ውዱ ነብዬ

የኸይበር ድል

በብርሃናማዋ መዲና በውጫዊ ገጽታ ሙስሊም፣ በእውነት ግን መናፍቃን የሆኑ አይሁዶች ነበሩ። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ወደ መዲና ከመሰደዳቸው በፊት የመዲና ሰዎች ዐብዱላህ ኢብኑ ኡበይ ኢብኑ ሰሉልን መሪያቸው አድርገው ነበር። በዕንቁ የተጌጠ ዘውድም ሰጥተውት ነበር። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) መዲናን በመምጣታቸው ባከበሩ ጊዜ የመዲና ሰዎች ሁሉ ለውዱ ክቡር ነብያችን አክብሮትና ፍቅር ማሳየት ጀመሩ፤ ተከተሏቸውም። ኢብኑ ሰሉል ክብሩን ሁሉ አጥቶ በአንድ ጥግ ቀረ። ለእርሱ ትኩረት መስጠታቸውንም ተዉ። በዚህ ጊዜ ኢብኑ ሰሉል ረሱሉላህን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ለመግደል ወይም ስቃይ ለማድረስ ተንቀሳቀሰ። አንድ ቀን አይሁዶች በእርሱ ዘንድ ተሰበሰቡ። በዚህ ጉዳይ አንዳንድ ዕቅዶችን አወጡ፤ ከለቢድ ኢብኑ ዓሲምም እርዳታ ጠየቁ። ለቢድ፦ «በእገሌ ሰፈር ኸይራ የምትባል አንዲት አሮጊት አለች። በድግምት እጅግ የተካነች ናት። ፈልጓት» አለ። ያችን ርጉም ሴት አግኝተው አንድ ሺህ የወርቅ ዲርሀምና አሥር ጥቅል ጨርቅ ሰጧት። «ሙሐመድን ካጠፋሽ ገና ብዙ እንሰጥሻለን» አሏት። አሮጊቷ በአንድ የርግብ ጫጩት ላይ መርፌዎችን ወጋች፤ ክሮችን ቋጥራ በርግብ ጫጩቱ ላይ ጠቀለለቻቸው። ከመዲና ውጭ በሚገኝ በአንድ የፈረሰ ጉድጓድ ውስጥ አስቀምጣ አፉን ዘጋችው። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ታመሙ። የአካል ክፍሎቻቸው ሳይንቀሳቀሱ ቀሩ። የተለያዩ መድኃኒቶች ቢሰጧቸውም አልጠቀመም። ይህ ሁኔታ ዘጠኝ ቀን ቆየ።

ከዚያም ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም መጥተው ሁኔታውን አሳወቁ። ረሱሉላህን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ወደዚያ ወሰዷቸው። ጉድጓዱን ከፍተው ርግቡን አወጡ። ነገር ግን በክሮቹ ላይ ያሉትን ቋጠሮዎች መፍታት አልተቻለም። ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም ሙዐዊዘተይንን (ሱረቱ አል-ፈለቅና ሱረቱ አን-ናስ) ይዘው መጥተው፦ «ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ሆይ! እነዚህን ሱራዎች በእነዚያ ቋጠሮዎች ላይ ያንብቡ!» አሉ። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እነዚያን ሱራዎች ማንበብ ጀመሩ። በሚያነቡት አንቀጽ ሁሉ ከቋጠሮዎቹ አንዱ መፈታት፣ ከመርፌዎቹም አንዱ መውጣት ጀመረ። ሱራዎቹን (የሁለቱን ሱራዎች 11 አንቀጾች) ሙሉ በሙሉ ባነበቡ ጊዜ ቋጠሮዎቹ ሁሉ ተፈቱ። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከበሽታው ፈጽመው ተፈወሱ፤ ጤናም አገኙ። ከዚያም እነዚያን ርጉም ሰዎች አስጠርተው ገሰጿቸው። የመዲና ሰዎችም እነዚያ ርጉማን እስኪጠፉ ድረስ ከባድ ቅጣት ቀጧቸው። አይሁዳዊው ለቢድም ተይዞ ወደ ክቡር ረሱሉላህ ፊት ቀረበ። ክቡር ነብያችን፦ «ይህን ለምን አስደረግህ?» ብለው ሲጠይቁት፦ «ለወርቅ ካለኝ ፍቅር የተነሣ» ሲል መለሰ። ከሶሓቦች አንዳንዶቹ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ቢፈቅዱ የዚህን አይሁዳዊ አንገት እንቁረጥ!» ባሉ ጊዜ ስለ ራሳቸው ማንንም የማይቀጡት ውዱ ነብያችን፦ «በመጨረሻ የሚያየው የአላህ ቅጣት የበለጠ ከባድ ነው» ብለው ለቢድ እንዲገደል አልፈቀዱም።1 አይሁዶች ከመዲና በተባረሩ ጊዜ ወደ ዓረቢያ ሰሜናዊ ክፍሎች ሄደው ነበር። ከእነርሱ አንድ ክፍል በኸይበር ቀርቶ ሰፈረ። ሌላው ክፍል በሰሜን ወደሚገኘው ወደ ሻም ሄደ። በክቡር ረሱሉላህ ላይ የግድያ ሴራ በመጠንሰሳቸው ከአገራቸው ተባረው ነበር። ነገር ግን በሙስሊሞች ላይ በውስጣቸው ያለው ቂም፣ ስግብግብነትና የበቀል ስሜት ፈጽሞ አልጠፋም። ይልቁንም ከቀን ወደ ቀን እየከረረ ሄደ፤ የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን የሆኑትን የአላሁ ተዓላ ሐቢብ ሕይወት በተቻለ ፍጥነት ለማቆም፣ የእስልምናን ሃይማኖትም ከምድር ላይ ለማጥፋት ይፈልጉ ነበር።

ከታላላቆቻቸው አንዳንዶቹ፦ «ወደ ገጠፋን ሄደን እርዳታ እንጠይቅ፤ ከእነርሱ ጋር ሆነን በሙስሊሞች ላይ እንዋጋ!» አሉ። ሌሎች ደግሞ፦ «የፈደክን፣ የተይማንና የዋዲል ቁራን አይሁዶችም ለእርዳታ እንጥራ፤ ሙስሊሞች እኛን ከማጥቃታቸው በፊት እኛ ከተማቸውን እናጥቃ፤ ቂማችንን ሁሉ እንበቀል!…» አሉ። የኸይበር አይሁዶች ይህን ሐሳብ ተቀብለው በአካባቢው ያሉትን የአይሁድ ነገዶችና የገጠፋን ሰዎች ለእርዳታ ጠሩ። ከገጠፋን ሰዎች ብቻ እጅግ ብዙ የተመረጡ ተዋጊዎች መጥተው በኸይበር ዝግጅት ጀመሩ። እነርሱ ይህን ዝግጅት ሲያደርጉ የዓለማት ሰይድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የአይሁዶችን ሁኔታ ሰሙ። ለሰይዲና ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሓ ሦስት ሶሓቦችን አብረው ሰጥተው በኸይበር የሚሆነውን ሁሉ እንዲያጣሩ ወዲያውኑ ላኳቸው። ዐብዱላህ ኢብኑ ረዋሓና ሦስቱ ጓደኞቻቸው በፍጥነት ኸይበር ደረሱ። ይህች ስምንት ጠንካራ ምሽጎች፣ ሌሎች ትናንሽ ምሽጎች፣ ለም መሬቶች እንዲሁም እጅግ ብዙ የወይንና የአትክልት ቦታዎች ያሏት ባለጸጋ ከተማ ነበረች። ሰይዲና ዐብዱላህ ከጓደኞቻቸው አንዱን ወደ ሺቅ ምሽግ፣ ሌላውን ወደ ከቲባ፣ ሦስተኛውን ወደ ናጣት ምሽግ ላኩ። እርሳቸውም ወደ ሌላ ምሽግ ገብተው ለሦስት ቀናት የአይሁዶችን ሁኔታና ለጦርነት የሚያደርጉትን ዝግጅት በቅርበት መረመሩ። ከሦስት ቀን በኋላ በመገናኛው ስፍራ ተሰብስበው በፍጥነት ወደ መዲና ተመልሰው አይሁዶች ያደረጓቸውን ዝግጅቶች አንድ በአንድ ለክቡር ነብያችን ተረኩ።

ውዱ ነብያችን ሶሓቦቻቸው በፍጥነት እንዲዘጋጁ አዘዙ። አይሁዶች መዲና አል-ሙነወራን እንዳያጠቁ ለመከላከል በኸይበር ላይ ለመዝመት ወሰኑ። በመዲና ያሉ አይሁዶች ይህን ውሳኔ ሲሰሙ ተደናገጡ። የሙስሊሞችን ሞራል ለመስበር፦ «እንምላለን፤ እናንተ የኸይበርን ምሽጎችና በዚያ የተሰበሰቡ ጀግና ተዋጊዎችን ብታዩ ኖሮ ፈጽሞ ወደዚያ እግራችሁን አታኖሩም ነበር!… በተራሮች ጫፍ ላይ ያሉትን ረጃጅም ግንቦች ያሏቸውን ምሽጎች ጥሩር የለበሱ ጀግኖች ይጠብቋቸዋል። ከየአቅጣጫው ሺዎች ወታደሮች ለእርዳታ መጥተውላቸዋል!… ኸይበርን ልትይዙ ትችላላችሁን?!…» ይሉ ነበር። በአንጻሩ ጀግኖቹ ሶሓቦች፦ «አላሁ ተዓላ ለሐቢቡ ኸይበርን እንደሚያሸንፉ ቃል ገብቷል» በማለት አይሁዶችን ፈጽሞ እንደማይፈሩ ገለጹ። ይህ የሶሓቦች ቆራጥነት አይሁዶችን የበለጠ አሳዘነ፤ አሳሰባቸውም። የመናፍቃን መሪ ዐብዱላህ ኢብኑ ኡበይ ወደ ኸይበር በችኮላ መልእክት ላከ፦ «ሙሐመድ በትንሽ ኃይል ወደ እናንተ እየመጣ ነው። የሚያስፈራ ነገር የለም፤ ነገር ግን ጥንቃቄ አድርጉ፤ ንብረታችሁንም በምሽጎቻችሁ ውስጥ ሙሉ። ከምሽጉ ወጥታችሁ ተቀበሏቸው!» ሶሓቦች ዝግጅታቸውን አጠናቀቁ፤ ቤተሰቦቻቸውን ይቅርታ ጠይቀው ተሰናብተው በክቡር ነብያችን ዙሪያ ተሰበሰቡ። ሁለት መቶ ፈረሰኞችና አንድ ሺህ አራት መቶ እግረኞች ነበሩ። የአላሁ ተዓላን ሃይማኖት ለማስፋፋት፣ ጂሃድ ለማድረግና የሸሂድነትን ማዕረግ ለማግኘት ለውዱ ነብያቸው ትእዛዝ ተዘጋጅተው ቆሙ። በዚህ ጊዜ አንዳንድ ሴቶች በጦርነት የሶሓቦችን ምግብ ለማዘጋጀት፣ የቆሰሉትንና የታመሙትን ለመንከባከብ፣ ቁስሎችን ለማሰር፣ መድኃኒት ለማዘጋጀትና ሌሎች የሚችሉትን ሥራዎች ለመሥራት ከክቡር ነብያችን ተልእኮ ጠየቁ። ክቡር ረሱሉላህ ራርተው ይህን ምንዳ አላሳጧቸውም። በዚህም ከሙጃሂዶቹ ጋር በውዱ ነብያችን የተባረከች ሚስት በሰይደቲና ኡሙ ሰለማ የሚመሩ ሃያ ሴት ሙጃሂዶች ተቀላቀሉ።2

ረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከጊፋር ነገድ ሰይዲና ሲባዕን በመዲና ተወካያቸው አድርገው ትተው ወደ ኸይበር የመነሣት ትእዛዝ ሰጡ። (ኑመይላ ኢብኑ ዐብዱላህ እንደተተወም ተዘግቧል።) ጉዞው በተክቢር ተጀመረ። በምክንያታቸው በጦርነቱ መሳተፍ ያልቻሉ እንዲሁም ገና ትንሽ በመሆናቸው ፈቃድ ያላገኙ ሶሓቦች ወደ ክቡር ነብያችንና ወደ ጀግኖቹ አባቶቻቸው፣ አያቶቻቸው፣ አጎቶቻቸው፣ የእናት ወንድሞቻቸውና ታላላቅ ወንድሞቻቸው በመልካም ቅናት ይመለከቱ ነበር፤ በተክቢርና በዱዓ ሸኟቸው።

«የኸይበር ግንብ በዐሊይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ አማካኝነት ይወረራል» ሐዲስ ሸሪፍ

የቀን መቁጠሪያው የሂጅራ ሰባተኛውን ዓመት የሙሐረም ወር ያሳይ ነበር። የክቡር ነብያችንን የተቀደሰ ሰንደቅ ሰይዲና ዐሊይ ይሸከሙ ነበር፤ የቀኝ ክንፍ አዛዥነትም በሰይዲና ዑመር ነበር።3 ለግራ ክንፍም ሌላ ሶሓቢይ ሾሙ። ጉዞው በደስታ ስሜት ተካሄደ። ባለቅኔዎቹ በግጥሞቻቸው አላሁ ተዓላን ስለሰጠው ጸጋዎች አመሰገኑ፤ ለውዱ ነብያችን ሶለዋት አወረዱ፤ ክብረ ገናናዎቹን ሶሓቦችም አሞገሱ። ሶሓቦችም ወደ በዓል እንደሚሄዱ ሆነው በአንድነት፦ «አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! ላ ኢላሀ ኢለላሁ ወላሁ አክበር!» እያሉ አካባቢውን ሁሉ አስተጋቡ።

በእያንዳንዱ ማረፊያ የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን ይህን ዱዓ ያደርጉ ነበር፦ «አላህ ሆይ! ስለ ወደፊት ከመጨነቅ፣ ስለ ያለፈው ከማዘን፣ ከአቅመ ቢስነትና ከስንፍና፣ ከስስትና ከፈሪነት፣ ጀርባን ከሚያጎብጥ ዕዳ እንዲሁም ከበዳዮችና ከግፈኞች ተጽዕኖ በአንተ እጠበቃለሁ!»

ኸይበርን ሲቃረቡ ውዱ ነብያችን ሶሓቦቻቸውን አቆሙ። እጆቻቸውን አንሥተው ዱዓ ማድረግ ጀመሩ፦ «የሰማያትና የሚያጠሏቸው ጌታ የሆንከው አላህ ሆይ! የምድሮችና በላያቸው ያለው ጌታ የሆንከው አላህ ሆይ! የሰይጣኖችና የሚያስቷቸው ጌታ የሆንከው አላህ ሆይ! የነፋሳትና የሚበትኑት ጌታ የሆንከው አላህ ሆይ! እኛ ከአንተ የዚህችን አገር መልካምና ደኅንነት፣ በዚህች አገር የሚኖሩ ሰዎችን መልካምና ደኅንነት፣ እንዲሁም በዚህች አገር ያለውን ሁሉ ነገር መልካምና ደኅንነት እንለምናለን። ከዚህች አገር ክፋት፣ ከሰዎች ክፋትና በውስጧ ካለው ሁሉ ክፋት በአንተ እንጠበቃለን!»

ከሶሓቦች ከንፈሮች «አሚን፣ አሚን» የሚል ድምፅ ተሰማ። ከዚያም ለሶሓቦቻቸው፦ «‹ቢስሚላሂ ረሕማኒ ረሒም› እያላችሁ ቀጥሉ» አሉ።

ሶሓቦች በረሱሉል አክረም ዙሪያ ተሰባስበው እንደገና ጉዞ ቀጠሉ። ከኸይበር እጅግ ጠንካራ ምሽጎች አንዱ ወደሆነው ወደ ናጣት ምሽግ ቀረቡ።

በዚያ ሰፈሩ። ምሽት ነበር። በክቡር ረሱሉላህ የተባረከ ልማድ መሠረት ጠዋት እስኪሆን ጥቃት አይደረግም ነበር፤ መጀመሪያ ወደ እስልምና ይጠራ ነበር። ጥሪውን ካልተቀበሉ ውጊያ ይጀምር ነበር። ስለዚህ ሶሓቦች ጠዋትን ጠበቁ። ከአይሁዶች አንዳቸውም የእስልምና ሠራዊት እንደመጣ አላስተዋሉም ነበር። የፍጥረተ ዓለሙ ሰይድ የሱብሒን ሶላት ካሰገዱ በኋላ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ሙጃሂዶቹን አንቀሳቀሱ። ሁለት መቶ ፈረሰኞችና አንድ ሺህ አራት መቶ እግረኞች በተደራጀ ሰልፍ ወደ ናጣት ምሽግ ቅጥር ቀረቡ። በዚህ ጊዜ በወይን እርሻዎች፣ በአትክልት ቦታዎችና በማሳዎች ለመሥራት ከምሽጉ የወጡ አይሁዶች ድንገት ከእስልምና ወታደሮች ጋር ተፋጠጡ፤ በድንጋጤም ተዋጡ።

«እንምላለን፤ እነዚህ ሙሐመድና የተደራጀ ሠራዊቱ ናቸው!…» እያሉ ወደ ኋላ መሸሽ ጀመሩ። ውዱ ነብያችን እነርሱን በዚህ ሁኔታ ሲያዩ፦ «አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! ኸይበር ፈረሰች» አሉ፤ ይህንንም የተባረከ ቃል ሦስት ጊዜ ደገሙ። ክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አይሁዶች ወይ ሙስሊም እንዲሆኑ ወይም እጅ ሰጥተው ኸራጅና ጂዝያ እንዲከፍሉ፣ አለበለዚያ ጦርነት እንደሚሆንና ደም እንደሚፈስ አሳወቁ። አይሁዶች ከታላላቆቻቸው ወደ አንዱ ወደ ሰላም ኢብኑ ሚሽከም ሄደው ሁኔታውን አቀረቡለት። ሰላም፦ «ቀደም ብዬ በሙሐመድ ላይ ዝመቱ ብዬ ነበር፤ እናንተ አልፈለጋችሁም። ቢያንስ አሁን ከእርሱ ጋር በሚደረገው ውጊያ ደካማ አትሁኑ። ከሙስሊሞች ጋር እየተዋጋችሁ መሞት ብቸኛና ያለ ረዳት በሕይወት ከመቆየት ይሻላል!…» ብሎ ለውጊያ አነሣሳቸው። አይሁዶች በፍጥነት ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን በከቲባ ምሽግ፣ ስንቃቸውን በናኢም፣ ወታደሮቻቸውንም በናጣት ምሽግ ሰበሰቡ።

የእስልምና ሠራዊት ሙስሊም እንዲሆኑ ላቀረበው ሐሳብ አይሁዶች በፍላጻ መለሱ። ሙጃሂዶቹ ፍላጻዎቹን በጋሻዎቻቸው ተቀበሉ። በውዱ ነብያችን ትእዛዝ ቀስቶች ተወጠሩ፤ «አላሁ አክበር!…» በሚል ጩኸትም ፍላጻዎች በምሽጉ ማማዎች ላይ ባሉ አይሁዶች ላይ ተወነጨፉ። ውጊያው ተጀመረ። በአንድ በኩል የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣንና ጀግኖቹ ሶሓቦቻቸው እስልምናን ለማስፋፋትና አይሁዶች ሙስሊም ሆነው ከጀሀነም እንዲድኑ ለማድረግ ይዋጉ ነበር። በሌላ በኩል ምንም ምክር የማይሰሙ፣ ሙስሊሞችን በየአጋጣሚው ከጀርባ ለመምታት የሚፈልጉ፣ እውነትን ለማየት በግትርነት እምቢ ያሉ አይሁዶች ነበሩ። የነብያት መደምደሚያ (ኻተሙል አንቢያ) ከራሳቸው ሕዝብ እንዳልተገኙ ሲያዩ በቅናት ተነሣስተው አልተቀበሏቸውም ነበር። ከክቡር ነብያችን የልጅነት ዘመን ጀምሮ ሊያስወግዷቸው በአእምሯቸው የመጣውን ዘዴ ሁሉ ሞክረው ነበር፤ ነገር ግን በአላሁ ተዓላ ጥበቃ ምንም ማድረግ አልቻሉም።

ከአሥር ሺህ በላይ የአይሁድ ወታደሮች በአንድ ሺህ ስድስት መቶ ክብረ ገናና ሙጃሂዶች ላይ ፍላጻ ይወነጭፉ ነበር። ሶሓቦች አንዱ ከሌላው በኋላ ከሚመጡት ከእነዚህ ፍላጻዎች በጋሻዎቻቸው ይጠበቁ ነበር፤ አጋጣሚ ባገኙም ጊዜ መሬት ላይ የወደቁትን ፍላጻዎች ወደ አይሁዶች ይመልሱ ነበር። ነገር ግን አንዳንድ ሶሓቦች ቆሰሉ።

በአንድ ወቅት ሰይዲና ሑባብ ኢብኑ ሙንዚር በታላቅ ጨዋነት ወደ ሐቢቡላህ ቀርበው፦ «ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ሰፈራችንን ሌላ ቦታ ብናደርግ አይሻልምን?» ሲሉ ጠየቁ። ክቡር ነብያችን፦ «ኢንሻአላሁ ተዓላ፣ ምሽት ሲሆን እንለውጠዋለን!» አሉ። ሙጃሂዶቹ በፍላጻ ርቀት ውስጥ ገብተው ነበር። አይሁዶች ከምሽጉ የሚወነጭፏቸው ፍላጻዎች እስከ እስልምና ሰፈር ጀርባ ድረስ ይደርሱ ነበር።4 በዚያ ቀን ጦርነቱ እስከ ምሽት በፍላጻ ቀጠለ። ሃምሳ ያህል ሶሓቦች በፍላጻ ቆሰሉ። ምሽት ሲሆን ሰይዲና ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ አዲስ የሰፈር ቦታ እንዲፈልጉ ተመደቡ። ረጂዕ የሚባለው ስፍራ ተስማሚ መሆኑን ሲያመለክቱ የእስልምና ሰፈር ወደዚያ ተዛወረ።

«እኛ ነብያት ውርስ አንተውም። የተውነው ለድሆች ሰደቃ ይሆናል» ሐዲስ ሸሪፍ

የኸይበር ድል

ቁስለኞች ታከሙ።5 በማግሥቱ ጀግኖቹ ሶሓቦች በናጣት ፊት ቀርበው እስከ ምሽት ተዋጉ። በሦስተኛው፣ በአራተኛውና በአምስተኛው ቀንም ከበባው ቀጠለ። አይሁዶች ሁልጊዜ በመከላከል ላይ ቆዩ። በእነዚያ ቀናት ውዱ ነብያችን ከባድ ራስ ምታት ስለያዛቸው ለሁለት ቀን በሙጃሂዶቹ መካከል መገኘት አልቻሉም። በመጀመሪያው ቀን ሰንደቁን ለሰይዲና አቡበክር፣ በሁለተኛው ቀን ለሰይዲና ዑመር ሰጡ። ሁለቱም በሶሓቦች ራስ ላይ ሆነው በአይሁዶች ላይ እጅግ ከባድ ውጊያ ተዋጉ፤ ነገር ግን ምሽጉን መያዝ አልተቻለም። በዚህ መካከል ድፍረታቸው የጨመረው አይሁዶች የምሽጉን በሮች ከፍተው ወደ ጥቃት ሲሸጋገሩ ታዩ። አሁን ደረት ለደረት መዋጋት ተጀመረ። ውጊያው እጅግ ጋመ። ክቡር ነብያችን ለሶሓቦቻቸው፦ «ተክቢር በሉ፦ አላሁ አክበር! አላሁ አክበር!…» ባሉ ቁጥር እነርሱም በተክቢር ድምፅ መካከል በፍቅርና በወኔ ጠላት ላይ ሰይፍ ያወርዱ ነበር። በአንድ ወቅት የሙሐመድ ኢብኑ መስለማ ወንድም መሕሙድ ሸሂድ ሆኑ። ግጭቶቹ እስከ ምሽት በከባድ ሁኔታ ቀጠሉ።

በማግሥቱ ከኸይበር እጅግ ታዋቂ አዛዦች አንዱ የሆነው መርሐብ ጥሩር ለብሶ ከምሽጉ ወጣ። ጠንካራና ኃይለኛ፣ እጅግ ግዙፍ ሰው ነበር። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሊያሸንፈው የሚችል ተፋላሚ ፊቱ ቆሞ አያውቅም ነበር። ወደ ሙጃሂዶቹ ዞሮ፦ «እኔ በድፍረቴና በጀግንነቴ የታወቅሁት መርሐብ ነኝ!» እያለ መኮፈስ ጀመረ። እንዲህ እየኮራ ሳለ ከሶሓቦች መካከል አንድ ሙጃሂድ ወደ ፊት ተስፈንጥረው ወጡ። መርሐብን፦ «እኔም በአስፈሪና በጠንካራ ጦርነቶች መካከል ራሴን ለመወርወር የማልፈራ ዓሚር ነኝ!» ብለው ጮኹና ወዲያውኑ ፊት ለፊቱ ቆሙ። ግዙፉ መርሐብ «የነካውን ሁሉ ያጠፋል!…» የሚል ጽሑፍ ባለበት ሰይፉ በሙሉ ኃይሉ ሰይዲና ዓሚርን መታ። ጀግናው ዓሚር በዚያው ቅጽበት ጋሻቸውን አነሡ። ሰፊው ሰይፍ ጋሻውን ሲመታ ከባድ ድምፅ ዙሪያውን አስተጋባ፤ ሰይፉም ጋሻው ውስጥ ተሰካ።

ሰይዲና ዓሚር ወደ ፈጣሪ ተጠግተው፦ «አላህ ሆይ!» እያሉ ሰይፋቸውን በጥሩር በተሸፈኑት የመርሐብ እግሮች ላይ አሳረፉ። ሰይፉ የብረት ጥሩሩን እንደነካ ወደ ኋላ ተመልሶ በድንገት የሶሓቢዩን እግር መታ። የሰይፉ ኃይለኛ መመለስ በሰይዲና ዓሚር እግር ላይ ያለውን የደም ሥር ቆረጠው። ሶሓቦች እየሮጡ መጥተው ዓሚርን በእቅፋቸው አድርገው ለሕክምና ወደ ሰፈር ወሰዷቸው። ዓሚር (ረዲየላሁ ዐንሁ) ግን እዚያ ሸሂድ ሆነው ወደ ከፍተኛይቱ ጀነት በረሩ።6

ጦርነቱ በሙሉ ጥንካሬው ቀጠለ። ወደ ምሽት ገደማ ውዱ ነብያችን አይሁዶችን ለመርዳት በአራት ሺህ ወታደሮች ለመጡትና በውጊያው ለተሳተፉት አጋሪ የገጠፋን ሰዎች ተለይተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሐሳብ አቀረቡ። ይህን ካደረጉ ለአንድ ዓመት የሚሆን የኸይበር የተምር ምርት እንደሚሰጧቸውም ቃል ገቡ። የገጠፋን ሰዎች ግን ይህን ሐሳብ አልተቀበሉም። በዚህ ጊዜ የዓለማት ሰይድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሶሓቦቻቸው የገጠፋን ሰዎች ባሉበት ምሽግ ዙሪያ ሌሊቱን እንዲያሳልፉ አዘዙ። የገጠፋን ሰዎች ሙጃሂዶቹ ሌሊት እንዳያጠቁ እጅግ ፈርተው መተኛት አልቻሉም። በዚያ ሌሊት ከየት እንደመጣ የማይታወቅ አንድ ድምፅ የገጠፋን አገር እንደተወረረና ሚስቶቻቸው፣ ልጆቻቸውና ንብረታቸው እንደተማረከ አወጀ። ይህ ድምፅ ሦስት ጊዜ ተደገመ፤ የገጠፋን ሰዎችም ሁሉ በታላቅ ፍርሃት ሰሙት። አዛዣቸው ዑየይናም ያንኑ ድምፅ ሦስት ጊዜ ሰማ፤ ጎህ ሊቀድ ሲል ወታደሮቹን ይዞ ከኸይበር በፍጥነት ርቆ ወደ አገሩ መንገድ ያዘ። ጠዋት አይሁዶች የገጠፋን ሰዎች ያለ ምክንያት ኸይበርን በመተዋቸው ተገረሙ፤ ተስፋም ቆረጡ። ለእርዳታ በመጥራታቸውም እጅግ ተጸጸቱ።

«የኸይበርን ምሽግ በያዝንበት ቀን ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የቤት አህያ ሥጋ መብላትንና በሙትዐ ኒካሕ ሴት ማግባትን ከለከሉ» ሰይዲና ዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ)

የሰይዲና ዐሊይ ጀግንነት

በዚያ ቀንም በኸይበር ፊት ከባድ ውጊያ ተደረገ፤ ምሽጉ ግን አልተያዘም። ምሽት ላይ የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን የምሥራች አበሠሩ፦ «ነገ ሰንደቁን አላሁ ተዓላንና መልዕክተኛውን ለሚወድ፣ አላሁ ተዓላና መልዕክተኛውም ለሚወዱት ጀግና እሰጣለሁ። አላሁ ተዓላ ድሉን በእጁ ያደርሳል!»

በዚያ ሌሊት ሶሓቦች በጉጉት ጠዋትን ጠበቁ። እያንዳንዳቸው ሰንደቁ ለእርሳቸው እንዲሰጥ ተስፋ በማድረግ ወደ አላሁ ተዓላ ዱዓ ያደርጉ ነበር። ሰይዲና ቢላል አል-ሐበሺ ልብ በሚነካና በሚያምር ድምፃቸው የሱብሒን አዛን አሰሙ። አዛን ሲሰማ በሁሉም ዘንድ ልዩ ስሜትና ልዩ ደስታ ተፈጠረ፤ ከዚያ ከአላህ የሆነ ደስታ ማንም አልጠገበም። ውዱ ነብያችን ሶሓቦቻቸውን የሱብሒን ሶላት ካሰገዱ በኋላ ተነሡ። የተባረከውን የእስልምና ሰንደቅ እንዲመጣ አዘዙ። የተቀደሰው ሰንደቅ ሲመጣ ሶሓቦች ቆመው እየጠበቁ ከረሱሉል አክረም የተባረኩ ከንፈሮች የሚወጡትን ቃላት ለመስማት በጉጉት ትኩረት ሰጡ።

በመጨረሻ የዓለማት ሰይድ፦ «የሙሐመድን ማንነት በነብይነት ባከበረው በአላሁ ተዓላ እምላለሁ፤ ይህን ሰንደቅ መሸሽ ምን እንደሆነ ለማያውቅ ጀግና እሰጣለሁ» ካሉ በኋላ የተባረኩ ዓይኖቻቸውን በሶሓቦቻቸው መካከል አዙረው፦ «ዐሊይ የት ነው?» አሉ። ሶሓቦች፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ዓይኖቻቸው ያማሉ» ሲሉ ሰይዳችን፦ «ወደ እኔ ጥሩት» አሉ። በእነዚያ ቀናት ሰይዲና ዐሊይ የዓይን ሕመም ይዟቸው ዓይኖቻቸውን መክፈት አልቻሉም ነበር። ወደ እርሳቸው ሄደው ሁኔታውን አሳወቁ፤ የተባረከ ክንዳቸውን ይዘው ወደ ክቡር ረሱሉላህ ፊት አመጧቸው። የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን ለሰይዲና ዐሊይ ፈውስ እንዲሆን ወደ አላሁ ተዓላ ዱዓ አደረጉ፤ የተባረኩ ጣቶቻቸውንም በአፋቸው አርጥበው በዓይኖቻቸው ላይ ቀቡ። በዚያ ቅጽበት በሰይዲና ዐሊይ ዓይኖች ውስጥ ምንም ሕመም አልቀረም። በተጨማሪ፦ «ጌታዬ ሆይ! ከእርሱ የሙቀትንና የቅዝቃዜን ችግር አስወግድ!» ብለው ለእርሳቸው ዱዓ አደረጉ። ከዚያም በተባረኩ እጆቻቸው ጥሩር አለበሷቸው፤ የራሳቸውን ሰይፍ በወገባቸው አሰሩላቸው፤ ነጩን የእስልምና ሰንደቅ በእጃቸው ሰጡና፦ «አላሁ ተዓላ ድል እስኪሰጥህ ድረስ ተዋጋ። ተጠንቀቅ፣ ወደ ኋላ አትመለስ!» አሉ። ሰይዲና ዐሊይ፦ «ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ወደ እስልምና ሃይማኖት እስኪገቡ ድረስ እዋጋቸዋለሁ» አሉ። ውዱ ነብያችንም፦ «በአላህ እምላለሁ፣ በአንተ ምክንያት አላሁ ተዓላ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ ወደ ቅን መንገድ ቢመራ፣ ብዙ ቀይ ግመሎች ኖረውህ በአላሁ ተዓላ መንገድ ሰደቃ ከመስጠትህ ይልቅ ለአንተ የተሻለ ነው» አሉ።7

ሰይዲና ዐሊይ ሰንደቁን በእጃቸው ይዘው ወደ አይሁዶች ምሽግ ሲሄዱ ክብረ ገናናዎቹ ሶሓቦች ከኋላቸው ተከተሉ። ወደ ምሽጉ በጣም ተጠግተው ሰንደቁን በአንድ ዓለት ሥር ሲተክሉ የናጣት ምሽግ በር ተከፈተ።

የአይሁዶች የጥቃት ክፍሎች ወጡ። የኸይበር እጅግ የተመረጡ ጀግኖች ነበሩ። እያንዳንዳቸው ድርብ ጥሩር ለብሰው በብረት ጥበቃ ተሸፍነው ነበር። ከእነርሱ አንዱ ወደ ሰይዲና ዐሊይ እየሄደ ለመዋጋት ፊት ለፊታቸው ቆመ። በጀግንነት አቻ የማይገኝለት የመርሐብ ወንድም ሐሪስ ነበር። በፍጥነት አጠቃ… የሁለቱ ብረቶች ድምፅ አውደ ውጊያውን ሲሞላ ዙልፊቃር እንደ መብረቅ ወርዶ የሐሪስን ራስ ከአካሉ ለየ። በዚህ ጊዜ «አላሁ አክበር! አላሁ አክበር!» የሚሉ ድምፆች ወደ ሰማይ ወጡ። ወንድሙ እንደተገደለ የሰማው መርሐብ በሥሩ ካሉ ወታደሮች ጋር በሙሉ ፍጥነት ወደ አውደ ውጊያ ገሠገሠ። በሰይዲና ዐሊይ ፊት ተገትሮ ቆመ። እርሱም ድርብ ጥሩር ለብሶ ነበር። ሁለት ሰይፍ ታጥቆ በትልቅ ሰውነቱ ልክ ግዙፍ ሰው ይመስል ነበር። በቁጣው ሁሉ ራሱን ማሞገስ ጀመረ፦ «እኔ ጦርነቶች እጅግ በሚበረቱበት ጊዜ ራሴን ወደ መሀል ጥዬ በጀግንነት የምዋጋው መርሐብ ነኝ! እኔ የሚያገሱ አንበሶችን እንኳ በጦሬ ወይም በሰይፌ እበሳለሁ!…»

ሰይዲና ዐሊይ (ከረመላሁ ወጅሀሁ ወረዲየላሁ ዐንሁ) መለሱ፦ «እኔ እናቴ ሐይደር (አንበሳ) ብላ የሰየመችኝ ነኝ። እኔ እንደ አስፈሪ አንበሳ ነኝ! እኔ አንተን በአንድ ምት መሬት ላይ የምጥልህ ጀግና ነኝ!…»

መርሐብ ከሰይዲና ዐሊይ «ሐይደር» የሚለውን ቃል ሲሰማ ፍርሃት ልቡን ያዘው። ምክንያቱም በዚያ ሌሊት አንድ አንበሳ በሕልሙ ቦጫጭቆት ነበር። በሕልሙ ያየው አንበሳ ይህ ይሆን? ከዚያም ግዙፉ መርሐብ አጠቃ፤ ሰይዲና ዐሊይም በጋሻቸው ተቀበሉት። ከዚያም ወደ አላሁ ተዓላ ተጠጉ፤ «አላህ ሆይ!…» ብለው ዙልፊቃርን በከሓዲው ራስ ላይ እንዲህ ባለ ኃይል አወረዱት፤ ሰይፉ ታላቁ መርሐብ በላዩ የያዘውን ወፍራም የብረት ጋሻና የብረት ራስ ቁሩን ለሁለት ከፍሎ ራሱን ከአናቱ እስከ ማጅራቱ ሰነጠቀ። ደም ከአንገቱ እንደ ምንጭ ፈለቀ፤ ግዙፉ ሰውነቱም መሬት ላይ ተዘረረ። የዙልፊቃር አስፈሪ ድምፅ በኸይበር ማዕዘናት ሁሉ ተሰማ። ክቡር ነብያችን፦ «ደስ ይበላችሁ! የኸይበር ድል አሁን ቀላል ሆነ።» አሉ። ሶሓቦች በዚህ የሰይዲና ዐሊይ ጀግንነት ተደንቀው ሰማዩን «አላሁ አክበር! አላሁ አክበር!…» በሚል ጩኸት አስተጋቡት።

ውጊያው በሙሉ ጥንካሬው ቀጠለ። ሶሓቦች እየተዋጉ እስከ ምሽጉ በር ድረስ በደረሱበት ወቅት አንድ አይሁዳዊ በሰይፉ የሰይዲና ዐሊይን ጋሻ መታ። ጋሻው መሬት ላይ ወደቀ፤ ነገር ግን ጎንበስ ብሎ ለማንሣት ጊዜ አልነበረም። ዕድሉን ማጣት ያልፈለገው አይሁዳዊ ጋሻውን ነጥቆ ወደ ኋላ ሸሸ። በዚህ እጅግ ያዘኑት የአላሁ ተዓላ አንበሳ በዙልፊቃር በዙሪያቸው ያሉትን ጠላቶች ከበተኑ በኋላ የምሽጉን በር ጋሻ ለማድረግ ወሰኑ። «ቢስሚላሂ ረሕማኒ ረሒም» ብለው የግዙፉን የብረት በር ቀለበቶች ያዙ። መንጠቆዎቹን ከግድግዳው ነቀነቁ፣ ነቀሉም… ሰይዲና ዐሊይ በሩን ሲነቅሉ ምሽጉ ከመሠረቱ ተናወጠ። ስምንት ወይም አሥር ብርቱ ሰዎች ከስፍራው ሊያንቀሳቅሱት ያልቻሉትን ይህን በር በአንድ እጃቸው ጋሻ አድርገው መዋጋት ጀመሩ። ይህ የማይታመን ክስተት የውዱ ነብያችን ተአምርና የሰይዲና ዐሊይ ከራማ ነበር።8

አንድ በአንድ ከአይሁዶች እጅግ ጀግኖች ሌሎች ስድስት ተፋላሚዎች በፊታቸው ቆሙ። እነርሱንም ሰይዲና ዐሊይ በአላሁ ተዓላ ፈቃድ አሸንፈው ከጀግኖቹ ጓደኞቻቸው ጋር ወደ ምሽጉ ገቡ። አሁን ውጊያው በምሽጉ ውስጥ ነበር። በአጭር ጊዜ ፊታቸው የሚቆም ማንም አልቀረም። የእስልምናን ሰንደቅ በምሽጉ ላይ ተከሉ። እንዲህ ሲሆን እጅግ ጠንካራው ምሽጋቸው ናጣት ተያዘ። ውዱ ነብያችን የሰይዲና ዐሊይን ዓይኖች ከሳሙ በኋላ፦ «ባሳየኸው ጀግንነት ምክንያት አላሁ ተዓላና መልዕክተኛው ከአንተ ተደስተዋል።» አሉ። ዐሊይ ይህን የተባረከ ቃል ሲሰሙ ከደስታቸው አለቀሱ። ክቡር ነብያችን፦ «ለምን ታለቅሳለህ?» ሲሉ፦ «ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከደስታዬ አለቅሳለሁ። ምክንያቱም አላሁ ተዓላና መልዕክተኛው ከእኔ ተደስተዋል» አሉ። በዚህ ጊዜ ውዱ ነብያችን፦ «እኔ ብቻ አይደለሁም፤ ጂብሪል፣ ሚካኢልና መላእክት ሁሉ ከአንተ ተደስተዋል» አሉ። በዚህ ጊዜ ከደውስ ነገድ አራት መቶ ሙስሊሞች ክቡር ነብያችንን ሊረዱ መጡ።9 ከዚያም ሌሎቹን ምሽጎች ለመያዝ ውጊያው በከባድ ሁኔታ ቀጠለ። የቀሩት ሰባቱ የኸይበር ጠንካራ ምሽጎችም አንድ በአንድ ሲወድቁ፣ ምንም አማራጭ ያልቀራቸው አይሁዶች ልዑካን ልከው ሰላም ጠየቁ። ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ይህን ሐሳብ ተቀብለው በሚከተሉት አንቀጾች ተስማሙ፦ 1. በዚህ ዘመቻ ከሙስሊሞች ጋር የተዋጉ አይሁዶች ደም አይፈስም። 2. ኸይበርን የሚለቁ አይሁዶች ልጆቻቸውንና አንድ የግመል ጭነት የሚሆን አስፈላጊ የቤት ዕቃ ብቻ ይዘው መሄድ ይችላሉ። 3. የቀሩት ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሁሉ፤ ጥሩር፣ ሰይፍ፣ ጋሻ፣ ቀስትና ፍላጻን የመሳሰሉ ሁሉም የጦር መሣሪያዎች፤ ከለበሱት ልብስ በቀር ያሏቸው ልብሶች በሙሉ፤ ጨርቆች፣ ወርቆች እንዲሁም ሀብቶች፤ እንደ ፈረስ፣ ግመልና በግ ያሉ ሁሉም እንስሳት… ያለው ሁሉ ለሙስሊሞች ይቀራል። 4. ለሙስሊሞች መተው ያለበት ማንኛውም ነገር በምንም መልኩ አይደበቅም። የሚደብቅ ከአላሁ ተዓላና ከመልዕክተኛው ዋስትናና ጥበቃ ውጭ ይሆናል…

«እኔ እናቴ ሐይደር (አንበሳ) ብላ የሰየመችኝ ነኝ። እኔ እንደ አስፈሪ አንበሳ ነኝ!» ሰይዲና ዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ)

እነዚህን ስምምነቶች ያላከበረውና ሀብቱን በቆዳ ከረጢቶች ውስጥ መሬት ውስጥ የቀበረው ኪናና ኢብኑ ረቢዕ ተቀጣ። የተገኘው ምርኮ ሊቆጠር የማይችል ነበር። የኸይበር ለም መሬቶችና የተምር እርሻዎች በሙሉ ለእስልምና ሠራዊት ሆኑ።10 በዚህ ጊዜ ወደ አገራቸው ተመልሰው የነበሩት የገጠፋን ሰዎች አይሁዶችን ለመርዳት ወደ ኸይበር ተመልሰው መጡ። ክቡር ነብያችን ኸይበርን እንደያዙና አይሁዶች እጅ እንደሰጡ ሲያዩ፦ «ሙሐመድ ሆይ! ኸይበርን ብንለቅ የአንድ ዓመት የኸይበር ተምር እንደምትሰጠን ቃል ገብተህልን ነበር። እኛ ቃላችንን ጠብቀናል። ና፣ ስጠን!» አሉ። ሰይዳችን፦ «እገሌ የተባለው ተራራ የእናንተ ይሁን» አሏቸው። የገጠፋን ሰዎች፦ «እንዲያ ከሆነ እንዋጋችኋለን» ብለው ሊያስፈራሩ ሞከሩ። ረሱሉል አክረም፦ «የውጊያችን ስፍራ ጀናፋ ይሁን» አሉ። ጀናፋ ከገጠፋን ምድሮች የአንዱ ስም ነበር። የገጠፋን ሰዎች ይህን ሲሰሙ በፍርሃት ወደ ኋላ አፈገፈጉና ሄዱ።

ውዱ ክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እና ጀግኖቹ ሶሓቦቻቸው በኸይበር ድል ወቅት እጅግ ደክመው ነበር። በአንድ በኩል ቁስለኞች ሲታከሙ በሌላ በኩል ዕረፍት ያደርጉ ነበር።

ከአይሁዶች ታዋቂ ሰዎች አንዱ የሆነው የሰላም ኢብኑ ሚሽከም ሚስት ዘይነብ ክቡር ነብያችንን መርዝ አብልታ ልትገድላቸው ፈለገች። ለዚህ በግ አርዳ አብስላ በሥጋው ውስጥ ብዙ መርዝ ጨመረች። ከዚያም ወደ ክቡር ረሱሉላህ ቀርባ ስጦታ እንዳመጣች ተናገረች። ረሱሉል አክረም ተቀብለው ሶሓቦቻቸውን ጠሩ፤ ሁሉም ለመብላት አብረው ተቀመጡ። የዓለማት ሰይድ ከተጠበሰው በግ አንድ ቁራጭ ቀድደው «ቢስሚላሂ ረሕማኒ ረሒም» ብለው ወደ ተባረከ አፋቸው አቀረቡ። ጥቂት ጊዜ ካኘኩት በኋላ ወዲያው ከተባረከ አፋቸው አውጥተው፦ «ሶሓቦቼ ሆይ! እጆቻችሁን ከዚህ ምግብ ሰብስቡ! ይህ የትከሻ ቁራጭ መርዝ እንደተደረገበት አሳውቆኛልና።» አሉ። ሶሓቦች ወዲያውኑ እጆቻቸውን ከምግቡ አነሡ። ነገር ግን ከሥጋው አንድ ጉርሻ የበላው የሰይዲና ቢሽር ኢብኑ በራእ አካል ወዲያው ሰማያዊ ሆነ፤ እርሳቸውም ሸሂድ ሆኑ። ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም ወደ ውዱ ነብያችን መጥተው ከተባረኩ ምራቃቸው ጋር ከተቀላቀለው መርዝ ጉዳት ለመዳን በተባረኩ ትከሻዎቻቸው መካከል ዋግምት አስደርገው ደም እንዲያስወጡ ነገሯቸው። ተደረገም። ከዚያም የተመረዘው ጥብስ መሬት ውስጥ ተቀበረ። ይህን ያደረገችው ዘይነብ ተይዛ ወደ ፊታቸው ቀረበች።

ሰይዳችን፦ «ይህን የተጠበሰ በግ መርዝ ያደረግሽበት አንቺ ነሽን?» አሏት። ያደረገችውን አምና፦ «አዎ! እኔ መርዝ አደረግሁበት!» አለች። ክቡር ነብያችን፦ «ይህን ለምን ማድረግ ፈለግሽ?» ብለው ሲጠይቁ፦ «አንተ ባለቤቴን፣ አባቴንና አጎቴን ገድለሃል። ለራሴ፦ ‹እርሱ በእርግጥ ነብይ ከሆነ አላህ ያሳውቀዋል። ካልሆነ ይህ መርዝ ይሠራበትና ይሞታል። በዚህም ከእርሱ እንገላገላለን› አልሁ» አለች። ሶሓቦች በዚህ ድርጊት እጅግ አዘኑ። «ነፍሳችን ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እንግደላት?» ብለው ሲጠይቁ በራሳቸው ላይ የተፈጸመን ማንኛውንም ስድብ ይቅር የሚሉት የዓለማት ሰይድ ይህንንም ይቅር አሉ። ዘይነብ ይህን ታላቅ ርኅራኄ ስትመለከት የሸሃዳን ቃል ተናግራ ሙስሊም ሆነች።11 በኸይበር ከተገኙት ምርኮና ምርኮኞች መካከል የሑየይ ኢብኑ አኽጠብ ልጅ ሶፊያም ነበረች። በጦር አዛዥ መብት የክቡር ነብያችን ድርሻ ሆና ነበር። የዓለማት ሰይድ ምርኮኛቸውን ነጻ አወጡ። እርሷም እጅግ ተነክታ ከልብ የሸሃዳን ቃል ተናግራ ሙስሊም ሆነች። ውዱ ነብያችን በዚህ እጅግ ተደሰቱ፤ እናታችን ሰይደቲና ሶፊያን በማግባት አከበሯቸው፤ አስደሰቷቸውም። ሰይደቲና ሶፊያም የምእመናን እናት ሆኑ። ሠርጋቸው ሰሕባእ በሚባል ቦታ ተካሄደ፤ ከሸማምና ከተምር የተዘጋጀ ወሊማ (የሠርግ ግብዣ) ተሰጠ።12

በእናታችን ሶፊያ የተባረኩ ዓይኖች ውስጥ ሰማያዊ ምልክት ይታይ ነበር።

ውዱ ነብያችን፦ «ይህ ምልክት ምንድን ነው?» ብለው ሲጠይቁ እንዲህ አሉ፦ «አንድ ሌሊት በሕልሜ ጨረቃ ከሰማይ ወርዳ በጉያዬ ውስጥ ስትወድቅ አየሁ። ለባለቤቴ ኪናና ስነግረው፦ ‹አንቺ በእኛ ላይ ለሚዘምተው ለዚያ የዓረብ ንጉሥ ሚስት ለመሆን ተመኝተሻል!› አለና በዓይኔ ላይ በጥፊ መታኝ፤ እንደሚያዩት ሰማያዊ ሆነ።» ከኸይበር ድል በኋላ አይሁዶች ይህን ሐሳብ ይዘው ወደ ክቡር ነብያችን መጡ፦ «ሙሐመድ ሆይ! ከኸይበር እንወጣለን። ነገር ግን እኛ እርሻን፣ የወይን ቦታዎችንና የፍራፍሬ ተክሎችን በመንከባከብ ብዙ ዕውቀት አለን። ከፈለግህ እነዚህን ለም መሬቶች ለእኛ አከራይ። እነዚህን መሬቶች እናርሳቸውና የምርቱን ግማሽ እንስጥህ!» ውዱ ነብያችንና ሶሓቦቻቸው በእርሻ ሥራ የሚሰማሩበት ጊዜ አልነበራቸውም። የእስልምናን ሃይማኖት ለማስፋፋት ተግተው በአላህ መንገድ ለሚደረግ ጂሃድ ቀንና ሌሊት ሳያቋርጡ ይሠሩ ነበር።13 ክቡር ነብያችን በዚህ ሐሳብ ተደስተው፦ «በፈለግን ጊዜ እናስወጣችኋለን በሚል ቅድመ ሁኔታ» አሉ። አይሁዶች ይህን ተቀብለው የኸይበርን መሬቶች ማረስ ጀመሩ።14 ክቡር ነብያችን ከሶሓቦቻቸው ጋር በድል ወደ መዲና ተመለሱ። በእነዚያ ቀናት በሐበሻ በስደት የቀሩት የመጨረሻዎቹ ሶሓቦች፣ ኡሙ ሐቢባም (ረዲየላሁ ዐንሃ) ጭምር፣ በጀዕፈር ኢብኑ አቢ ጧሊብ መሪነት ነጃሺ ባዘጋጀላቸው በሁለት መርከቦች ተሳፍረው በጃር ወደብ ወረዱ። ከዚያ በግመሎች ወደ መዲና መጡ። ከአሥራ ሁለት ዓመት በፊት ወደ ሐበሻ የተሰደዱት ሶሓቦቻቸው በጀዕፈር ኢብኑ አቢ ጧሊብ መሪነት ሲመጡ ሲያዩ እጅግ ተደሰቱ። ሰይዲና ጀዕፈርን በግንባራቸው ሳሟቸው፤ ወደ ደረታቸውም አቀፏቸውና እንዲህ አሉ፦

«ሶሓቦቼ ሆይ! እጆቻችሁን ከዚህ ምግብ ሰብስቡ! ይህ የትከሻ ቁራጭ መርዝ እንደተደረገበት አሳውቆኛልና» ሐዲስ ሸሪፍ

«በኸይበር ድል ልደሰት ወይስ በጀዕፈር መምጣት ልደሰት አላውቅም። ሂጅራችሁ ሁለት ጊዜ ነው፤ ወደ ሐበሻ ምድርም ወደ መኖሪያዬም ተሰድዳችኋል።» ለረሱሉላህ ነጃሺ አስሐማ የላኩትን ስጦታና ደብዳቤ አስረከቡ። የእናታችን የኡሙ ሐቢባ ሠርግም በዚያ ዓመት ተካሄደ። እናታችን ኡሙ ሐቢባ በዚያ ጊዜ ሠላሳ ስድስት ዓመታቸው ነበር። በኸይበር የተገኘው ምርኮ በሑደይቢያ ስምምነት ለተሳተፉት ሶሓቦች ሁሉ፣ በኸይበር ድል ለተሳተፉት፣ ከሐበሻ ለተመለሱት ሶሓቦችና በድሉ ለተሳተፈው ለደውስ ነገድ ተከፋፈለ።15

በኸይበር ድል የዓረብ ምድር አይሁዶች ሁሉ በክቡር ነብያችን ትእዛዝ ሥር ገቡ። አጋሪዎችን የመርዳት ዕድል ከእንግዲህ አልነበራቸውም። በዙሪያ ያሉ ነገዶችና መንግሥታትም በጦር መሣሪያና በወታደር ረገድ የማይደፈር የሚመስለውን የኸይበር ምሽግ የያዙት ሙስሊሞች ታላቅ ኃይል እንዳላቸው ተረድተው ለዚህ የእስልምና መንግሥት ጥንቃቄ ማድረግ ጀመሩ። የመካ አጋሪዎች በኸይበር ድል ምክንያት ወደ ታላቅ ሐዘንና ተስፋ መቁረጥ ወደቁ። ከዚህ ድል በኋላ ብዙ ነገዶች፣ ትልቅም ትንሽም፣ ሙስሊም ሊሆኑ ወደ መዲና አል-ሙነወራ መጡ፤ የሶሓቦችም ክብር አገኙ፤ የገጠፋን ሰዎች እንኳ… ያልታዘዙ ጥቂት ነገዶች ደግሞ ወታደር በመላክ ተገዙ።