት አቁማዳ ሙሉ ውኃ የያዘች አንዲት ሴት አይተው አመጧት። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ከሴቲቱ ጥቂት ውኃ ጠየቁ፤ በአንድ ዕቃ ውስጥም እንዲፈስ አደረጉ። ሠራዊቱ ሁሉ መጥቶ በየተራ ዕቃዎቹንና አቁማዳዎቹን ሞላ። ለሴቲቱ ጥቂት ተምር ሰጥተው የውኃ አቁማዳዎቿንም ሞሉላት።

ረሱሉላህም፦ «ከውኃሽ ምንም አልቀነስንም። ውኃውን የሰጠን አላሁ ተዓላ ነው» አሉ።

23. በመዲና ሚንበር ላይ ኹጥባ ሲያደርጉ አንድ ሰው፦ «የአላህ መልዕክተኛ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሆይ! ከውኃ እጦት የተነሣ ልጆቻችን፣ እንስሶቻችንና እርሻዎቻችን እየጠፉ ነው። ይድረሱልን!» አለ። እጆቻቸውን አንሥተው ዱዓ አደረጉ። በሰማይ አንድም ደመና ሳይኖር የተባረኩ እጆቻቸውን ፊታቸው ላይ ገና ሳያሳልፉ ደመናዎች ተሰበሰቡ። ወዲያውኑ ዝናብ ጀመረ፤ ለጥቂት ቀናትም ቀጠለ። እንደገና ሚንበር ላይ ኹጥባ ሲያደርጉ ያ ሰው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከዝናቡ የተነሣ ልንጠፋ ነው!» ባለ ጊዜ መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ፈገግ ብለው፦ «ጌታዬ ሆይ! እዝነትህን ለሌሎች ባሪያዎችህም ለግስ!» አሉ። ደመናዎቹ ተገፈው ፀሐይ ታየች። 24. ጃቢር ኢብኑ ዐብዱላህ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) እንዲህ ይላሉ፦ ብዙ ዕዳ ነበረብኝ። ለረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ነገርኳቸው። ወደ አትክልት ቦታዬ መጥተው በተምሩ ክምር ዙሪያ ሦስት ጊዜ ዞሩ። ከዚያም፦ «አበዳሪዎችህን ጥራ፤ ይምጡ!» አሉ። ለእያንዳንዳቸው መብታቸው ተሰጠ፤ ከክምሩም ምንም አልጎደለም። 25. አንዲት ሴት ማር በስጦታ ላከች። ማሩን ተቀብለው ባዶውን ዕቃ መለሱ። በአላሁ ተዓላ ችሎታ ዕቃው በማር ተሞልቶ ተመለሰ። ሴቲቱ መጥታ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ኃጢአቴ ምንድን ነው? ስጦታዬን ለምን አልተቀበሉም?» አለች። እርሳቸውም፦ «ስጦታሽን ተቀብለናል። ያየሽው ማር አላሁ ተዓላ ለስጦታሽ የሰጠው በረከት ነው» አሉ። ሴቲቱ ተደስታ ማሩን ወደ ቤቷ ወሰደች። ከቤተሰቧ ጋር ለወራት በሉት፤ ፈጽሞም አልጎደለም። አንድ ቀን ተሳስተው ማሩን በሌላ ዕቃ ውስጥ አደረጉት። ከዚያም እየበሉ ጨረሱት። ይህን ለረሱሉላህ ነገሩ። እርሳቸውም፦ «በላክሁት ዕቃ ውስጥ ቢቆይ ኖሮ ዓለም እስካለች ድረስ ይበሉት ነበር፤ ፈጽሞም አይጎድልም ነበር» አሉ።

26. አቡ ሁረይራ እንዲህ ይላሉ፦ ለረሱሉላህ ጥቂት ተምሮች አመጣሁ። በረከት እንዲሰጣቸው ዱዓ እንዲያደርጉ ጠየቅኋቸው። በረከት እንዲኖራቸው ዱዓ አደረጉና፦ «እነዚህን ውሰድ፤ በዕቃህ ውስጥ አድርጋቸው። ከእርሱ ለመውሰድ በፈለግህ ጊዜ እጅህን አስገብተህ ውሰድ፤ ገልብጠህ ከመሬት ላይ አትልቀም!» አሉኝ። ተምሮቹ ያሉበትን ከረጢቴን ሌሊትም ቀንም ከአጠገቤ ሳልለይ እስከ ዑስማን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ዘመን ድረስ ሁልጊዜ ከእርሱ በላሁ። አብረውኝ ለነበሩትም አበላሁ፤ እፍኝ ሙሉም ሰደቃ ሰጠሁ። ዑስማን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ሸሂድ በሆኑበት ቀን ከረጢቴ ጠፋ። 27. ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንደ ሱለይማን ዐለይሂ ሰላም የእንስሳትን ሁሉ ቋንቋ ይረዱ ነበር። መጥተው ስለ ባለቤታቸው ወይም ስለ ሌሎች የሚያማርሩ እንስሳት ብዙ ጊዜ ታይተዋል። ረሱሉላህ ይህን ለሶሓቦች ይነግሩ ነበር። በሑነይን ጦርነት የተቀመጡባትን «ዱልዱል» የተባለችውን ነጭ በቅሎ፦ «ተንበርከኪ!» አሏት። ዱልዱል ወዲያውኑ በተንበረከከች ጊዜ ከመሬት እፍኝ አሸዋ አንሥተው በከሓዲዎቹ ላይ በተኑ።

28. አንድ ቀን ባለቤታቸውን ሐፍሷን (ረዲየላሁ ዐንሃ)፦ «አቡበክርና አባትሽ የኡማዬን አስተዳደር በእጃቸው ይይዛሉ» አሏቸው። በዚህ ቃል አቡበክርና የሐፍሷ አባት ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ኸሊፋ እንደሚሆኑ አበሠሩ።

«ሐፍሷ ሆይ! አቡበክርና አባትሽ የኡማዬን አስተዳደር በእጃቸው ይይዛሉ» ሐዲስ ሸሪፍ

29. በመዲና በዘካ የመጡትን ተምሮች እንዲጠብቁ አቡ ሁረይራን (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) ሾመዋቸው ነበር። አቡ ሁረይራ አንድን ሰው ተምር ሲሰርቅ ያዙትና፦ «ወደ ረሱሉላህ እወስድሃለሁ» አሉት። ሌባው ግን፦ «ድሃ ነኝ፤ ቤተሰቤም ብዙ ነው» እያለ በለመነ ጊዜ ለቀቁት። በማግሥቱ ረሱሉላህ አቡ ሁረይራን ጠርተው፦ «ትናንት ሌሊት የለቀቅኸው ሰው ምን አድርጎ ነበር?» አሉ። አቡ ሁረይራ በተናገሩ ጊዜ፦ «አታልሎሃል። እንደገና ይመጣል» አሉ። በሚቀጥለው ሌሊት እንደገና መጣ፤ ተያዘም። ደግሞ እየለመነ፦ «ለአላህ ብለህ ልቀቀኝ!» አለና ተለቀቀ። በሦስተኛው ሌሊት እንደገና መጥቶ በተያዘ ጊዜ ልመናው አልጠቀመውም። ያን ጊዜ፦ «ብትለቀኝ አንዳንድ ነገሮችን አስተምርሃለሁ፤ ብዙ ይጠቅምሃል» አለ። አቡ ሁረይራ ተስማሙ። «ሌሊት ስትተኛ አየቱል ኩርሲይን ብታነብ አላሁ ተዓላ ይጠብቅሃል፤ ሰይጣንም ወደ አንተ አይቀርብም» ብሎ ሄደ። በማግሥቱ ረሱሉላህ አቡ ሁረይራን እንደገና ጠይቀው መልስ ባገኙ ጊዜ፦ «አሁን እውነት ተናግሯል። ነገር ግን እርሱ ራሱ እጅግ ውሸታም ነው። ለሦስት ሌሊት ከማን ጋር እንደተነጋገርህ ታውቃለህን?» አሉ። አቡ ሁረይራ፦ «አይ፣ አላውቅም» ባሉ ጊዜ፦ «ያ ሰው ሰይጣን ነበር» አሉ።

30. ከሩሙ ንጉሥ ሠራዊት ጋር ለመዋጋት ሙእታ ወደተባለው ስፍራ ወታደሮችን በላኩ ጊዜ ከሶሓቦች ሦስት አዛዦች (ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳ፣ ጀዕፈር ኢብኑ አቢ ጧሊብ እና ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሓ) ተከታትለው ሸሂድ መሆናቸውን፣ እርሳቸው ራሳቸው በመዲና ሚንበር ላይ ሳሉ፣ አላሁ ተዓላ አሳይቷቸው አዩ፤ አጠገባቸው ለነበሩትም ነገሩ። 31. ሙዓዝ ኢብኑ ጀበልን (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) አገረ ገዥ አድርገው ወደ የመን በላኳቸው ጊዜ እስከ መዲና ውጭ ድረስ ሸኟቸው፤ ብዙ ምክሮችንም ሰጧቸው። «ከአሁን በኋላ አንተና እኔ እስከ ቂያማ ድረስ አንገናኝም» አሉ። ሙዓዝ በየመን ሳሉ ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በመዲና አረፉ።

32. ሊያርፉ ሲሉ ልጃቸውን ፋጢማን፦ «ከዘመዶቼ መካከል መጀመሪያ ከእኔ ጋር የምትገናኚው አንቺ ነሽ» አሏቸው። ከስድስት ወር በኋላ ፋጢማ (ረዲየላሁ ዐንሃ) አረፉ። ከዘመዶቻቸው መካከል ከእርሳቸው በፊት ማንም አላረፈም።

33. ቀይስ ኢብኑ ሸማስን (ረዲየላሁ ዐንሁ)፦ «መልካም ሆነህ ትኖራለህ፤ ሸሂድ ሆነህም ትሞታለህ» አሏቸው። አቡበክር (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) ኸሊፋ ሳሉ በየማማ ከሙሰይሊማ አል-ከዛብ ጋር በተደረገው ጦርነት ሸሂድ ሆኑ። ሰይዲና ዑመር አል-ፋሩቅ፣ ሰይዲና ዑስማን እና ሰይዲና ዐሊይ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁም አጅመዒን) ሸሂድ እንደሚሆኑም ተናገሩ። 34. የፋርስ ንጉሥ የኪስራና የሩሙ ንጉሥ የቄሳር አገሮች በሙስሊሞች እጅ እንደሚገቡና ግምጃ ቤቶቻቸውም በአላህ መንገድ እንደሚከፋፈሉ አበሠሩ። 35. ከኡማቸው ብዙ ሰዎች በባሕር ለዘመቻ እንደሚሄዱና ከሶሓቦች የሆኑት ኡሙ ሐራም የተባሉ እመቤት በዘመቻው እንደሚገኙ ተናገሩ። ሰይዲና ዑስማን ኸሊፋ ሳሉ ሙስሊሞች በመርከቦች ወደ ቆጵሮስ ደሴት ሄደው ተዋጉ። እኚህ እመቤትም ከእነርሱ ጋር ነበሩ። በዚያም ሸሂድ ሆኑ።3

36. መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም አንድ ቀን ከፍ ባለ ስፍራ ተቀምጠው ነበር። ወደ አጠገባቸው ወዳሉት ዞረው፦ «እኔ የማየውን እናንተም ታያላችሁን? በቤቶቻችሁ መካከል፣ በመንገዶች ላይ የሚነሡትን ፊትናዎች እንደማይ እምላለሁ» አሉ። ዑስማን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ሸሂድ በተደረጉበት ቀናትና ከዚያም በኋላ በየዚድ ዘመን በመዲና ታላላቅ ፊትናዎች ተነሡ። በመንገዶች ላይ የብዙ ሰዎች ደም ፈሰሰ።

37. አንድ ቀን ከራሳቸው ባለቤቶች አንዷ በኸሊፋው ላይ እንደሚያምፁ ተናገሩ። ዓኢሻ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሃ) በዚህ ቃል በሳቁ ጊዜ፦ «ሑመይራ4 ሆይ! ይህን ቃሌን አትርሺ! ይህች ሴት አንቺ እንዳትሆኚ!» አሉ። ከዚያም ወደ ዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ዞረው፦ «የእርሷ ጉዳይ በእጅህ ቢወድቅ በለስላሳ ሁኔታ ያዛት!» አሉ። ከሠላሳ ዓመት በኋላ ዓኢሻ (ረዲየላሁ ዐንሃ) ከዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ጋር ተዋጉ፤ በእርሳቸውም ተማረኩ። ዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በክብርና በአክብሮት ከበስራ ወደ መዲና ላኳቸው።

38. ሰይዲና ሙዓዊያን፦ «አንድ ቀን በኡማዬ ላይ ገዥ ብትሆን መልካም የሚሠሩትን ሸልም! ክፉ የሚያደርጉትንም ይቅር በል!» አሏቸው። ሰይዲና ሙዓዊያ በሰይዲና ዑመርና በሰይዲና ዑስማን ዘመን በደማስቆ ሃያ ዓመት አገረ ገዥ፣ ከዚያም ሃያ ዓመት ኸሊፋ ሆኑ። 39. አንድ ቀን፦ «ሙዓዊያ ፈጽሞ አይሸነፍም» አሉ። ዐሊይ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) በሲፊን ጦርነት ይህን ሐዲስ በሰሙ ጊዜ፦ «ቀደም ብዬ ሰምቼው ቢሆን ኖሮ ከሙዓዊያ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) ጋር አልዋጋም ነበር» አሉ። 40. ዐማር ኢብኑ ያሲርን (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ)፦ «አንተን በመሪ ላይ የሚያምፁና የማይታዘዙ ሰዎች ይገድሉሃል» አሏቸው። ከዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ጋር ሆነው ሙዓዊያን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ሲዋጉ ሸሂድ ሆኑ። 41. የልጃቸው የፋጢማ ልጅ ስለሆኑት ሐሰን (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁማ)፦ «ይህ ልጄ እጅግ በላጭ ነው። አላሁ ተዓላ በሁለት ታላላቅ የሙስሊሞች ሠራዊቶች መካከል ለሚደረገው ዕርቅ እርሱን ምክንያት ያደርገዋል» አሉ። ሐሰን በታላቅ ሠራዊት ሙዓዊያን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ሊዋጉ በተነሡ ጊዜ ፊትናን ለመከላከልና የሙስሊሞች ደም እንዳይፈስ መብታቸው የነበረውን ኺላፋ ለሙዓዊያ (ረዲየላሁ ዐንሁ) አስረከቡ። 42. ዐብዱላህ ኢብኑ ዙበይር (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁማ) ረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ዋግምት ሲደረጉ የወጣውን ደማቸውን ጠጡ። ይህን ባዩ ጊዜ፦ «ከሰዎች በአንተ ላይ ምን እንደሚደርስ ታውቃለህን? ከአንተም በሰዎች ላይ ብዙ ነገር ይደርሳል። የጀሀነም እሳት አያቃጥልህም» አሉ። ዐብዱላህ ኢብኑ ዙበይር በመካ ኸሊፋነታቸውን ባወጁ ጊዜ ዐብዱልመሊክ ኢብኑ መርዋን ከደማስቆ ሐጃጅን በታላቅ ሠራዊት ወደ መካ ላከ። ዐብዱላህን ይዘው ገደሏቸው። 43. የዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስን እናት ተመልክተው፦ «ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ። በተወለደ ጊዜ ወደ እኔ አምጪው!» አሉ። ልጁን ባመጡ ጊዜ በጆሮው አዛንና ኢቃማ አድርገው ከተባረከ አፋቸው ምራቅ በአፉ ውስጥ ቀቡለት። ስሙን ዐብዱላህ ብለው ለእናቱ እቅፍ ሰጡና፦ «የኸሊፋዎቹን አባት ውሰጂው!» አሉ። የልጁ አባት ሰይዲና ዐባስ ይህን ሰምተው መጥተው በጠየቁ ጊዜ፦ «አዎ፣ እንዲህ አልኩ። ይህ ልጅ የኸሊፋዎቹ አባት ነው። ከእነርሱ መካከል ሰፋሕ፣ መህዲና ከዒሳ ዐለይሂ ሰላም ጋር ሶላት የሚሰግድ ሰው ይገኛሉ» አሉ። በዐባሲዮች መንግሥት ራስ ላይ ብዙ ኸሊፋዎች መጡ። እነዚህ ሁሉ ከዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ ዘር የተገኙ ነበሩ።

«ሙዓዊያ ሆይ! አንድ ቀን በኡማዬ ላይ ገዥ ብትሆን መልካም የሚሠሩትን ሸልም! ክፉ የሚያደርጉትንም ይቅር በል!» ሐዲስ ሸሪፍ

44. አንድ ቀን፦ «በኡማዬ መካከል ራፊዲ የሚባሉ ብዙ ሰዎች ይነሣሉ። እነርሱ ከእስልምና ሃይማኖት ይለያሉ» አሉ።

45. ለብዙ ሶሓቦቻቸው መልካም ዱዓዎችን አደረጉ፤ ሁሉም ተቀባይነት አግኝተው ፍሬያቸውን አዩ። ዐሊይ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) እንዲህ ይላሉ፦ ረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ቃዲ (ዳኛ) አድርገው ወደ የመን ሊልኩኝ ፈለጉ። «የአላህ መልዕክተኛ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሆይ! እኔ ዳኝነት እንዴት እንደሚሠራ አላውቅም» አልኩ። የተባረከ እጃቸውን ደረቴ ላይ አድርገው፦ «ጌታዬ ሆይ! ለልቡ ትክክለኛውን ነገር አሳውቀው። ሁልጊዜ እውነትን መናገርን ለግሰው!» አሉ። ከዚህ በኋላ ወደ እኔ ከሚመጡት ከሳሾች ትክክለኛውን ወዲያውኑ እረዳ፣ በሐቅም እፈርድ ነበር።

46. ረሱሉላህ ወደ ጀነት እንደሚገቡ ያበሰሯቸው አሥር ሰዎች «ዐሸረቱል ሙበሸራ» ይባላሉ። ከእነርሱ አንዱ ለሆኑት ለሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በኡሑድ ጦርነት፦ «ጌታዬ ሆይ! ፍላጻዎቹን ዒላማቸው ላይ አድርስ፤ ዱዓዎቹንም ተቀበል!» አሉ። ከዚህ በኋላ የሰዕድ ዱዓ ሁሉ ተቀባይነት አገኘ፤ የወረወሩትም ፍላጻ ሁሉ ጠላትን መታ።

47. የአጎታቸውን ልጅ የዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስን ግንባር ላይ የተባረከ እጃቸውን አድርገው፦ «ጌታዬ ሆይ! ይህን በሃይማኖት ጥልቅ ዓሊም አድርገው፤ የጥበብ ባለቤት አድርገው! የቁርኣን ከሪምን ዕውቀቶች ለግሰው!» አሉ። ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ ከዚህ በኋላ በዕውቀቶች ሁሉ፣ በተለይም በተፍሲር፣ በሐዲስና በፊቅህ ዕውቀቶች በዘመናቸው ብቸኛ ሆኑ። ሶሓቦችና ታቢዒኖች ሁሉንም ነገር ከእርሳቸው ይማሩ ነበር። «ተርጁማኑል ቁርኣን»፣ «በሕሩል ዒልም» እና «ረኢሱል ሙፈሲሪን» በሚሉ ስሞች ታወቁ፤ የእስልምና አገሮችም በተማሪዎቻቸው ተሞሉ።5

48. ከአገልጋዮቻቸው አንዱ ለሆኑት ለአነስ ኢብኑ ማሊክ፦ «ጌታዬ ሆይ! ገንዘቡንና ልጆቹን አብዛለት፣ ዕድሜውን አርዝምለት፣ ኃጢአቶቹንም ይቅር በልለት!» ብለው ዱዓ አደረጉ። ጊዜ በሄደ ቁጥር ገንዘባቸውና ንብረታቸው በዛ። ዛፎቻቸውና የወይን ቦታዎቻቸው በየዓመቱ ፍሬ ሰጡ። እጅግ ብዙ ልጆች ወለዱ። መቶ አሥር ዓመት ኖሩ። በዕድሜያቸው መጨረሻ፦ «ጌታዬ ሆይ! ሐቢብህ ለእኔ ካደረጓቸው ዱዓዎች ሦስቱን ተቀበልክ፤ ለገስክልኝም! አራተኛው የሆነው የኃጢአቶቼ ይቅር መባል እንግዲህ እንዴት ይሆን?» ባሉ ጊዜ፦ «አራተኛውንም ተቀብያለሁ። ልብህ ይረጋጋ!» የሚል ድምፅ ሰሙ።

«ጌታዬ ሆይ! ይህን (ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስን) በሃይማኖት ጥልቅ ዓሊም አድርገው፤ የጥበብ ባለቤት አድርገው! የቁርኣን ከሪምን ዕውቀቶች ለግሰው!» ሐዲስ ሸሪፍ

49. ለማሊክ ኢብኑ ረቢዓ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ)፦ «ልጆችህ የተባረኩ ይሁኑ!» ብለው ዱዓ አደረጉ። ሰማንያ ወንዶች ልጆች ወለዱ።

50. ናቢጋ የተባሉት ታዋቂ ገጣሚ ከግጥሞቻቸው ጥቂቶቹን ባነበቡ ጊዜ በዓረቦች ዘንድ የታወቀውን «አላሁ ተዓላ ጥርሶችህን አያርግፋቸው!» የሚለውን ዱዓ አደረጉላቸው። ናቢጋ መቶ ዓመት ሆኗቸው ነበር፤ ጥርሶቻቸው ግን ነጭና ጥርት ያሉ ሆነው እንደ ዕንቁ ተደርድረው ይታዩ ነበር። 51. ለዑርዋ ኢብኑ ጀዕድ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ)፦ «ጌታዬ ሆይ! በንግዱ ላይ በረከትን ስጥ!» አሉ። ዑርዋ እንዲህ ይላሉ፦ «ከዚህ በኋላ ያደረግኋቸው ንግዶች ሁሉ ትርፋማ ሆኑ። ፈጽሞ አልከሰርኩም።» 52. አንድ ቀን የራሳቸው ልጅ ፋጢማ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሃ) ወደ እርሳቸው መጡ። ከረሃብ የተነሣ መልካቸው ገርጥቶ ነበር። እጃቸውን በልጃቸው ደረት ላይ አድርገው፦ «የተራቡትን የምታጠግብ ጌታዬ ሆይ! የሙሐመድን ልጅ ፋጢማን ተርባ አትተዋት!» አሉ። የፋጢማ ፊት ወዲያውኑ ደም ገባበት፤ ነፍስም ዘሩ። እስኪያርፉ ድረስ ፈጽሞ ረሃብ አልተሰማቸውም።

53. ከዐሸረቱል ሙበሸራ አንዱ ለሆኑት ለዐብዱረሕማን ኢብኑ ዐውፍ በረከትን ለምነው ዱዓ አደረጉ። ገንዘባቸው እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ የሰዎች መነጋገሪያ ሆነ።

54. «የእያንዳንዱ ነብይ ዱዓ ተቀባይነት ያገኛል። እያንዳንዱ ነብይ ለኡማቸው በዱንያ ዱዓ አድርገዋል። እኔ ግን በቂያማ ቀን ለኡማዬ ሸፋዐ እንዳደርግ ፈቃድ እንዲሰጠኝ ዱዓ አደርጋለሁ። ኢንሻአላህ ዱዓዬ ተቀባይነት ያገኛል። አጋሪ ላልሆኑት ሁሉ ሸፋዐ አደርጋለሁ» አሉ።

55. በመካ አካባቢ ወዳሉ አንዳንድ መንደሮች ሄደው እንዲያምኑ እጅግ ጣሩ። አልተቀበሉም። በዩሱፍ ነብይ (ዐለይሂ ሶላቱ ወሰላም) ዘመን በግብጽ እንደታየው ረሃብ ያለ ችግር እንዲደርስባቸው ዱዓ አደረጉ። በዚያ ዓመት በዚያ አካባቢ ሬሳ እስኪበሉ ድረስ ረሃብ ሆነ። 56. የአጎታቸው የአቡ ለሀብ ልጅ ዑተይባ የረሱሉላህ (ዐለይሂ ሶላቱ ወሰላም) አማች ሆኖ ሳለ በረሱሉላህ አላመነም፤ እኒያንም መሪ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እጅግ አሳዘናቸው። የተባረከች ልጃቸውን እመቤት ኡሙ ኩልሱምን ፈታ፤ አስጸያፊ ነገሮችንም ተናገረ። በዚህ እጅግ አዝነው፦ «ጌታዬ ሆይ! ከውሾችህ አንዱን በእርሱ ላይ ላክበት!» አሉ። ዑተይባ ለንግድ ወደ ሻም ሲሄድ አንድ ሌሊት በጓደኞቹ መካከል ተኝቶ ነበር። አንድ አንበሳ መጥቶ ጓደኞቹን አሽትቶ ተዋቸው። ተራው ወደ ዑተይባ በደረሰ ጊዜ ነጥቆ ቦጫጨቀው። 57. አንድ ሰው በግራ እጁ ምግብ ይበላ ነበር። «በቀኝ እጅህ ብላ!» አሉት። ሰውየውም፦ «ቀኝ ክንዴ አይንቀሳቀስም» ብሎ ዋሸ። «እንግዲያውስ ቀኝ እጅህ ከእንግዲህ አይንቀሳቀስ!» አሉ።6 ያ ሰው እስኪሞት ድረስ ቀኝ እጁን ወደ አፉ ማድረስ አልቻለም።

58. የፋርስ ንጉሥ ኹስረው ፐርቪዝ እንዲያምን ደብዳቤ ላኩለት። ወራዳው ኹስረው ደብዳቤውን ቀደደ፤ ያመጣውንም መልዕክተኛ ሸሂድ አደረገ። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ «ጌታዬ ሆይ! ደብዳቤዬን እንደቀደደ ሁሉ ንግሥናውን ቀዳደው!» አሉ። ረሱሉላህ በሕይወት ሳሉ ልጁ ሺረወይህ ኹስረውን በጩቤ ቆራረጠው። ዑመር (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) ኸሊፋ ሳሉ ደግሞ ሙስሊሞች የፋርስን አገር በሙሉ ድል አደረጉ፤ ከኹስረውም ዘርም ንግሥናም አልቀረም።

59. መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም በገበያ ውስጥ በመልካም ሲያዝዙና ከመጥፎ ሲከለክሉ፣ ምክርም ሲሰጡ የመርዋን አባት የሆነው ሐከም ኢብኑ አቢል ዓስ የተባለ ወራዳ ሰው ከረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ኋላ እየመጣ ዓይኖቹን እየከፈተና እየዘጋ፣ ፊቱንም እያጨማደደ ያፌዝባቸው ነበር። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ወደ ኋላ ዞረው ይህን አስቀያሚ ሁኔታውን ባዩ ጊዜ፦ «ራስህን ባሳየህበት ሁኔታ ቅር!» አሉ። እስኪሞት ድረስ የዚያ ሰው ፊትና ዓይኖች ሲርገበገቡ ቀሩ። 60. አላሁ ተዓላ ሐቢቡን ከመከራዎች ይጠብቅ ነበር። አቡ ጀህል የረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ታላቁ ጠላት ነበር። የተባረከ ራሳቸውን ለመምታት አንድ ትልቅ ድንጋይ ባነሣ ጊዜ በረሱሉላህ ሁለቱም ትከሻዎች ላይ በእያንዳንዳቸው አንድ እባብ አየ፤ ድንጋዩ ከእጁ ወደቀ፤ ሸሸም።

61. በካዕባ አል-ሙዐዘማ አጠገብ ሶላት ሲሰግዱ ወራዳው አቡ ጀህል እንደገና፦ «አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው» ብሎ በቢላዋ ወደ እርሳቸው ሊሄድ ሲል ድንገት ወደ ኋላ ዞሮ ሸሸ። ጓደኞቹ፦ «ለምን ፈራህ?» ባሉት ጊዜ፦ «በሙሐመድ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እና በእኔ መካከል እሳት የሞላበት ቦይ አየሁ። ብዙ ሰዎች ይጠብቁኝ ነበር። አንድ እርምጃ ብራመድ ኖሮ ይዘው ወደ እሳቱ ይጥሉኝ ነበር» አለ። ሙስሊሞች ይህን ሰምተው ረሱሉላህን (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በጠየቁ ጊዜ፦ «የአላሁ ተዓላ መላእክት ይዘው ይቆራርጡት ነበር» አሉ።

62. በሂጅራ አራተኛው ዓመት በበኑ ነዲር ዘንድ ረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከሶሓቦቻቸው ጋር በአይሁዶቹ ምሽግ ግድግዳ ሥር ሲነጋገሩ አንድ አይሁዳዊ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ ከላይ ሊጥልባቸው ፈለገ። ወደ ድንጋዩ እጁን በዘረጋ ጊዜ ሁለቱም እጆቹ ሽባ ሆኑ። 63. በሂጅራ ዘጠነኛው ዓመት ከሩቅ ቦታዎች ሰዎች እየጎረፉ መጥተው ያምኑ ነበር። ዓሚር እና አርበድ የተባሉ ሁለት ከሓዲዎች ከመጡት ሰዎች ጋር ተቀላቀሉ። ዓሚር ለረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ለማመን እንደመጡ ሲናገር አርበድ ወደ ኋላቸው ሄዶ ሰይፉን ከሰገባው ሊመዝዝ ፈለገ። እጁ ግን አልታዘዘውም። ዓሚር ከፊት ለፊት «ምን ትጠብቃለህ?» ለማለት በምልክት ባሳየው ጊዜ መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም፦ «አላሁ ተዓላ ከሁለታችሁ ጉዳት ጠበቀኝ» አሉ። ከዚያ ስፍራ በተለዩ ጊዜ ዓሚር አርበድን፦ «ለምን ቃልህን አልጠበቅህም?» አለው። እርሱም፦ «ምን ላድርግ? ሰይፉን ለመምዘዝ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! ሁልጊዜ አንተን በሁለታችን መካከል አየሁ» አለ። ከጥቂት ቀናት በኋላ አየሩ ጥርት ያለ ሆኖ ሳለ ድንገት ደመና ሸፈነ። አርበድ ላይ መብረቅ ወድቆ ከግመሉ ጋር ሞተ።

64. መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም አንድ ቀን ውዱእ አድርገው ከቆዳ ካልሲዎቻቸው አንዱን አጥልቀው ሁለተኛውን ለማንሣት እጃቸውን ሲዘረጉ አንዲት ወፍ ካልሲውን ነጥቃ በአየር ላይ አራገፈችው። ከውስጡ አንድ እባብ ወደቀ። ከዚያም ወፏ ካልሲውን መሬት ላይ ጣለችው። ከዚህ ቀን ጀምሮ ጫማ ሲለበስ በመጀመሪያ ማራገፍ ሱና ሆነ። 65. መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም በዘመቻዎችና በበረሃዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ ከሶሓቦቻቸው ጠባቂዎችን መድበው ነበር። በሱረቱ አል-ማኢዳ ውስጥ ያለው ትርጓሜው «አላህ ከሰዎች ጉዳት ይጠብቅሃል» የሆነው 67ኛው ክቡር አንቀጽ በወረደ ጊዜ ይህን ተዉ። በጠላቶች መካከል ብቻቸውን ይዘዋወሩ፣ ብቻቸውን ይተኙ ነበር፤ ምንም አይፈሩም ነበር።

«የተከበርክ ነብይ ሆይ! አላህ ከሰዎች ጉዳት ይጠብቅሃል» ማኢዳ: 67

66. ሰይዲና አነስ እንዲህ ይላሉ፦ ረሱሉላህ የተባረከ ፊታቸውን የሚያብሱበት መሐረብ ነበራቸው። በእርሱ ፊታቸውን ያብሱ ነበር፤ በቆሸሸ ጊዜም እሳት ውስጥ ይጥሉት ነበር። ቆሻሻው ይቃጠል ነበር፤ መሐረቡ ግን አይቃጠልም ነበር፤ ፍጹም ንጹሕ ሆኖ ይወጣ ነበር። 67. ከአንድ ጉድጓድ ውኃ በባልዲ ቀድተው ከባልዲው ጠጡ፤ የተረፈውንም ወደ ጉድጓዱ መለሱት። ከዚያ በኋላ ከጉድጓዱ ሁልጊዜ የሚስክ መዓዛ ይወጣ ነበር። 68. በዑትባ ኢብኑ ፈርቀድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ሰውነት ላይ ቀፎ (ኡርቲከር) የሚባል በሽታ ወጣ። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ልብሳቸውን አስወልቀው በራሳቸው የተባረኩ እጆች ላይ ተፍተው ሰውነታቸውን በእጆቻቸው ዳበሱ። ሕመምተኛው ፈውስ አገኙ። ሰውነታቸው እንደ ሚስክ ይሸት ነበር፤ ይህም ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ቀጠለ። 69. መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ሶላት ሲሰግዱ ሰይጣን መጥቶ ሶላታቸውን ሊያበላሽ በፈለገ ጊዜ በተባረኩ እጆቻቸው ያዙት። ዳግመኛ መጥቶ ሶላቱን እንደማያበላሽ ቃል አስገብተውት ለቀቁት።

70. በመዲና የመናፍቃን አለቃ የነበረው ዐብዱላህ ኢብኑ ኡበይ ኢብኑ ሰሉል ሊሞት በተቃረበ ጊዜ ረሱሉላህን አስጠራቸው። «የለበሱትን ቀሚስ ከፈኔ ያድርጉልኝ» ብሎ ለመነ። የተጠየቁትን ሁሉ መስጠት ልማዳቸው ስለነበረ ቀሚሳቸውን ለገሱት። የጀናዛ ሶላቱንም እንኳ ሰገዱለት። በመዲና የነበሩ አንድ ሺህ መናፍቃን በዚህ የረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ልግስና ተደንቀው ሁሉም ወደ ኢማን መጡ። 71. ከቁረይሽ ከሓዲዎች መካከል ወሊድ ኢብኑል ሙጊራ፣ ዓስ ኢብኑ ዋኢል፣ ሐሪስ ኢብኑ ቀይስ፣ አስወድ ኢብኑ የጉስ እና አስወድ ኢብኑ ሙጠሊብ ረሱሉላህን (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በማሰቃየትና በማስጨነቅ ከሌሎች ሁሉ ያለፉ ነበሩ። ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም መጥተው ትርጓሜው «በአንተ የሚያላግጡትን ቅጣታቸውን እንሰጣቸዋለን…» የሆነውን የሱረቱ አል-ሒጅር 95ኛ አንቀጽ አመጡ፤ ወደ ወሊድ እግር፣ ወደ ሁለተኛው ተረከዝ፣ ወደ ሦስተኛው አፍንጫ፣ ወደ አራተኛው ራስና ወደ አምስተኛው ዓይኖች አመለከቱ። በወሊድ እግር ላይ ፍላጻ ተሰካ። እጅግ ትዕቢተኛ ስለነበረ ጎንበስ ብሎ ፍላጻውን አውጥቶ መጣል ከብዶት ተወው። ብረቱ በተረከዙ ጅማት ውስጥ ገብቶ በሲያቲካ በሽታ ተያዘ። በዓስ ተረከዝ ላይ እሾህ ተሰካ፤ እንደ አቁማዳ አበጠ። ከሐሪስ አፍንጫ ያለማቋረጥ ደም ፈሰሰ። አስወድ ከአንድ ዛፍ ሥር ተደስቶ ተቀምጦ ሳለ ራሱን ዛፉ ላይ አጋጨ፤ ሌላኛው አስወድ ደግሞ ታወረ፤ ሁሉም ጠፉ።

72. በመዲና ከበኑ ነጃር ጎሳ የሆነች እጅግ ውብ ሴት ነበረች። አንድ ጂን በእርሷ ፍቅር ተይዞ ሁልጊዜ ይመጣ ነበር። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ወደ መዲና ከመጡ በኋላ አንድ ቀን ይህ ጂን በሴቲቱ ቤት ፊት ለፊት ባለው ግድግዳ ላይ ተቀምጦ ሳለ ሴቲቱ አወቀችው። «ለምን ወደ እኔ መምጣት ተውክ?» አለች። ጂኑም፦ «የአላሁ ተዓላ ነብይ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ዝሙትንና ሐራሞችን ሁሉ ከልክለዋል» አለ።

73. ቢእሩ መዑና በተባለው ጦርነት ከሓዲዎቹ የሰጡትን ቃል አፍርሰው ከሰባ ሶሓቦች ከአንድ ሁለቱ በስተቀር ሁሉንም ሸሂድ አደረጉ። ከእነርሱ መካከል የአቡበክር (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባሪያ ሆነው ሳሉ ነጻ ያወጧቸውና በመጀመሪያ ካመኑት አንዱ የሆኑትን ዓሚር ኢብኑ ፉሀይራን (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) በጦር በወጓቸው ጊዜ በከሓዲዎቹ ዓይን ፊት መላእክት ወደ ሰማይ አነሷቸው። ይህን ለረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በነገሯቸው ጊዜ፦ «እርሱን የጀነት መላእክት ቀበሩት፤ ነፍሱም ወደ ጀነት ወጣች» አሉ።

74. ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) በኸንደቅ (የቦይ) ጦርነት ቆሰሉ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አረፉ። በጀናዛ ሶላታቸው ሰባ ሺህ መላእክት እንደተገኙ ረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ተናገሩ። ቀብራቸው ሲቆፈር በየአቅጣጫው የሚስክ መዓዛ ተሰራጨ። 75. ከረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ባለቤቶች አንዷ የሆኑት ኡሙ ሰለማ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሃ) ነጻ ያወጧቸው ሰፊና የተባሉ ሶሓቢይ ከረሱሉላህ አገልግሎት ፈጽሞ አይለዩም ነበር። በሩሞች ላይ በተደረገ ዘመቻ ከሠራዊቱ ተለይተው በከሓዲዎች ተማረኩ። አምልጠው ሲመለሱ አንድ አስፈሪ አንበሳ ፊት ለፊት ገጠማቸው። «እኔ የረሱሉላህ አገልጋይ ነኝ» ብለው የደረሰባቸውን ለአንበሳው ነገሩት። አንበሳውም ፊቱንና ዓይኑን በእርሳቸው ላይ አሻሽቶ አጠገባቸው ሄደ። ከጠላት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከአጠገባቸው አልተለየም። የእስልምና ሠራዊት በታየ ጊዜ ዞሮ ሄደ። 76. ጀህጃህ አል-ጊፋሪ የተባለ አንድ ሰው በኸሊፋው ዑስማን (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) ላይ አመፀ። ረሱሉላህ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሁልጊዜ በእጃቸው ይይዙት የነበረውን በትር በጉልበቱ ሰበረው። ከአንድ ዓመት በኋላ በጉልበቱ ላይ ሺር ፐንጀ (አንትራክስ) የተባለ በሽታ ተከስቶ ለሞቱ ምክንያት ሆነ።

77. ሙዓዊያ (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁ) ከደማስቆ ለሐጅ መጥተው በመዲና የሚገኘውን የረሱሉላህን (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የተባረከ ሚንበር ለበረከት ወደ ደማስቆ ሊወስዱ ፈለጉ። ሚንበሩን ከቦታው ባንቀሳቀሱት ጊዜ ፀሐይ ጨለመች። በየአቅጣጫው ጨልሞ ከዋክብት ታዩ። ይህን ፍላጎታቸውን ተዉ። 78. በኡሑድ ጦርነት የአቡ ቀታዳ አንዱ ዓይን ወጥቶ ጉንጫቸው ላይ ወደቀ። ወደ ረሱሉላህ አመጧቸው። በተባረከ እጃቸው ዓይኑን ወደ ቦታው መልሰው፦ «ጌታዬ ሆይ! ዓይኑን ውብ አድርገው!» አሉ። ይህ ዓይን ከሌላው ይበልጥ ውብ ሆነ፤ ከእርሱም ይበልጥ አጥርቶ ያይ ነበር። ከአቡ ቀታዳ የልጅ ልጆች አንዱ ወደ ኸሊፋው ዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ መጣ። ኸሊፋውም፦ «አንተ ማን ነህ?» አሉት። እርሱም አንድ ቤት ግጥም አንብቦ ረሱሉላህ በተባረከ እጃቸው ዓይኑን ወደ ቦታው የመለሱለት ሰው የልጅ ልጅ መሆኑን አሳወቀ። ኸሊፋው እነዚህን ስንኞች በሰሙ ጊዜ እጅግ አከበሩት፤ ብዙ ስጦታም ሰጡት። 79. ኢያስ ኢብኑ ሰለማ እንዲህ ይላሉ፦ በኸይበር ዘመቻ ረሱሉላህ ልከውኝ ዐሊይን (ረዲየላሁ ዐንሁ) አስጠሩ። የዐሊይ ዓይኖች ታመው ነበር። እጃቸውን ይዤ በችግር አመጣኋቸው። በተባረኩ ጣቶቻቸው ላይ ተፍተው የዐሊይን ዓይኖች ቀቡ። ባንዲራውን በእጃቸው ሰጥተው በኸይበር በር እንዲዋጉ ላኳቸው። ለረጅም ጊዜ ሊከፈት ያልቻለውን በር ዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ከቦታው ነቀሉት፤ ሶሓቦችም ወደ ምሽጉ ገቡ። 80. ክቡር ረሱሉላህ አንድ ቀን የልጃቸውን የሰይደቲና ፋጢማን ቤት ጎብኝተው ሁኔታቸውን ጠየቁ። ሰይደቲና ፋጢማም፦ «አባዬ! ከሦስት ቀን ጀምሮ ከልጆቼ ጋር ምንም አልበላንም፣ አልጠጣንም። ረሃብን እየታገሥን ነው። የእኔ ነገር አያሳስብም። ነገር ግን የሐሰንና የሑሰይን ሁኔታ እጅግ ያሳዝነኛል» ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ የዓለም መሪ፦ «ፋጢማ ሆይ! ውድ ልጄ! አንቺ ከሦስት ቀን ጀምሮ ተርበሻል። እኔ ግን ከአራት ቀን ጀምሮ ተርቤአለሁ» አሉ። የተባረኩት የልጅ ልጆቻቸው ሰይዲና ሐሰንና ሑሰይን በመራባቸው እጅግ አዘኑ… 81. ሰይዲና ዐሊይ ሠርተው አግኝተው ለተባረኩት ልጆቻቸው አንድ ነገር ለመግዛትና እነርሱን ለማጥገብ ተነሡ። ከመዲና ወጥተው ሳሉ በአንድ ጉድጓድ አጠገብ ግመሎቹን ውኃ ለማጠጣት የሚሞክር አንድ የገጠር ሰው አዩ። ወደ እርሱ ቀርበው፦ «አንተ ዓረብ ሆይ! ግመሎችህን በክፍያ የሚያጠጣልህ ሰው ያስፈልግሃልን?» አሉ። የገጠሩ ሰው፦ «አዎ። እኔም እንደዚህ ያለ ሰው እፈልግ ነበር። ከፈለግህ ና፣ ግመሎቼን አጠጣ! ለምትቀዳው ለእያንዳንዱ ባልዲ ሦስት ተምር እሰጥሃለሁ» አለ። ሰይዲና ዐሊይ ተቀብለው ውኃ መቅዳት ጀመሩ። ዘጠኝ ባልዲ አውጥተው ነበር፤ ድንገት የባልዲው ገመድ ተበጠሰ፤ ባልዲውም ጉድጓዱ ውስጥ ቀረ። ይህን ያየው የገጠር ሰው በቁጣ ከቦታው ተነሥቶ የሰይዲና ዐሊይን ፊት በእጁ የመምታት መጥፎ ዕድል ገጠመው። ከዚያም ለስምንት ባልዲ ውኃ ሃያ አራት ተምር ሰጠ። በዚህ እጅግ ያዘኑት ሰይዲና ዐሊይ እጆቻቸውን ወደ ጉድጓዱ ዘረጉ። በውስጡ ያለውን ባልዲ አውጥተው በጉድጓዱ አፍ ላይ አስቀመጡትና ከዚያ ሄዱ። የገጠሩ ሰው በመደነቅ ደርቆ ቀረ! እጃቸው የዚህን ያህል ጥልቅ የሆነ ጉድጓድ ታች እንዴት ደረሰ?!.. ወይስ እኚህ ሰው መምጣቱ የተነገረለት ሃይማኖት ተከታይ ናቸውን? በእነዚህ ሐሳቦች ውስጥ ተደናግጦ የገጠሩ ሰው፦ «የእርሳቸው ነብይ እውነተኛ ነብይ ናቸው። አመንኩ!» አለ። ጥቂት ቀደም ብለው ባሳዩት ድፍረትና በፈጸሙት ታላቅ ወንጀል ተጸጸቱ። «በእንደዚህ ያለ ሰው ላይ የተነሡ እጆች መቆረጥ፣ አጥንቶቻቸውም መሰበር አለባቸው» ብለው ሰይፋቸውን በአንድ እጃቸው ይዘው በሌላኛው አንጓቸው ላይ በኃይል አሳረፉት… የፈለጉት ሆነ። እጅግ ታላቅ ሕመም ተሰማቸው፤ ነገር ግን አሁን ልባቸው ረጋ። የተቆረጠውን እጃቸውን በሌላኛው እጃቸው ይዘው በቀጥታ ወደ መስጂደ ነበዊ መጡ። ሶሓቦችን ነብያቸው የት እንዳሉ ጠየቁ። ወደ ልጃቸው እንደሄዱ ነገሯቸው። የሰይደቲና ፋጢማን ቤት ጠይቀው ሄዱ። በዚያን ጊዜ ክቡር ነብያችን የልጅ ልጆቻቸውን ሰይዲና ሐሰንንና ሰይዲና ሑሰይንን በተባረኩ ጉልበቶቻቸው ላይ አስቀምጠው ዐሊይ ያመጧቸውን ተምሮች ያበሏቸው ነበር። የገጠሩ ሰው የሠሩትን ስሕተት ታላቅነት ባሰቡ ቁጥር ሊያብዱ እስኪደርሱ ድረስ ይጨነቁ ነበር፤ ከዓይኖቻቸውም እንደ ምንጭ እንባ ያፈስሱ ነበር። በዚህ ሁኔታ ወደ ሰይደቲና ፋጢማ ቤት መጥተው በሩን አንኳኩ። ከውስጥ የዓለማት ሰይድ እንደ ፀሐይ ኑር እየፈነጠቁ ወደ ውጭ ወጡ። የገጠሩ ሰው ሰይዳችንን እንዳዩ፦ «አመንኩ፤ እርስዎ የአላህ መልዕክተኛ ነዎት! ባደረግሁት ተጸጽቻለሁ፤ ይቅር ይበሉኝ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!» እያሉ ተማጸኑ። ውዱ ነብያችን፦ «እጅህን ለምን ቆረጥከው?» ብለው በጠየቋቸው ጊዜ፦ «በእርስዎ ያመነውን የተባረከ ፊት የመታውን ይህን እጅ መሸከም ስላፈርኩ ነው!.. ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!» አሉ። የእዝነት ውቅያኖስ የሆኑት ውዱ ነብያችን የተቆረጠውን እጅ ከገጠሩ ሰው እጅ ወስደው «ቢስሚላሂ ረሕማኒ ረሒም» ብለው ደም ከሚፈስሰው አንጓቸው ጋር አገጣጠሙት። እጁ በአላሁ ተዓላ ፈቃድ የክቡር ነብያችን ተአምር ሆኖ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ። አላሁ ተዓላ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነው፤ ሁሉንም ነገር ይችላል።

«ጌታዬ ሆይ! ይህ አጎቴ፣ የአባቴ ወንድም ነው። እነዚህም አህለል በይቴ ናቸው። በዚህ መሸፈኛዬ እንደሸፈንኳቸው አንተም ከጀሀነም እሳት ሸፍናቸው፤ ጠብቃቸውም!» ሐዲስ ሸሪፍ