ውዱ ነብዬ

የረጂዕ ክስተት

በኡሑድ ጦርነት ከምርጥ ቀስተኞች አንዱ የነበሩት ሰይዲና ዓሲም ኢብኑ ሳቢት በዚህ ጦርነት ከአጋሪዎቹ ሙሳፊዕ ኢብኑ ጦልሐንና ወንድሙን ሐሪስን ገድለው ነበር። በከፍተኛ ቂመኝነቷ የምትታወቀው እናታቸው ሱላፋ ቢንት ሰዕድ ሁለቱን ልጆቿን የገደሉትን የሰይዲና ዓሲም ኢብኑ ሳቢትን ራስ ላመጣላት መቶ ግመል እንደምትሰጥ ቃል ገባች። በሰይዲና ዓሲም የራስ ቅል ወይን ጠጅ ለመጠጣት ማለች። በተጨማሪም ክቡር ረሱሉላህ በላኩት አንድ ሰሪያ (ዘመቻ) ዐብዱላህ ኢብኑ ኡነይስ ከሊሕያን ልጆች ኻሊድ ኢብኑ ሱፍያንን በመግደላቸው ምክንያት የሊሕያን ልጆች ከዐደልና ከቃራ ጎሳዎች ጋር ተስማሙ። በመካ አካባቢ የሚኖሩት እነዚህ ሁለት ጎሳዎች ዕቅድ አውጥተው መልዕክተኞችን አዘጋጁ። ለእነርሱም እንዲህ አሉ፦ «ሙስሊም መሆናችሁን ትናገራላችሁ። ‹ዘካ እንሰጣለን፤ ይህን ለመቀበልና እስልምናን እንዲያስተምሩን መምህራንን እንፈልጋለን› ትላላችሁ። ከሚመጡት ከፊሎቹን ገድለን በቀላችንን እንወጣለን። ከፊሎቹን ደግሞ ወደ መካ ወስደን ለቁረይሽ እንሸጣቸዋለን።»

በሂጅራ አራተኛው ዓመት በሰፈር ወር ከእነዚህ ሁለት ጎሳዎች ስድስት ወይም ሰባት ሰዎች ያሉት ልዑክ ወደ ክቡር ነብያችን መጥቶ፦ «ሙስሊም ሆነናል፤ ቁርኣን ከሪምንና ሃይማኖትን የሚያስተምሩን መምህራንን ላክልን» አሉ።

በዚህ ጊዜ ውዱ ነብያችን የመካ አጋሪዎች የጦርነት ዝግጅት ላይ መሆን አለመሆናቸውን ለማጣራት ከአሥር ሰዎች የተዋቀረ ሰሪያ አዘጋጅተው ነበር። ከዐደልና ከቃራ ጎሳም እንዲህ ያለ ልዑክ መጥቶ መምህራንን በጠየቀ ጊዜ ሁኔታውን እንዲመረምሩ፣ እንዲያጣሩና እንዲያሳውቁ ይህን የአሥር ሰዎች የቅኝት ቡድን ከመጡት ጋር ላኩ።

በዚህ ሰሪያ ውስጥ ከሶሓቦች መካከል መርሰድ ኢብኑ አቢ መርሰድ፣ ኻሊድ ኢብኑ አቢ ቡከይር፣ ዓሲም ኢብኑ ሳቢት፣ ኹበይብ ኢብኑ ዐዲይ፣ ዘይድ ኢብኑ ደሲና፣ ዐብዱላህ ኢብኑ ጧሪቅ፣ ሙዐቲብ (ሙጊር) ኢብኑ ዑበይድና ስማቸው የማይታወቅ ሌሎች ሦስት ሶሓቦች (ረዲየላሁ ዐንሁም) ነበሩ።

ይህ የቅኝት ቡድን በቀን እየተደበቀ በሌሊት እየተጓዘ በአንድ የንጋት ጊዜ የረጂዕ ውኃ አጠገብ ደረሰ። እዚያ ለጥቂት ጊዜ ዕረፍት አድርገው ዐጅዋ ከሚባለው ጥሩ የመዲና ተምር በሉ። ከዚያም ከዚያ ተነሥተው በአቅራቢያቸው ወዳለ ተራራ ወጥተው ተደበቁ።

ከሁዘይል ጎሳ በግ የምትጠብቅ አንዲት ሴትም ወደ ረጂዕ ውኃ መጥታ ነበር። የተምሩን ዘሮች አይታ የመዲና ተምር እንደተበላ ተረዳች። «እዚህ ከመዲና የመጡ ሰዎች ነበሩ!» ብላ እየጮኸች ለጎሳዋ አሳወቀች።

በዚህ ጊዜ ከእነዚህ አሥር ሶሓቦች ሰሪያ ጋር የነበረው የዐደልና የቃራ ጎሳ ልዑክ አባል የሆነ አንድ ሰው በአንድ ሰበብ ከእነርሱ ተለየ። ወዲያውኑ ወደ ሊሕያን ልጆች ሄዶ ነገራቸው።

የሊሕያን ልጆች በዚህ ወሬ ተንቀሳቀሱ። መቶው ቀስተኞች የሆኑ ሁለት መቶ ሰዎች ያሉት ኃይል በዚህች ትንሽ ሰሪያ ላይ ላኩ። የመጣው ይህ የአጋሪዎች መንጋ ሰይዲና ዓሲም ኢብኑ ሳቢትንና ጓደኞቻቸውን በተራራው አናት ላይ አግኝቶ ከበባቸው። በዚህ መካከል የአሥሩን ሶሓቦች ሁኔታ ለአጋሪዎቹ ያሳወቀው ሰውም ተቀላቀላቸው። ሶሓቦች በዚያን ጊዜ መታለላቸውን ተረዱ፤ ለመዋጋትም ወስነው ሰይፎቻቸውን መዘዙ። ይህን የተረዱት አጋሪዎች ሊያታልሏቸው እየሞከሩ፦ «ወደ እኛ ብትወርዱ ከእናንተ አንዳችሁንም አንገድልም። ቁርጥ ቃል እንገባላችኋለን። ወላሂ እናንተን መግደል አንፈልግም። ነገር ግን በእናንተ ምክንያት ከመካ ሰዎች ቤዛ ማግኘት እንፈልጋለን» አሉ።

«ከቆሰሉ በኋላም የአላሁ ተዓላንና የነብዩን ጥሪ ተቀብለው ለሮጡት፣ በተለይም ከእነርሱ መካከል መልካም ለሠሩትና ከክፋት ለተጠነቀቁት እጅግ ታላቅ ምንዳ አለ» ኣሊ ዒምራን: 172

የረጂዕ ክስተት

ዓሲም ኢብኑ ሳቢት፣ መርሰድ ኢብኑ አቢ መርሰድና ኻሊድ ኢብኑ አቢ ቡከይር (ረዲየላሁ ዐንሁም)፦ «የአጋሪዎችን ቃልና ቃል ኪዳን ፈጽሞ አንቀበልም» ብለው ሐሳቦቻቸውን ሁሉ ውድቅ አደረጉ። ሰይዲና ዓሲም ኢብኑ ሳቢት፦ «የአጋሪዎችን ከለላ ፈጽሞ ላልቀበል ምያለሁ። ወላሂ በከለላቸውና በቃላቸው ተታልዬ ወርጄ እጄን አልሰጥም» አሉ። እጆቻቸውን ዘርግተው፦ «አላህ ሆይ! ነብይህን ስለ ሁኔታችን አሳውቅ» ብለው ዱዓ አደረጉ። አላሁ ተዓላ የሰይዲና ዓሲምን ዱዓ ተቀበለ፤ ክቡር ረሱሉላህንም ስለ እነርሱ አሳወቀ።

ሰይዲና ዓሲም ለአጋሪዎቹ፦ «እኛ መሞትን አንፈራም፤ ምክንያቱም በሃይማኖታችን አስተዋዮች ነን (ብንሞት ሸሂድ ሆነን ወደ ጀነት እንሄዳለን)» አሉ። የአጋሪዎቹ አለቃ፦ «ዓሲም ሆይ! ራስህንና ጓደኞችህን አታጥፋ፤ እጅህን ስጥ!» ባለ ጊዜ ዓሲም ኢብኑ ሳቢት በቀስት መለሱ። ቀስት እየወረወሩ እነዚህን ስንኞች ያነብቡ ነበር፦

እኔ ብርቱ ነኝ፤ ምንም ጉድለት የለብኝም።
የደጋኔ ወፍራም አውታር ተወጥሯል።
ሞት እውነት ነው፤ ሕይወት ከንቱና ጠፊ ነው።
የተወሰነው ሁሉ መድረሱ አይቀርም።
ሰዎች ይዋል ይደር ወደ አላህ ተመላሾች ናቸው።
እኔ ከእናንተ ጋር ባልዋጋ፣
እናቴ (ከሐዘኗ የተነሣ) አእምሮዋን ታጣለች።

በሰይዲና ዓሲም ኮሮጆ ውስጥ ሰባት ቀስቶች ነበሩ። በወረወሩት እያንዳንዱ ቀስት አንድን አጋሪ ገደሉ። ቀስታቸው ባለቀ ጊዜ ብዙዎቹን በጦራቸው በሳሷቸው። ነገር ግን ጦራቸውም ተሰበረ። ወዲያውኑ ሰይፋቸውን መዘዙ፤ ሰገባውን ሰብረው ጣሉት። (ይህም፦ «እስክሞት ድረስ እዋጋለሁ፤ እጄን አልሰጥም» ማለት ነበር።) ከዚያም፦ «አላህ ሆይ! እኔ እስከ ዛሬ ድረስ ሃይማኖትህን ጠበቅሁ። በዚህ ቀን መጨረሻ ሰውነቴን እንድትጠብቅልኝና እንድታቆይልኝ እለምንሃለሁ» ብለው ዱዓ አደረጉ። የሰይዲና ዓሲም ኢብኑ ሳቢትና የሌሎቹ ሶሓቦች «አላሁ አክበር!» የሚሉ ድምፆች ተራሮቹን ያስተጋቡ ነበር። አሥር ሙጃሂዶች ከሁለት መቶ ሰዎች ጋር እስከ ሞት ድረስ ይዋጉ ነበር፤ ወደ እነርሱ የቀረቡትም የሥራቸውን ቅጣት ያገኙ ነበር። በመጨረሻም ዓሲም (ረዲየላሁ ዐንሁ) በሁለቱም እግሮቻቸው ቆስለው መሬት ላይ ወደቁ። ከሓዲዎቹ እርሳቸውን እጅግ ይፈሩ ስለነበር መሬት ላይ ከወደቁ በኋላ እንኳ ሊቀርቧቸው አልደፈሩም፤ ከሩቅ ቀስት እየወረወሩ ሸሂድ አደረጓቸው። በዚያን ቀን እዚያ ከነበሩት አሥር ሶሓቦች ሰባቱ ሸሂድ ሆኑ፤ ሦስቱ ደግሞ ተማረኩ።

የሊሕያን ልጆች ለሱላፋ ቢንት ሰዕድ ለመሸጥ የዓሲም ኢብኑ ሳቢትን የተባረከ ራስ ለመቁረጥ ፈለጉ። ነገር ግን አላሁ ተዓላ የሰይዲና ዓሲም ኢብኑ ሳቢትን ዱዓ ስለተቀበለ የንብ መንጋ ላከ። እንደ ደመና በዓሲም ኢብኑ ሳቢት ላይ ቆሙ። አጋሪዎቹ ወደ እርሳቸው መቅረብ አልቻሉም። በመጨረሻም፦ «ተዉት፤ ሲመሽ ንቦቹ ይበታተናሉ፤ እኛም ራሱን ቆርጠን እንወስዳለን» አሉ።

ማታ አላሁ ተዓላ ኃይለኛ ዝናብ አዘነበ። ከሸለቆዎቹ ጎርፍ ፈሰሰ፤ የሰይዲና ዓሲም ኢብኑ ሳቢትን የተባረከ ሬሳ ወስዶ ወደማይታወቅ ስፍራ አደረሰው። ምንም ያህል ቢፈልጉም አላገኙትም። በዚህም አጋሪዎቹ ከሰይዲና ዓሲም ኢብኑ ሳቢት ምንም ነገር መቁረጥ አልቻሉም።

«አላህ ሆይ! እኔ እስከ ዛሬ ድረስ ሃይማኖትህን ጠበቅሁ። በዚህ ቀን መጨረሻ ሰውነቴን እንድትጠብቅልኝና እንድታቆይልኝ እለምንሃለሁ» ዓሲም ኢብኑ ሳቢት (ረዲየላሁ ዐንሁ)

ንቦቹ ሰይዲና ዓሲምን የጠበቁበት ክስተት በተወሳ ጊዜ ሰይዲና ዑመር፦ «አላሁ ተዓላ በእርግጥ ምእመን ባሪያውን ይጠብቃል። ዓሲም ኢብኑ ሳቢት በሕይወት ሳሉ ከአጋሪዎች እንደተጠበቁ ሁሉ አላሁ ተዓላም ከሞታቸው በኋላ ሰውነታቸውን ጠብቆ አጋሪዎች እንዲነኩት አላደረገም» አሉ። ስለዚህ ዓሲም ኢብኑ ሳቢት በተወሱ ጊዜ «ንቦች የጠበቋቸው ሰው» ተብለው ይጠሩ ነበር።1

የተማረኩት ሦስቱ ሶሓቦች ኹበይብ ኢብኑ ዐዲይ፣ ዘይድ ኢብኑ ደሲናና ዐብዱላህ ኢብኑ ጧሪቅ (ረዲየላሁ ዐንሁም) ነበሩ። የሊሕያን ልጆች ሦስቱንም በደጋን አውታሮች አሰሯቸው። ከእነርሱ መካከል ዐብዱላህ ኢብኑ ጧሪቅ ወደ መካ አጋሪዎች መወሰድን አልተቀበሉም። ላለመሄድ ተቃወሙ። «ሸሂድ የሆኑት ጓደኞቼ በጀነት ተከበሩ!» እያሉ ጮኹ። የእጆቻቸውን ማሰሪያ በጠሱ፤ ነገር ግን የሊሕያን ልጆች በድንጋይ ወግረው እርሳቸውንም ሸሂድ አደረጓቸው። ሰይዲና ኹበይብ ኢብኑ ዐዲይና ዘይድ ኢብኑ ደሲና፦ «ምናልባት ረሱሉላህ የሰጡንን የቅኝት ተልእኮ ለመፈጸም ዕድል እናገኝ ይሆናል» በሚል ሐሳብ ታገሡ።

የሊሕያን ልጆች ሁለቱንም ወደ መካ ወሰዷቸው። በበድርና በኡሑድ ጦርነቶች ዘመዶቻቸው የተገደሉባቸው አጋሪዎች በቂምና በበቀል ስሜት ይቃጠሉ ነበር፤ አጋጣሚም ይፈልጉ ነበር። ሰይዲና ኹበይብን ከአጋሪዎቹ መካከል ሑጀይር ኢብኑ አቢ ኢሃብ አት-ተሚሚ በበድር ጦርነት የተገደለበትን ወንድሙን ለመበቀል፣ ሰይዲና ዘይድ ኢብኑ ደሲናን ደግሞ ሶፍዋን ኢብኑ ኡመያ በበድር ጦርነት የተገደለበትን አባቱን ኡመያ ኢብኑ ኸለፍን ለመበቀል ገዟቸው። የአጋሪዎቹ ሐሳብ ሁለቱንም መግደል ነበር። ነገር ግን ጦርነት ማድረግን የተከለከለ አድርገው በሚቆጥሯቸው ወራት ውስጥ ስለነበሩ አስረው ጊዜው እስኪያልፍ ጠበቁ። በተለያዩ ቦታዎች አሰሯቸው። ሁለቱም ሶሓቦች በዚህ ምርኮ ፊት ታላቅ ትዕግሥት፣ ጽናትና ክብር አሳዩ።

ሰይዲና ኹበይብ ኢብኑ ዐዲይ በታሰሩበት ቤት የነበሩትና ነጻ የወጡ ባሪያ የሆኑት ማዊያ (እኚህ ሴት በኋላ ሙስሊም ሆነዋል) እንዲህ ብለው ተርከዋል፦

«ኹበይብ እኔ በምኖርበት ቤት ውስጥ በአንድ ክፍል ታስረው ነበር። ከእርሳቸው የበለጠ መልካም ምርኮኛ አላየሁም። አንድ ቀን ስመለከት በእጃቸው እንደ ማንቆርቆሪያ የገዘፈ የወይን ዘለላ ነበር። ከእርሱ ይበሉ ነበር። በየቀኑ እንዲህ ያለ የወይን ዘለላ በእጃቸው ይታይ ነበር። በዚያ ወቅት፣ በዚያውም በመካ ወይን ማግኘት ፈጽሞ የማይቻል ነበር። አላሁ ተዓላ ሲሳይ ይሰጣቸው ነበር። በታሰሩበት ክፍል ሶላት ይሰግዱ፣ ቁርኣን ከሪም ያነብቡ ነበር። የሚያነብቡትን ቁርኣን ከሪም የሚያዳምጡ ሴቶች ያለቅሱ ነበር፤ ያዝኑላቸውም ነበር። አንዳንድ ጊዜ፦ ‹የምትፈልገው ነገር አለ?› ብዬ ስጠይቃቸው፦ ‹ጣፋጭ ውኃ ስጪኝ፤ ለጣዖታት ከሚታረዱ እንስሳት ሥጋ አታምጪልኝ፤ ደግሞም ሊገድሉኝ ሲሆን አስቀድመሽ ንገሪኝ፤ ሌላ ምንም አልፈልግም› ይሉ ነበር። የሚገደሉበት ቀን በተወሰነ ጊዜ ሄጄ ነገርኳቸው። ይህን ባወቁ ጊዜ ትንሽም ለውጥ፣ ቅንጣት ያህልም የሐዘን ምልክት አላሳዩም።

ያ ቀን በቀረበ ጊዜ ከመሞታቸው በፊት የሰውነት ንጽሕና ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናገሩ፤ ምላጭም ጠየቁ። እኔም በልጄ እጅ ምላጭ ሰጥቼ ላክሁት። ልጁ ወደ እርሳቸው በሄደ ጊዜ ድንገት ፈራሁ። ‹ወይኔ! ይህ ሰው ልጁን በምላጩ ይገድለዋል። እርሱ እንደሆነ መገደሉ አይቀርም› አልኩ። ሮጬ ልጁን ተመለከትኩ። ኹበይብ የላክሁትን ምላጭ ከልጁ እጅ ወስደው ልጁን ለማጫወት በጉልበታቸው ላይ አስቀምጠውት ነበር። እኔ ይህን ሁኔታ ባየሁ ጊዜ እጅግ ፈርቼ መጮኽ ጀመርኩ። ሁኔታውን በተረዱ ጊዜ፦ ‹ይህን ልጅ የምገድለው መሰለሽን? በሃይማኖታችን እንዲህ ያለ ነገር የለም። ያለ አግባብ ነፍስ ማጥፋት ከሁኔታችንና ከክብራችን አይደለም› አሉ።»

አጋሪዎቹ ኹበይብ ኢብኑ ዐዲይንና ዘይድ ኢብኑ ደሲናን ለመግደል የወሰኑት ቀን ደረሰ። በዚያን ቀን ማልደው የምርኮኞቹን ሰንሰለቶች ፈትተው ከመካ ውጭ ተንዒም ወደሚባለው ስፍራ ወሰዷቸው። (ተንዒም ከካዕባ ከ5–8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። እዚያ ያለው ተራራ ስምም የተንዒም ተራራ ነው።) የመካ ሕዝብና የአጋሪዎቹ ታላላቆች የእነርሱን መገደል ለመመልከት ተሰብስበው ነበር። በዙሪያው ታላቅ ሕዝብ ነበር።

አጋሪዎቹ ምርኮኞቹን በሚገድሉበት ቦታ ሁለት መስቀያዎችን አቁመው ነበር። ሰይዲና ኹበይብን ወደ መስቀያው አውጥተው ሊያስሯቸው ሲሉ፦ «ተዉኝ፤ ሁለት ረከዓ ሶላት ልስገድ» አሉ። ተዉአቸውና፦ «እዚያ ስገድ» አሉ። ኹበይብ ወዲያውኑ ሶላት ጀምረው በኹሹዕ ሁለት ረከዓ ሰገዱ። የተሰበሰቡት አጋሪዎች፣ ሴቶችና ልጆች በጉጉት ይመለከቷቸው ነበር። ሶላታቸውን ከጨረሱ በኋላ፦ «ወላሂ ሞትን ፈርቼ ሶላቱን ያራዘምኩ ባይመስላችሁ ኖሮ ሶላቱን አራዝሜ ብዙ እሰግድ ነበር» አሉ። እንዲህ በሚገደሉበት ጊዜ ሁለት ረከዓ ሶላት በመጀመሪያ የሰገዱትና ልማድና ሱና እንዲሆን ምክንያት የሆኑት ሰይዲና ኹበይብ ኢብኑ ዐዲይ ናቸው። ክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ኹበይብ ሲገደሉ ሁለት ረከዓ ሶላት መስገዳቸውን በሰሙ ጊዜ ይህን ተግባራቸውን ትክክለኛና ተገቢ አድርገው ተመለከቱት።2

ሰይዲና ኹበይብን ሶላታቸውን ከሰገዱ በኋላ ወደ መስቀያው አውጥተው አሰሯቸው። ፊታቸውን ከቂብላ አዙረው ወደ መዲና አቅጣጫ አደረጉት። ከዚያም፦ «ና፣ ከሃይማኖትህ ተመለስ! እንለቅሃለን» አሉ። እርሳቸውም እንዲህ ብለው መለሱ፦ «ወላሂ አልመለስም! ዓለም ሁሉ የእኔ ቢሆንና ቢሰጠኝ እንኳ ከእስልምና አልመለስም!»

ይህን መልስ ያገኙት አጋሪዎች፦ «አሁን በአንተ ቦታ ሙሐመድ እንዲሆንና እርሱ እንዲገደል ትፈልጋለህን? ‹አዎ› ካልክ ትድናለህ፤ በቤትህም በምቾት ትቀመጣለህ!» አሉ። ኹበይብም፦ «እኔ በሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም እግር ላይ እሾህ እንኳ እንዲወጋ ፈጽሞ አልፈቅድም!» አሉ።

አጋሪዎቹ እያፌዙና እየተሳሳቁ፦ «ኹበይብ ሆይ! ከእስልምና ሃይማኖት ተመለስ! ካልተመለስክ በእርግጥ እንገድልሃለን!» አሉ። ኹበይብም፦ «በአላሁ ተዓላ መንገድ ላይ ከሆንኩ በኋላ መገደል ለእኔ ምንም ቁም ነገር የለውም» ብለው መለሱላቸው።

ከዚህ በኋላ ኹበይብ፦ «አላህ ሆይ! እዚህ ከጠላት ፊት በቀር ሌላ ፊት አላይም። አላህ ሆይ! ከእኔ ዘንድ ለመልዕክተኛህ ሰላምታ አድርስ። በእኛ ላይ የተደረገውን ይህን ነገር ለመልዕክተኛህ አሳውቅ!» ብለው ዱዓ አደረጉ፤ «አሰላሙ ዐለይከ፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!» አሉ። ኹበይብ ይህን ዱዓ ባደረጉበት ጊዜ ውዱ ነብያችን ከሶሓቦች ጋር ተቀምጠው ነበር። ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳ እንዲህ ብለው ተርከዋል፦ «አንድ ቀን ረሱሉላህ ከሶሓቦቻቸው ጋር ተቀምጠው ሳሉ፦ ‹ወዐለይሂ ሰላም› አሉ። ሶሓቦችም፦ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ይህ የማን ሰላምታ መልስ ነው?› አሉ። እርሳቸውም፦ ‹የወንድማችን የኹበይብ ሰላምታ መልስ ነው። ጂብሪል (ዐለይሂ ሰላም) የኹበይብን ሰላምታ አደረሱልኝ› አሉ።»3

በኹበይብ ዙሪያ የተሰበሰቡት የቁረይሽ አጋሪዎች፦ «አባቶቻችሁን የገደለው ይህ ሰው ነው» እያሉ ወጣቶቹን በጦሮቻቸው በእርሳቸው ላይ አነሣሡ፤ እነርሱም የተባረከ ሰውነታቸውን ማቁሰል ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የኹበይብ ፊት ወደ ካዕባ ዞረ። አጋሪዎቹ ወደ መዲና አቅጣጫ መለሱት። ሰይዲና ኹበይብ፦ «አላህ ሆይ! እኔ በአንተ ዘንድ ተቀባይነት ያለኝ ባሪያ ከሆንኩ ፊቴን ወደ ቂብላ አዙር» ብለው ዱዓ አደረጉ። ፊታቸው እንደገና ወደ ቂብላ ዞረ። ከአጋሪዎቹ አንዳቸውም የኹበይብን ፊት ከካዕባ ውጭ ወደ ሌላ አቅጣጫ ማዞር አልቻለም። በዚህ መካከል ኹበይብ በመስቀያው ላይ ሆነው በጠላቶች መካከል ብቻቸውን እንደ ባዕድ ሆነው ሸሂድ እየተደረጉ መሆናቸውን የሚገልጽ ግጥም አሉ። አጋሪዎቹ በእጆቻቸው ያሉትን ጦሮች በሰውነታቸው ላይ እየሰኩ ማሰቃየት በጀመሩ ጊዜ፦ «ወላሂ ሙስሊም ሆኜ እስከተገደልኩ ድረስ ተመትቼ በየትኛውም ጎኔ ብወድቅ አልተክዝም! ይህ ሁሉ በአላሁ ተዓላ መንገድ ነው» አሉ።

«እኔ በሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም እግር ላይ እሾህ እንኳ እንዲወጋ ፈጽሞ አልፈቅድም!» ኹበይብ ኢብኑ ዐዲይ (ረዲየላሁ ዐንሁ)

ከዚህ በኋላ ኹበይብ አጋሪዎቹን እንዲህ ብለው ረገሙ፦ «አላህ ሆይ! የቁረይሽ አጋሪዎችን ሁሉ አጥፋ! ስብስባቸውን በትን! አንድ በአንድ ነፍሳቸውን ውሰድ፤ ሕያው አትተዋቸው!» አጋሪዎቹ ይህን እርግማን በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ከፊሎቻቸውም ከዚያ ሸሽተው ራቁ። ከቀሩት አንዳንዶቹ ጦሮቻቸውን አከታትለው መሰካት ጀመሩ፤ ከእነርሱ አንዱ ጦሩን በደረታቸው ሰካ፤ ጦሩም በጀርባቸው በኩል ወጣ። ኹበይብ ከሰውነታቸው ደም እየፈሰሰና በመስቀያው ላይ እየተወዛወዙ የመጨረሻ እስትንፋሳቸውን ሲሰጡ፦ «አሽሀዱ አን ላ ኢላሀ ኢለላህ ወአሽሀዱ አነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉህ» ብለው ሸሂድ ሆኑ።4

የኹበይብ ኢብኑ ዐዲይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ሬሳ በመስቀያው ላይ አርባ ቀን ተሰቅሎ ቆየ። ሰውነታቸው አልፈረሰም፤ አልሸተተምም። ዘወትር ትኩስ ደም ይፈስ ነበር። ውዱ ነብያችን ሬሳቸውን እንዲያመጡ ከሶሓቦች መካከል ሰይዲና ዙበይር ኢብኑል ዐዋምንና ሚቅዳድ ኢብኑል አስወድን ላኩ። በሌሊት በስውር ወደ መካ ገቡ። ኹበይብን ከተሰቀሉበት መስቀያ አውርደው በግመል ላይ ጭነው ወደ መዲና ጉዞ ጀመሩ። ሁኔታውን የሰሙት አጋሪዎች በታላቅ ብዛት ወደ እነርሱ ገሠገሡ። ሁለቱም ሶሓቦች ራሳቸውን ለመከላከል ሬሳውን መሬት ላይ አስቀመጡ። ትንሽ ቆይተው ሬሳውን ያስቀመጡበት ቦታ ተሰንጥቆ ሬሳውን ወደ ውስጥ ወስዶ እንደገና መገጠሙን አዩ፤ ወደ መዲናም መንገዳቸውን ቀጠሉ።

ሰይዲና ዘይድ ኢብኑ ደሲናንም ባቆሙት እንጨት ላይ አሰሯቸው። ከሃይማኖታቸው እንዲመለሱ አስገደዷቸው። ነገር ግን የዘይድን ኢማን ከማጠናከር በቀር ምንም ነገር አላገኙም። በዚህም ዘይድን በቀስት ዝናብ ደበደቧቸው። በመጨረሻም የሶፍዋን ኢብኑ ኡመያ ነጻ የወጣ ባሪያ በሆነው በኒስጧስ እጅ ሸሂድ ሆኑ።