ውዱ ነብዬ

የበኑ ነዲር ዘመቻ

ዐምር ኢብኑ ኡመያ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በመዑና ተማርከው ሳሉ ከማሰሪያው አምልጠው ወደ መዲና ሲመለሱ በመንገድ ላይ ከበኑ ዓሚር ሁለት አጋሪዎችን አገኙ። እነዚያን ሁለት ከሓዲዎች ገደሉ። እነዚህ ሁለቱ በረሱሉላህ ከለላ ሥር ገብተው ነበር። ዐምር ይህን አያውቁም ነበር። ወደ መዲና መጡ። ሁኔታውን ለረሱሉላህ አቀረቡ። ክቡር ነብያችንም ዐምር ስሕተት መሥራታቸውን አሳወቁ፤ የደም ካሳቸውም ለወራሾቻቸው እንዲሰጥ አዘዙ።

በበኑ ዓሚርና በበኑ ነዲር ጎሳዎች መካከል ወዳጅነት ነበር። በኑ ነዲር የጉርብትናንም መብት ይጠብቁ ነበር። ስለዚህ ለዚህ የደም ካሳ የበኑ ነዲር ጎሳ አማላጅነት አስፈለገ።

ከኡሑድ ጦርነት በኋላ በሂጅራ አራተኛው ዓመት በረቢዑል አወል ወር ረሱሉላህ ከሶሓቦች መካከል ሰይዲና አቡበክርን፣ ዑመርን፣ ዐሊይን፣ ዙበይርን፣ ጦልሐን፣ ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝንና ኡሰይድ ኢብኑ ሑደይርን (ረዲየላሁ ዐንሁም) ይዘው ወደ በኑ ነዲር ሄዱ። ሁኔታውን ገለጹላቸው። እነርሱም ለእነዚያ ሁለት ከሓዲዎች የደም ካሳ ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፦ «ትንሽ ቆዩ፤ ምግብ እናዘጋጅ» አሉ። በዚያን ጊዜ መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም በተቀመጡበት ቤት ግድግዳ ላይ ጀርባቸውን ተደግፈው ነበር፤ ሶሓቦችም ተሰብስበው በዙሪያቸው ተቀምጠው ነበር። በዚያን ጊዜ ሑየይ ኢብኑ አኽጠብ፦ «እናንተ አይሁዶች ሆይ! ሙሐመድን እንዲህ ለብቻው የምታገኙበት ዕድል ፈጽሞ አይገኝም። ከእናንተ አንዱ የዚህን ቤት ጣሪያ ይውጣ። ከዚያ ድንጋይ በራሱ ላይ ይጣልበት፤ ከእርሱ እንገላገል» አለ። ዐምር ኢብኑ ጀሓሽ፦ «እኔ ይህን ሥራ እሠራለሁ» አለ። ሰላም ኢብኑ ሚሽከም ምንም ያህል ከዚህ ሊከለክላቸው ቢሞክርም አልጠቀመም። «ከዚህ ሥራ ተቆጠቡ። ይህ ይነገረዋል። ይህ ሥራ ቃል ኪዳናችን እንዲፈርስ ምክንያት ይሆናል። ከዚህ እጅግ መጥፎ ነገሮች ሊመጡ ይችላሉ» አለ። የበኑ ነዲር አይሁዶች አልሰሙትም። በዚያን ጊዜ ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም መጥተው ይህን ሁኔታ ለረሱሉላህ አሳወቁ። ክቡር ነብያችን ለሶሓቦች ምንም ሳይናገሩ ለአንድ ጉዳይ እንደሚሄድ ሰው ከዚያ ጉባኤ ተነሥተው ወደ መዲና ሄዱ። የግድያ ሴራው ያለ ውጤት ቀረ።

በዚህም የዓለማት ሰይድ ቃል ኪዳኑን ወደ አፈረሰው ወደዚህ የአይሁድ ጎሳ ሙሐመድ ኢብኑ መስለማን ልከው እንዲህ አሉ፦ «ወደ ነዲር ልጆች አይሁዶች ሂድ! እንዲህ በላቸው፦ ‹ረሱሉላህ ይህን ትእዛዝ እንዳደርስላችሁ ወደ እናንተ ልከውኛል፦ ከአገሬ ውጡና ሂዱ! እዚህ ከእኔ ጋር አትቀመጡ! እናንተ በእኔ ላይ የግድያ ሴራ አዘጋጃችሁ። አሥር ቀን ጊዜ እሰጣችኋለሁ። ከዚህ ጊዜ በኋላ ከእናንተ እዚህ የታየ ሁሉ አንገቱ ይቀላል።›»

ሰይዲና ሙሐመድ ኢብኑ መስለማ ይህን ትእዛዝ ባሳወቁ ጊዜ ከፍርሃታቸው የተነሣ የጉዞ ዝግጅት ጀመሩ። ነገር ግን የመናፍቃኑ አለቃ ዐብዱላህ ኢብኑ ኡበይ፦ «በምንም ዓይነት ከምሽጋችሁ አትውጡ። ንብረታችሁንና አገራችሁን ትታችሁ አትሂዱ። ከሰዎቼ ሁለት ሺህ ሰዎችን ይዘን ልንረዳችሁ እንመጣለን» ብሎ መልእክት ላከላቸው።

ይህን የሰሙት የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን ከሶሓቦቻቸው ጋር ከመስጂደ ነበዊ አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወዳለው የነዲር ልጆች ምሽግ ዘመቱ። በመዲና ሰይዲና ኢብኑ ኡሙ መክቱም በምትክነት ቀርተው ነበር። ሰንደቅ ዓላማውን ሰይዲና ዐሊይ ይዘው ነበር። ምሽጉ ተከቦ ከበባው ተጀመረ። ቀደም ብለው ሶሓቦችን የተገዳደሩት አይሁዶች ከምሽጉ ለመውጣት አልደፈሩም። የመናፍቃኑም እርዳታ አልደረሰም።

ሶሓቦች ምሽጉን በቁጥጥር ሥር አድርገው ወፍ እንኳ እንዲበር አልፈቀዱም። ከሃያ ቀን በላይ ከቆየው ከበባ በኋላ አይሁዶች እጃቸውን ሰጡ። መሣሪያዎቻቸውን ሁሉ፣ ወርቃቸውንና ብራቸውን ለሙስሊሞች ትተው ከፊሎቹ ወደ ሻም፣ ከፊሎቹ ደግሞ ወደ ኸይበር ተባረሩ። በዚህም በመዲና ክልል ከአይሁዶች የቁረይዟ ልጆች ብቻ ቀሩ።1

«አይሁዶች ሊገድሉኝ አሴሩ! ጂብሪል ይህን ባሳወቁኝ ጊዜ ተነሣሁ!» ሐዲስ ሸሪፍ

በሂጅራ አራተኛው ዓመት የተከሰቱ ጠቃሚ ክስተቶች

በዚህ ዓመት አስካሪ መጠጥ መጠጣትን ሐራም ያደረገው ክቡር አንቀጽ ወረደ።2 ከረሱሉል አክረም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የተባረኩ ሚስቶች መካከል አንዷ የሆኑት ሰይደቲና ዘይነብ ቢንት ኹዘይማ በሂጅራ አራተኛው ዓመት በረቢዑል አኺር ወር፣ በሠላሳ ዓመታቸው፣ ከረሱሉላህ ጋር ከተጋቡ ስምንት ወር በኋላ አረፉ።3 በዚሁ ዓመት የሰይዲና ዐሊይና የሰይደቲና ፋጢማ ሁለተኛ ልጅ ሰይዲና ሑሰይን ተወለዱ።4 በኡሑድ ጦርነት ቆስለው ከዚያ በኋላ ያረፉት የሰይደቲና ኡሙ ሰለማ ባል ጥቂት ልጆችን ትተው ነበር። እናታችን ኡሙ ሰለማ በእርጅና ዕድሜያቸው በችግር ላይ ወድቀው ነበር። ውዱ ነብያችን እጅግ አዝነውላቸው በእዝነት በኒካሕ አግብተው አከበሯቸው።5

የፋጢማ ቢንት አሰድ ዕረፍት

የሰይዲና ዐሊይ እናት ፋጢማ ቢንት አሰድም በዚህ ዓመት አረፉ።6 በዚህ ውዱ ነብያችን እጅግ አዝነው፦ «ዛሬ እናቴ አረፉ!» አሉ። ውዱ ነብያችን አያታቸው ዐብዱልሙጠሊብ ካረፉ በኋላ በእርሳቸው ዘንድ አድገው ነበር። ነብይነታቸውን ባሳወቁ ጊዜም ወዲያውኑ ሙስሊም በመሆን ተከብረው ነበር። በዚህ ምክንያት የፍጥረተ ዓለሙ ሱልጣን በእናት ቦታ ያዩአቸው ነበር፤ ታላቅ አክብሮትም ያሳዩአቸው ነበር። ለእርሳቸው ካላቸው ርኅራኄ የተነሣ የለበሱትን የተባረከ ሸሚዝ አውልቀው በእርሱ እንዲገነዙ አዘዙ። የጀናዛ ሶላታቸውን ካሰገዱ በኋላ ሰባ ሺህ መላእክት በሶላቱ ላይ መገኘታቸውን አሳወቁ። እስከ ቀብሩ ድረስ ሄደው ወደ ውስጡ ወረዱ። የቀብር ሕይወት ለእርሳቸው ምቹና አስደሳች እንዲሆን ቀብሩን ወደ ማዕዘኖቹ እንደሚያሰፉ ዓይነት ምልክት ካደረጉ በኋላ በቀብሩ ውስጥ ተጋደሙ።

ከቀብሩ በወጡ ጊዜ የተባረኩ ዓይኖቻቸው በእንባ ተሞልተው ነበር፤ የተባረከ እንባቸውም በቀብሩ ላይ ፈስሶ ነበር። ጌታዬ ሆይ! ይህ እንዴት ያለ እዝነት ነበር?… እኚህስ እንዴት ያሉ ዕድለኛ እመቤት ነበሩ?… ሰይዲና ዑመር እንኳ ራሳቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ነፍሴ ለእርስዎ መሥዋዕት ትሁን! ለማንም ያላደረጉትን ለእኚህ እመቤት አደረጉ!» ብለው በጠየቁ ጊዜ ከታማኞች ሁሉ ይበልጥ ታማኝ የሆኑት ውዱ ነብያችን እንዲህ አሉ፦ «ከአቡ ጧሊብ በኋላ እንደ እኚህ ደግ እመቤት መልካም ያደረገልኝ ማንም የለም። እርሳቸው እናቴ ነበሩ። የራሳቸው ልጆች ተርበው ሳሉ መጀመሪያ እኔን ያጠግቡኝ ነበር። የራሳቸው ልጆች በአቧራና በአፈር ተለውሰው ሳሉ እርሳቸው መጀመሪያ የእኔን ጸጉር አበጥረው በጽጌረዳ ዘይት ይቀቡልኝ ነበር። እርሳቸው እናቴ ነበሩ! ከጀነት ልብሶች እንዲለበሱ ሸሚዜን ከፈን አድርጌ አለበስኳቸው። የቀብር ሕይወት ለእርሳቸው ልስልስና ቀላል እንዲሆን በቀብሩ ውስጥ ከጎናቸው ተጋደምኩ። ጂብሪል ከአላሁ ተዓላ ዘንድ፦ ‹እኚህ እመቤት የጀነት ሰው ናቸው› ብለው አሳወቁኝ።» ከዚህ በኋላ ለእናታችን ፋጢማ ቢንት አሰድ እንዲህ ብለው ዱዓ አደረጉ፦ «አላሁ ተዓላ ምሕረት ያድርግልሽ፤ ይቅር ይበልሽ፤ ምንዳሽንም ይስጥሽ። እናቴ ሆይ! አላሁ ተዓላ ይዘንልሽ። ራስሽ ተርበሽ ሳለ እኔን አጠገብሽኝ። ራስሽ ሳትለብሺ እኔን ታለብሺኝ፣ ራስሽ ሳትበዪ እኔን ታበዪኝ ነበር። ሕያው የሚያደርግም የሚገድልም አላሁ ተዓላ ነው። እርሱ ዘወትር ሕያው ነው። እርሱ አይሞትም። አላህ ሆይ! እናቴን ፋጢማ ቢንት አሰድን ይቅር በል፤ ማራት! ማስረጃዋን አሳውቃት። ቀብሯን አስፋላት። ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ የሆንክ አላህ ሆይ! በእኔ በነብይህና ባለፉት ነብያት ሐቅ ይህን ዱዓዬን ተቀበል።»

በሂጅራ አራተኛው ዓመት የተከሰቱ ሌሎች ጠቃሚ ክስተቶች

የሰይዲና ዑስማን ከሰይደቲና ሩቀያ የተወለደው የስድስት ዓመቱ ልጃቸው ዐብዱላህ አረፈ። የዓለማት ሰይድ የልጅ ልጃቸውን የጀናዛ ሶላት አሰገዱ፤ ራሳቸውም በቀብሩ ውስጥ አኖሩት። እጅግ አዝነው ነበር፤ የተባረከ እንባቸው በቀብሩ ላይ ፈሰሰ። የመቃብሩን ድንጋይ በተባረኩ እጆቻቸው አቆሙ፤ እንዲህም አሉ፦ «አላሁ ተዓላ ከባሮቹ መካከል ለአዛኞችና ልበ ርኅሩኆች ይራራል።»7

እርስዎ የመልዕክተኞች ሱልጣን፣ የተከበሩ መሪ ነዎት፣ ሰይዴ ሆይ።
ለአቅመ ቢሶች ዘላለማዊ ዕድል ነዎት፣ ሰይዴ ሆይ።
በአላህ ዲዋን ውስጥ ቀዳሚው እርስዎ ነዎት፣ ሰይዴ ሆይ።
በ«ለዐምሩከ» አዋጅ የጸኑ ነዎት፣ ሰይዴ ሆይ።
እርስዎ አሕመድ፣ መሕሙድና ሙሐመድ ነዎት፣ ሰይዴ ሆይ፤
ከሐቁ ዘንድ ለእኛ የጸኑ ሱልጣን ነዎት፣ ሰይዴ ሆይ።
ማንነትዎ ረቂቅ ነፍሶችን ያበራል፤
የደጃፍዎ አፈር መላእክት ጉንጫቸውን የሚያሹበት ነው።
እይታዎ የአላህ መገለጥ የሚታይበት መስታወት ነው፤
አቡበክር፣ ዑመር፣ ዑስማንና ዐሊይ ወዳጆችዎ ናቸው።
እርስዎ አሕመድ፣ መሕሙድና ሙሐመድ ነዎት፣ ሰይዴ ሆይ፤
ከሐቁ ዘንድ ለእኛ የጸኑ ሱልጣን ነዎት፣ ሰይዴ ሆይ።
ኹጥባዎ በዘላለማዊው ዓለም ሚንበር ላይ ይነበባል።
ፍርድዎ በብድራት ቀን ችሎት ይጸናል።
የመምጣትዎ የደስታ ጩኸት በአላህ ዐርሽ ይሰማል።
የተከበሩ ስሞችዎ በምድርና በሰማይ ይወሳሉ።
እርስዎ አሕመድ፣ መሕሙድና ሙሐመድ ነዎት፣ ሰይዴ ሆይ፤
ከሐቁ ዘንድ ለእኛ የጸኑ ሱልጣን ነዎት፣ ሰይዴ ሆይ።
Şeyh Galib

«ከአቡ ጧሊብ በኋላ እንደ እኚህ ደግ እመቤት (ፋጢማ ቢንት አሰድ) መልካም ያደረገልኝ ማንም የለም። እርሳቸው እናቴ ነበሩ» ሐዲስ ሸሪፍ

የትንሹ በድር ዘመቻ