መግቢያ
ሕያው ፍጡርን ሁሉ የፈጠረውን፣ ያለውን ነገር ሁሉ በየቅጽበቱ በሕልውና የሚያቆየውንና ሁሉንም ከፍርሃትና ከድንጋጤ የሚጠብቀውን አላሁ ተዓላን እናመሰግናለን። ከእኛ የሆነ ሶላት (ዱዓ) እና ሰላም ከሰዎች ሁሉ በሁሉም ረገድ እጅግ ያማሩ፣ እጅግ በላጭና እጅግ የላቁ በሆኑት በእርሱ ውድ ነብይ በሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ላይ ይሁን፤ ዕውቀትን፣ ጥበብንና መልካም ስነ ምግባርን በሚያሰራጩት ቤተሰባቸው (ኣል) እና በዘመዶቻቸው ላይ ይሁን፤ ለነፍሳት ፈውስ የሆነውን ውብ ፊታቸውን በማየትና ጠቃሚ ንግግራቸውን በመስማት በተከበሩትና በዚህም ከሰዎች ሁሉ እጅግ ውድ በሆኑት በሶሓቦቻቸው1 (ረዲየላሁ ተዓላ ዐንሁም / አላሁ ተዓላ በእነርሱ ይደሰት) ሁሉ ላይ ይሁን፤ የእነርሱንም ፈለግ በሚከተሉት ሁሉ ላይ ይሁን።
አላሁ ተዓላ በዚህ ዓለም ለሰዎች ሁሉ በማዘን የሚጠቅማቸውን ነገሮች ፈጥሮ ይልክላቸዋል። በአኺራ ደግሞ ወደ ጀሀነም መሄድ የሚገባቸውን ምእመናን በችሮታው2 ይቅር ብሎ ወደ ጀነት ያደርሳቸዋል። ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም የአላሁ ተዓላ ነብይ3፣ መልዕክተኛ (ረሱል) እና ሐቢብ (ተወዳጅ) ናቸው፤ የአደም ልጆች ሰይድ (አለቃ) ናቸው። እንዲህ ባሉ የተከበሩ ነብይ ያመኑና በመንገዳቸው የሄዱ ሰዎች በእርግጥም ከኡማዎች ሁሉ በላጮቹ ሆኑ።
ክብሩ የላቀው አላህ በእዝነቱ የእርሳቸው ኡማ አድርጎን ከጸጋዎቹ ሁሉ ታላቁን አጎናጸፈን።4 እርሳቸውን መከተልና መታዘዝ እንደሚገባ በግልጽ አሳወቀ። ስለዚህ ግዙፍ ጸጋው ጌታችንን ምንም ያህል ብናወድሰውና ብናመሰግነው ያንሳል። አላሁ ተዓላ ምንም ነገር ከመፍጠሩ በፊት የዓለም መሪ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የተባረከውን ብርሃን (ኑር) ፈጠረ። በቁርኣን ከሪም ክቡር ነብያችንን በማነጋገር፦ «ለዓለማት እዝነት አድርገን ላክንህ» ተባለ። በሐዲስ ቁድሲ5 ደግሞ፦ «አንተ ባትኖር ኖሮ፣ አንተ ባትኖር ኖሮ ፍጥረታትን ባልፈጠርኩ ነበር» ተብሏል።
የኢማን (እምነት) ዋነኛ መስፈርት «ሑብ ፊላህ ወቡግድ ፊላህ»፣ ማለትም የአላሁ ተዓላን ወዳጆች መውደድና ጠላቶቹን አለመውደድ ነው። ይህ እስካልተገኘ ድረስ የትኛውም ዒባዳ ተቀባይነት አያገኝም፤ በባለቤቱ ፊት ላይ ተመልሶ ይወረወራል። ስለዚህ «የዓለማት ሰይድን» መውደድ በእኛ ላይ ፈርድ ሆኗል፤ የተባረከ ፍቅራቸውንም በልባችን እንድናኖርና በመልካም ስነ ምግባራቸው እንድናጌጥ ታዘናል። ይህ ፍቅር ጸንቶ እንዲኖር፣ የክቡር ነብያችንን የተባረከ ሕይወት የሚተርኩ መጻሕፍት ከብዙ ዘመናት ጀምሮ ተጽፈዋል፤ አሁንም እየተጻፉ ናቸው። ይበልጥ በትክክል ለመናገር፣ በተባረከ ስማቸው በረከት ይገኛል። እኛም ከዚህ በረከት ተቋዳሽ ለመሆንና ፍቅራቸው በልቦቻችን ሞልቶ እንዲትረፈረፍ፣ የአህለል ሱና ዓሊሞችን መጻሕፍት በረጅም ምርምር በማጥናት የተዘጋጀውን፣ የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን የሆኑትን የክቡር ረሱሉላህን የተባረከ ሕይወት እንድታነቡ እንመክራችኋለን። አላሁ ተዓላ በዚህ ሥራ በደከሙት ሁሉ ይደሰት። ክብሩ የላቀው አላህ የሁላችንንም ልብ በክቡር ነብያችን ፍቅር ሞልቶ፣ የአህለል ሱና ዓሊሞች ባሳወቁት ቀጥተኛ መንገድ ላይ ያኑረን! አሚን።
ዶ/ር ኤንቨር ኦረን
ካዕባ አል-ሙዐዘማ እና መስጂደል ሐራም መካ አል-ሙከረማ
