ውዱ ነብዬ

የሐዘን ዓመት

የልጆች ሐዘን

የክቡር ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ታላቅ ልጅ ቃሲም በአሥራ ሰባት ወር ዕድሜያቸው አርፈው ነበር። ከዚህ አሳዛኝ ክስተት ከዓመታት በኋላ ሌላው ልጃቸው ዐብዱላህም አረፉ። ክቡር ረሱሉላህ ከተባረኩ ዓይኖቻቸው እንባ እየፈሰሰ ወደ ተራራው ዘወር ብለው፦ «ተራራ ሆይ! በእኔ ላይ የደረሰው በአንተ ላይ ቢደርስ ኖሮ መሸከም አቅቶህ በፈረስክ ነበር!» አሉ፤ ሐዘናቸውንም ገለጹ። እናታችን ሰይደቲና ኸዲጃ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እነርሱ አሁን የት ናቸው?» ብለው ለጠየቁትም፦ «እነርሱ በጀነት ናቸው» ብለው መለሱ።

የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን የሆኑት የውዱ ነብያችን ሁለቱም ወንዶች ልጆች በማረፋቸው አጋሪዎቹ እጅግ ተደሰቱ። እንደ አቡ ጀህል ያሉ ከሓዲዎች ይህን እንደ ዕድል ቆጥረው፦ «ከእንግዲህ ሙሐመድ አብተር ነው፤ ዘሩ ተቆርጧል። ዘሩን የሚያስቀጥል ወንድ ልጅ አልቀረለትም። እርሱም ሲሞት ስሙና ዝናው ይረሳል» እያሉ በየቦታው ጫጫታ አሰሙ።

በዚህ ጊዜ አላሁ ተዓላ ሱረቱ አል-ከውሰርን አውርዶ መልዕክተኛውን አጽናና። በትርጓሜ እንዲህ ተባለ፦ «(ሐቢቤ ሆይ!) እኛ በእርግጥ ከውሰርን ሰጠንህ (የከውሰርን ገንዳና እጅግ ብዙ መልካም ነገርን ለገስንህ)። ስለዚህ ለጌታህ ሶላትን ስገድ፤ እርድንም እረድ። በእርግጥ ከመልካም ነገር ሁሉ የተራቆተውና ዘሩ የተቆረጠው አንተን (‹ዘሩ የተቆረጠ› በማለት) የሚዘልፍህ ነው። (አንተን አብተር የሚልህ ራሱ ዘር የሌለው፣ ክብርና ስም የሌለው ነው። ሐቢቤ ሆይ! አንተ ግን ንጹሕ ዘርህ፣ ዝናህና ክብርህ እስከ ቂያማ ቀን ድረስ ይቀጥላል። በአኺራም ለአንተ በአእምሮ የማይታሰቡ ብዙ ታላላቅ ክብሮች ተዘጋጅተውልሃል።)»1

የአቡ ጧሊብ ዕረፍት

የክቡር ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ወንዶች ልጆች ካረፉ በኋላ ባሉት ቀናት አቡ ጧሊብ ታመሙ፤ ሕመማቸውም ከቀን ወደ ቀን ጠና። ይህን የሰሙ የቁረይሽ አጋሪዎች እንዲህ ብለው አሰቡ፦ «አቡ ጧሊብ በሕይወት ሳሉ ሙሐመድን ለመጠበቅ እጅግ ደክመዋል። አሁን የሚሄዱበት ጊዜ ቀርቧል። በመጨረሻ ሰዓታቸውም ቢሆን እንጎብኛቸው። ምክንያቱም አቻ የሌለው የዓረብ ጀግና ሐምዛ፣ ግርማውና ብርታቱ፣ ጀግንነቱም እንደ ፀሐይ ግልጽ የሆነው ዑመርም ሙስሊሞች ሆነዋል። በየቀኑ ከዓረብ ጎሳዎች ሰዎች እየመጡ በቡድን በቡድን ይከተሉታል። በዚህም ሙስሊሞች ከቀን ወደ ቀን እየበዙ ነው፤ ድምፃቸውም ዓለምን ሞልቷል። በዚህ ሁኔታ ወይ እኛ እነርሱን መከተል፣ ወይ ለጦርነትና ለውጊያ መዘጋጀት አለብን። ወደ አቡ ጧሊብ ሄደን ሁኔታውን እንንገራቸው፤ በመካከላችንም ያስታርቁን። የእርሱን ሃይማኖት አንንካ፤ እርሱም የእኛን ሃይማኖት አይንካ።» በዚህ ሐሳብ ወደ አቡ ጧሊብ መጡ። እንደ ዑቅባ፣ ሸይባ፣ አቡ ጀህልና ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ ያሉ የታወቁ ሰዎች በአቡ ጧሊብ አልጋ አጠገብ ባሉት ትራሶች ላይ ተቀመጡ፤ እንዲህም አሉ፦ «በታላቅነትዎ እናምናለን፤ ብልጫዎንም እንቀበላለን። ስለዚህ በምንም ጊዜ አልተቃወምንዎትም። እርስዎ ካለፉ በኋላ ሙሐመድ ከእኛ ጋር እንዳይጋጭና ጠላትነቱ በመካከላችን እንዳይቀጥል እንፈራለን። እርስ በርሳችን የአንዳችንን ሃይማኖት እንዳንነካ ያስታርቁን።»

«ተራራ ሆይ! በእኔ ላይ የደረሰው በአንተ ላይ ቢደርስ ኖሮ መሸከም አቅቶህ በፈረስክ ነበር!» ሐዲስ ሸሪፍ

የእናታችን ሰይደቲና ኸዲጃ መቃብር ቤት / ጀነቱል ሙዐላ

እንደ ብዙዎቹ የእስልምና ታላላቅ ሰዎች መቃብሮች ሁሉ፣ የውዱ ነብያችን (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የመጀመሪያ የተከበሩ ባለቤት የሆኑት የእናታችን ሰይደቲና ኸዲጃ (ረዲየላሁ ዐንሃ) መቃብር ቤትም ፈርሶ ከቦታው ተወግዷል።

አቡ ጧሊብ ክቡር ነብያችንን አስጠርተው እንዲህ አሉ፦ «የቁረይሽ ታላላቆች ሁሉ በሃይማኖታቸው ጣልቃ እንዳትገባ ይለምኑሃል። ይህን ከተቀበልክ በትእዛዝህ ሥር ይሠራሉ፤ ረዳቶችህም ይሆናሉ።» የዓለማት ሰይድ እንዲህ አሉ፦ «አጎቴ ሆይ! እኔ እነርሱን ወደ አንድ ቃል ብቻ ልጠራቸው እፈልጋለሁ፤ በዚያ ቃል ዓረቦች ሁሉ ይገዙላቸዋል፤ ዓረብ ያልሆኑትም ጂዝያ ይከፍሏቸዋል።» የቁረይሽ መኳንንትንም፦ «አዎ! አንድ ቃል ብትነግሩኝ በእርሱ ዓረቦችን ሁሉ ትገዛላችሁ፤ ዓረብ ያልሆኑትም ይገዙላችኋል» አሉ። አቡ ጀህል፦ «ይሁን። አሥር ጊዜ እንለዋለን። ያ ቃል ምንድን ነው?» አለ። ክቡር ረሱሉላህ፦ «‹ላ ኢላሀ ኢለላህ› ብትሉና ከአላሁ ተዓላ በስተቀር የምታመልኳቸውን ጣዖታት አንሥታችሁ ብትጥሉ» ባሉ ጊዜ አጋሪዎቹ ወዲያውኑ፦ «ከዚህ ሌላ ነገር ጠይቀን!…» አሉ። ክቡር ነብያችንም፦ «ፀሐይን አምጥታችሁ በእጆቼ ላይ ብታኖሩ እንኳ ከዚህ በስተቀር ከእናንተ ሌላ አልጠይቅም» አሉ።

አጋሪዎቹ፦ «አቡል ቃሲም ሆይ! እጅግ እንግዳ የሆነ ሐሳብ ታቀርባለህ። እኛ ልናከብርህ እንፈልጋለን፤ አንተ ግን የእኛን ልብ ደስ አታሰኝም!» ብለው ተነሥተው ሄዱ። እነርሱ ከሄዱ በኋላ አቡ ጧሊብ ክቡር ነብያችንን፦ «ከቁረይሽ የጠየቅከው ነገር እጅግ ተገቢ ነበር። እውነት ተናገርክ» አሉ። የአጎታቸው ይህ ቃል ለክቡር ረሱሉላህ ተስፋ ሰጣቸው፤ አቡ ጧሊብ ወደ ኢማን ሊመጡ እንደሚችሉ ተረድተው፦ «አጎቴ ሆይ! አንድ ጊዜ ‹ላ ኢላሀ ኢለላህ› በል!.. በቂያማ ቀን ሸፋዐ እንዳደርግልህ» አሉ። አቡ ጧሊብም፦ «ሰዎች ‹ሞትን ፈርቶ ነው ሙስሊም የሆነው› ብለው እንዳይነቅፉኝ እፈራለሁ። ያለበለዚያ ልብህን ደስ ባሰኘሁ ነበር» ብለው ለነፍሳቸው ከባድ እንደሆነባቸው ገለጹ፤ ሕመማቸውም እየጠና ሄዶ አረፉ።2

የእናታችን ሰይደቲና ኸዲጃ ዕረፍት

በቢዕሳ አሥረኛው ዓመት፣ ከአቡ ጧሊብ ዕረፍት ከሦስት ቀን በኋላ፣ የክቡር ረሱሉላህ የሐዘን ተካፋይና ለሃያ አምስት ዓመታት የሕይወት አጋራቸው የነበሩት የተባረኩት እናታችን ሰይደቲና ኸዲጃም በስቃይና በሐዘን ካለፉት የሦስት ዓመታት ከበባ በኋላ፣ ከሂጅራ ሦስት ዓመት በፊት፣ በረመዳን ወር መጀመሪያ፣ በ65 ዓመታቸው አረፉ።3 የፍጥረተ ዓለሙ ኩራት (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እናታችን ሰይደቲና ኸዲጃን በገዛ የተባረኩ እጆቻቸው ቀበሯቸው። በመለየታቸውም እጅግ አዘኑ።

በአንድ ዓመት ውስጥ የእናታችን ሰይደቲና ኸዲጃና የአጎታቸው የአቡ ጧሊብ ተከታትሎ ማረፍ ክቡር ነብያችንን በሐዘን አሰጠማቸው። ስለዚህ ይህ ዓመት «ሰነቱል ሑዝን»፣ ማለትም የሐዘን ዓመት ተባለ።

የእናታችን ሰይደቲና ኸዲጃ ማረፍ ውዱ ነብያችንን አናወጣቸው፤ ከመጠን በላይም አሳዘናቸው። ምክንያቱም ከሁሉ አስቀድመው ያመኑትና ክቡር ረሱሉላህን ያረጋገጡት እርሳቸው ነበሩ። በተጨማሪም ታላቁ ድጋፋቸውና አጽናኛቸው ነበሩ። ሁሉም ጠላት በሆነበት ጊዜ እርሳቸው ልባቸውን ሙሉ በሙሉ ከፍተው በነብያችን ፍቅር ተሞልተው ነበር። ንብረታቸውን፣ ሀብታቸውን፣ ያላቸውን ሁሉ ለእስልምና ሲሉ አውጥተው ነበር፤ ውዱ ነብያችንን ለማገልገልም ሌሊታቸውን ከቀናቸው ጋር አገናኝተው ነበር። ረሱሉላህን በምንም ጊዜ አላሳዘኑም፤ ልባቸውንም ፈጽሞ አልሰበሩም። ክቡር ነብያችን ይህን አልፎ አልፎ ይናገሩ ነበር፤ በዚህም የተባረኩ ባለቤታቸውን መልካም ባሕርያት ያስታውሱ ነበር።

«አጎቴ ሆይ! አንድ ጊዜ ‹ላ ኢላሀ ኢለላህ› በል!.. በቂያማ ቀን ሸፋዐ እንዳደርግልህ» ሐዲስ ሸሪፍ

አንድ ቀን ሰይደቲና ኸዲጃ ነብያችን ከቤት ውጭ ሳሉ እርሳቸውን ለመፈለግ ወጥተው ነበር። ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም በሰው አምሳል ለሰይደቲና ኸዲጃ ተገለጡላቸው። እናታችን ሰይደቲና ኸዲጃ ስለ ክቡር ነብያችን ሊጠይቋቸው ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ከጠላቶች አንዱ ሊሆን ይችላል ብለው አስበው ተመለሱ። ውዱ ነብያችንን በቤት ባገኟቸው ጊዜ የሆነውን ነገሯቸው። የፍጥረተ ዓለሙ ኩራት እንዲህ አሉ፦ «ያየሽውና ስለ እኔ ልትጠይቂው የፈለግሽው ያ ሰው ማን እንደሆነ ታውቂያለሽን? እርሳቸው ጂብሪል (ዐለይሂ ሰላም) ነበሩ። ሰላምታቸውን እንዳደርስልሽ ነገሩኝ። ደግሞም በጀነት ከዕንቁዎች የተሠራ ሕንጻ ለአንቺ እንደተዘጋጀ እንዳሳውቅሽ ነገሩኝ። በዚያ እንደዚህ ያሉ አሳዛኝ፣ አስጨናቂ፣ አድካሚና አሰልቺ ነገሮች በእርግጥ አይኖሩም።»

የአንዱ እጅ በአየር ላይ ቀረ፣ ሌላው ታወረ

ውዱ ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከሰዎች ሁሉ እጅግ ዕድለኞች ለሆኑት ሶሓቦቻቸው አቻ በሌላቸው ንግግሮች ልቦቻቸውን በኑር ያበሩ ነበር። የሚወርዱትን ክቡር አንቀጾች ያብራሩ ነበር፤ ያልተነገረና ያልተረዳ ምንም ነገር አይተዉም ነበር። በዚሁ መካከል አጋሪዎቹም ወደ ኢማን እንዲመጡ በሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች እየሄዱ ሳይሰለቹና ሳይታክቱ ወደ ኢማን ይጠሯቸው ነበር። በዚህ ሁኔታ አቡ ጀህልና ወሊድ ኢብኑል ሙጊራ እጅግ ተናደው፦ «በዚህ ከቀጠለ ሙሐመድ ሁሉንም ወደ ሃይማኖቱ ይመልሳል፤ ጣዖቶቻችንን የሚያመልክ አንድም ሰው አያስቀርም» ይሉ ነበር። አንድ ቀን ይህን ጉዳይ ለመጨረስ ብቸኛው መፍትሔ የዓለማት ሰይድ የሆኑትን ውዱ ነብያችንን መግደል እንደሆነ ወሰኑ። አቡ ጀህል ወሊድ ኢብኑል ሙጊራንና ከበኑ መኽዙም ጥቂት ወጣቶችን ይዞ ወደ በይቱላህ መጣ። በዚያን ጊዜ ውዱ ነብያችን ሶላት እየሰገዱ ነበር። አቡ ጀህል በእጁ በያዘው ድንጋይ ወዲያውኑ ወደ ፊት ዘለለ። ሐቢቡል አክረምንና የተከበሩትን ነብይ በድንጋዩ ለመምታት እጁን ባነሣ ቅጽበት እጆቹ በአየር ላይ ሳይንቀሳቀሱ ቀሩ። ምንም ማድረግ አልቻለም፤ ግራ ተጋባ። በዚያው ሁኔታ ወደመጣበት ተመለሰ። ወደ አጋሪዎቹ በደረሰ ጊዜ እጁ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ተመለሰ፤ ድንጋዩም መሬት ላይ ወደቀ። ከበኑ መኽዙም አንዱ ያንኑ ድንጋይ ነጥቆ፦ «ታያላችሁ! እርሱን እኔ እገድለዋለሁ!..» እያለ ወደ ክቡር ነብያችን ተራመደ። በቀረበ ጊዜ በቅጽበት ዓይኑ ታውሮ በዙሪያው ያለውን ማየት አቃተው። በዚህ ጊዜ የበኑ መኽዙም ሰዎች ሁሉም በአንድነት ወደ ውዱ ነብያችን ገፉ። ወደ ክቡር ነብያችን በጣም በቀረቡበት ቅጽበት እርሳቸውን ማየት አቃታቸው። ነገር ግን የተባረከ ድምፃቸውን ይሰሙ ነበር። ድምፁ ወደሚመጣበት ስፍራ ሲሄዱ ድምፁ ከኋላቸው፣ ወደ ኋላ ሲዞሩ ደግሞ ከቀድሞው ስፍራ ይመጣ ጀመር። ይህንኑ ሁኔታ ብዙ ጊዜ አዩ። በመጨረሻም ግራ ተጋብተው በክቡር ረሱሉላህ ላይ ምንም ሳያደርጉ ስፍራውን ለቀው ሄዱ።

የሰይደቲና ዓኢሻና የሰይደቲና ሰውዳ እጮኝነት

ሰይደቲና ኸዲጃ (ረዲየላሁ ዐንሃ) ባረፉ ጊዜ የረሱሉላህን ቤት የሚያስተዳድር ማንም አልቀረም። እመቤት ኸውላ ቢንት ሐኪም ይህን ሁኔታ አይተው ወደ ዓለም መሪ ፊት ቀርበው እንዲህ አሉ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን)! ለእርስዎ የምትስማማ የሕይወት አጋርና ለአገልግሎትዎ የምትገባ ባለቤት ያስፈልግዎታል። ከፈለጉ ሚስት ልጠይቅልዎ።» ረሱሉላህ፦ «ኸውላ ሆይ! ለዚህ አገልግሎት የምትገባ ሴት የት አለች?» አሉ። ኸውላም፦ «ልጃገረድ ከፈለጉ የወዳጅዎ የአቡበክር ልጅ ዓኢሻ ናቸው። ባልቴት ከፈለጉ ደግሞ ሰውዳ ቢንት ዘምዓ ይስማማሉ» አሉ። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም፦ «ሁለቱንም ጠይቂልኝ» አሉ። ረሱሉላህ በመጀመሪያ ከሰይደቲና ዓኢሻ፣ ከዚያም ከሰውዳ ጋር ታጩ። ሰይደቲና ሰውዳን በመካ ወደ ቤታቸው ወሰዷቸው። ከሰይደቲና ዓኢሻ ጋር ሠርጋቸው በሂጅራ ሁለተኛው ዓመት በሸዋል ወር በመዲና ተደረገ።

በዐቀባ የተደረገው ግንኙነት

ውዱ ነብያችን በየዓመቱ ካዕባን ለመጎብኘት የሚመጡትን ጎሳዎች ወደ ሃይማኖት ይጠሩ ነበር፤ ከጀሀነም እሳት ድነው ዘላለማዊ ደስታን እንዲያገኙ ይጥሩ ነበር፤ ማንኛውንም ስድብ ከቁብ ሳይቆጥሩ የነብይነት ተግባራቸውን መፈጸማቸውን ቀጠሉ። ጎሳዎቹ በሚሰፍሩባቸው ስፍራዎች እየቆሙ ለሚመጡት ሰዎች፦ «አላሁ ተዓላ የሰጠኝን የነብይነት ተግባር እስክፈጽም ድረስ የሚያስጠልለኝና የሚረዳኝ ማን ነው? (በዚህም) ጀነት ይሰጠዋል» ይሉ ነበር፤ ነገር ግን የሚያስጠልልም ሆነ የሚረዳ ማንም አልተገኘም።

የቢዕሳ አሥረኛው ዓመት የዙልሒጃ ወር ነበር። ክቡር ነብያችን በገበያው ስፍራ ካዕባን ለመጎብኘት ከመጡት የመዲና ሰዎች አንድ ቡድን ጋር ተገናኙ። «እናንተ እነማን ናችሁ?» ብለው በጠየቋቸው ጊዜ ከመዲና እንደሆኑና ከኸዝረጅ ጎሳ እንደሆኑ ነገሯቸው። የነብያችን አያት የዐብዱልሙጠሊብ እናት እመቤት ሰልማም ከኸዝረጅ ጎሳ የበኑ ነጃር ቅርንጫፍ ነበሩ። ነብያችን ከእነዚህ ስድስት የኸዝረጅ ሰዎች ጋር በዐቀባ ለተወሰነ ጊዜ ተቀምጠው የሱረቱ ኢብራሂምን ከ35ኛው እስከ 52ኛው ያሉትን ክቡር አንቀጾች አነበቡላቸው፤ እስልምናንም አስረዷቸው። ወደዚህ ሃይማኖት እንዲገቡም ጋበዟቸው።

በመዲና ከጥንት ጀምሮ የአውስና የኸዝረጅ ጎሳዎች የአይሁዶች ጠላቶች ነበሩ፤ ዕድል ባገኙ ቁጥር እርስ በርሳቸው ይጠቃቁ ነበር። በመካከላቸው ጠብ በተነሣ ቁጥር አይሁዶች፦ «በቅርቡ አንድ ነብይ ይመጣሉ። ብዙ አልቀረም፤ ዛሬ ነገ ይገለጣሉ። እኛ እርሳቸውን ተከትለን እንበረታለን። እናንተንም እንበቀላችኋለን» ይሉ ነበር። የአውስና የኸዝረጅ ሰዎች በበኩላቸው ከአይሁዶች በፊት ሙስሊም ሆነው በእስልምና ቢከበሩ በእነርሱ ላይ እንደሚያሸንፉና ከመዲና እንደሚያስወጧቸው ያምኑ ነበር።

ከጎሳቸው ታላላቆችና በመዲና ከሚኖሩት አይሁዶች በቅርቡ አንድ ነብይ እንደሚመጡ የሰሙት እነዚህ ዕድለኛ ሰዎች በረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ላይ የነብይነትን ምልክቶች አዩ። ወደ ሃይማኖት በጠሯቸው ጊዜ እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከዚያም በመካከላቸው፦ «አይሁዶች ያወሩልን ነብይ እነሆ እኚህ ናቸው!» ተባባሉ።

ስለዚህ ወዲያውኑ በረሱሉላህ ፊት የሸሃዳን ቃል ተናግረው ሙስሊሞች ሆኑ። ክቡር ነብያችንንም እንዲህ አሏቸው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ሕዝባችንን ከአይሁዶች ጋር ሲዋጋ ትተነው መጥተናል። አላሁ ተዓላ እነርሱንም በእርስዎ ምክንያት በኢማን እንደሚያከብራቸው ተስፋ እናደርጋለን። እንደተመለስን እነርሱንና ሕዝባችንን የእርስዎን ነብይነት እንዲቀበሉ እንጠራቸዋለን። ከዚህ ሃይማኖት የተቀበልነውንም እንነግራቸዋለን። አላሁ ተዓላ በዚህ ሃይማኖት ላይ ቢሰበስባቸውና ቢያዋህዳቸው ከእርስዎ የበለጠ ውድና የተከበረ ማንም አይኖርም።»

እነዚህ ስድስት ሰዎች በእውነት አምነው ነበር፤ አላሁ ተዓላ ለነብያችን ያሳወቀውን ተቀብለው አረጋግጠው ነበር።

«አላሁ ተዓላ የሰጠኝን የነብይነት ተግባር እስክፈጽም ድረስ የሚያስጠልለኝና የሚረዳኝ ማን ነው? (በዚህም) ጀነት ይሰጠዋል» ሐዲስ ሸሪፍ